
ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የአማራ ክልሏ ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚ ከተማ ጉብኝት አለን:: ተጎብኚው ግዙፉ የለሚ ብሄራዊ ሲሚንቶ ፋብሪካን ነው:: ከአዲስ አበባ ከጠዋቱ 12፡30 ላይ ተነስተን በከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ ሱሉልታን፣ ጫንጮንና ሌሎች መለስተኛ ከተሞችን እያለፍን ሙከ ጡሪ ከተማ ደረስን:: ዋናውን መንገድ ትተን ወደ ቀኝ ታጥፈን ወደ ለሚ፣መርሃ ቤቴ ዓለም ከተማ የሚወስደውን መንገድ ተያያዝን::
መንገዱ በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ የገባ ስለመሆኑ በራሱ ይናገራል:: የተሽከርካሪው ብዛትና በተለይ ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚበዙበት መሆኑ ዋናውን የጎጃም መንገድ የለቀቁ አያስመስልም:: ሲሚንቶ የሚጭኑ/ በኩንታልና በብትን/ ፣ እነሲኖ፣ ወዘተ ይሄዳሉ ይመጣሉ፤ ብዙ ናቸው::
የትራፊክ ፍሰቱ ለሚ ከተማ ስንቃረብ ባሰ:: ከተማዋ በተሽከርካሪ ተሞልታለች:: የመንገድ ግንባታው ይህን ፍሰት ታሳቢ ያደረገ አይመስልም:: ከተሽከርካሪዎቹ አብዛኞቹ ሊባል በሚችል መልኩ ደግሞ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የወለዳቸው ስለመሆናቸው ነጋሪ አያሻም::
ከከተማው ወደ ፋብሪካው መጓዝ ጀምረናል፤ ይህም መንገድ እንዲሁ በከባድ መኪኖች ተጨናንቋል፤ የቆሙት፣ የሚገቡ የሚወጡት ብዙ ናቸው:: በቅርብ ርቀት በስተግራችን እጅግ በርካታ ከባድ ተሽከርካሪዎች በሰፊ ሜዳ ላይ ቆመው ይታያሉ:: አካባቢውን ወደብ አስመስለውታል::
እየቀረብን ስንሄድ መኪኖቹ ገና ሰሌዳ ያልተለጠፈባቸው መሆናቸውን ተረዳን፤ ከ500 በላይ ናቸው ተባልን:: ሌሎች በርካታ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሲሚንቶ ለመጫን ወደ ፋብሪካው ለመግባት ተራ እየጠበቁ ናቸው:: ጥሬ እቃ ይዘው የሚገቡም አሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ ሲሚንቶ ጭነው ሲወጡ ይታያሉ::
እኛም የፋብሪካውን ሚዛን አልፈን ቁልቁል ወደ ግቢው ዘለቅን፤ በመግቢያዬ እንዳነሳሁት በፋብሪካው የመገኘታችን ዓላማ ፋብሪካውን ለመጎብኘት ነው፤ በዚህ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃንና ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በቅርቡ ባዘጋጀው የጉብኝት መርሀ ግብር በርካታ ጋዜጠኞችና ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል::
ከጉብኝቱ በፊት አጭር የአቀባበል መርሃ ግብር ተካሄደ:: ከዚያም ጉብኝቱ ተከተለ፤ በቅድሚያ ወደ ፋብሪካው ሴፍቲ/ ደኅንነት / ክፍል እንድንገባ ተደረገ:: የሴፍቲ አስፈላጊነትን የተመለከቱ መግለጫዎች ተሰጡ፤ አጭር ዶክመንታሪም ቀረበ:: በዚህም በጉብኝት ወቅት ማድረግ ስላለብን ጥንቃቄ ተነገረን:: ለጥንቃቄው የሚያስፈልጉ ኮፊያና አንጻባራቂ ጃኬት ለበስን ጉብኝቱን ተያያዝነው::
የፋብሪካው የመካኒካል ዲፓርትመንት ማናጀር እስራኤል እና የሥራ ባልደረቦቹ የየክፍሎቹን የሥራ እንቅስቃሴዎች አስቃኙን:: የፋብሪካውን አጠቃላይ የምርትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠረውን ክፍል ጎበኘን፤ ለሲሚንቶ ምርት የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ምን ምን እንደሆኑ፣ በምን ያህል መጠን ጥቅም ላይ እንደሚውሉና ኦፒሲና ፒፒሲ ሲምንቶዎች እንዴት እንደሚመረቱ ተነገረን::
ከዚያም የሲሚንቶ ግብዓቶች ተቃጥለው ክሊንከር ወደ ሚመረትበት የፋብሪካው ክፍል አቀናን፤ ይህን ጉብኝት ያደረግነው ከውጭ ሆነን ነው:: እዚህ ያለው ማሽን የሲምንቶ ግብዓቶችን በአንድ ሺ 500 ሴንቲግሪድ ሙቀት አቅልጦ ክሊንከር እንዲመረት የሚያደርግ ነው፤ በአንድ ጊዜ 10 ሺ ቶን ግብዓት አቃጥሎ ኪሊንከር ያመርታል፤ ይህ ማሽን በዓይነቱ በኢትዮጵም፣ በምስራቅ አፍሪካም፣ በአፍሪካም ልዩ ግዙፍ መሆኑ ተገለጸልን፤
ቀጣዩ ጉብኝት ደግሞ የሲሚንቶ ምርት ወደ ተሽከርካሪዎች የሚጫንበት ነው:: የሲምንቶ ምርቱ በተለያየ መንገድ ነው የሚጫነው:: ሰው መሸከም ማድረስ መጫን ሳይኖርበት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚጫንበት መንገድ አንዱ ነው፤ አውቶሜትድ መንገድ፤ በአንዱ ማሽን ላይ ከአራት የማያንሱ ሌሎች ማሽኖች በተሽከርካሪው ላይ ሲደረድሩ ይታያል፤ ሎቤድ የሚባለውን ተሽከርካሪ ለመጫን አፍታም አያቆያቸውም:: ይህን ዓይነቶቹ ማሽኖች አራት መሆናቸው ተነገረን::
ሌላው መንገድ በአብዛኛዎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥቅም ላይ የሚውለው ነው:: በሰው ኃይል የሚጫንበት መንገድ ፤ ይህ ዓይነቱ ማሽን ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ያስቻለ ነው::
ግብዓቶች ከ12 ሜትር ርቀት ከጀማ በመኪና ተጓጉዘው እንድ ስፍራ ላይ እንዲያርፉ ተደርጎ በቤልት አማካይነት ወደ ፋብሪካው እንደሚገቡ፣ የፋብሪካው የምርት ሰንሰለት አንድ ኪሎ ሜትር እንደሚደርስም አብራሩልን::
በአቀባበል መርሃ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው፤ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ሽርክና የተቋቋመ ነው:: ፋብሪካው በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን የሲሚንቶ እጥረት በመፍታትና የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል:: ይህ በቀን 150 ሺ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ወደ ሥራ ከገባ ካለፈው መስከረም ጀምሮ ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ሲሚንቶ አምርቶ ለገበያ አቅርቧል::
ፋብሪካው በሲምንቶ አቅርቦቱ የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ግብአት ፍላጎት ከማርካት ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብም ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን አስገኝቷል:: በሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች በቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል:: ለለሚ ከተማ መነቃቃትም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል::
አቶ አብርሃም ጉሩምስ ይትባረክ የሥራ እድል ካገኙት የፋብሪካው ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ነው:: በለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሴፍቲ ማኔጅመንት ክፍል ቋሚ ሠራተኛ ነው:: ፋብሪካው ለአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ክልሎችና ወረዳዎች ነዋሪዎችም የሥራ ዕድል ይዞ መጥቷል ይላል::
ወጣቱ በጂኦግራፊና ኢንቫይሮመንታል ስተዲስ የመጀመሪያ ዲግሪ አለው፤ በኢንቫይሮመንታል ስተዲ ሁለተኛ ዲግሪውን ለመያዝ እየተማረ ነው:: ባለትዳሩ አብርሃም በፋብሪካው ከመቀጠሩ በፊት በህዝብ አንድ አሽከርካሪነት ሰርቷል፤ ፋብሪካው ይዞት በመጣው ዕድል ለመጠቀም በሴፍቲ ላይ ስልጠና ወስዶ ከ2015 ግንቦት አንስቶ በሴፍቲ ሠራተኛነት እየሠራ ይገኛል::
በዚህም ከቀድሞ ሥራው የበለጠ ተከፋይ መሆኑን ጠቅሶ፣ በወር 13 ሺ 600 እንደሚያገኝም ተናግሯል:: በቀጣይም በእዚሁ በሴፍቲና ኢንቫይሮሜንታል ፕሮቴክሽን ላይ መሥራት ይፈልጋል::
የእንሳሮ ወረዳ መሬት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሳየሁ ማሙዬ እንዳሉት፤ ፋብሪካው የሚገኝበት የአማራ ክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በ13 የገጠር ቀበሌዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር የተዋቀረች ናት፤ ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ፣ ከባህር ዳር 513 ከደብረ ብርሃን ደግሞ 83 ኪሎ ሜትር ላይ ትገኛለች::
ፋብሪካው ለእንሳሮ ወረዳ እንዲሁም ለለሚ ከተማ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ለከተማዋ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል:: የሀገሪቱን የሲሚንቶ እጥረት መፍታት ከማስቻሉም በላይ ለሚ ፤ በንግዱ ዘርፍ የሚሳተፈው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፤ ለሃያና ሰላሳ ዓመት እንቅልፍ ውስጥ የነበረች ከተማ አሁን ነቅታ ትልቅ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለዋል:: ለወጣቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ አርሶ አደሩ ከግብርናው በተጨማሪ በንግዱ ዘርፍ እንዲሰማራ ያስቻለ ሲሉም ገልጸውታል::
ኃላፊው እንዳሉት፤ ፋብሪካው ከህብረተሰቡ ጋር ቅርብ ግንኙነት አለው:: የልማት ተነሺዎች ከፋብሪካው ምርቶች ጋር በትስስር እንዲሰሩ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ ይሠራል:: በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ተነሺዎቹን ይበልጥ በልማቱ ተጠቃሚ በሚያደርግባቸው ሁኔታዎች ላይ ወረዳው ከፋብሪካው ኃላፊዎች ጋር እየተወያየ ነው::
‹‹አካባቢው ሰላም መሆኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴው እንደሚናገርም ኃላፊው ጠቅሰው፣ ‹‹ከአዲስ አበበ ተነስታችሁ 130 ኪሎ ሜትር ተጉዛችሁ ለሚ ደርሳችኋል፤ መንገድ ላይም ከተማ ከደረሳችሁ በኋላም ምንም ያጋጠማችሁ የሰላም ችግር የለም፤ ፋብሪካውን እየጎበኛችሁ ነው፤የመንግሥት የፕሮጀክት የኢንቨስትመንት ሥራዎች ባግባቡ እየተሠሩ ናቸው›› ሲሉም አስታውቀዋል::
ለዚህ ግዙፍ ፋብሪካ የሚያስፈልገው ግብዓት ከ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ከጅማ በመኪና እየመጣ ያለበት እንዲሁም እናንተም እንደተመለከታችሁት የፋብሪካውም፣ የደንበኞችም መኪኖች እየጫኑ እየወጡ ያሉበትን ሁኔታ ሌሎች የአካባቢው ሰላም መሆን ማስረጃዎች ናቸው ሲሉ አብራርተዋል::
የሰላሙ ባለቤት አንደኛው ህብረተሰቡ መሆኑን ገልጸው፣ ሁለተኛው ደግሞ በወረዳው ላይ ያለው የመንግሥት አካል የአካባቢውን ማህበረሰብ ሰላም የማስከበር ሥራ መሥራቱ ነው ይላሉ:: ህብረተሰቡን በማወያየት በእኔነት ስሜት ፋብሪካውን እንዲጠብቀው ለማድረግም ወረዳው እንደሚሠራ ተናግረው፣ ህብረተሰቡ እንዲህ ዓይነት ጸጋ አይቶ አያውቅምና ፋብሪካውን እንደ አይኑ ብሌን ይመለከተዋል ብለዋል::
በአመራሩ በኩልም በመሬት አቅርቦት እንዲሁም በካሳ ጉዳይ ላይ በፍጥነት እንደሚሠራ ተናግረዋል፤ ያለምንም ውጣ ውረድ የፋብሪካውን ጥያቄዎች በወቅቱ በመመለስ ባለሀብቱ ፋብሪካው መሬቱን ተረክቦ ማዕድኑን እንዲጠቀምበት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል::
የፋብሪካው ባለአክሲዮን የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና የናሽናል ሲሚንቶ ተወካይ አቶ አዳነ ዓለሙ እንደተናገሩት፤ ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ በሲሚንቶ ግዙፍ የሚባል ብዙም ተወዳዳሪ የሌለው ዘመናዊ ፋብሪካ ነው::
ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ ከግንባታ ጀምሮ በመንግሥት ደረጃ ትልቅ ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል:: አቶ አዳነ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ የማክሮ ቲም ተቋቁሞ ሲደግፈው ነበር፤ ያ ሁኔታ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ አስችሏል የመንግሥት ድጋር አሁንም አልተለየውም ብለዋል::
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱን የሲሚንቶ እጥረት በመፍታት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ የሀገሪቱን የሲሚንቶ ማምረት አቅምን በ50 በመቶ የጨመረ ነው:: ይህን ዓይነት ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ማድረግ የተለመደ ተብሎ አይወሰድም::
የዚህ ፋብሪካ ጠንሳሽ የሆነው የኢስት አፍሪካ ሆልዲግ ኩባንያ የተለያዩ ቅርጾችን በመያዝ ከ130 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ነው:: በበርካታ የአምራች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ የሪልስቴት የአገልግሎትን የሎጂስቲክስ ዘርፎች ላይ ይሠራል:: ከ16 በላይ እህት ኩባንያዎችም አሉት፤ በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፤፡ ከ10 ሺ በላይ ዜጎችን የቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ ነው፤
እንደ አቶ አዳነ ገለጻ፤ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ170 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ በቀን 150 ሺ ኩንታል ሲሚንቶ ማምረት ይችላል፤ በፋብሪካ ደረጃ ከ1000 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፤ ይህም ለለሚ ከተማ መስፋፋትና ዕድገት ዋነኛ የልማት አጋር መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው ብለን እናስባለን ብለዋል::
ከመስከረም 2017 አንስቶ ባለፉት ስድስት ወራትም ከ12 ሚሊየን በላይ ኩንታል ሲሚንቶ አምርቶ በመላ ሀገሪቱ እያሰራጨ ይገኛል:: ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከዚያም አልፎ ኢስት አፍሪካ ናሽናል ዲስትሪቢውሽንን የተሰኘ የሎጂስቲክስ ኩባንያ በማቋቋም የትራንስፖርት ፋሲሊቲና እሴት በመጨመር ሲሚንቶውን በመላ ሀገሪቱ እያሰራጨ በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን የሲሚንቶ አለመረጋጋት የቀረፈ ነው::
ፋብሪካውና እህት ኩባንያው ድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ አሁን ሀገሪቱ ከምታቀርበው ሲምንቶ 45 በመቶውን የገበያ ድርሻ ወስደው እየሠሩ መሆናቸውንም ተወካዩ አስታውቀዋል::
በዘመናዊ አሠራር በመታገዝ የፋብሪካዎቹን የኦፒሲና ፒፒሲ ሲሚንቶ ምርቶች ያለምንም መስተጓጎል በማጓጓዝ የሎጂስቲክስ ኩባንያው ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው፤ ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉ ምርቶችንም እያቀረበ ይገኛል:: በዚህም ለትላልቅ ፕሮጀክቶችና የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራቾችና መሰል ፕሮጀክቶች አጋር በመሆን እየሠራ ነው:: በአጭር ጊዜ ውስጥም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል::
የለሚና የድሬዳዋ የሲሚንቶ ምርቶች ባላቸው ከፍተኛ ጥራትና በፋብሪካዎቹ ከፍተኛ የማምረት አቅም ባልተቋረጠ የምርት አቅርቦታቸው በቀልጣፋ አሠራራቸው ማናቸውም ደንበኛ፣ ፕሮጀክት አከፋፋይ፣ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከፍለው ወዲያው ምርቶቹን የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር በአጭር ጊዜ ትልቅ የግንባታ አጋር መሆን ችሏል:: ለእዚህ ደግሞ አከፋፋዮቻችንና ተጠቃሚዎቻችን ምስክር ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል::
አቶ አዳነ የፋብሪካውንና የህብረተሰቡን ትስስር በተመለከተ ሲያብራሩ እንዳስታወቁት፤ ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ በሥሩ የሚገኙ ኩባንያዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉትን ማህበረሰቦች ለመደገፍም እንደሚሠራ አመልክተዋል፤ ይህንንም ለማሳለጥ ብዙአየሁ ታደለና ቤተሰቦቹ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በመመስረት በለሚ፣ በድሬዳዋ፣ በጨዋቃ ፣ በቢሾፍቱ አካባቢዎች የማህበረሰብ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል:: ይህን ሥራውን በአንድ ማዕቀፍ በማከናወን በቤት ግንባታ፣ በማዕድ ማጋራትና በመሳሰሉት ላይ እየሠራ ነው::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም