ዓለም አቀፉ የጉዞና የቱሪዝም ምክር ቤት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ባወጣው ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ አሳይታለች። በተለይ በ2018 የበጀት ዓመት ከ185 አገራት የዘርፉ ንፅፅር ጋር ስትመዘን በዓለም የሦስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፣ ከአፍሪካ ደግሞ አምስት ነጥብ ስድስት በመቶ ዕድገት አሳይታለች። ይህም ለሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሰዎች የሥራ ዕድል የከፈተ ሲሆን በአጠቃላይ በሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ የ ስምንት ነጥብ ሦስት በመቶ ድርሻ እንዳለው በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል።
ዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞ ምክር ቤቱ ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍሰቱ እንደሚጨምር ተገምቶ ነበር። በ2020 ብቻ በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች እስከ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ጎብኝዎች ይገኛሉ የሚል ትንበያ ነበር። ይህን ቅድመ ግምት ግን ያልታሰበው የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ከምክር ቤቱ የትግበራ ትንተና ባሻገር የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በ2019 ብቻ 812 ሺህ የሚጠጉ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህም ሦስት ቢሊዮን 200 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ሀብት መገኘቱን ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ ማለት በጥቅሉ የአገሪቷን ዘጠኝ ነጥብ አራት በመቶ ኢኮኖሚ እንደሆነ ይገመታል።
በአሁኑ ሰዓት ልክ እንደ ሌሎቹ ዘርፎች ቱሪዝም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ተደቁሷል። በዚህ ዘርፍ ላይ በቅርቡ እየወጡ ያሉት ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ድንበሮች ተዘግተዋል፣ አጠቃላይ የየብስም ሆነ የአየር ጉዞዎች ተሰርዘዋል፤ ይሄ ደግሞ ሆቴሎች፣ ሎጅ፣ ሪዞርት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችና ማህበረሰብ፣ አስጎብኚዎች፣ የቱር ኦፕሬተሮችን ሳይቀር ከፍተኛ ተጽዕኖውን አሳርፏል። እውነታው ይሄ ቢሆንም እጅግ በፈጠነ ሁኔታ ክፉኛ የተጎዳው ዘርፍ የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ከገባበት ችግር ፈጥኖ እንደሚወጣ የሚያመላክቱ ዕቅዶችም እየወጡ ነው። ከዚህ መካከል የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ ማገገሚያ ስልት›› በሚል በግንቦት ወር አዲስ ስልት ይዞ መምጣቱን ይፋ አድርጓል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይፋ የተደረገው አዲሱ የማገገሚያ ስልት አሁን ላይ ዘርፉ ከገባበት ቅርቃር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚችል የሚያመላክት ነው። ለትግበራ ዝግጁ ሆነው የተነደፉ አዳዲስ ስልቶችም በዕቅዱ ውስጥ ይፋ ተደርጓል። በተለይ የመዳረሻ ስፍራዎችን ማልማት፣ ማደስና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ዋነኛው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የቱሪዝም ኮምኒኬሽን ዘርፉን ማጠናከርና የዲጂታል ሚዲያ ተሳትፎ ማሳደግ ይገኝበታል። ይህን በተመለከተም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እሁድ ገፅ የባህልንና ቱሪዝም አምድ የመስሪያ ቤቱን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ አቶ እንደገና ደሳለኝን አነጋግሮ ነበር። በምላሹም የማገገሚያ ስልቱን የትግበራ ሂደትና የዕቅዱ ዋና ዋና ቁልፍ ጉዳዮች ምን እንደሆኑ መረዳት ችሏል። አጠቃላይ የስልቱ አንድምታዎችና እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ከዚህ እንደሚከተለው አቅረበነዋል።
በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተወካይ አቶ እንዳሉት በወረርሽኙ ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል። ይህም የቱሪዝም ዘርፉ ቀዳሚ ተጎጂ እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራሉ። ተጠሪ ተቋማትንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በመተባበር በጋራ የማገገሚያ ስልት ተነድፏል። የቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የሆቴልና የአስጎብኚ ማህበራት በዚህ ስልት ላይ በቀጥታ ተሳታፊ ሆነዋል። ዕቅዱ በዋነኛነት የመዳረሻ ስፍራዎችን በጥንቃቄ ማዘጋጀትን እንደ ቀዳሚ ጉዳይ ይዘውታል። በተለይ ከዚህ ቀደም ያልተሰሩ የመዳረሻ ልማቶችን ማልማት፣ መጠገን
እንዲሁም የመሰረተ ልማት ስራዎችን የማሟላት ተግባት በዕቅዱ ላይ ተካቷል።
በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን የሚያቀላጥፉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሚገባው ልክና ፍጥነት ተሠርተው አልተጠናቀቁም። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያሳጣት እንደሆነ ይገለፃል። ታዲያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሮና ወረርሽኝን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ጊዜውን መሰረተ ልማት የማዘጋጀት ሥራዎች ላይ ለማተኮር ማሰቡን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካዩ ገልፀውልናል። ይህን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግም የተያዙ አማራጮች ሁሉ ለመጠቀም ማሰባቸውን ነው ያነሱት።
ከዚህ ባለፈ በስልቱ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፎችን በማሰባሰብ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴክተሮች ይደግፋል የሚሉት የዳይሬክተሩ ተወካይ፤ ይሄ በግል ሲሆን በመንግሥት ደረጃ ደግሞ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የቱሪዝም ዘርፍ ተቋማት ባንኮች በዝቅተኛ ወለድ ብድር የማመቻቸት ሥራ እንዲሠራ ለማድረግ በማገገሚያ ስልቱ ላይ ዋነኛ ግቡ አድርጎ በማስቀመጥ ለትግበራው እየሠራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በተጨማሪ ግብርን በተመለከተ መንግሥት በገቢዎች ሚኒስቴር በኩል የረጅም ጊዜ ውዝፍ ግብር እስከ 2007 ዓ.ም ያለባቸውን ተቋማት ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝላቸው፤ እስከ 2011 ዓ.ም ያሉት ደግሞ የትርፍ ጥቅም ቅናሽ የተደረገላቸው እንዳሉ ይገልፃሉ። በአጠቃለይ የግብር ወለድና ቅጣት የነበረባቸው ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር መደረጉንም ያስታውሳሉ። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተደረጉ ማበረታቻዎች የማገገሚያ ስትራቴጂው አንዱና ዋናው አካል እንደሆኑም ተናግረዋል።
ፕሮሞሽንና ገፅታን መገንባት
የቱሪዝም ዘርፍ ከሌሎቹ ዘርፎች በተለየ ገፅታን የመገንባትና የማስተዋወቅ ሥራን የሚጠይቅ ነው። ዓለም አቀፍ ትኩረትን ለመሳብና ኢትዮጵያ ያሏትን ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብቶች በማስተዋወቅ ጎብኝዎች ወደነዚህ መስህቦች እንዲመጡ ለማስቻል ትልቁ ሥራ መሠራት ያለበት በገፅታ ግንባታና በተለያዩ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች ነው። ለዚህ ደግሞ የሚኒስቴር መስሪያ
ቤቱ፣ የተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በቀጥታ ከዚህ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት በማስተባበር መሥራት ይኖርበታል። ይሄን ለማድረግ ደግሞ የኮሚኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዘርፉን በተገቢው መንገድ ማጠናከር ይጠበቅበታል።
የዳይሬክተሩ ተወካይ አቶ እንደገና እንደሚናገሩት፤ የኦላይን ሚዲያና የኮሚኒኬሽን ዘርፉን ለማጠናከር እንዲሁም ተገቢውን የፕሮሞሽንና የገፅታ ግንባታ ለመሥራት ዝግጅቶች ተጠናቀው ወደ ትግበራ ገብተዋል። በተለይ በቱሪዝም ማገገሚያ ስልት ዕቅዱ ላይ ይሄ አንዱ ቁልፍ ተግባር ሆኖ ተቀምጧል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን ይገልፃል።
‹‹ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት የየአገራቱን ወቅታዊ የቱሪዝም ማገገሚያ ስልት በማየት እገዛ እያደረገ ነው›› የሚለው አቶ እንደገና፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዚህ ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ይገልፃሉ። በተለይ ይህ ወረርሽኝ በሚያበቃበት ወቅት ኢትዮጵያ ምን ምን አይነት ልዩ ልዩ መስህብ አላት፣ ጎብኚዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍላት ለጉብኝት ሲመጡ ምን ያገኛሉ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አጫጭር የቪዲዮ ፖስት ካርዶችን በማዘጋጀት ለመላው ዓለም በኦላይን መገናኛ ዘዴ የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ ነው። እስካሁንም የኢትዮጵያን መልከአምድራዊ አቀማመጥ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመስህብ ሥፍራዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
የመገናኛ ብዙሃን ፎረም
የገፅታ ግንባታ ከሚከናወንባቸው መንገዶች አንዱ የመገናኛ ብዙሃን የቱሪዝም ሀብቶችን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ማስተዋወቅ ነው። ይህ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊትም ሆነ ከዚያ ቀደም ብሎ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ጋር በቅርበት እየሠራ ነው። ለዚህ ማረጋገጫ የሚሰጠው ደግሞ የዳይሬክተሩ ተወካይ አቶ እንደገና ነው።
‹‹መሥሪያ ቤታችን ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ ይህ የተሳካ እንዲሆን ደግሞ የሚዲያ
ፎረም አቋቁመው እየሠሩ የሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞች አሉ›› የሚለው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተወካይ፤ እነዚህ አባላት በሚሰሩባቸው የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ፣ ኦላይን፣ የህትመት ሚዲያዎች ላይ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ በልዩ ሁኔታ በማተኮር የተያዩ ዘገባዎችን ለአድማጭ ተመልካች እንዲሁም የማህበራዊ ገፅ ተከታታይ እንደሚያቀርቡ ነው የሚናገረው።
በወቅታዊ ወረርሽኝ ምክንያት የማገገሚያ ስልት ሲነደፍም አባላቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው የጋራ ስምምነት የወጣ ሲሆን፤ ለቀጣይ ሦስት ወራት የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ ዘርፉን በምን መልኩ ማነቃቃት ይቻላል በሚለው ጉዳይ ምክክር ተደርጎ ዕቅድ ተነድፏል። በዚህም የኮሮና ወረርሽኝ በሚያበቃበት ወቅት ጎብኚዎች አስቀድመው ወደየትኛው አካባቢ ሄደው እራሳቸውን በጉብኝት ማዝናናትም ሆነ መጎብኘት ይችላሉ የሚል ጠቋሚ ፕሮጀክቶች በማውጣት የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩንም ይናገራሉ። በምሳሌነትም በኢትዮጵያ ራዲዮ ‹‹ቀጠሮ ይዣለሁ›› የሚል ለሁለት ወራት የሚቆይ የዘገባ ሥራ መጀመሩን ይገልፃሉ።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እውቅናና ድጋፍ አግኝቶ የሚንቀሳቀሰው የጋዜጠኞች ፎረም በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ ይታወቃል። ነገር ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተደራሽነቱን ከማስፋት አንፃር ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የመሥራት አቅሙ ከፎረሙ ጋር ብቻ መወሰን እንደሌለበት ትችት የሚሰነዝሩ አንዳንድ አካላት አሉ። ፎረሙም ቢሆን በአገር ውስጥና በመላው ዓለም እውቅናንና ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ የሚፈልገውን የቱሪዝም ዘርፍ ተደራሽ በማድረግ ውጤት የማምጣት አቅሙ እጅግ አናሳ እንደሆነ ከተለያዩ ጉዳዩ ይመለከተናል ከሚሉ ወገኖች የሚቀርቡ ሃሳቦች ያመለክታሉ። ይህን ትችት ምላሽ እንዲሰጡበት ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ እንደገና የሚከተለውን ሃሳብ ያነሳሉ።
‹‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፎረሙ ጋር ላለፉት ስምንት ዓመታት ሠርቷል›› የሚሉት አቶ እንደገና፤ ጠንካራ ጋዜጠኞች ያሉበትና የኢትዮጵያን ቱሪዝም በተገቢው መንገድ ያስተዋወቁ ብሎም ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው ይላሉ። መስሪያ ቤቱም ከዚህ በተሻለ ሊደግፋቸውና ሊያጠናክራቸው እንደሚገባም ይገልፃል። ሆኖም ግን ፎረሙ ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ በኤጀንሲ ደረጃ አለመቋቋሙ፤ የአባላቱን ተሳትፎ ከማጠናከርና ከማስፋት አንፃር የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ይቀበላሉ። ከተደራሽነት አንፃር ግን ሁሉም በአገሪቱ ባሉ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሠሩ ከመሆኑ አኳያ የተደራሽነት ጥያቄ ሊነሳ አይገባም በማለት ሃሳቡን ያነሳል። በተጨማሪም መስሪያ ቤቱ ከፎረሙ ውጭ ካሉ በርካታ ሚዲያዎች ጋር እንደሚሠሩ በማንሳት ሁሉንም ያሳተፈ ትግበራ እየተከናወነ እንደሆነ ይናገራል።
ውጤት ግምገማና መደምደሚያ
የቱሪዝም ዘርፉ የማገገሚያ ስልት ወደ ትግበራ እንዲገባ ከፀደቀ ሁለት ወራት ገደማ ሊሆነው ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥም አነሰም በዛም ውጤት ይጠበቃል። ይህንን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችንም ስልቱ ተነድፎ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ምን ፋይዳ እያመጣ ይሆን? የሚል ጥያቄ ሰንዝሮ ነበር።
‹‹በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ተገድቦ ነው ያለው›› በማለት ስለ ሁኔታው ማብራራት የሚጀምሩት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተወካይ፤ ሆኖም ግን ሙሉ ለሙሉ ሥራዎች ቆመዋል ማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ የማገገሚያ ስልቱ ተግባራዊ የሆነው በቅርብ ጊዜ በመሆኑ የውጤት ግምገማ የሚደረግበት ወቅት እንዳልደረሰ ይገልፃሉ። ይህ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ የሚገባበትን ፍጥነት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት እንደሆነም ያስረዳሉ። በነዚህ ጥቂት ጊዜያቶች ግን በተለይ በኦላይን የመገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ የገፅታ ግንባታና የቱርዝም ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን አንስተዋል። ትግበራው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም የውጤት ግምገማ ሥራ እንደሚከናወን አሳውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
ዳግም ከበደ