በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር አመቺ ጊዜ ላይ ትገኛለች:: ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲሱ የለውጥ አመራር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አበረታች ቢሆኑም ሀገራችን ያላት ውስብስብ ችግር በቀላሉ የሚፈታ አይደለም:: ይሁን እንጂ በሀገራችን ብዙ ትኩረት የተነፈጋቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ:: ከእነዚህ መካከል አምስቱ ይበልጡን አንገብጋቢ ናቸው:: አምስቱን አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፦
1. የሥነ-ህዝብ ጉዳይ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ 110 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ያላት ግዙፍ የአፍሪካ ሀገር ናት:: በዚህም በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች:: በ2.5% የሚጨምረው የሀገራችን የህዝብ ቁጥር በየዓመቱ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይጨመርበታል:: የውልደት ቁጥር በሚፈለገው መጠን አለመቀነስና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሚፈለገው መጠን አለመዳረስ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው የሀገራችን የህዝብ ቁጥር በአፍሪካ 2ኛና በዓለም 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል:: በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የዓለም የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛውንና ከ50% በላይ ድርሻ ከሚይዙ 9 ሀገራት 5ቱ አፍሪካ ውስጥ ሲሆኑ አንዷ የኛዋ ኢትዮጵያ ናት:: እንደ ግሪጎሪያን የጊዜ አቆጣጠር እ.ኤ.አ. በ2050 የዓለም የህዝብ ቁጥር 9.8 ቢሊዮን ይደርሳል:: የሀገራችን የህዝብ ቁጥር ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2050 168.8 ሚሊዮን ይሆንና ከዓለም አስረኛዋ የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ትሆናለች:: በተለይ በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል በአንድ ካሬ ኪ.ሜትር የሚኖረው የህዝብ ቁጥር በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ በመሆኑ የህዝብ ጥጊጊቱ ወደ አሳሳቢነት ደረጃ እየደረሰ ነው:: በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ የምትመደበው ሀገራችን እንደዚህ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ላለው የህዝብ ቁጥር የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት እጅግ አዳጋች ይሆንባታል:: እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ተርታ ለመመደብ ያወጣችው ዕቅድም ገቢራዊ መሆን አይችልም:: በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሬት ለምነት መቀነስና ጥበት ምክንያት የሚሰደደው ትውልድ ለከተማማ አካባቢዎች ፈታኝ እየሆነ መጥቷል:: 70% የሚሆነው ከ30 ዓመት በታች የሆነው ትውልድ ሥራ ፈላጊ ነው:: የስራ ዕድል ፈጠራውም በሚፈለገው መጠን ባለማደጉ ይህ የስራ- አጥ የመሆን ዕድል ያለው ትውልድ ለፀጥታ ችግር፣ ለወንጀልና ለስደት ይዳረጋል:: የሀገራችን ነፍስ-ወከፍ ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል:: ማህበራዊ ቀውሶች ይበረክታሉ:: በእነዚህ ዝርዝር ምክንያቶች መንግስት በስነ-ሕዝብ ላይ አተኩሮ መስራትና ራሱን የቻለ የስነ-ሕዝብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቋቁሞ የህዝብ ቁጥሩ እንዲረጋጋ ማድረግ ይኖርበታል::
2. የማህበራዊ ጉዳዮች ነገር
ማህበራዊ ችግሮች ለሌሎች ችግሮች እናት ናቸው:: ብዙ ሀገራዊ ችግሮች መሠረታቸው ማህበራዊ ችግር ነው:: በእኔ እምነት መሰረት ላይ ያለው ማህበራዊ ዘርፍ ስለተዘነጋና ሌሎች ችግሮች ላይ በማተኮራችን ችግሮች ከስር መሠረታቸው መቅረፍ አልተቻለንም:: ማህበራዊ መሠረተ-ልማቶች ስላልተሟሉ የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የአከባቢያዊ ችግሮች ሆነው ብቅ ይላሉ:: ለምሳሌ፦ በአንድ አካባቢ ማህበራዊ አገልግሎት ባለማግኘቱ አንድ ዜጋ የሲጋራ ሱስ ተጠቂ ቢሆን የሲጋራ ሱሰኝነት በሚያመጣው ካንሰር ይጠቃና ለጤና ችግር ይዳረጋል:: በሁለተኛ ምሳሌ፦ ወጣቱ የህዝብ ክፍል ስራ-አጥ ሲሆን ስራ-አጥነት የሚባል ማህበራዊ ችግር ይፈጠርና ስራ አጥ የሆነው ወጣት በተለያዩ ወንጀሎችና ጥፋቶች ላይ ይሰማራና የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮች ይፈጥራሉ:: ሱሰኝነት፣ ስደት፣ ፍቺ፣ ስርዓት አልበኝነት፣ ተባብሮ ወንጀል፣ ፀጥታ አለመረጋጋትና ስራአጥነት ማህበራዊ ችግሮች ናቸው:: እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ሲቀሩ ግን ሌላ ዓይነት ችግር ሆነው ብቅ ይላሉ:: አሁን ላይ ያለው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና የደሃ ደሃዎች ላይ በማተኮሩ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል ቁመና ላይ አይገኝም:: በዚህ ምክንያት ማህበራዊ ተቋሙን በሰፊው አደራጅቶ ማህበራዊ ችግሮችን አንድ በአንድ መፍታት የሚችልና ወደፊት እየበዙ የሚሄዱትን ማህበራዊ ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ጊዜውን ያሳለጠ ቁመና ያስፈልገዋል::
3. የልዩ ክህሎትና ተሰጥዖ የማሳደግ ጉዳይ
ከሰላሳ በላይ ልዩ ተሰጥዖዎችና ተውህቦዎች አሉ:: 2-10% የሚሆነው የህዝብ ክፍል ልዩ ተሰጥዖ አለው:: ለእነዚህ ልዩ ተሰጥዖ ላላቸው ዜጎች ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የተለየ የትምህርት ስርዓት ያስፈልጋቸዋል:: በሀገራችን ኢትዮጵያ ልዩ ተሰጥዖን መሠረት ያደረገ ትምህርት አይሰጥም:: ጠቅላላ ትምህርትን መሠረት ያደረገው የትምህርት ሥርዓታችን ልዩ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች አመቺ አይደለም:: ሁሉም ትውልድ በአንድ ዓይነት የትምህርት መስመር እንዲያልፍ ይደረግና ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ሲደርሱ ባመጡት ነጥብ ተወዳድረው የት/ት መስክ ላይ ይመደባሉ:: የትምህርቱ መስክ በውድድር እንጂ በክህሎት አይደለም:: ወጣቶች በአብዛኛው በቶሎ ሥራ የሚያስገኝ የትምህርት መስክ ላይ ስለሚሰማሩ ውስጣቸው ያለው ልዩ ተሰጥኦ ይኮመሽሻል:: ለሀገር የሚኖራቸው ልዩ አበርክቶ ወደ ገደል ይገባል:: ሀገርም ከየትውልዱ የምታገኘውን ታጣለች:: ለዚህም የልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ዜጎች ለሀገራቸው ልዩ አበርክቶ እንዲያደርጉ የሚያስችል የተለየ የትምህርት ስርዓት ከመደበኛው በተጨማሪ ሊቀረፅና ሊተገበር ይገባል::
4. የምግብ ዋስትና ጉዳይ
ለሰው ልጅ በህይወት መቆም ምግብ አስፈላጊ ነው:: የሰው
ልጅ በዛ ቢባል ያለምግብ ለአስራ አምስት ቀናት ብቻ ይቆያል:: በሀገራችን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማስጠበቅ የሴፍቲ-ኔት የውጪ ድጋፍ ይገኛል:: 22% አካባቢ የሚሆነው የህዝባችን ክፍል በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይገኛል:: በ2017 እ.ኤ.አ እንደ የተባበሩት መንግስታት ጥናት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦች 70% የሚሆነውን ገቢያቸውን ምግብ ላይ ያውላሉ:: እንደዚህ አብዛኛውን ገቢያቸውን ምግብ ላይ አውለውም የምግብ ዋስትና ችግር በከፍተኛው ሰለባ ናቸው:: በእነዚህ ምክንያቶች ሀገራችን የምግብ ዋስትና ማስጠበቅ ፈተና ሆኖባታል:: በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የመሬት ለምነት መቀነስና ጥበት የምግብ ዋስትናን ማስጠበቅ ፈታኝ እያደረገው መጥቷል:: በአብዛኛው የሚራበውም ምግብ አምራች ከሆነው የሀገሪቱ የህዝብ ክፍል የሚገኘው ዜጋ ነው:: ችግሩም ቀጥሏል:: የዕርዳታ ጥገኝነታችንም ማብቂያ አጥቷል፤ ስጋት ከቦናል:: ለዚህም የምግብ ዋስትናን ለማስጠበቅ ልዩና ዘመናዊ አደረጃጀት ተፈጥሮለት ከምግብ አመራረት፣ አዘገጃጀት፣ ግብይት፣ አሰረጫጨት፣ ደህንነቱንና ጤንነቱን አጠባበቅ፣ ከቦታ ወደ ቦታ አጓጓዝና አጠቃቀም ስርዓት በመፍጠር ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል::
5. የደረቅ ቆሻሻ ጉዳይ
በሀገራችን 70% አካባቢ የሚሆነው ደረቅ ቆሻሻ በራሱ ጊዜ የሚበሰብስ ቆሻሻ ነው:: አንድ ዜጋ በአማካይ 0.45 ኪ.ግ ቆሻሻ በየቀኑ ያወጣል:: በዚህም ከ45 ሚሊዮን ኪ.ግ በላይ ቆሻሻ በሀገራችን በየቀኑ ከየግለሰቡ ይወጣል ማለት ነው:: ይህ ብዛት ያለው ቆሻሻ በአግባቡ ሊወገድ ይገባል:: ቆሻሻ በአግባቡ ካልተወገደ ደግሞ ለአካባቢ ብክለት፣ ለአየር ንብረት መለወጥ፣ ለጤና ችግር፣ ለተፈጥሮ ውድመት፣ አካባቢ ለመኖሪያ አለመመቸትና ለመሳሰሉት ችግሮች ይዳርጋል:: ሳይንሳዊ የቆሻሻ አወጋገድ መንገድ በመከተል ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድና መልሶ በመጠቀም ለአካባቢ ጠንቅነቱን ማስወገድ አስፈላጊ ነው:: ሰብስቦ ማቃጠል፣ መልሶ መጠቀም፣ በጉድጓድ መቅበርና ወደ ማዳበሪያነት መቀየር መፍትሄዎች ናቸው:: ከእነዚህ ሁሉ ግን ለዘመናዊው ዓለም ምቹ የሆነው ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ነው:: ደረቅ ቆሻሻን ፕሮሰስ በማድረግ አዲስ ሀብት አድርጎ መጠቀም የዘመኑ ፈጠራ ነው:: ለዚህም የደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀሚያ ማዕከል በማዘጋጀት ደረቅ ቆሻሻን በመሰብሰብ፣ በመለየት፣ በማጠራቀም፣ በማሽን ፕሮሰስ ማድረግና መልሶ ሀብት አድርጎ ዋጋ ማሰራጨት ትልቅ መፍትሄ ነው::
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች በመንግስት በኩል ጊዜው በፈቀደ ሰዓት መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው:: የእነዚህ ጉዳዮች የተሟላ ሰነድ በእጄ ስለሚገኝ መንግስት ጠቃሜታነቱን ካመነበት ሰነዱን ለማስረከብ ፍቃደኛ መሆኔንም እገልጻለሁ::
አዲስ ዘመን ሰኔ 22
በላይ አበራ(ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ)
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።