የሐረሪ ሕዝብ የሠርግ እና የሀዘን ሥርዓት

በለቹ የሐረሪ ሰርግ (ድግስ) ሥርዓት

የጋብቻ ሥነ – ሥርዓት ወይም ሠርግ ሠዎች በጋብቻ ውስጥ ለመተሳሰር ቃል የሚገቡበት ዝግጅት ነው። የሀዘን ሥነሥርዓትም ከሀዘን መገለጫ መድረክነቱ ባሻገር እንዲሁ ማኅበረሰቡ ማኅበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክርበት ነው። በመደጋገፍ፣ በመረዳዳተ ሀዘንተኞችን ደግሞ በማስተዛዘን ማኅበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክሩበት ነው። የጋብቻ እና የለቅሶ ሥርዓቶች በሁሉም አካባቢ የሚከወኑ በመሆናቸው ተመሳሳይ መልክ አላቸው። እንደየ ሕብረተሰቡ አኗኗራቸው እና ባሕል የሚለያዩበት መኖሩም መዘንጋት የለበትም። በተጨማሪም ሁለቱም የሕዝቡን ማኅበራዊ መስተጋብር ያጠናክራሉ። እንደዚሁም የሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤ እና ባሕል መገለጫ ናቸው። ሆኖም አከናወናቸው ከአካባቢ አካባቢ፤ ከቦታ ቦታም ይለያያል።

በመሆኑም ለዛሬ ይሄው ድባብ የሚንፀባረቅበትን የሐረሪ ሕዝብን ማኅበራዊ መስተጋብር በማጠናከሩ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ”በለቹ‘ የተሰኘ የሰርግ (ድግስ) ሥርዓት እንዲሁም ተወላጆቹ ”አሙታ” እያሉ የሚጠሩትን የሀዘን ሥነ-ሥርዓት ምን መልክ አለው የሚለውን የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ባሕል፤ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ያሳተመውን ጽሑፍ አገላብጠን ያገኘነውን እንደሚከተለው ልናስነበባችሁ ወደናል።

በለቹ በሐረሪ ሰርጉ ከሚይዛቸው ክንውኖችና አካሄድ ተጠቃልሎ የሚገለጽበት ቃል ነው። ታዲያ የወንዱ ወገን ለጋብቻ ጥያቄ ሲደርስ እንዲሁም የልጅቱ ቤተሰቦች ሲስማሙበት ከጥቂት ቀናት በኋላ የፍጥምጥሙን እለት በቀጠሮ ያስይዛሉ። በቀጠሮው እለትም የሙሽራ አባት ወዳጆች፤ እውቅና ያላቸው አዋቂዎች፤ የሙሽራው ጓደኞች ይገኛሉ። በሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት ባሕል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የሐረርና ሐረሪዎች ታሪክ በሚል በ2012 ታትሞ በወጣ በጥናት የተደገፈ መረጃ የብሔረሰቡ ተወላጅ መሀመድ አብዱረህማን እንዳሰፈሩት የልጅቷ ቤተሰቦችም በታላቅ ክብርና ማዕረግ ይቀበሏቸዋል።

በዚህ ዕለት በወሳኝነት የሙሽራው ቤተሰቦች የሙሽሪትን ቤተሰቦች ልጃቸውን ለልጃቸው (ስም በመጥቀስ) በቀጥታው በግልፅ እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ። ሁለቱም ወገኖች እዚያው ስምምነት ላይ ሲደርሱ በቦታው የሚገኘው ቃዲው (የሸሪአ ፍርድ ቤት ዳኛ) ያረጋግጣል። ወደዚሁም ለሙሽሪት የተዘጋጀው ስጦታ የአባቶች ጫት፣ ቀለበት፣ ልብሶች፣ ጣፋጮችና ገንዘብ እዚያው መድረክ ላይ ይቀርባሉ። የጋብቻ ሰርጉ ዕለትም ተቆርጦ ስምምነት ላይ ይደርስና፣ ቀኑ ሲደርስ ዘመድ አዝማድ በሁለቱም ቤት ይሰበሰባል።

እዚህ ጋር የልጅቱ ጓደኞች ተሰብስበው «አሩዝ መዋለል » የሰርግ ጥሪ ይከናወናል። «አያች ከረቡ» የእናቶች ጨዋታ ቅዳሜ ጠዋት ሲሆን «ዘገን ከረቡ» ደግሞ ከሰዓት በኋላ ይጨፍራሉ። ጨለም ሲል ‘አንቀር ማህጠብ’ በወጣቶች የአገቡት ጭምር (ከአባቶች በስተቀር) ሞቅ ይላል። በምሽቱ ‘ጥንስስ’ ወጣቶች ያላገቡት ብቻ ሥነሥርዓቱን ይጀምሩታል። የተጋበዙ ወጣቶች ብቻ በቡድን መጥተው ዘመናዊና ባሕላዊ ጨዋታ በአብዛኛው ሙሽሪት ሙሽራ ጓደኞችና ዘመድ አዝማድ ቤተሰቦች በዘፈኖች የሚሞገሱበት ምሽት ነው። ዋናው የሰርግ እለት እሁድ ጠዋት፣ ለእለቱና ለባሕሉ ኃላፊነት ያለበት ተቋም (አፎቻ የወንድና የሴቶች) በተለያየ መድረክ ኃላፊነቱን ይወጣል። ዋናው አፎቻ መውሊድ የነቢዩን (ሰዐወ) ዚክር ከጠዋት እስከ ቀትር ድረስ በደባል (የዚክር ጭፈራ) ይሞቃል።

ከዚያም በዕለቱ የተጋበዙ እንግዶች ምሳ ሥነ ሥርዓት ይሆናል። ከሰዓት በኋላ እሁድ ሙሽራው ከጓደኞቹ ከአባቶች ጓደኞችና እውቅ ሰዎች ጋር ሙሽሪት ቤት ይደርሳሉ። በመስመር ፊት ለፊት ይቀመጣሉ። ዱአ (ምረቃ) ተደርጎ፤ የሚጠባበቀው ሙሽራ ገባ ብሎ ሙሽሪትን ይወስዳል። ሙሽሪትን ከአስፈላጊው እቃዎቹ (ትራስ፡ ስፌቶች፤ ምንጣፎች እና ሌሎች) በአሩዝ መግበእ (ሙሽሪት በሽኝት) ሥነ ሥርዓት ትሸኛለች። ሙሽሪት ቤቷ የሙሽራው ጓደኞች ባሸበረቀች በቅሎ ላይ ተቀምጣ ወንድሟ በዣንጥላ እየጋረዳት ከኋላ ተደግፋ ትመጣለች። ከፊት በሙሽራው ጓደኞች ደባል (ጭፈራ) በኋላ በሙሽሪት ጓደኞች ”አው ቀሃቴይ” ዜማ ሙሽሪትን እያሞገሱ ወደ ‘አሩዝ ጋር’ ጫጉላ ቤት ደርሰው በናፍቆት የሚጠብቀው ሙሽራ ይቀበላል። በዚህ የተጋቡት በጓደኞቻቸው አጃቢነት ሞቅ ባለ ሁኔታ በጫጉላ የሚቆዩት አልፎ አልፎ የሙሽሪት ጓደኞች ይጎበኟታል ሲሉ የብሔረሰቡ ተወላጅ እና ታሪክ አዋቂው መሐመድ አብዱረህማን በሰነዱ ውስጥ ገልፀውታል።

በነጋታው ሰኞ የሚደረገውን አስመልክተውም እንደገለፁት፤ የሙሽሪት ቅርብ ጓደኞች ‘ሂና ጌላች’ አዲሱን ሕይወቷን ታሳቢ በማድረግ በእንኳን ደስ አለሽ መንፈስ፣ አንዳንድ የሚያስፈልጓትን የምትቀባባውና ይስማማታል ብለው ያሰቡትን ልብሶቿን ያቀርቡላታል። የሚቀርበው ልብስ ማግባቷን ሊገልጽ የሚችል ነው።

የአልባሳቱን ዓይነት አስመልክቶ እ.እ.እ በ1856 የፃፈውን መጻፍ ዋቢ በማድረግ በጽሑፉ እንዳሰፈረው ማንነትን አመልካች አንፀባራቂ ከሆኑት ቅርሶች አንዱ እንደ ቀንዲል ጮራ የሚፈነጥቀው በሚወረወር ብርሃን፣ ከሩቅ ሳይቀር የሚታየው፡ ውብ ንድፍ ያለው የሐረሪ አልባሳት ሲል የገለፀው ሁሉ በዚህ ጊዜ ይቀርባል። የሐረሪው አልባሳት ለልጃገረዶች፡ ለአገቡት፣ ለአዛውንቱና የሚለበሱት በግልጽ የሚለይ ሲሆን « ጠይ ኢራዝ” (ጥቁር ልብስ) ረዥም ሰፊ ከጥጥ የተሠራ ሀምራዊ ቼኮሌት፤ቀለሙ ባለ ንድፍ ሶስትዮሽ ቦግ ብሎ ከፍ ተደርጎ በነጭ መቀነት ወገብ ላይ ታስሮ ንድፉን የያዘው ወረድ ያለም አልባሳት ‘አጥላስ’ እና የፈከው ጀዊ ንድፍ ‘ጋር ወሪ’ የቤት በር ምስል ያሸበረቀው እነኚህ ሁለት አጥላስና ጀዊ ልብስ በአገቡት ሰዎች ለሙሽሪቷ ይቀርባሉ።

‘ኢናይ ገበታ’ የሠርጉ የመጨረሻው ሂደት ሲሆን እናቶች የሚያዘጋጁትና ሁለት ከፍ ከፍ ያሉ ጥቁር የእንጨት ገበታ በቅቤ የተራሰ በስሱ የተጋገረ የስንዴ እንጀራ ‘ዙሁቅ’ በዋቃሊም ተሸፍኖ ጫጉላ ቤትና የሙሽራው ቤተሰብ መኖሪያ ይቀርባል። እንግዶች ጎረቤቶች ገበታን አጣፍጠው ቁርስ ያደርጉታል። ይህ ማክሰኞ ንጋት ላይ የሚሆን ሲሆን እሮብ ”አባ-መጦራ‘ ተብሎ የወንዱ ሙሽራ ዘመድ እና ልጃገረዶች በውብ ስፌት የተከደነ ጣፋጭ ምግቦች ጫጉላ ቤት ያመጣሉ። በዚሁ እለት የሙሽሪት ወንድሞች በትልቅ «ሰህፋ ሀላዋ» (ጣፋጭ) ያመጣሉ። በዚሁም ዕለት ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ከሙሽሮች ጋር ይተዋወቃሉ።

ሐሙስ ከጫጉላ መውጫ እለት ነው። በዚህ እለት በሐረሪ ልዩ የሚሆነው ትኩረት የሚስበው ‘የጉፍታ መጎድ’ ሥነ ሥርዓት ስለመሆኑ መሐመድ አብዱረህማን በጽሑፉ ጠቅሰዋል። ሙሽሪት በርጩማ ላይ ተቀምጣ ወጣት ዘመድ አዝማዶች ከበዋት ፀጉሯን ትሰራለች። ሥነ ሥርዓቱ በዘፈን ይታጀባል። ፀጉሯ ሁለት ቦታ በግራ በኩል በቀኝ የተከፈለው ፀጉር ይታሰራል። የወደፊት ኃላፊነትና ሕይወቷን ያመለክታል። ዘፈኑ ቅብብሎሽ ‘መምሰስ መልሐድ’ በወንዱ በኩል በሴቷ በኩል ያሉት ሰዎች ይቀባበሉታል። ይህ ሥርዓት አሩዝ መውጠእ ይባላል፤ የጫጉላ ቤት ማብቂያ እንደማለት ነው ሲሉ ገልፀውታል።

አሙታ የሀዘን ሥነ-ሥርዓት

በሐረሪ ብሔረሰብ ሞት እንደተነገረ ጎረቤቶች፤ ዘመዶች ቅርብ ወዳጆችና ጓደኞች ይደርሳሉ። ሐዘንተኞች ሰው መሞቱኑን ለአፎቻው መሪዎች ያሳውቃሉ። የቀሩት አባላት በነጋሪ አባል አማካኝነት ይነገራቸዋል። ከወንዶች አፎቻ አባላቱ ከፊሉ ቁርዓን በሐዘኑ ቤት እስኪቀበር ድረስ ያነባሉ። አብዛኛው የአፎቻ አባላቱ ወደ መቃብር ይሄዱና መቃብሩን ያዘጋጃሉ። የሴቶች አፎቻ ግን ሞቱ እንደተሰማ ‘ከፋራ እንጨት’ የሚባል ይዘው ‘ሲሪ’ ባሕላዊ ቂጣ፣ በመቃብር ሂደት ውስጥ የሚከፋፈልና ከሟች ቤተሰብ የእንባ አድርቅ ተደርጎ የሚታደል ይዘጋጃል።

በአሙታ ሥነ ሥርዓት ሟቹን አስክሬን በማጠብ ይጀምራል። ውስብስብ ሥራ አስክሬኑን የተለያዩ ቅባቶች በመጠቀም መላ ሰውነቱ ለማንቀሳቀስና መዘርጋት ማጠፍ ይከናወናል። ይህ ተግባር በዝግና ግርዶሽ በአዋቂ ሰዎች ብቻ የሚከናወን ስለመሆኑ መሐመድ አብዱረህማንን ዋቢ በማድረግ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ባሕል፤ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የታተመው ጽሑፍ እኛም ለሠርጉም ለሀዘኑም እንደ ምንጭ ተጠቀምንበት ጽሑፍ አስፍሮታል።

ታዲያ እንደዚህ ጽሑፍ አስክሬኑን ማጠቡና መሸፈኑ (መገነዙ)፤ የመቃብር ቁፋሮው ሲጠናቀቅ ከመቃብር የመጡትና ቁራን አንባቢው ሲፈጽሙ መዘጋጀቱን አረጋግጠው ቀሪው ቀብር የሄደው ቡድንም ሌሎች ታክሎ ወደ ሟች ቤት መጥተው አስክሬኑን በተዘጋጀ የእንጨት ጠፍር አልጋ የተሠራው የአስክሬን መሸከሚያ ‘ዳዋእ’ አድርገው በመውሰድ በእስልምና ሕግጋትና ትዕዛዝ መሠረት ቀብሩ ይፈፀማል። በሟች መኖሪያ ቤት የተሰበሰቡት ሴቶች ቀብሩ ተፈጽሞ ቀባሪዎች ተመልሰው መኖሪያ ቤት ሲደርሱ በሥነ ሥርዓቱ ዳዋእ ተደርጎ በሥነ ሥርዓቱ ፍፃሜነት ይበተናሉ። የቅርብ ዘመዶች፣ ለሦስት ቀን ያህል ቤታቸውን ትተው ከሐዘንተኛው ቤተሰብ ጋር ሐዘኑን ሲያስተዛዝኑ ይቆያሉ። ወንዶች ሁሉ በአንድ ቦታና ክፍል፣ ሴቶች በሌላ ክፍል ተለያይተው ይቆያሉ እንጂ አይቀላቀሉም። መቀመጡ በሦስት ቀናት በጠዋቱ ሀዘን የሚደርሱትን መቀበል ነው።

በተለምዶው የሴቶች አፎቻ በሦስት ቀናት ‘ቁራን ገበታ’ ሲያዘጋጁ ወንዶች አፎቻ በሦስት ቀናት መግሪብና ኢሻኢ መሐል ቁራን ያነባሉ። የሀዘን ሥነ ሥርዓቱ የሚደመደመው አፎቻቸው በመቃብሩ ‘ቀብሪ ኡን’ አራት ማዕዘን ድንጋዮች መቃብሩን የሚለይ ምልክ ቶች ሲያስቀምጡ ይሆናል።

በሐረሪ ባሕል በሠርጉም ሆነ በሀዘኑ በተለያየ መልኩ የተቋቋሙ ባሕላዊ ተቋማት ጉልህ ሚና አላቸው። የወንድማማች ጎልማሶቹ እስከ አዋቂዎች ጀማአ ድረስ ያሉት እነዚሁ ባሕላዊ ተቋማት በተለይ በሀዘንና በሰርግ የሐረሪውን ሕይወት በራሳቸው ያራምዳሉ። ሥነ-ሥርዓታዊ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡን በማሰባሰብ፤ ምቹ የሆነ ምህዳር በመፍጠሩ ለሕዝቡ የሐረሪውን እሴቶች በማስጨበጡ እና በማራመዱ አስተዋጾአቸው የጎላ ስለመሆኑ በጽሑፉ ውስጥ ሰፍሯል።

ባሕላዊ አፎቻ አቢይ ተግባሩ ሥራው የሀዘንና የሠርግ ሥርዓትን ማስፈፀም ስለመሆኑም ተጠቅሷል።

ሙጋድ ጉዳይ፤ (ጡንስስ) የሠርግ ጊዜ ጨዋታም በመምራት እና በማድመቁም አስተዋጾው ከፍተኛ ነው። በደምሳሳው እነኚህ ባህላዊ ተቋማት የሐረሪውን ማንነት ማቆየት የሕብረተሰቡን አንድነት ማጠናከር፤ በባሕላዊው ልማድ ተመስርቶ ማንነትን መቅረጽ ማቆየትና ማበልፀግ ላይ ያላቸው ተሳትፎም ጉልህ ስለመሆኑ በጽሑፉ ሰፍሯል። ቅራኔ የመፍታት፣ ለምሳሌም ውርስን የማከፋፈል፤ ፍቺ የመገላገልና ሰላምን ማስፈን እና ሌሎች መሰል ተግባራት ማከናወን ከተግባራቱ የሚጠቀሱ ስለመሆናቸው በጽሑፉ ተጠቅሷል።

ሠላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You