እንግሊዝ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የጨብጥ መከላከያ ክትባት ይፋ አደረገች

እንግሊዝ በወሲባዊ ግንኙነት የሚተላለፈውን ጨብጥ መከላከል የሚያስችል ክትባት በመስጠት በዓለም ላይ የመጀመሪያዋ ሀገር ልትሆን ነው።ክትባቱ ለሁሉም ተደራሽ እንደማይሆን ተገልጿል።ክትባቱ ከ30 እስከ 40 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለ ሲሆን፤ የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት እየጨመረ የመጣውን የጨብጥ ሕሙማን ቁጥር ይቀንሳል ብሎ ተስፋ ጥሎበታል።እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ከ85 ሺህ በላይ ሰዎች በጨብጥ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከ1918 ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

ጨብጥ ብዙ ጊዜ ምልክቶችን የማያሳይ ሲሆን፤ ነገር ግን ሕመም፣ ያልተለመደ ፈሳሽ፣ የመራብያ አካል አካባቢ ማቃጠል እና መውለድ አለመቻልን ያስከትላል።እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች ክትባቱን ይወስዳሉ የሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።ነገር ግን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን በሠራው ግምት ክትባቱ ተቀባይነት ካገኘ የ100 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የሚታደግ ሲሆን፤ የብሔራዊ ጤና አገልግሎትንም በሚቀጥሉት አስርታት 8 ሚሊዮን ፓውንድ ማዳን ይችላል ተብሏል።

የሥነ ተዋልዶ ጤና ለሁሉም እንዲዳረስ የሚወተውተው ማክስ እንደተናገረው፤ “በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ በጨብጥ መያዜን በምርመራ ማረጋገጤን ተከትሎ ክትባቱን ለመውሰድ መቶ በመቶ ዝግጁ ነኝ” ብሏል።”ይህ ነገር እንደሚጀመር መገለፁ በጣም ትልቅ ነገር ነው” ካለ በኋላ፣ “በክሊኒኮች ላይ ያለው ጫና ይቀንሳል፣ በሁሉም ረገድ ትልቅ ድል ነው” ብሏል።

ክትባቱ በነሐሴ ወር ስለ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አቅራቢዎች በኩል መሰጠት ይጀምራል ተብሏል።የስኮትላንድ የማኅበረሰብ ጤና ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ግለሰቦች የራሱን ፕሮግራም ለመጀመር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።ክትባቱ ለጨብጥ የተሠራ አይደለም። ክትባቱ በአሁኑ ወቅት ለሕጻናት እየተሰጠ ያለው የመንጋጋ ቆልፍ ቢ ክትባት ነው።ነገር ግን ሁለቱን ሕመሞች የሚያስከትሉት ባክቴሪያዎች ተመሳሳይ በመሆናቸው የመንጋጋ ቆልፍ ቢ ክትባት የጨብጥ ኢንፌክሽንን በአንድ ሦስተኛ እንደሚቀንስ ተገልጿል።

ክትባቱ በጨብጥ መያዝን ስለማያስቀር ከሥነ ተዋልዶ ጤና ክሊኒኮች ጋር ጥንቃቄ የተሞላበት፤ ንግግር ማድረግ ይጠይቃል።ጨብጥ ከኮንዶም ውጪ በሚደረግ የወሲባዊ ግንኙነት የሚተላለፍ ነው።ክትባቱ እንዲሰጥ ሃሳብ ያቀረቡት ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድ ምንም እንኳ 30 በመቶ ብቻ ውጤታማ ቢሆንም “መውሰድ የተሻለ ሲሆን” እንደ አጠቃላይም “ትልቅ አስተዋጽኦ” ይኖረዋል ብለዋል።

ውሳኔው የመጣው ከፍተኛ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ብቻ አይደለም። ጨብጥ ለማከም አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ በሽታ ነው።አብዛኛዎቹ የጨብጥ ሕሙማን ፀረ ባክቴሪያ በመውሰድ ቢድኑም ባለፉት 80 ዓመታት ጨብጥን የሚያስከትለው ባክቴሪያ በተደጋጋሚ መድኃኒትን የመቋቋም ችሎታ እያዳበረ መምጣቱ ታይቷል።አሁን ለመስጠት ለታሰበው ክትባትም ባክቴሪያው የመቋቋም ችሎታ እንዳለው በመታወቁ የተወሰኑ የሕክምና ባለሙያዎች ጨብጥ በአንድ ወቅት መታከም የማይችል ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You