
ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ከትራምፕ አስተዳደር ራሱን ማግለሉን አስታውቋል። መስክ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የተባረሩበት የዶጅ ንቅናቄ ኃላፊ ነበር። ዶጅ እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የብክንት ቅነሳ መሥሪያ ቤት ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ሲያገለግል ቆይቷል። መስክ በማኅበራዊ ሚድያው ኤክስ በኩል በለቀቀው መግለጫ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን አመስግኗል።
ዋይት ሐውስ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ኤለን መስክ የመንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የተሰኘ መለያው እንዲነሳ አድርጓል።የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ዶጅን እየመራ እንደማይቆይ እና ኃላፊነቱ ጊዜያዊ እንደሆነ ሲያስታውቅ ቆይቷል።”ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብክነትን እንድቀንስ ዕድሉን ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ። ነገር ግን ዶጅ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።
ደቡብ አፍሪካ የተወለደው ጉምቱ የቴክኖሎጂ ሰው “ልዩ የመንግሥት ሠራተኛ” የሚል ኃላፊነት ተሰጥቶት በዓመት 130 ቀናት እንዲሠራ ተፈቅዶለት ነበር።ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ባለፈው ጊዜ ስሌት መሠረት በያዝነው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር መገባደጃ 130 ቀናት ይሞሉታል።ነገር ግን መስክ በትራምፕ የበጀት ረቂቅ አዋጅ “እንደተከፋ” ባስታወቀ ማግስት ኃላፊነቱን መልቀቁ አነጋጋሪ ሆኗል።
የትራምፕ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የግብር እፎይታ እና የመከላከያ በጀት እንዲጨምር የሚያበረታታ ነው።የስፔስኤክስ እና ቴስላ ኩባንያዎች ኃላፊ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ከሆነው ሲቢኤስ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ትራምፕ “ትልቁ እና ውቡ” ያሉት አዋጅ የፌዴራል መንግሥቱን ዕዳ ውስጥ የሚከት ነው ብሏል። እንዲሁም አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ዶጅ ሲሠራ የነበረውን “ሥራ የሚያወርድ” ነው ሲል ተደምጧል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር እና በአሜሪካ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ቁልፍ ሰው ኢሎን መስክ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የግብር እፎይታ መተቸቱ አነጋጋሪ ሆኗል። የቅርብ አጋሩ ትራምፕ “ትልቅና ውብ” ሲሉ የጠሩትን የትሪሊዮን ዶላር ግብር መስክ ተችቷል። ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብር እፎይታ በማጽደቅ የአሜሪካን የመከላከያ ወጪ ለመጨመር ቃል ገብቷል። ረቂቁ በቀጣይ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ያመራል።
“አዋጅ ትልቅ ሊሆን ይችላል። ውብም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሁለቱን ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለኝ” ሲል መስክ ትችቱን አሰምቷል።መስክ የትራምፕ አስተዳደርን ሲቀላቀል 2 ትሪሊዮን ዶላር ብክነት እቀንሳለሁ ብሎ ነበር የተነሳው። ነገር ግን ይህን ቁጥር ወደ 150 ቢሊዮን ዝቅ አድርጎታል።በዶጅ ምክንያት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የፌዴራል ሠራተኞች መካከል 260 ሺህ የሚሆኑት ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል።
መስክ ለውጭ ሀገራት የሚላክ ርዳታን ጨምሮ የተለያዩ የወጪ ቅነሳዎች አድርጓል። ከእዚህ ኃላፊነቱ ከመራቁ በተጨማሪ ለፖለቲካ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚቀንስም ገልጿል።”እውነቱን ለመናገር ከፍተኛ ወጪ ያለው ረቂቅ መቅረቡ አስከፍቶኛል። የትራምፕ ዕቅድ የበጀት ጉድለቱን የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም” ብሏል። የቀረበው ረቂቅ የበጀት ጉድለት እንደሚጨምር ተገልጿል። በየዓመቱ የአሜሪካ መንግሥት ወጪ ከገቢው በላይ የ600 ቢሊዮን ዶላር ልዩነት እንዲኖረው ያደርጋልም ተብሏል።መስክ ረቂቁ “የዶጅን (የሚመራው መሥሪያ ቤት) ሥራ የሚያራክስ ነው” ሲልም ነቅፏል።
በግብር ዕቅድ በሪፐብሊካኖች መካከል ያለውን ልዩነት የመስክ ተቃውሞም ያስተጋባል። ረቂቁ ብዙ ተቃውሞ ቀርቦበት ነው ያለፈው።እአአ በ2017 የቀረቡ የግብር እፎይታዎችን የሚሽር ሲሆን ለመከላከያ ከፍተኛ የበጀት ጭማሪ የሚያስገኝ ይሆናል። ስደተኞችን ከአሜሪካ ለማባረርም ገንዘብ ፈሰስ ይደረግበታል።
መስክ ባለፈው ሚያዝያ ከመንግሥት ኃላፊነት ገሸሽ ብሎ ትኩረቱን የግል ኩባንያዎቹ ላይ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር። ኤለን መስክ የዋይት ሐውስ ልዩ ሠራተኛ ሳለ የቴስላ መኪና ሽያጭ 13 በመቶ አሽቆልቁሏል። የቴስላ የአክሲዮን ገበያም 45 በመቶ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም