ብዙዎች ከእጁ በማይጠፋው ፒፓው ያውቁታል፤ ጉንጩን በፍጥነት ወደ ውስጥ አንዴ ወደ ውጪ እያለፈ ካፉ የሲጃራውን ጭስ ያንቦለቡለዋል። አይደክምም። በዓለም ላይ ከታዩ ጥቂት ባለ ልዩ ተሰጥኦ እና ለውጥ አራማጆች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ መካከል ይመደባል። ሲግመንድ ፍሮይድ ይባላል፣ ኑሮውን ቬና አድርጎ ለዓለም እና ለሰው ልጅ በሙሉ አዲስ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰደውን እሳቤዎቹን በሰፊው በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አበረከተ።
ወቅቱም ጠንካራ የሳይንስ አብዮት የተነሳበት እና በሚኖርበት ከተማም ህዝቡ ጥብቅ በሆነ ባህል ስር የታጠረ ነበር። መለስ ብለን ካየን ኒኮላስ ኮፐርኒከስ ምእራባውያንን ያስደነገጠ እና ተቃውሞ ያስነሳበትን መሬት ሳትሆን ፀሐይ ነች ማዕከሏ የሚለው ሀሳብ ብዙዎቹ በሚያውቁት ነገር ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አደረገ። ቀጥሎም ዳርዊን ሰው በአካባቢው ላይ ያለውን እውቀት ብቻ ሳይሆን በራሱም አመጣጥ ላይ የነበረውን እውቀት ናደው፤ ሰውም ሆነ ሌላ ፍጡር በዝግመተ ለውጥ ውስጥ እዚህ፣ አሁን እምናየው ላይ መድረሱንና ቀጥሎም ከአካባቢው ጋር በሚያደርገው መስተጋብር ራሱን እያዳበረ እንደሚሄድ ተናገረ፤ እኛ ሰዎችም የተለየን ሳንሆን ከሌሎች የእንስሳት ቤተሰብ መገኘታችንን አረዳን።
በመጀመሪያ አካባቢያችሁን አታውቁም፤ የምታዩት እንደምታዩት አይደለም ተባልን። ቀጥሎም ይሄ አይብቃችሁ ዘራችሁ ከጦጣ (ቺንፓዚ) የተለየ አይደለም ተባልን፤ ታዲያ ማሳረጊያውን ባለፒፓው ፍሮይድ ይህ አይግረማችሁ ራሳችሁን እራሱ ራሳችሁ አትቆጣጠሩትም፤ በራሳችሁ ላይ የማዘዝ ስልጣን የላችሁም፤ እነሆ በድብቁ አዕምሮ ክፍል ባለፋ ግን በተቄሙ ትውስታዎች ቁጥጥር ስር ናችሁ አለ።
ይህ እንግዲህ ከፍልስፍና ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በሳይካትሪው እና ሳይኮሎጂው ዓለም በመጠኑም ቢሆን ሳይንሳዊ ይዘት ያለው ንድፈ ሃሳብን ያስገኘ ስራ ነበር። ፍሮይድ ከብዙ ጉዞ በኋላ ጀርመን በመግባት በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።
ስራዎቹም ባለፈ የግል ህይወቱ ተጽእኖ ስር የዋሉና በዘመኑ አስተሳሰብ የተቃኙ ናቸው። በዚህ ጽሑፍ ላይ በጣም በተመጠነ መልኩ ከሰፊው የሲግመንድ ፍሮይድ ህይወት እና ስራ ቆንጠር አድርገን እናቀርባለን። በመጀመሪያ ስለልጅነት እና የቤተሰብ ታሪኩ ካወራን በኋላ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ጠቅለል አድርገን መሰረታዊ ንድፈ- ሐሳቦቹን ዳሰን ጉዟችንን እናጠናቅቃለን።
ሲግመንድ ፍሮይድ በያኔዋ ፊርቡርግ፣ ሞሪቪያ ባሁኑዋ ቺኮዝላቫኪያ በ1856 ከአይሁድ ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን፣ ለቤተሰቡም ከአባቱ ሁለተኛ ሚስት የተገኘ የመጀመሪያ ልጅ ነው። አብረውትም አምስት እህት እና ሁለት ወንድም ይኖሩ ነበር። ለአባቱ ጠንከር ያለ ጥላቻ የነበረው ሲሆን አብዝቶም ወደ እናቱ የቀረበ ነበር።
ለዚህም ነው ራሱ ባወጣው ንድፈ ሃሳብ ተጠቅመው አንዳንዶች ፍሮይድ ኦዲፐስ ኮምፕሌክስ (በልጅነት ጊዜ ለናት የተለየ እና የበዛ ቅርበት ሲኖር፣ ይሄም በቀጣይ ህይወት ላይ ተጽዕኖ ሲያሳድር) አለበት የሚሉት። ፍሮይድ ሲበዛ ቁምነገረኛ ነው። እናም ብዙውን ሰዓት ትምህርቱን በማጥናት ያሳልፋል፤ ቤት ገብቶም ከንባብ ውጪ ምንም አይነት ሥራ እንዲሰራ አይፈቀድለትም ነበር፤ ሲያነብም እንዳይረበሽ በማለት ሙሉ የቤተሰብ አባል በፀጥታ ይዋጣል፤ እጅ በደረት ያህል።
ታዲያ ፍሮይድ ያነበባቸውን፤ የሰማቸውን ሳይንሳዊ ውጤቶች ለቅሞ ይመዘግባል፤ አብዛኛውን ጊዜ ሙሉ ይዘቱን ሳያጓድል ነበር የሚገለብጠው (የሚቀዳው)፤ በአጭሩ እጅግ በጣም ጥሩ የማስታወስ፤ የመያዝ ችሎታ ነበረው ማለት ይቻላል። ከሚያነባቸውም መጽሐፍት የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፤ የተውኔት ድርሰቶችን፣ ግጥም፣ ፍልስፍና፣ እንዲሁም የእነጎቴህ፣ ሄግል፣ ሼክስፒር፣ ካንትን የመሳሰሉ እውቅ ሰዎች ስራዎችን ለንባቡ ይመርጥ ነበር።
በወጣትነት ጊዜውም ቬየና ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሎ በ1881 የህክምና ዶክተሬቱን አግኝቷል። ከአምስት ዓመት በኋላም ማርታ ቢርናስ የተባለችውን ወይዘሪት በማግባት ሶስት ወንድና ሶስት ሴት ልጆች አፍርቷል። ከማርታም ጋር ፍቅር እንደነበረው ራሱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይነበባል። በኋላም ላይ ባለቤቱ ስትሞት የቀረውን ህይወቱን ከመጀመሪያ ልጁ አና ፍሮይድ ጋር ነበር ያሳለፈው።
ከአናም ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረው፣ የሳይኮ ዓናሊስስን ፈለግ እንድታስቀጥል አድርጓል፤ አናም ለጋብቻ ራሷን ሳታቀርብ ሳይኮዓናሊስስን ኑሮዋ አድርጋው ነበር እስከ እለተ ሞቷ የቆየችው። በርከት ያሉ የምርምር ስራዎችን ይሰራ የነበረው ራሱ ከስነ-ልቦና ችግር ነፃ ሆኖ አልነበረም። እንደሚታወቀው አንዳንድ የፈጠራ ባለሙያዎች በአእምሮ መታወክ እና ተያያዥ የነርቭ ችግር ሲሰቃዩ ይስተዋላል።
ፍሮይድ እና ንድፈ ሐሳቦቹ ስለ ግለ-ታሪኩ ይሄን ያህል ካልን ከቆየን በቀጥታ ወደ መሰረታዊ የሰው ልጅ አረዳዱ እና ሳይኮሎጂካል ይዘቱ እንግባ። የባለፒፓውን ንድፈ ሀሳብ ወይም ቲዎሪ በእንግሊዝኛው ዲተርሚኒስቲክ ነው እያሉ ይጠሩታል፤ ይህ ማለት የሰው ልጅ ባህሪ በአንድ በሌላ ነገር፣ ሁኔታ የተወሰነ ነው እንደማለት ነው። ይህ ሁኔታ ግን ከሰውዬው ውጪ ሳይሆን በግለሰቡ ውስጥ ያለ ስነ-ሕይወታዊ (ባዮሎጂካል) ሃይል ነው።
ሌላው ከጨቅላነት ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት ባለው እድሜ ውስጥ የሚፈጠሩ አስቸጋሪ ኩነቶችን ወደ ድብቁ አምሮአችን በማስገባት (በማቄም) ቀጣይ ህይወታችንን እና ማንነታችንን ሲሰሩት ይኖራሉ ይላል ፍሮይድ።
በፍሮይድ አገላለጽ የሰው ልጅ፣ ኢአመክንዮአዊ (እንስሳዊ ባህሪ) ወይም ደመ-ነፍሳዊ፣ ረብሸኛ፣ እና ስሜታዊ (ሴክሽዋል) ነው፤ በዚህ የተነሳ ጨለምተኛው ቲዎሪስት እየተባለ ይጠራል።
ሳይኮዓናሊስስ አራት አምዶች ሲኖሩት ከእነዚህም የመጀመሪያው መልከዓ-አይምሮ ወይም በእንግሊዝኛው ቶፓግራፊ ሲሆን በውስጡም ሶስት መልኮች፣ ንብርብሮች ይዟል፣ እነዚህም ንቁ አዕምሮ፣ ቅድመ ንቁው አዕምሮ ወይም በከፊል የነቃው እና ያልነቃው አዕምሮ ናቸው። ሁለተኛው የስብእና መዋቅር ሆኖ በአንድ ሰው ሰብዕና ውስጥ ሶስቱ በሚያደርጉት መስተጋብር የግለሰቡ ባህሪ እንደሚቀረፅ ባለፒፓው ያምናል። እነዚህም፡- ኢድ፣ ኢጎ፣ እና ሱፐር ኢጎ ናቸው። ሶስተኛው የስብዕና እንቅስቃሴ ነው (ዲፌንስ ሜካኒዝም፣ ሊቢዶና የመሳሰሉትን ያካተተ ነው)፣ እናም የመጨረሻው እድገታዊ ደረጃዎች ናቸው (እነዚህም ኦራል፣ ፋሊክ፣ ላተንትና ጄነታል) ናቸው። ሙሉ ንድፈ ሃሳቡን ማየት ለአሁን ባይቻልም ለዛሬ ይህን ያህል እንደመነሻ ካልን ላሁን በዚህ አበቃሁ፤ ሰናይ ጊዜ ይሁንላችሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ኖኅ ውብሸት