
የአፍሪካ ወጣቶች የቦክስ ስፖርት ቻምፒዮና ከአምስት ቀን በፊት በጊኒ ኮናክሬ አስተናጋጅነት ተጀምሯል። የአህጉሪቱ ወጣት የቡጢ ተፋላሚዎች በሚሳተፉበት ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በአንድ ወንድና በአንድ ሴት የቦክስ ተወዳዳሪዎች ተወክላ እየተሳተፈች ትገኛለች።
በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ወጣት የቦክስ ስፖርት ብሔራዊ ቡድን በኢ/ር መኮንን ጌታቸው እየተመራ ባለፈው ሰኞ ወደ ጊኒ ማቅናቱ ታውቋል።
ለአስር ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በወንድና በሴት በሁለት ወጣት የቡጢ ተፋላሚዎች ስትወከል፤ በወንድ 51ኪሎ ግራም ይድነቃቸው ብርሀኑ እና በሴት 48 ኪሎ ግራም ነፃነት ታምሩ ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ታውቋል። ውድድሩ በቀጣይ ዓመት 2026 ላይ ሴኔጋል ዳካር ላይ ለምታዘጋጀው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ለመሳተፍ እንደማጣሪያ የሚያገለግልም ነው።
ከወጣቶቹ የቡጢ ተፋላሚዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው በሁለት የስፖርቱ ባለሙያዎች እንደተወከለችም ታውቋል። ይህም በቻምፒዮናው ሁለት ኢንተርናሽናል የቦክስ ስፖርት ዳኞች መመረጣቸውን ተከትሎ ነው። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሕይወት ብዙወርቅ እና ኢንተርናሽናል ዳኛ ፋንቱ ፍቃዱ በቻምፒዮናው ሙያዊ አገልግሎታቸውን የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
አህጉራዊው ቻምፒዮና የአፍሪካን ወጣት ቦክሰኞች በአንድ ላይ በማሰባሰብና የውድድር ልምድ እንዲያዳብሩ ለማስቻል ያለመ ሲሆን፣ በእዚህም አፍሪካ ወደፊት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የቡጢ ውድድሮች ብቁ ተፎካካሪዎችን ለማፍራት ያስችላታል ተብሎ ታምኖበታል። ከውድድሩ በተጨማሪ ለተለያዩ ባለሙያዎች ሦስት ዓለም አቀፍ የዳኝነት እና የአሠልጣኝነት ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ታውቋል።
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኢያሱ ወሰን አህጉራዊው የወጣቶች ቻምፒዮና ላይ ለመታደም ኮናክሬ በደረሱበት ወቅት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ፕሬዚዳንቱ የወጣቶቹን ቻምፒዮና በተመለከተ በሰጡት መግለጫም፤ “ይህ ቻምፒዮና የቦክስ ውድድር ብቻ አይደለም፣ ለአፍሪካ ቦክስ ስፖርት የወደፊት እጣ ፋንታ አንድነትና ትልቅ እድል የሚፈጠርበት ነው፣ በእዚህ ቻምፒዮና የሚሳተፉ ወንድና ሴት ወጣቶችም የወደፊቶቹ የአፍሪካ ቦክስ ስፖርት ኮከቦች ናቸው” ብለዋል።
በተያያዘ የቦክስ ስፖርት ዜና ሦስተኛው ዙር የብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ቻምፒዮና ዛሬ እንደሚጀመር ታውቋል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በጋራ የሚያዘጋጀው ይህ ሦስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች ቻምፒዮና ለተከታታይ አራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ በውድድሩ ሰባት ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል። በእዚህ ዓመት የተቋቋመውና በኢ/ር ቃለአብ ዋጃ የሚመራው ዩናይትድ ስዊት የቦክስ ቡድን በውድድሩ ተካፋይ እንደሚሆን ታውቋል።
አዲስ አበባ ፖሊስ ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ኦሜድላ ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ድሬ ከነማ ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ቦክስ ቡድን እንዲሁም ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል።
በዓመት አራት ጊዜ በተለያዩ ዙሮች የሚደረገው ይህ የብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ቻምፒዮና ዛሬ ሦስተኛው ዙር ውድድር ሲጀመር ፉክክሩ ቦሌ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ቃና ዌር ሀውስ በደማቅ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም