ሃሳብ የደረቀባቸው ፖለቲከኞቻችን !

አንዳንድ ፖለቲከኞች አዝጎች ናቸው:: ከጊዜ ጋር የማይለወጡ፤ ከወቅቱ ጋር የማይዘምኑ ችኮ ፖለቲከኞች በየሥርቻው አሉ:: ትላንት ብቻ እያላዘኑ ዛሬን መሻሻል የማይፈልጉ የትላንት እስረኞች ፖለቲካችን ጥቁር ቀለሞች ናቸው:: ትላንት የሚዘምሩትን መዝሙር የዛሬውም ወጣት ሳያላምጥ እንዲውጥላቸው ይሻሉ፤ ባስ ሲልም ዘመኑን ያልዋጀ የፖለቲካ ዕሳቤ ለመጋት ይሞክራሉ::

ለውጥ ተፈጥሯዊ ነው:: ከጊዜና ከሁኔታ ጋር ነገሮች መለወጣቸው አንዱ የተፈጥሮ ግዴታ ነው:: አንድ ቦታ የሚቆም ነገር የለም:: ለሕይወት አስፈላጊ ነው የሚባለው ውሃ እንኳን ካልተንቀሳቀሰ እና በአዲስ ወራጅ ውሃ ካልተተካ እያደረ ማነሱ እና የጣዕምም ሆነ የሽታ ለውጥ ማምጣቱ አይቀሬ ነው:: ብረትም ቢሆን አንድ ቦታ ሲቀመጥ ይዝጋል:: አንዳንድ ፖለቲከኞችም ልክ እንደዚሁ የዛጉ ይመስለኛል::

እነዚሁ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ጥላቻን፤ መጠፋፋትን፤ መገፋፋትን ለመወቃቀስን፤ መወነጃጀልን በየሶሻል ሚዲያው እና በየመድረኩ ሲሰብኩና ሲጠምቁ ይውላሉ:: ከአፋቸው እንኳን አንዲት በጎ ቃል ጠብ ሲል አይደመጥም:: ለዘመናት የመጡት ችግሮችም እንዲፈቱና ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር ከመሥራት ይልቅ ችግሮቹ ይበልጥ ጥልቀት እንዲኖራቸውና ስር እንዲሰዱ ያለመታከት ሲሠሩ ይታያሉ::

ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ነች:: ሥራ አጥነት፤ የኑሮ ውድነት፤ የባለሙያዎች ደመወዝ ዝቅተኛ መሆን፤ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ወዘተ እያሉ መደርደር ይቻላል:: ሆኖም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ባለበት በዚህ ወቅት አንዳንድ ፖለቲከኞች ችግሮችን ከልክ በላይ በመለጠጥ ሕዝቡ ብሶት ውስጥ እንዲገባ ሲቆሰቁሱት ይታያሉ:: ከላይ ያነሳናሳቸው ችግሮች ለዘመናት ያህል ሲንከባለሉ የመጡ እና ችግሮቹንም ለመቅረፍ ጊዜ እንደሚስፈልግ እየታወቀ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል በአንድ ጀንበር እንዲፈቱ ግፊት ሲደረግ ይታያል::

ሆኖም ኢትዮጵያ ገና ከችግሮቿ ለመላቀቅ እየተውተረተረች ያለች ሀገር መሆኗ እየታወቀ በአንድ ጀንበር ዘርፈ ብዙ ችግሮቿ እንደሚፈቱ አድርጎ ሕዝብን ማደናገር ትዝብት ላይ ከመጣሉም ባሻገር ለህሊና ወቀሳ የሚዳርግም ነው:: ሆኖም አንዳንድ የከሠሩ ፖለቲከኞቻችን ህሊናም ስለሌላቸው ወቃሳም ሆነ የህሊና ጥያቄን የሚፈሩ አይደሉም::

እንዲያውም እነዚሁ ሰዎች ጥቂት ችግሮች ሲፈጠሩ አቧራቸውን አራግፈው በመነሳት ቤንዚን ሲያርከፈክፉና ሕዝብ እና ሀገርን ለማንደድ ሲውተረተሩ ይታያሉ:: የእነሱ መኖር የሚታወቀው የሚፈጠሩ ችግሮችን በማጎን እና ከልክ በላይ በማሳበጥ ነው:: መጠነኛ ችግሮችን በየሶሻል ሚዲያው በማቀጣጠል ሀገር የነደደች እና የተቃጠለች ያህል ለማስመሰል ሲሞክሩ መታየት አንዱ የፖለቲካ መገለጫቸው ነው::

እነዚህ ሰዎች ሃሳብ የላቸውም:: የሃሳብ ድርቅ የመታቸው በመሆኑ አድብተው የሚጠብቁት በሌሎች ወገኖች ላይ ተፈጠሩ የሚባሉ ችግሮችን ነው:: ልክ ሰሞኑን እንደሆነው የጤና ባለሙዎች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ እነዚሁ ፖለቲከኞቻችን ከመቃብር ውስጥ አቧራቸውን አራግፈው ይነሳሉ::

እነዚህ ሰዎች ያደፈ ታሪካቸውን ይዘው ተሸፋፍነው መተኛት ሲገባቸው እኔ ያላቦካሁት አይጋገርም በሚል ፈሊጥ ችግሩን ፈጥረው ራሳቸውም የመፍትሔ አካል ሆነው ለመቅረብ ይሞክራሉ:: ሰሞነኛ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር የተለያዩ ሰሞነኛ አጀንዳዎችን በመፍጠር ውዥንብር መፍጠር ልማዳቸው ነው::

እነዚህ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ሌት ተቀን የሕዝብን ስም በመጥራት፤ በመማል እና በመገዛት የራሳቸውን ንዋይ የሚያሳድዱ ጥቅመኞች ናቸው:: ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ሀብቱን፤ ሕይወቱን፤ ወጣትነቱንና እና ወደፊት ተስፋውን እየነጠቁት ይገኛሉ:: እንደማማሰያ በተጣደው ነገር ሁሉ እንግባ የሚሉ እና የወሬ ሽታ እና ቅሬታ ባለበት ሁሉ ቤንዚን ሆነው የሚያቀጣጥሉ ናቸው::

የእኛ ሀገር የፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤ የሚመነጨው በተገኘው አማራጭ ሁሉ ወደ ሥልጣን መምጣት እንጂ ባላቸው ጊዜ ለሕዝብ እና ለሀገር በጎ ሥራ መሥራት አይደለም:: እነሱ ሥልጣን ካልያዙ በስተቀር ሀገር የሌለች ይመስል ከፖለቲካ ወቀሳና ማጣጣል በስተቀር አባሎቻቸውን አስተባብረው ይህ ነው የሚባል ሀገራዊ ሥራ ሲሠሩ አይታዩም::

ብዙዎቹ የሃሳብ ድርቅ ያጠቃቸው በመሆኑ ፖለቲካውን በሃሳብ የበላይነት ከመምራት ይልቅ ችግሮችን በማጉላት እና ሆድ በማባባስ ፖለቲካው ውስጥ መቆየትን የሚሹ ናቸው:: ብዙ ጊዜ መኖራቸው የሚታወቀውም ኅብረተሰቡ ውስጥ አንድ ችግር ሲፈጠር ወይም በምርጫ ዋዜማ ወቅት ነው::

እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተቋቋሙ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ስትጎዳ ተመልክተዋል:: ድርቅ በየዓመቱ እየደጋገመ እየመጣ በርካቶችን ከአካባቢያቸው ሲያፈናቅል፤ ሲያሰደድና ሰዎች በረሃብ ሲሞቱ ተመልክተዋል:: ሆኖም የእኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግረን ቁጭ ብሎ ከመመልከት ወይንም ደግሞ ወቃሽ ከመሆን ድርቅን በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ሲጠቁሙ አይታዩም::

አለፍ ሲልም ያላቸውን ዕውቀትና የአባላት ብዛት በመጠቀም አስተባብረው ችግኝ ሲተክሉ አይታዩም:: አረንጓዴ ዐሻራ መትከል በጎ ፍላጎትንና ቅን አሳቢነትን እንጂ ሥልጣንን ወይንም ገንዘብን አይጠይቅም:: ስሙ እንዲህ የሚባል ፓርቲ አባላቱን አስተባብሮ ይሄን የሚያክል ችግኝ ተከለ የሚባል ዜና የምንሰማው መቼ ይሆን?

በተመሳሳይም አንድ ፖለቲከኛ አባላቱን አስተባብሮ የድሃ ቤት ማደስ ለሀገር ለወገን ማሰብን እንጂ የተለየ ጥበብን አይጠይቅም:: እንዲሁ ለአፍ እና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ለድሃው የቆምኩ ነኝ የሚለው ፕሮፖጋንዳ ትዝብትን ከማትረፍ ውጭ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም:: በወሬም የተገነባ ሀገር የለም::

ሀሰተኛ በቃሉ ስደተኛ በቅሉ እንደሚባለው የእነዚህ ሰዎች ቃል አባይነት በየጊዜው ከሚሰነዝሩት ሃሳብ መረዳት ይቻላል:: ትላንት የተናገሩትን ዛሬ አይደግሙትም:: ትላንት ቆመንለታል የሚሉት አላማ ዛሬ አያውቁትም:: ለፖለቲካ ፍጆታቸው እስከጠቀማቸው ድረስ ትላንት ትክክል ነው ብለው የተሟገቱለትን ሃሳብ ዛሬ አሽቀንጥረው ለመጣል ሼም የላቸውም:: የፖለቲካ ምኞታቸውን የሚያሳካላቸው እስከመሰላቸው ድረስ ትላንት ሰይጣን ያሉትን ዛሬ መላእክ ነው ብለው ከመሟገት አልፈው ዓይናቸውን በጨው አጥበው አደባባይ ከመውጣት አይመለሱም::

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምስረታቸው ጀምሮ እስከ ሥልጣን ድረስ ያሰቡትን አላማ ማሳካት የሚችሉት ሀገር ስትለማ ነው:: ሀገር የምትለማው ደግሞ በፖለቲካ ዲስኩር ወይም በፖለቲካ ሽኩቻ አይደለም::

በሰለጠኑት ዓለማት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱና ዋነኛ መመዘኛ የበጎ ፈቃድ ሥራ ነው:: ተወዳድሮ ለማሸነፍና ሥልጣን ለመያዝ የመጀመሪያው መመዘኛ ፓርቲው ወይም ግለሰቡ የሠራቸው በጎ ፈቃድ ሥራዎችና ያመጣው ውጤት ነው:: ያለበለዚያ በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብና የመንግሥትን ህጸጽ እየፈለጉ ብቻ በመውቀስ ሥልጣን ላይ ፊጥጥ ማለት አይታሰብም::

የእኛ ሀገር የፖለቲከኞች እሳቤ የሚመነጨው በተገኘው አማራጭ ሁሉ ወደ ሥልጣን መምጣት እንጂ ባላቸው ጊዜ ለሕዝብ እና ለሀገር በጎ ሥራ መሥራት አይደለም:: ለማንም ክፍት የሆነውና ሁሉም በሰብዓዊነት የሚሳተፍበትን የበጎ ፈቃድ ሥራ ለፖለቲከኞቻችን የተከለከለ ይመስል በአጠገቡም ዝር አይሉም:: እነሱ ሥልጣን ካልያዙ በስተቀር ሀገር የሌለች ይመስል ከፖለቲካ ወቀሳና ማጣጣል በስተቀር የሚሳተፉበት ይህ ነው የሚባል የበጎ ፈቃድ ሥራ ሲሠሩ አይታይም::

በአጠቃላይ በጎነት አንዱ የፖለቲኮቻችን መገለጫ መሆን ሲገባው በተቃራኒው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት እና ህጸጽ እየለቀሙ መንግሥት እና ሕዝብ ማራቅ እንደ መፍትሔ የያዙት ይመስላሉ:: አሁን በእጃቸው ያለውን የበጎ ፈቃድ ሥራ ሳይሠሩ ነገ ሥልጣን ጨብጠው የሚሠሩትን ሥራ እና የሚለውጡትን ሀገር ያልማሉ:: ይህ ደግሞ ህልም እንጂ እውን ሊሆን አይችልም::

ሲሰርቀኝ ያየሁትን ቢመርቀኝ አላምነውም እንደሚለው ብሂል ዛሬ በጎ ሆነው ያላየናቸው ሰዎች ነገ ሥልጣን ይዘው በጎ ይሆናሉ ብለን አናስብም:: እነዚህ ሰዎች ከሀገር ሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ዝና ሀብት ለማከማቸት ሕዝብን ከሕዝብ፤ ሃይማኖት ከሃይማኖት ሲያጋጩ የኖሩ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው:: ታዲያ አሁን ደርሰው የተበዳዮች ጠበቃ እንሁን ሲሉ እንደምን እንመናቸው:: እንዲያውም የሠሩት በደል እና ያደረሱት የሕዝብ ዕልቂት አልበቃ ብሎ ዛሬም ያንኑ ዘግናኝ ድርጊት ለመድገም ዳር ዳር ሲሉ ማየት በእጅጉ ያስፍራል፤ ያሳምማልም::

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት:: ስለዚህም ሕዝቡ የሚሻው ለችጎሮቿ መፍትሔ የሚያመላክታትን እንጂ ችግሮቿን የሚያባብሱላት አይደለም:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉድለት ፖለቲካን ከሸፍጥ ጋር መቆራኘቱ ነው:: ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በጎ ሥራ መሥራት የተከለከለ ይመስላል:: ይልቁንም ሴራ መተንተንና መንግሥትን መውቀስ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጥንካሬ መለኪያ ተደርጎ እየተወሰደ ሀገር እና ሕዝብም ከፖለቲከኞች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እያጡ ነው፤ ይባሱንም ሀገርና ሕዝብን በማያራምድ አጀንዳ ሰቅዘው የኋሊት እንድንጓዝ እያደረጉን ነው::

የፖለቲካ ሥርዓታችን ለሀገር በጎ ማሰብና አለፍ ሲልም በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ውስጥ ተሳትፎ ሕዝብና ሀገርን ከመጥቀም ይልቅ ሀገር በትብብር እንዳትቆም የጥላቻ መርዝ መንዛት ላይ የሚተኩር ነው:: ተባብሮ ተደጋገፎ ሀገርን ማቆም ፖለቲከኞቻችን በሩቁ የሚሸሹት ጉዳይ ነው::

ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው:: አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሠረት ሌሎችን አጥፍቶና አንቋሾ፤ ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው::

በጋራ ሠርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ መልካም ሥራ ሊሠራ የተነሳን ወገን ማንቋሸሽና በሕዝብ ዘንድም በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ የኖርንበትና እየኖርንበት ያለ ሀቅ ነው:: በየጊዜው ጥላቻና ግጭትን መፈብረክ ሀገርን የኋሊት እንድትጓዝ ማድረግ አንዱ ፖለቲካ ታሪካችን ነው::

ሀገርን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀምና የአቅምን ያህል ሃሳብ ከማዋጣት ይልቅ ሀገርን በሚያፈርሱ አጀንዳዎች ውስጥ መጠመድ፤ ችግሮችን እና ህጸጾችን እየፈለጉ መንግሥት እና ሕዝብን ማጋጨት አንዱ የፖለቲካ ባሕላችን ሆኖ ዛሬ ድረስ ዘልቋል:: አለፍ ሲልም ሃሳብን በነፍጥ ለመጫን ማዳከር አንዱ የእኛነታችን መለያ ሆኖ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ዛሬም የሚታየው ሀቅ ይኸው ነው::

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You