
በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚጠቁ/የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል። ለሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መጠቃት (መያዝ) ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት መካከል ደግሞ ሲጋራ ማጨስ እና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም መሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ምን ያህል?
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የትምባሆ ተጠቃሚዎች አሉ። ትምባሆ አጫሽነት ወይም ተጠቃሚነት በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ከሚዳርጉ ትላልቅ የሕብረተሰብ ጤና ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው። በትምባሆ ጭስ ጉዳት ምክንያት ከሚሞቱት ከእነዚሁ ሰዎች መካከል ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በቀጥታ ትምባሆን የሚያጨሱ ሲሆኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተገደው ለጭሱ በተለያየ መንገድ የሚጋለጡ በተለምዶ ሁለተኛ ወገን አጫሽ (Second hand smoker) ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ናቸው።
የጤና ጉዳት
ትምባሆ በቅጠሉ ውስጥ ብቻ ከ7000 በላይ ኬሚካሎችን በውስጡ ይዟል። ከእነዚህ ኬሚካሎች ውስጥ አብዛኞቹ ጎጂ ሲሆኑ በተለይ 70 የሚሆኑ ካንሰር አምጪ ኬሚካል ናቸው። ሲጋራ ማጨስ እና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም በሱስ ለመያዝ፣ ለአደገኛ የሳንባ በሽታ፣ ለካንሰር፣ ለልብ በሽታ መዳረግ፣ ለፅንስ መጎዳት፣ በሚጨስበት አካባቢ በሚኖሩ እና በማያጨሱ ሰዎች ላይ ጭምር ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክ እና ሌሎችንም ጉዳቶች እያስከተለ ይገኛል። የአጫሾች የሕይወት ቆይታም ከማያጨሱ ሰዎች ቢያንስ 10 ዓመት ያነሰ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዓለም አቀፍ ማሕቀፍና ድንጋጌዎች
በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተዛመተ እና በሰው ልጆች ጤና፣ ማኅበራዊ ኑሮ እና ኢኮኖሚ ላይ ችግር እየፈጠረ ያለን የትምባሆ ጉዳት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት ማሕቀፍን (WHO FCTC) እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ በማጽደቅ ማሕቀፉን በሁሉም የዓለም ሀገራት ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርጓል።
የትምባሆ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ ጠቃሚና በጣም ወጪ ቆጣቢ የትምባሆ ቁጥጥር እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መመሪያዎችን እና መስፈርቶችን የያዘው ይሄ የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት ማሕቀፍ የተፈራረሙ ሀገሮች ማድረግ ስለሚገባቸው ተግባራትም በግልፅ አስቀምጧል።
ሀገራት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ከሚያስገድዱ ዋና ዋና ድንጋጌዎች መካከልም በትምባሆ ምርቶች ላይ ግብር መጨመር፣ በሁሉም የሥራ ቦታዎች እና የሕዝብ መሰብሰቢያዎች እና በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ የሲጋራ ጭስ እንዳይጨስ መከላከል አስፈላጊ መሆኑን በማመን ማስፈፀም አንደኛው ነው። እንዲሁም በትምባሆ ምርቶች ማሸጊያ ላይ ዝቅተኛውን 50 በመቶ በምስል የተደገፈ/ግራፊክ የጤና ማስጠንቀቂያዎች እንዲኖር ማድረግን ጨምሮ የትምባሆ ማስታወቂያ፣ ስፖንሰርሺፕ እና ማስተዋወቅ ላይ አጠቃላይ እገዳ እንዲጥሉ ያስገድዳል።
እነዚህ ርምጃዎች ለስምምነቱ ሁለንተናዊ ትግበራ እንደ መነሻ ሊወሰዱ ይችላሉ። ስምምነቱ በትምባሆ ምርቶች ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች ይፋ መውጣት እና መቆጣጠር፣ የትምባሆ ምርቶችን ለአካለ መጠን ላልደረሱ ሕጻናት እንዳይሸጥ መከልከልን፣ የትምባሆ ሱስ ሕክምናን፣ ጥናትና ምርምርን እና የመረጃ ልውውጥን እና የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች እንዲተገበሩ አበክሮ ይመክራል።
ኢትዮጵያና የትምባሆ ሕጎች
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ማሕቀፍ (WHO FCTC) እ.ኤ.አ በ2005 ተቀብላ በአዋጅ ቁጥር 822/2006 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቃ ተግባራዊነቱን እንዲከታተል እና የማስተባበር ሥራውን እንዲያከናውን ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ሰጥታለች። የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 ጠንካራ የሆኑ የትምባሆ ቁጥጥር አንቀፆችን በማካተት የተለያዩ ሥራዎችን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሠራ ቆይቷል። ከአዋጅ 1112/11 በተጨማሪ የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 771/2013ን፣ በምስል የተደገፈ የጤና ማስጠንቀቂያ መመሪያ ቁጥር 46/2012 እና የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመሪያ ቁጥር 1003/2016ን አውጥቶ ሰፋፊ ሥራዎችን እንዲሠሩ አድርጓል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱም ስልጣንና ኃላፊነቱን በመጠቀም ሀገር አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም እና የ8 ዓመት ሀገር አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ሥትራቴጅክ እቅድ በመንደፍ ሥራዎች እየሠራ ሲሆን ከክልል ተቆጣጣሪ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን በተለይ ከአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጋር በመሆን እና ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶችን ጭምር በማስተባባር አዲስ አበባ ከተማን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ለማድረግ በርካታ የኢንሼቲቭ ሥራዎች በመሥራት አበረታች ውጤቶች ማግኘት ተችሏል።
የትምባሆ ቁጥጥር በተለይ በሕግ የተቀመጡ ክልከላዎችን ተፈፃሚ ለማድረግ ከፌደራል እስከ ክልል በየተዋረዱ የሚሠሩ የቁጥጥር ባለሙያዎችን አቅም ከማጎልበት፣ ሕገወጥ የትምባሆ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሕብረተሰብ ጤናና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሱትን ሁለንተናዊ ጉዳቶችን ለመከላከል ያለሙ ሥራዎች በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ሀገር አቀፍ ጥናቶች እና የተገኙ ውጤቶች
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የተሠሩ ሥራዎች የአሉበትን ደረጃ ገምግሞ ዝቅተኛ ውጤት የመጣባቸውን ለማሻሻል ጥሩ ውጤት የመጣባቸውን ደግሞ ውጤቶቹን አጠናክሮ ለመቀጠል ሁለት ጊዜ ሀገር አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም የዳሰሳ ጥናትን ከባላድርሻ አካላት ጋር እንዲጠና አድርጓል (GATS 2016 እና GATS 2024)። በተለይ ለሁለተኛ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2024 በተካሄደውና ከወራት በፊት ይፋ በተደረገው ሀገር አቀፍ የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ውጤት ላይ በግልፅ እንደታየው እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ በሆናቸው ሀገር አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም (GATS 2024) ጥናት ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
ይህም ማለት በመጀመሪያ በተጠናው የGATS 2016 ጥናት በኢትዮጵያ አጠቃላይ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር 5% የነበረ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ በተጠናው የGATS 2024 ጥናት ደግሞ 4ነጥብ 6 በመቶ ነው። በሌላ በኩል በGATS 2016 በተጠናው ጥናት ሰዎች በሚሰሩባቸው የሥራ ቦታዎች የነበረው ለትምባሆ ሁለተኛ ወገን አጫሽነት መጋለጥ (Second hand smoker) 29ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን በGATS 2024 ጥናት ግን 19ነጥብ 8 በመቶ ነው። በ2016 ጥናት ሰዎች በባር እና ምሽት መዝናኛ ቦታዎች 60ነጥብ4 በመቶእንዲሁም በሬስቶራንቶችና ምግብ ቤቶች ደግሞ 31ነጥብ 1 በመቶ ለሁለተኛ ወገን አጫሽነት (Second hand smoker) የተጋለጡ ቢሆንም በተሠራው ከፍተኛ የትምባሆ ቁጥጥር ሥራ በ2024 ጥናት ወደ 20ነጥብ 2 በመቶ ቀንሷል። ከዚህ በተጨማሪም በ2016 የነበረው 1ነጥብ 2 በመቶ የሴት አጫሾች ቁጥር በ2024 ጥናት ላይ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ 0ነጥብ 4 በመቶ ሆኗል።
ትምባሆ የማይጨስበት ቀን
ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ ግንቦት 23/2017 በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ይከበራል። የዓለም ጤና ድርጅት ‹‹በትምባሆ እና በኒኮቲን ምርቶች ላይ የትምባሆ ኢንዱስትሪ አሳሳችና ድብቅ ስልቶችን በማጋለጥ ወጣቶችን እንታደግ›› ‘’Unmasking the Appeal: Exposing Industry Tactics on Tobacco and Nicotine Products’’! በሚል መሪ ቃል እንዲከበር ወስኗል። ዘመቻው የትምባሆ እና የኒኮቲን ኢንዱስትሪዎች ጎጂ ምርቶቻቸውን ማራኪ ለማስመሰል የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች በማጋለጥ ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ ነው የተቀረፀው።
ዘንድሮስ
የዘንድሮው የዘመቻ ርዕስ የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት በአሁን ወቅት ካሉት ግንባር ቀደም የሕብረተሰብ ጤና ችግሮች መካከል በተለይም ለወጣቶች ጤና ተግዳሮቶች ከሆኑት ውስጥ ትምባሆ፣ ኒኮቲን እና ተዛማጅ ምርቶችን ማራኪነት/ሳቢነት ባላቸው መንገድ መቅረባቸው ነው።
የትምባሆ ኢንዱስትሪው እነዚህን ምርቶች አጓጊ ለማድረግ ሽታቸው፣ ጣዕማቸው ወይም መልካቸውን የሚቀይሩ ቅመሞችን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በመጨመር ያለማቋረጥ /Consistent/ ሙከራዎች በማድረግ የትምባሆ ምርቶች ጉዳት ለመደበቅ ጥረት በማድረግ ላይ በመሆኑ ነው።
በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም ጣዕም ያላቸውን ብዙ ኒኮቲኖች የትምባሆ ምርቶች ውስጥ በመጨመር ምርቶችን ለመጠቀም እንደ ቁጥር አንድ ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ። በመሆኑም እነዚህ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ጎጂ የሆኑ የትምባሆ ምርቶችን እና ሱስ የሚያስይዙ የኒኮቲን ምርቶቻቸውን በመጠቀም በተለይም ለወጣቶች ማራኪ እንዲሆኑ በማድረግ ስውር ስልቶችን ይጠቀማሉ።
በተለይ ማጣፈጫዎች /Additives/ የትምባሆ ጉዳትን ለመደበቅ የተነደፉ ስልቶች ሲሆኑ በዚህም በወጣቶች ያለውን ተቀባይነት /Palatability/ ለመጨመር በርካታ ሥራዎች እየሠሩ መሆናቸው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል ማራኪ ግብይት /Glamorized marketing/፡ ቄንጠኛ ዲዛይኖች፣ ማራኪ ቀለሞች እና ማራኪ ጣዕሞች በዲጂታል ሚዲያ ቻናሎችን ጨምሮ ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል ለመሳብ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጥቅም/ገበያ ላይ ያውላሉ።
አሳሳች ንድፎች /Deceptive designs/፡- አንዳንድ ምርቶች ጣፋጭ ጣዕም እንዲኖራቸው፣ ከረሜላዎችን እና ሌላው ቀርቶ ካርቶኑ/ፓኬቱ ላይ ማራኪ ምስሎች ይጠቀማሉ—ወጣቶች/ልጆች በተፈጥሯቸው የሚማርካቸው ነገሮች ይጠቀማሉ። ማቀዝቀዣች እና ተጨማሪ ማጣፈጫዎች /Coolants and additives/፡- እነዚህ ልምዶችን ምርቱ ሳቢ ያደርጉታል፣ ቀጣይነት ያለው ተጠቃሚነት እድል ይጨምራሉ እንዲሁም የማቆም እድልን በመቀነስ የዚህ ሱስ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ሰዎችን በተለይም ሕጻናትን እና ወጣቶችን ወደ ሱስ በመሳብ በጤና ዋጋ ላይ ከፍተኛ ትርፍ እያጋበሱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች እንደ ትልቅ ገበያ በመሆን የሚታዩ የኤሌክትሮኒክስ ሲጋራዎችን እና ሱስ አምጭ ኒኮቲን ፓኬቶችን ማራኪና ጣዕም ባላቸው፣ ቄንጠኛ እና ወቅታዊ ንድፎችን በመጠቀም፣ እንዲሁም እነዚህን ምርቶች እንደ አዝናኝ እና ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማሳሳት ‘ጉዳት የለሽ’ አስመስለው በማቅረብና ማራኪ ማሸጊያዎችን በመጠቀም ስልታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
እነዚህ የኒኮቲን እና የትምባሆ ምርቶች ሱስ የሚያስይዙ እና ተጠቃሚዎችን በጥገኝነት ዑደት ውስጥ በማጥመድ አጠቃቀሙን ለማስቀጠል የተነደፉ ናቸው። ማጣፈጫዎች የትምባሆ ጎጂ ባኅርያትን በመደብቅ በእጅጉን ይታወቃሉ፣ ይህም ለመጀመር ቀላል እና ሱስን ለማቆም አስቸጋሪ የሚያደርግ ባሕሪያቸው ተጠቃሽ ነው።
ይህ ስልታቸውም በማር የተለወሰ ሬት ተደርጎ ይገለፃል። በፈጠራና በቴክኖሊጂ የታገዙ አማላይ የማስተዋወቂያና የማታላያ ዘዴዎችም ወጣቶች ቀድመው ማጨስ ወይም ኒኮቲንን መጠቀም እንዲጀምሩ በማድረግ የዕድሜ ልክ ሱስኛ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር ለከፋ የጤና ችግር ያጋልጣቸዋል።
የትምባሆ ኢንዱስትሪው እነዚህን ምርቶች አጓጊ ለማድረግ፣ ከዕይታቸው ጀምሮ ያማሩ ሽታውን፣ ጣዕማቸውን ወይም መልካቸውን የሚቀይሩ ቅመሞችን እና ሌሎች ግብዓቶችን በመጨመር ያለማቋረጥ እየሞከረ ይገኛል። እነዚህ ስልቶች ትምባሆ በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመደበቅ ሆን ተብለው በጥንቃቄ የተነደፉ ናቸው።
የመፍትሄ እርምጃዎች
የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ለሕብረተሰቡም ግንዛቤ በመፍጠር የቁጥጥሩ ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ይህን የግንዛቤ ማስጨበጫ አካል የሆነውና በየዓመቱ ግንቦት 23 የሚከበረው በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን አንዱ ኩነት ነው።
ይህን የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ጣልቃገብነትና ድብቅ ሴራ ለማጋለጥ የዘንድሮ በዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን መሪ ሀሳብና ጭብጥ በመጠቀም የሕብረተሰቡን ግንዛቤን ማሳደግ ወሳኝ ተግባር ተደርጎ መወሰድ አለበት።
ሌላው የትምባሆ ምርቶችን ማስተዋወቅ እና ስፖንሰርሺፕ ሙሉ በሙሉ እገዳ እንደተደረገባቸው ለሕብረተሰቡ መረጃውን በማቀበል በተለይም ወጣቶች በትምባሆ ላይ ያላቸውን ፍላጎትን መቀነስ፣ በመጨረሻም ለኒኮቲን እና ለትንባሆ ምርቶች ያላቸውን ተጋላጭነት ትርጉም ባለው ደረጃ ማስረፅ በእጅጉ ያስፈልጋል።
በመሆኑም የዓለም የትምባሆ ቀን ከትምባሆ ነፃ የሆነ ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲኖር ግንዛቤን ለማሳደግ እና ለመደገፍ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ጣልቃገብነትና ድብቅ ሴራ ለማጋለጥ ሁሉም የዘመቻው ተወናይ መሆን ይኖርበታል።
ሰውቢሆን
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም