የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከሰኔ 22 ምሽት ጀምሮ ግጭት ጠማቂዎች ባስነሱት ሁከትና ነውጥ አያሌ ንፁሀን ወገኖቻችን ሕይወታቸው አልፏል፤ የጸጥታ አካላት ተገድለዋል። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የግለሰቦች፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ዶግ አመድ ሆኗል። ብዙዎች በከባዱ ጨለማ የሐምሌ ክረምት ቤት ንብረታቸውን አጥተውና ተፈናቅለው የእርዳታ እጅ ጠባቂ ሆነዋል። በሁከቱ ያጡትን ቤተሰባቸውን ኀዘን እንኳን ለማዘንና ለመጽናናት ተስኗቸዋል። ይሄ ሁሉ ግፍ የተፈጸመው በሴራ ጠንሳሾች እና የእነሱን ተልዕኮ ለማስፈጸም በተንቀሳቀሱ ኃይሎች ነው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ወንጀለኞች ህዝብን እንዳሰቃዩና እንዳስለቀሱ፤ የሀገርን ሰላምና ደህንነት እንዳመሱ አልቀሩም። ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በወንጀሉ የተጠረጠሩ እና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች፣ አመራሮች እና የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ≪አይነኬ≫የሚመስሉ አንዳንድ ታዋቂ ግለሰቦች እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጭምር በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በህግ አግባብ እየታየ ይገኛል። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው።
ማህበረሰቡም ከመንግሥት ጎን በመሆን ወንጀል ሰርተው ስርቻ ለመግባት የተሯሯጡትን ሁሉ አጋልጦ በመስጠት ለህግ መከበር አጋርነቱን አሳይቷል። በዚሁ መሰረት በአጭር ቀናት ውስጥ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ገዳይና ተባባሪዎች በቁጥጥር ሥራ ማዋል መቻሉን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በወቅቱ አስታውቋል። አሁንም ቢሆን ማንኛውም ወንጀል የሚፈጸመው በህብረተሰቡ ውስጥ በመሆኑና ምንም ነገር ከህብረተሰቡ የተሰወረ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት እንዲሁም በቀጣይ ተመሳሳይ የሆነ ችግር በየአካባቢው እንዳይፈጠር የጀመረውን
የትብብር ሂደት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። የራሱንና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በማስከበር በኩል የበኩሉን ሚና መወጣትም አለበት። ከመንግሥት ጎን ቆሞ የሚያደርጋቸውንም ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ህግን ከማስከበሩና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ደግሞ ትልቁ ሥራ መሆን ያለበት ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸውንና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መደገፍና ማቋቋም ነው። በዚህ ዙሪያ መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የተጎዱትን ለማቋቋም እንደሚሠራ አስታውቋል። መንግሥት ከሚሰራው ሥራና ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ከተጎዱ ወገኖቻችን ጎን መቆምና አለኝታነታችንን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ማሳየት ይጠበቅብናል። ኢትዮጵያዊ ርህሩህ አዛኝና ለጋስም ነው። ይሄንን ባህሪውን በተለያየ ጊዜ በሀገራችን የተለያዩ ችግሮች ባጋጠሙ ጊዜ አይተናል፤ አስተውለናል። እቁብ፣ እድር፣ ማህበር የመሳሰሉት ማህበራዊ መስተጋብሮቻችን ሁሉ የመረዳጃ መስመሮቻችን ናቸው።
ያዘነን በማስተዛዘን ፣ የተቸገረን በመርዳት፣ በሀብት ንብረቱ ላይ አደጋ ያገጠመውን በማቋቋምም አጋርነታችንን አስመስክረናል ። ዛሬ ለገጠመን ችግርም ይሄ አጋርነት ወሳኝ ነው። በዚህ ወቅት ነው ማንነታችንን ይበልጥ በትክክል የሚመሰክረው።
በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ለተጎጂ ወገኖቻችን የተቃጠለና የወደመ ንብረታቸውን በመተካት አጋርነታችንን እናሳያቸው፤ ቁስላቸው ጠገግ እስኪል እናክማቸው፤ ከአስከፊው የሐምሌ ጭለማ፣ ቁርና ብርድ ወጥተው የነበረ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እንዲኖሩ የፈራረሰ ቤታቸውን ልንገነባላቸው ይገባል። የተጎዳን ወገን በኢኮኖሚም በስነ ልቦናም መደገፍ፣ ያዘነን ማስተዛዘን ባህላችን ነው። ይሄ ባህላችን ያለ የነበረና የሚኖር ቢሆንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ ፈጥኖ መድረስ የግድ ይላል። የምንታወቅበትን ባህል በተግባር በማሳየትም ለወገኖቻችን መድረስ ቀጠሮ ልንይዝለት የሚገባ ተግባር አይሆንም።
በሁሉም ዘርፍ ያሉ መሪዎች ለዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሆነው መልካም አርአያ መሆን አለባቸው። ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው፣ በየመጠለያው ያሉ ተጎጂ ወገኖቻችንን በሞራል፣ በኢኮኖሚና በባህላዊ መንገድ ደግፈን ወደነበሩበት እንዲመለሱም ተባብረን ልናቋቁማቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012