ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአትሌቲክሱ ዓለም በተለይም በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች ትኩረት እያገኘ የመጣው ወጣት አትሌት ሰለሞን ባረጋ የስኬት ማማ ላይ ለመቆም ብዙ ጊዜ አልወሰደ በትም። ከዕድሜው ከፍ ብሎ ከታላላቆቹ ጋር በመፎካከርም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለማመን የሚከብዱ ድሎችን አጣጥሟል። ይህም በረጅም ርቀት በተለይም በአምስት ሺ ሜትር ኢትዮጵያ ከነ ቀነኒሳ በቀለ ወዲህ ማግኘት ያልቻለችውን ሁነኛ ተተኪ አትሌት በቅርቡ ልታገኝ እንደምትችል ፍንጭ የሰጠ መሆኑን የስፖርቱ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
በዳይመንድ ሊግ ተሳትፎው ገና በሁለተኛ ዓመቱ የአምስት ሺ ሜትር አጠቃላይ አሸናፊ መሆን የቻለው ሰለሞን ዕድሜው አስራ ሰባት ዓመት ቢሆንም በልምድ የሚበልጡትን አትሌቶች የሚያስንቅ የሩጫ ተሰጥኦ እንዳለው በተለያዩ አጋጣሚዎች ማሳየት ችሏል። 2018 የውድድር ዓመትም ስኬታማ የሆነበት ነው ማለት ይቻላል። ይህም እ.ኤ.አ ከ2011 ወዲህ አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት በዓለም የዓመቱ ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከአስሮቹ እጩዎች ውስጥ እንኳን ባልተካተቱበት ሁኔታ ሰለሞን በወጣቶች ዘርፍ ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች መካከል አንዱ እንዲሆን አስችሎታል። ሽልማቱን የማሸነፍ ሰፊ ዕድል እንደሚኖረውም ይጠበቃል።
የደቡብ ፖሊሱ ክለብ አትሌት የሆነው ሰለሞን ባረጋ እያስመዘገበ ላለው ስኬት ከሁለት ወራት በፊት ክለቡ የኢንስፔክተርነት ማዕረግ የሰጠው ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት እያሳየ ያለው አስደናቂ ብቃት ወደ ፊት ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል። በ2018 የውድድር ዓመት የአምስት ሺ ሜትር አጠቃላይ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ሲሆን በርቀቱ ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ክብረወሰንን 12፡43፡02 በሆነ ሰዓት ከመጨበጡ ባሻገር እ.ኤ.አ 2005 ላይ ቀነኒሳ በቀለ በርቀቱ ካስመዘገበው ሰዓት ወዲህ ፈጣን ሰዓት መሆኑ ይታወሳል። ሰለሞን በዓለም ከሃያ ዓመት በታች ቻምፒዮናና በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮናም በርቀቱ አራተኛ ደረጃን ይዞ በመፈፀም በውድድር ዓመቱ በርካታ ስኬቶችን አግኝቷል። ይህንንም በተመለከተ ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ድረ ገፅ ጋር ሰሞኑን ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
የ2018 የውድድር ዓመት ልምምዱን ሲጀምር ከውድድሮች ይልቅ ልምምዱ ላይ ትኩረት አድርጎ በተለየ መንገድ ለመሥራት ከአሰልጣኞቹ ጋር እንደተስማማ የሚናገረው ሰለሞን በውድድር ዓመቱ የተለየ ብቃት ለማሳየቱ ምክኒያቱ ይህ መሆኑን ይናገራል።
ሰለሞን በውድድር ዓመቱ በቤት ውስጥና ከቤት ውጭ ውድድሮች አስደናቂ ብቃት ቢያሳይም በብራሰልስ ዳይመንድ ሊግ ፈጣን የተባለውን 12፡43፡02 ሰዓት ለመሮጥ እንዳላሰበ ያብራራል። ይሁን እንጂ ይህን ጣፋጭ ድል የግሉ ካደረገ በኋላ ሰዓቱን ሲመለከተው ለማመን ተቸግሮ እንደነበር አልሸሸገም። «የዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ለእኔ አስገራሚ ስኬት ነው፤ ይህን ሰዓት ማስመዝገብ ደግሞ ፈፅሞ ሊታመን የማይችል ነበር» ያለው ወጣቱ አትሌት ይህ የሩጫ ዘመኑ ሁሉ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ይናገራል።
ቀደም ሲል በአምስት ሺ ሜትር ከነበረው የራሱ ምርጥ ሰዓት 12፡55 በታች መሮጥ የሁል ጊዜም ፍላጎቱ እንደሆነ የሚናገረው ሰለሞን 12፡43 በሆነ ሰዓት ርቀቱን ማጠናቀቅ መቻሉ ሁሉንም ነገር እንደቀየረው ያስረዳል። ይህም ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ በቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የቆየውን የአምስት ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን አንድ ቀን በእጁ ለማስገባት ጠንክሮ እንዲሠራ እንዳነሳሳው ያብራራል።
ከ18 እና ከ2o ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና አሸናፊ መሆን የቻለው ሰለሞን ባለፈው የለንደን የዓለም ቻምፒዮና በቀጥታ ወደ ትልቅ ደረጃ ተሸጋግሮ የኢትዮጵያውያንን የአምስት ሺ ሜትር ስብስብ ምን ያህል አስፈሪ እንዳደረገው ይታወሳል፡፡
በሁለት ኦሊምፒኮችና በሦስት የዓለም ቻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ በሞ ፋራ የተነጠቀችውን የአምስት ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለንደን ላይ በሙክታር ኢድሪስ አማካኝነት ስታስመልስ የሰለሞን ሚና ቁልፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በበርሚንግሃሙ የዓለም ቻምፒዮና ዮሚፍ ወርቅ ባጠለቀበት ውድድር ሰለሞን የብር ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ያሳየው ድንቅ አቋም በቀጣይ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀቶች ኢትዮጵያውያን የበላይነታቸው ከወዲሁ ጎህ እየቀደደ እንደሚገኝ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው።