መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የኮሮና ተጠቂ በኢትዮጵያ መገኘቱ ይፋ ተደረገ። ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ ኮቪድ 19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያደርስ የነበረው ጉዳትና ሲታይ የነበረው ፍርሃት ይታወቅ ነበርና ቫይረሱ ወደ ሃገራችን መግባቱ ሲሰማ ድንጋጤው ትልቅ ሆነ።
ከዚህ ክስተት በኋላ ወዲያውኑ በሚባል ሁኔታ መንግሥት ት/ቤቶች እንዲዘጉ ወሰነ፤ የጥንቃቄ እርምጃዎች ያለምን ማወላወል እንዲወሰዱም አሳሰበ። የግድ ቢሮ የሚያስገባ ሥራ ከሌለ በስተቀርም ሠራተኞች ቤት ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲመቻችም ታዘዘ። በዚህ ሁኔታ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ቢታሰብም በኅብረተሰቡ ዘንድ ይታይ የነበረው መዘናጋት ግን አሳሳቢ ነበረና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጠበቅ ባለ ዲስፕሊን እንዲከበሩ ተወሰነ።
በዚህም መጠጥና ጭፈራ ቤቶች እንዲዘጉ፣ ተሽከርካሪዎች ከመጫን አቅማቸው በግማሽ ብቻ እንዲጭኑ፣ የሃገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት ዋጋ ከፍ በማድረግ የህዝብ ምልልስ እንዲቀንስ፣ በሆቴሎችና ካፍቴሪያዎች በአንድ ጠረጴዛ ከሦስት ሰዎች በላይ እንዳይስተናገዱና ከቤት ውጭ ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ተደነገገ።
የእነዚህ መመሪያዎች መውጣትና ኮሮና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በጣሊያን፣ ስፔንና አሜሪካ እያደረሰ የነበረውን ጉዳት በመስማት ይመስላል የኮቪድ 19 በሃገራችን መከሰት የመጀመሪያ ሰሞን ኅብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር በኩል ያሳየው ፈጣን ምላሽ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። ሳኒታይዘርና አልኮል ለመግዛት በየመድሃኒት መሸጫ የነበረው ሰልፍ፣ ወጣቶች ተደራጅተው ሲሰሩት የነበረው እጅ የማስታጠብ አገልግሎት ወዘተ የወረት ተግባር ቢሆኑም የጥንቃቄ እርምጃው በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ግለቱ ከፍተኛ እንደነበር ግን አይታበይም።
ይሁንና በዚያም ወቅት ቢሆን የጥንቃቄ እርምጃዎቹን አወሳሰዱ ከቦታ ቦታና ከጥንቃቄ መንገዶች አንጻር
ወጥነት የጎደለውና ያልተሟላ ነበር። ከዚህ አንጻር በተለይም በእጅ መታጠብና በማስክ አጠቃቀም ዘሪያ የታዩ ጠንካራ አተገባበሮች ቢኖሩም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ይታይ የነበረው የጥንቃቄ እርምጃ አወሳሰድ ክፍተት ሰፊ ነበር።
የእኛ መዘናጋት በጨመረ ቁጥርም የኮቪድ 19 የስርጭትና የጥቃት መጠን እየጨመረ መምጣቱ እውነት ሆኗል። መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም አንድ ብሎ የጀመረው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከአምስት ወራት በኋላ 8,181 ሲደርስ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎቻችን ቁጥርም 146 ሆኗል። ከዚህ ቁጥር በላይ አስደንጋጩ ነገር የቫይረሱ የስርጭት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳየው ፍጥነት ነው። ቀድሞ በቀን 1 እና 2 ብሎም 8 አካባቢ የነበረው በቫይረሱ የመያዝ መጠን ዛሬ ላይ ግን በቀን ከሁለት መቶ የሚወርድበት እድል እጅግ ጠባብ ሆኗል።እንደ ጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጀ ድጉማ ወቅታዊ መረጃ ደግሞ በተለይም በቅርብ ጊዜ እየታዩ ያሉ መዘናጋቶች ሃገራችንንና ህዝባችንን ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ ይገመታል።
እውነት ነው ኮቪድ 19ን በመከላከል ረገድ በተለይም በቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው መዘናጋት እጅግ አሳሳቢ ነው። በየአካባቢው ተቀምጠው የነበሩ የእጅ መታጠቢያዎች ከፊሎቹ ተነስተዋል። ሌሎች ደግሞ የውሃና የሳሙና ድርቅ መቷቸዋል። በመጠጥ ቤቶች አካባቢ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በርከት ብሎ መዝናናት ህጋዊ የሆነ መስሏል። ማስክ አጠቃቀም ላይ ያለ ጥንቃቄም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄዷል። በገበያና በአንዳንድ የእምነት ተቋማት አካባቢ ያለው የህዝብ አጀብም ኮሮና ከሃገራችን ጠፍቷል ተባለ እንዴ የሚያስብል ነው። ቀድሞውንም ቢሆን ያላማረው ከአዲስ አበባ ውጪ ያለ የጥንቃቄ መላላት ዛሬ ላይ ምን ደረጃ እንደደረሰ ለመገመት ከባድ አይሆንም።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ደግሞ በተለይም በሴራ ፖለቲካ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያና ግድያውን ተከትሎ የተከሰተው ውጥንቅጥ በቫይረሱ መከላከልና ጥንቃቄ ሂደት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል። በዚያን ሰሞን የነበሩ ሰልፎችና የህዝብ አጀቦች ላይ ሲታይ የነበረው የጥንቃቄ ጉድለት ኮሮና ነገ የከፋ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል የሚያመላክት ነው። ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞም መገናኛ ብዙሃን በቫይረሱ ስርጭት ዙሪያ ያሳዩት መለሳለስ የሽፋን መቀነስም እጅግ አሳሳቢ ነው።
በአጠቃላይ በኮቪድ 19 ዙሪያ አሁን ላይ የሚታየው አገራዊና ህዝባዊ መዘናጋት እጅግ አስፈሪ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ረፈደ እንጂ አልመሸምና አሁኑኑ ነቃ ብለን ወደ ቀልባችን በመመለስ እና የረሳነውን እሱ ግን ያልረሳንን የኮቪድ ቫይረስ ስርጭት መግታቱ ላይ እንስራ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2012