
ማንኛውም የትውልድ ሂደት በጎ ይሉትን ጤናማ መንፈስ ይዞ ይቀጥል ዘንድ ጠንካራ የቅብብሎሽ ሂደት ሊኖረው ግድ ይላል::ይህ እውነት በአግባቡ እንዲተገበርም የቤተሰብ፣ የአካባቢና የዕድሜ ጠገቦች ልምድና ተሞክሮ አስተዋጽኦ ያበረክታል::
እንዲህ ዓይነቱ መልካም ልምድም ወጣቱ የሚያጋጥመውን የሕይወት ፈተናዎች በድል እንዲወጣና መልካም ስብዕናን እንዲላበስ ያግዛል:: መጪውን ትውልድም ከበረከቱ ውስብስብ ችግሮች ይታደጋል::
ሰሞኑን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ክፍል የተዘጋጀው መድረክም ይህን ይዘት የሚያጠናክር ዓላማን አንግቧል:: የአረጋውያንን ሁለንተናዊ ዕውቀት ለወጣቱ ለማስተላለፍ እንዲቻል ታስቦ በተዘጋጀው የትውልድ ቅብብሎሽ መድረክ ወጣቶችን ጨምሮ ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉ ምሁራን ጭምር ታድመዋል::
በእዚህ መድረክ ልምድና ተሞክሯቸውን የሚያጋሩ ብርቱ ተምሳሌቶች ነበሩ:: በዕድሜ ጠገብ የሆኑ አባቶችም የዘመናት የሕይወት ልምዳቸውን በትዝታ እየመዘዙ ማስቃኘት ችለዋል:: ሁሉም ተሞክሮ ለወጣቱ ትውልድ በእጅጉ የሚበጅና በጎ ተፅዕኖን የሚፈጥር ነበር:: አቶ ጌታቸው በዳኔ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሯ አማካሪም በመድረኩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ይህንኑ ሀቅ አረጋግጠዋል::
እንደ አቶ ጌታቸው አባባል፤ አረጋውያን በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን ዕውቅት፣ ክህሎት ተሞክሮና የሥነልቦና ጥንካሬ ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፋቸው አስተዋጽኦው የላቀ ነው:: እነዚህ ወገኖች የካበተ ልምዳቸውን ለተተኪው ትውልድ በወጉ ማሳለፋቸው በማህበራዊ ጉዳዮች፣በኢኮኖሚ ልማቶች፣በፖለቲካ አመራር፣በሀገር አጠባበቅና በግጭት አፈታት ላይ ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል::
አረጋውያንና በዕውቀትና ልምድ በቂ ተሞክሮ ያካበቱ ወገኖች ለወጣቱ ትውልድ አመራርነትን፣ ታሪክና ባሕልን ሥነምግባርና ሥራ ወዳድነትን በራሳቸው ጥበብ ሲያስተምሩ ቆይተዋል::
ዶክተር ጃራ ሰማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ናቸው:: በሕክምናው ዘርፍ የዓመታት ልምድና ተሞክሮን አካብተዋል:: ወጣቱን ትውልድ ከሱስ ለመታደግ የሚያስችል መጽሐፍንም ለንባብ አበርክተዋል:: በተለያዩ ማህበራዊና ሙያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የማሰልጠንና የማማከር ሥራን በመከወን ላይ የሚገኙት ዶክተር ጃራ፤ በመንግሥት ተቋማትና በግላቸው በተለያዩ ተግባራት ተሳትፏቸውን በማበርከት ላይ ናቸው::
እንደ ዶክተር ጃራ አገላለጽ፤ ስለ ትውልድ ሲባል የሚቀመጠው ዱካ በቀላሉ የሚጠፋ አይሆንም:: አሻራውም እንዲሁ በዋዛ አይደበዝዝም:: አሁን ባለንበት ዘመን በአዎንታዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ የተገነባ ትውልድን መቅረጽ ደግሞ የግድ ይላል:: እንዲህ መሆኑ ለጋራ ሀገራዊ ዕድገት የሚተጋ ኃይልን ለመፍጠር ያስችላል::
ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በእዚህ ጊዜ የሀገርና የትውልድ ጉዳይ ‹‹ያገባኛል፣ ይመለከተኛል››ብሎ መምከር፣ መመካከር እንደሳቸው አባባል ፍጹም መታደል ነው:: ጤናማ የሚባል የትውልድ ቅብብሎሽን ለመፍጠር አዎንታዊ አመለካከትና አስተሳሰብ መኖሩ ግድ ነው የሚሉት ዶክተር ጃራ፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን በብዙ አቅጣጫዎች የሚከፈል ዋጋ መኖሩ አይቀሬ እንደሆነ ያረጋግጣሉ::
ለእዚህ መልካም ለሚባል የትውልድ ቅብብሎሽ ታላቅ አስተዋጽኦ ያላቸው አረጋውያን ዕድሜ ጠገብ እንደ መሆናቸው ልምድና ተሞክሯቸውን ለወጣቱ ያጋራሉ:: ያለፉበት የሕይወት መንገድም ለትውልዱ ማንነት መሠረት ለመጣል ወሳኝ የሚባል ነው:: በእዚህም ባህል፣ታሪክ ሥራ ወዳድነትና የመልካም ቤተሰብ ገጽታ ጠንካራ ምሳሌ በመሆን ለማነጽ ያግዛል::
በትውልድ ቅብብሎሹ መድረክ ለወጣቱ ኃይል ልምድና ተሞክሯቸውን ካጋሩ ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ያለምፀሀይ መኮንን አንዷ ናቸው:: ፕሮፌሰሯ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ፤ በሀገራችን የትምህርት ዕድል ለሴቶች ብርቅ በሚባልበት ዘመን አሸንፈው የወጡ ጠንካራ ሴት ናቸው:: ፕሮፌሰር ያለምፀሀይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የገቡት ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት ነበር:: ከፍ ያለ የእውቀት ደረጃ፣ የካበተ ልምድና ችሎታ ከበሳል ዕድሜ ጋር ተዳምሮ ያስጨበጣቸውን በሳል ፍሬ ዛሬ ‹‹እነሆ›› ለማለት ወደኋላ አላሉም::
ፕሮፌሰር ያለምፀሀይ እስካሁን እንደ ሕይወት መርህ እየተጠቀሙ ለተጓዙባቸው የጥንካሬ ዓመታት የሚጠቅሷቸው አምስት ወሳኝ ነጥቦችን ነው:: ፍላጎት፣ ጠንካራ ሥራ፣ በራስ መተማመን፣ የጊዜ አጠቃቀምና ተስፋ አለመቁረጥ:: በዕለቱ መድረክም የእነዚህን ነጥቦች አስፈላጊነት በማብራራት ለታዳሚያን ተሞክሯቸውን በስፋት አካፍለዋል::
ሌላዋ የትውልድ ቅብብሎሽ መድረክ ተጋሪ ኮማንደር መስከረም ብሩ ናቸው:: እሳቸው በፖሊስነት ሙያ ለሰላሳ ስምንት ዓመታት አገልግለው በክብር ተሰናብተዋል::ኮማንደሯ በሥራ፣ በትምህርት ፣በልጆች አስተዳደግና በቢዝነስ ዓለም ያሳለፉትን ልምድና የሕይወት ተሞክሮ በማጋራት ብርታትና ጥንካሬን ከእኔ ተማሩ ሲሉ ለወጣቱ ትውልድ ሃሳባቸውን አካፍለዋል::
በመጨረሻ መድረኩን የተረከቡት የዕድሜ ባለጸጋው አርበኛ ፀጋ መለሰ ናቸው::አባ ጸጋ 107 ዓመታቸው መሆኑን ይናገራሉ:: ይህ ዕድሜ ለእሳቸው በመልከ ብዙ ገጽታ ይፈረጃል:: በትዝታ የልጅነት ህልማቸውን ያወሱበታል:: በጀግንነት የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ይዘክሩበታል:: ካህን የሆኑበትን የቤተክርስቲያን ቆይታ ያወጉበታል:: ብዙ የተጉበት የትምህርትና የሥራ ሕይወትም ተሞክሮው የሰፋ ነው::
ጠላት ከተባረረ ወዲህ እስከ 1957 ዓ.ም ድረስ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ነበሩ:: ከሀገር ቤት አዲስ አበባ በመጡ ጊዜም በትምህርት ሚኒስቴር ለዓመታት በጥበቃ ሙያ አገልግለዋል::አባ ጸጋ በእዚህ ብቻ አልቆሙም:: በመንፈሳዊ ኮሌጅ ተምረው ዲፕሎማ ወስደዋል:: በአመሀ ደስታ ትምህርት ቤት ለዓመታት ከሠሩ በኋላም ያካበቱትን ዕውቀት በቴሌቪዥን ስርጭት ‹‹ይድረስ›› ሲሉ ቆይተዋል::
በተለያዩ ፕሮጀክቶችና የአስተዳደር ሥራዎች ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት አባ ጸጋ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ ቢሰናበቱም ያለፉበትን የሕይወት ጉዞና የካበተ የሥራ ልምዳቸውን ማካፈልን ነፍገው አያውቁም::
ዛሬም የእኚህ ብርቱ ሰው ጥንካሬ ከእሳቸው ጋር ነው:: ፍጹም ለስንፍናና ለወሬ እጅ አይሰጡም:: ልክ እንደ ትናንቱ ለዛሬው ትውልድ ልምድ ተሞክሯቸውን ሲያጋሩ በታላቅ ደስታ ነው:: አባት አርበኛ ፀጋ የሕይወት መንገዳቸውን በምዕራፍ ከፋፍለው እንዳሰፈሩት ጭምር ይናገራሉ::
እንዲህ ማድረጋቸው ታሪካቸውን በወጉ ሰንዶ ለመያዝ አስችሏቸዋል:: ለትውልድ ቅብብሎሹ መሠረት የሆናቸው ይህ መሰሉ ሀቅ ነውና ለሁሉም፣ስለሁሉም ያላቸው አክብሮት የላቀ ነው:: የ107 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው አባት አርበኛ ፀጋ መሰለ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም