
አቶ ሳሕሉ ባዬ የሳይኮሎጂና የሕፃናት እድገት ባለሙያ
አቶ ሳሕሉ ባዬ ይባላሉ። የሳይኮሎጂ፣ የሕፃናት እድገት እና የፕሮጄክት ማኔጅመንት ባለሙያ ናቸው። ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በመምህርነት፣ በአማካሪነት፣ በሀገር በቀልና በዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ተቋማት ተጠሪና ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል። በሥነ ልቦና ባለሙያ፣ የአቅም ግንባታ እና በልዩ ልዩ መስኮች ዛሬም ድረስ እየሠሩ ይገኛሉ። እንግዳችን የሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ የሙያ ማሕበራት አባል ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀሱት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ኔትወርክ አባል (The Global Alliance Inspiring Non-Tech Infant Nurturing and Growth) ሕብረት አንዱ ነው።
የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን በኮሌጅ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ኮሌጅ የዘለቀ መምህርነት ሙያ ለዓመታት ትውልድን ቀርፀዋል። ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የግል ኮሌጅ በመክፈት የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞችን ቀርፀው አስተምረዋል። ‹‹ኢንሪችመንት ሴንተር ኢትዮጵያ›› በሚል ስሙ የሚታወቅ ሀገር በቀል ኤን ጂኦ በመመስረት ላለፉት 22 ዓመታት በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
‹‹እኔ የሳይኮሎጂ ተማሪ እንጂ ባለሙያ አይደለሁም። ሁሌም በመማር ሂደት ውስጥ ነኝ›› የሚል እሳቤ ያላቸው የዛሬው እንግዳችን ሰዎች እራሳቸውን በትምህርት ውስጥ መቆየት እንዳለባቸው ያምናሉ። የዝግጅት ከፍላችን አቶ ሳሕሉ ባዬ የሕይወት ልምዳቸውን ቢያካፍሉ ወጣቶች፣ እና የነገ ሀገር ተረካቢዎች በብዙ ያተርፋሉ ብሎ በማመኑ አንግዳችን አድርጓቸዋል። መልካም ቆይታ!!
ትውልድና እድገት
የዓለም ትኩረት ባረፈባት፣ ጥንታዊውን የኢትዮጵያውያን የሕንፃ ጥበብ ዛሬም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚታይባት፣ ቀደምት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን እምነት፣ ወግና ሥርዓት ጠብቃ በቆየችው፣ ኢትዮጵያ ሲባል ቀድማ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ አፍ ውስጥ በምትገባው በላስታ ላሊበላ፣ በውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ምድር መሀል ከተማ ውስጥ የዛሬው እንግዳችን አቶ ሳሕሉ ባዬ ዓለሙ ተወለዱ። የያኔው ታዳጊ የዛሬው አንጋፋ መምህርና የሳይኮሎጂ ባለሙያ ያደጉት በከተማው ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ አንዱ በሆነው አማኑኤል ቤተክርስቲያን ሲሆን የትውልድ ዘመናቸው ደግሞ በ1952 ዓ.ም ነው።
አማኑኤል ቤተክርስቲያን በዘር ግንድ የሚተዳደረው በእሳቸው አባት ሲሆን የዓለም ሳይንቲስቶችን ዛሬም ድረስ የሚያመራምረውን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ልክ እንደ ቤታቸው ጓዳ በመዳፋቸው ዳስሰው ነው። የቅድመ አያቶቻቸው መቃብርም በዚያው ቤተክርስቲያን ነው።
አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዚያው በላሊበላ ነው የጨረሱት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ በወልዲያ ወልዲያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእግር ለሶሰት ቀናት ተጉዘው ነበር የተማሩት። በግዜው ላሊበላ ለትራንስፖርት ዝግ ነበር። አውሮፕላንም የጀመረው በዚያው በ1948 አካባቢ ነበር። በዚህ ምክንያት ደካማ ግንኙነት ነበር። ቱሪዝምም መነቃቃት የጀመረው ከግዜ በኋላ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሰራ፣ መብራትና ውሀ ሲገባ ነው።
አባታቸው አለቃ ባዬ አለሙ የላሊበላ ደብር ዋና ፀሀፊ ነበሩ። የላሊበላ ከተማ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አስተዋፆ ነበራቸው። የመጀመሪያው የልእልት ሂሩት ደስታ ሆቴል (የቱሪስት ማረፊያ) የፕሮጀክት ተቆጣጣሪ ሆነው ያሰሩት እርሳቸው ነበሩ። ውሀ ከአሸተን ማሪያም ጋራ ስር ከሸነት ውሀ ምንጭ ከሲሳይ በርሌና ገብርሀና በላይ ከተባሉ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ወደ ላሊበላ ከተማ ለሆቴሉ አስገብተዋል። በተመሳሳይ በከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሀ አለመኖሩን አለቃ ለልእልቷ ቀርበው በማስረዳታቸው በእሳቸው ትእዛዝ ለሕዝቡም ሶሰት የውሀ ጣቢያ (የከተማው ክፍል በሆኑት በአዲሻዴ፣ በሰባት ወይራ እና በቀደምት) እንዲሰራ ምክንያት ሆነዋል። ይህንን የውሀ ጣቢያ አባታቸው በሥራ ጫና ምክንያት ለተወሰኑ ግዜያት የአቶ ሳሕሉ እናት ወይዘሮ እንደሀብቷ ተሾመ ረታ እንዲያስተዳድሩት አድርገው ነበር።
ትምህርትና አስተዳደግ
ትምህርት የጀመሩት በቄስ ትምህርት ቤት ነው። መምህራቸው የእርሳቸው ወላጆች ቤተሰብ የነበሩ። እርሳቸው ጋር ሲማሩ በትምህርቱ አቀባበል ደካማ ነበሩ። በተቃራኒው የተለያዩ ጨዋታዎች ላይ ትኩረታቸው ይሳብ ነበር። ጓደኞቻቸው ዳዊትን ሲዘልቁ፤ እሳቸው አቦጊዳ ላይ ቀሩ። በዚህ ምክንያት መምህሩ ቀጥተዋቸዋል። በቅጣቱ ጠንካራ መሆን ምክንያት አባታቸው ቅር ተሰኝተው ወደ አስኳላ መደበኛ ትምህርት ቤት አንዲገቡ አደረጉ። በዚያም አራተኛ ከፍል እስኪደርሱ ደከም ያለ የትምህርት አቀባበል ነበራቸው። ለደካማ ትምህርት አቀባበላቸው እንደ ምክንያት የሚያነሱት በቄስ ትምህርት ቤት የነበረውን ጫና ነው።
ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ግን በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት አመጡ፤ ምክንያቱ የመምህራን ድጋፍ ነበር። በጥሩ የትምህት አቀባበል በላሊበላ ከተማ እስከ ሰድስተኛ ክፍል ተማሩ። በአካባቢው ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት ስለማይችሉ የግዴታ ወደ ወልዲያ ከተማ መሄድ ነበረባቸው። ወደዚያ ለመሄድ ቀለብ ተሸክመው የተለያዩ መልከዓ ምድር (ጋራ ሸንተረር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜን ተጋፍጠው) ነበር 160 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ትምህርት ቤቱ የሚደርሱት። ኩል መስክ፣ ደቦት እና የተከዜ በረሀን አቆራርጠው ነበር በእግር ለትምህርት ሲሉ ወልዲያ ድረስ ይሄዱ ነበር። ለትምህርት በሚከፈል መስዋዕትነት በእግራቸው እረጅም ርቀት አቆራርጠው ከ1965 እስከ 70 ድረስ ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ ተከታትለዋል። አቶ ሳሕሉ ለቁጥር ነክ ትምህርቶች እና ቋንቋ ትምህርቶች በተለይ አንግሊዘኛ ላይ ልዩ አቀባበልና ጉብዝና ነበራቸው።
በላሊበላ መወለዳቸው ከቱሪስቶች እና ከውጪ ዜጎች ጋር እንዲቀራረቡ ረድቷቸዋል። በዚህ ምክንያት በታዳጊነታቸው ፈጣንና ተግባቢ ነበሩ። ይህ ቅልጥፍናቸው ለትምህርታቸውም አጋዥ ነበር። ጓደኞቻቸው በልጅነታቸው ‹‹ፕሮፌሰር የሚል ቅፅዕል ስም›› ሰጥተዋቸው ነበር።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የትምህርት አቀባበላቸው መሻሻሉ ምንም ሳይቸገሩ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1971 ዓ.ም እንዲቀላቀሉ አግዟቸዋል። ግዜው የፖለቲካ ሙቀቱ ከፍ ያለበት በመሆኑ ሀገሪቱ ውስጥ መረጋጋት አልነበረም። ተማሪዎች በፖለቲካ ውስጥ በብዛት ይሳተፉ ነበር። እርሳቸው ግን በዙም ተሳታፊ አልነበሩም። ይሁን እንጂ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ባይሆኑም የጅምላ እስር 12ተኛ ክፍል እያሉ አጋጥሟቸዋል። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። በተማሪዎች አንዳንድ የንቅናቄ ወረቀቶች ይሰራጩ ነበር። እርሳቸው እነዚያን ወረቀቶች ከማንበብ የዘለለ ተሳትፎ አንዳልነበራቸው ይናገራሉ። ከዚያ ይልቅ ወደ መዝናኛና ጨዋታው ላይ ያዘነብሉ ነበር።
በፖለቲካ እንቅስቃሴ የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው የነበራቸው። በዩኒቨርሲቲ ፖለቲካን በሩቁ ያሉት እንግዳችን በ1996 ዓ.ም አካባቢ በኢዴፓ ውስጥ አባል በመሆን በሥራ አስፈፃሚ፣ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እና በፀሀፊነት እስከማገልገል ደርሰዋል። በወጣትነት ዘመናቸው በተለይ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ ተሳትፎ ላይ ግን ተቆጥበው ነበር። ይልቁኑ በግቢ ውስጥ የማህበራዊ ሕይወት ላይም ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በአካዳሚ ውጤታቸውም የተሻሉ ነበሩ። ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ ጥቂት ተማሪዎች ነበሩ። በእሳቸው ትውስታ ‹ከ3000 ላንበልጥ እንችላለን›› ይላሉ። በግዜው መደበኛው የትምህርት ግዜ ሲጠናቀቅ ክረምት ላይ ወደ ላሊበላ ከመመለስ ይልቅ እስኪመረቁ ድረስ በዚሁ በአዲስ አበባ የእረፍት ግዜያቸውን ያሳልፉ ነበር። የግቢው ወዳጆቻቸው ጋር በመሄድ ዳግም ምዝገባ እስኪጀመር ያርፋሉ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሩት የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል ነበር። ትምህርቱ በምደባ እንጂ በምርጫ አልነበረም። ግን እራሳቸውን ከሁኔታው ጋር አዋህደው የሰው ልጅ የሥነ ልቦናን በሳይንሳዊ መንገድ የሚያጠናውን ሙያ ለሶስት ዓመት ተማሩ። በቆይታቸው ጥሩ ውጤት አስመዘግበዋል። በወቅቱ ከገቡት 35 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ የቻሉት 20 እንደማይበልጡ ይናገራሉ። በትምህርት ክፍሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ ተማሪዎች (ከኤርትራ፣ ባሌጎባ፣ ሀረር፣ ላሊበላና ሌሎችም ክፍሎች) መኖራቸው ከሳይንሳዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ከብዝሀነታቸውም በባሕል፣ በኑሮ ዘይቤ፣ አብሮ የመኖር ክህሎት እና የተለያዩ እሴቶችን ተምረዋል። ዛሬም ድረስ ከጓደኞቻቸው ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ይገናኛሉ። በምረቃ ወቅት ድግሪያቸውን የተቀበሉት ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም እጅ ነበር።
እንግዳችን ትምህርታቸውን ሲማሩ የገንዘብ ችግር አልገጠማቸውም። ከቤተሰቦቻቸውም አይቀበሉም ነበር። ይልቁኑ በላሊበላ በነበሩበት ወቅት ቱሪስቶች ሲመጡ ፈጣን በመሆናቸው መልካም ግንኙነት ፈጥረው ነበር። ከእነሱም ጋር ይፃፃፉ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ከተዋወቋቸው ሁለት ጀርመናዊያን (ሉዊስና ጌርሃርድ) ከሚባሉ ወዳጆቻቸው ድጋፍ ያገኙ ነበር። በዚህም በየወሩ 100 የጀርመን ገንዘብ (በኢትዮጵያ 86 ብር ምንዛሬ) ይቀበሉ ነበር። በዚህ ምክንያት ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ይሸፍኑ ነበር። 36 ብሩን ተጠቅመው የቀረውን ደግሞ ለአባታቸው ይልካሉ። በዚህ የአባታቸው ምርቃት አግኝተዋል።
ከድግሪ በኋላ– ከወላይታ እስከ ሀዋሳ
በሳይኮሎጂ የተመረቁተ እንግዳችን፤ በ1974 ሀምሌ አንድ ነው ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁት። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በመንግስት ተመድበው በጋይዳንስ ኦፊሰርነት ተመድበው ይርጋለም ከተማ በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል አንዲሠሩ ታዘዙ። በግዜው መንግሥት እነሱን ለማበረታታት ቅድሚያ የሁለት ወር ደሞዝ ሰጥቶ ነበር የሸኛቸው። አሰፋሽ ሀይለስላሴ የተባለች ወዳጃቸው ደግሞ ወላይታ ሶዶ ተመድበው ነበር። እርሳቸው ለቤተሰባቸው ለመቅረብ ሲሉ ከተመደቡበት ወላይታ ወደ ይርጋለም መቀየር ፈልገው ነበር። አቶ ሳሕሉ ይህንን እድል ተጠቅመው በጓደኛቸው ጥያቄ መሰረት ወደ ወላይታ ሶዶ በመሄድ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የመጀመሪያ የመንግሥት ተቀጣሪ ሆነው አገለገሉ።
‹‹የመጀመሪያ ደሞዜን ያገኘሁበት፤ እራሴን የቻልኩበት ነው›› ይላሉ ሁኔታውን መለስ ብለው ሲያስታውሱ። ወላይታ የነበራቸው ቆይታ መልካም እንደነበርም ይናገራሉ። ኑሮ እርካሽ ነበር፤ የሥራ ሕይወትን አሀዱ ያሉበት የወጣትነት ትዝታቸው በወላይታ ማሳለፍ ችለዋል።
በወላይታ ሶዶ ዓመት ከመንፈቅ እንደቆዩ በኩባ የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ትምህርት ቤት እንደሚመደቡ በአለቆቻቸው ተነግሯቸው ወደ ሀዋሳ በግዜያዊነት አዘዋወሯቸው። ሆኖም ዛሬ ነገ ሲባል እቅዱ ሳይሳካ ይቀራል። በሁኔታው ግራ የተጋቡት አቶ ሳሕሉ፤ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እዚያው ሀዋሳ በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በቋሚነት የሳይኮሎጂ መምህር እና በሀዋሳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጋይዳንስ ኦፊሰርነት ለመሥራት ተመደቡ። መምህርነት ቀደም ሲልም የሚወዱት ሙያ በመሆኑ ደስተኛ ሆነው በሙያቸው ማገልገል ጀመሩ።
አቶ ሳሕሉ ሁሌም የሳይኮሎጂ ‹‹ምሁር›› ሳይሆን ተማሪ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት። የሰው ልጅ ባህሪ ተጠንቶ የማያልቅ በጣም ጥልቅና ውስብስብ ከመሆኑም ባሻገር ሁሌም አዳዲስ ሳይንሳዊ እውቀቶችን መማር ያስፈልጋል ይላሉ ስለሁኔታው ሲያብራሩ። ተማሪዎቻቸውንም በዚሀ መልክ ሁሌም ለእውቀት ጉጉ አንዲሆኑ አድርገው ሲቀርፁ መቆየታቸውን ያስረዳሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሀዋሳ ተጨማሩ ሁለት ተቋማት ውስጥ (የነርሶች ማሰልጠኛ ተቋም እና ተግባረ እድ ትምህርት ቤት) ሰርተዋል።
አቶ ሳሕሉ ከ1975 ዓ.ም አስከ 1985 ዓ.ም በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ እስራኤል ሀገር አቅንተዋል። እዚህ ላይ ነው የእንግዳችን ሌላኛው የሕይወት ምእራፍ እንደ አዲስ የሚጀምረው።
ትምህርት– እስራኤል
በ1985 ዓ.ም አቶ ሳሕሉ ወደ አስራኤል አቀኑ በዚያ በማውንት ካርሜል ኢንተርናሽናል ትሬኒንግ “Mount Carmel International Training (MCTC)” የሕፃናት ልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮግራም ‹‹The Education of the Young Child with Special needs›› ትምህርትን ተከታተሉ። በተመሳሳይ ለሁለተኛ ግዜ በዚያው ትምህርት ቤት በኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በተያዙ ታዳጊ ሕፃናት የሥነ ልቦና እንክብካቤ ‹‹Psychosocial Care and Support for children and Adolescence Affected and/or Inflected by HIV & AIDS›› ፕሮግራም ትምህርታቸውን ወሰዱ።
እነዚህን ሁለት ፕሮግራሞች ተከታትለው ሲያበቁ በዚያው ሀገር በሂብሪው ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ሂፒ ወይም ‹‹home instruction programs for pre youngsters (HIPPY)›› እየተባለ በሚታወቅ ትምህርት ተጨማሪ ስልጠና ውሰዱ በዚህ ሳያበቁ በዚያው እስራኤል ሀገር ሀይፋ ዩኒቨርሲቲ በሕፃናት እድገት (Chilled Development) የአንድ ዓመት የማስተርስ ፕሮግራም ወስደው ሙያዊ አውቀታቸውንና ልምዳቸውን ይበልጥ አዳበሩ።
በእስራኤል ሀገር ቆይታቸው ከመላው ዓለም ከተወጣጡ የሳይኮሎጂ ተማሪዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚውን አግኝተዋል። ‹‹ውድድሩ በጣም ከባድ ነበር። ሆኖም ግን ቆይታችን በጣም አሪፍ ነበር›› በማለት እርሳቸው ባስመዘገቡት ውጤት ተሸላሚ እንደነበሩ ይናገራሉ። አስራኤልን በወጣትነት ግዜያቸው አንደሚያውቋት የሚናገሩት አንግዳችን ከዚያን ግዜ ጀምሮ ከትምህርት ተቋማቶቹ እና ከሕዝቡ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ሁኔታውን በእርሳቸው አንደበት ሲገልፁ ‹‹ልክ እንደ ሀዋሳ እና እንደ ወላይታ ጥሩ ተዝታ አለኝ›› ይላሉ።
አቶ ሳሕሉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በርካታ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። እንግዳችን እንደሚሉት አንደ ቀልድ የሚያልፍ ምንም ግዜ የላቸውም። እስራኤል ሀገር ከወሰዱት ትምህርት እና ስልጠና ባሻገር የፕሮጀክት ማኔጅመንት የድግሪ ምሩቅም ናቸው። አሁን በዚህ ላይ ያልጠቀስናቸው የአጭርና የረጅም ገዜ ሥልጠናዎችንም ወስደዋል።
ሀገር የማገልገል ርዕይ
አቶ ሳሕሉ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ወጣ ገባ እያሉ በእስራኤል ሀገር እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ ቆይተዋል። ከዚያ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው ገብተዋል። እራሳቸውን በሙያ ቀርፀው እና ተጨማሪ ሥልጠናዎችን ወስደው ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ በሙያቸው ለማገልገል በማሰብ ነበር ወደ ሀገራቸው የተመለሱት።
ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ አንደገቡ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ‹‹ኢስት አፍሪካ አርትስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ›› የሚል የግል ኮሌጅ አቋቁመው ነበር። በኮሌጁ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ ግን እርሳቸው ኤን ጂኦ በማቋቋም በሕፃናት ዙሪያ የመሥራት ቀደም ያለ እቅድ ስለነበራቸው ከኮሌጁ የማኔጅመንት አባልነት እራሳቸውን በፍቃደኝነት አገለሉ። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2003 ኢንሪችመንት ሴንተር ኢትዮጵያ የሚል ኤን ጂኦ አቋቋሙ። ይህ ተቋም ሕጻናትና ታዳጊዎችን በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ለመደገፍ እና ለማብቃት የተመሰረተ ነው። እራሳቸው ካቋቋሙት ድርጅት ጎን ለጎን በጓደኞቻቸው ጥቆማ በሕፃናት ላይ የሚሠራ የስፔን ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆን ለ14 ዓመት አገልግለዋል። የእርሳቸው ተቋም ደግሞ ላለፉት 22 ዓመታት ትኩረቱን የሕፃናት እንክብካቤ፣ ድጋፍ ላይ አድርጎ አስካሁን ድረስ እየሠራ ይገኛል።
በዚህ መሃል አቶ ሳሕሉ አሜሪካን ሀገር የመሄድ እድል ገጥሟቸው ነበር። ወደዚያ ያቀኑት ለኮንፍረንስ ነበር። ቢሆንም ቨርጂኒያ በሚኖር አንድ ጓደኛቸው ጥያቄ መሰረት በዚያ አንዲቆዩ ግፊት ተደረገባቸው። ኒዮርክን ጨምሮ በተለያዩ ስቴቶች ለተወሰኑ ጊዜያት ለመቆየት ሞከሩ። ሆኖም ‹‹አሜሪካን ሀገር ከእኔ ባኅሪና የሥራ ልምድ ጋር አይሄድም ወደ ሀገሬ መመለስ እና ያስተማረኝን ወገኔን በሙያዬ አገለግላለሁ›› በሚል ተመልሰዋል። ቀደም ሲልም ላመኑበት ጉዳይ በፅናት የመቆም እሳቤ ያላቸው እንግዳችን በዚህ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው በመመለስ የጀመሩትን ተቋም ለማሳደግ ደፋ ቀና ብለዋል።
ሰዎችን ለመርዳት ንፁ ልቦና ሊኖረን ይገባል ይላሉ አቶ ሳሕሉ። የእርሳቸው መርህ ቅንነትና ግልፅነትን ከፊት ማስቀደም ነው። በዚህ ላይ የተመሰረተው ድርጅታቸው በብዙዎች ዘንድ እውቅናን እንዲያተርፍና ታዳጊ ሕፃናቱም ድጋፍ አንዲያገኙ አስችሏል።
ኢንሪችመንት ሴንተር
እንግዳችን ሕፃናት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሠራው ኢንሪችመንት ሴንተር በርከት ያሉ ፕሮግራሞችን ተፈፃሚ አድርገዋል። ከዚህ ውስጥ ለትምህርት ቤቶች፣ ሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የአቅም ገንባታ ሥልጠናዎች ይሰጣል። ታዳጊዎች በትምህርትና በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት በፅናት መቋቋም እንዲችሉ የማማከር ሥራም ይሠራል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እና ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋል። የክበበ ፀሀይ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋም ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሕንፃም አስገንብቷል። የምእራፍ አፀደ ሕፃናት ውስጥም 140 የሚደርሱ ታዳጊዎቸን ይደግፋል።
‹‹ርዳታ መስጠት ዋናው ግባችን አይደለም›› የሚሉት አቶ ሳሕሉ ዋናው ታዳጊ ሕፃናት ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እንክብካቤና ድጋፍ እንዲያገኙ መሰረት መጣል ተቀዳሚ አላማቸው መሆኑን ይናገራሉ። ይህንን ተፈፃሚ ለማድረግ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሕፃናትን የሚንከባከቡ ባለሙያዎችን ሳይንሳዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ ያስረዳሉ። ባለሙያዎቹ ብቁ ከሆኑ ሕፃናት በሚፈለገው ልክ እንክብካቤና ትኩረት አግኝተው እንደሚያድጉ እምነት አላቸው። በዚህም ኢንሪችመንት ሴንተሩ ኢትዮጵያዊ እሴትና ባሕልን ሳይለቅ ሳይንሳዊ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ስልጠናዎቹን በአማራ ክልል ደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት፣ ወልዲያ አደንጉር ትምህርት ቤት ውስጥ አስከ ቅርብ ገዜ ድረስ (በፀጥታው ሁኔታ እስኪቋረጥ ድረስ) ሲሰጡ ቆይተዋል። በሀረር የአወዳይ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎችን በማስገንባት፣ በደሴ የንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት ክሊኒክና የምግብ አዳራሽ በማስገንባት ተሳትፎ አድርገዋል።
‹‹እስካሁን አስር ሺህ በላይ ታዳጊ ሕፃናትን መድረስ ችለናል›› የሚሉት አንግዳችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የውጪ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ መቀዛቀዝ፣ የአንዳንድ ሕጎች ሥራዎች ላይ ጫና መፍጠር ተግባራቸው ላይ እክል እየፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ሆኖም ይህንን ተግዳሮት ለመፍታትና የቆሙለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በጎ ፈቃደኞችን በማሰባሰብ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሳደግ እየሠሩ ይገኛሉ።
አቶ ሳሕሉ ከመሰረቱት ተቋም ባሻገር የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን አማራጮችን በመጠቀም ታዳጊ ሕፃናት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ሲወተውቱ ቆይተዋል። በተለይ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በሕፃናት እድገት በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በርካታ መጣጥፎችን፣ በራዲዮ እና በአዲስ ዘመን፣ በሪፖርተር ጋዜጦችና በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በተለይ ‹‹የነገን ሰው ማነፅ›› በሚል ርዕስ የሕፃናት መፅሀፍ በማሳተም ለአንባቢያን አድርሰዋል።
ትውልዱ ምን ይማር
የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን አቶ ሳሕሉ በትዳር ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ ለ42 ዓመታት ከባለቤታቸው ሰኪና ሁሴን ጋር በትዳር እየኖሩ ነው። ሁለት ልጆችንም አፍርተዋል። ጥንዶቹ ከተለያየ ባሕል፣ አስተዳደግና እምነት የመጡ ቢሆንም ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን በሚችል መልኩ በሰላምና በፍቅር ቤተሰባቸውን መርተዋል። አቶ ሳሕሉ ለመልካም ትዳር መጎልበት ነፃነትና የሌላውን ሰው አመለካከትና እሳቤ ማክበር ቁልፍ ነው የሚል እምነት አላቸው። በዚህ መርህ ላይ የመሰረቱት ትዳር ወደ ልጆቻቸውም ተጋብቶ የተሻለ ሕይወትን እየመሩ ይገኛሉ።
እርሳቸው በመምህርነት፣ ታዳጊ ሕፃናትን የሕይወት መስመራቸው እንዲቃና በመደገፍ ሂደት ውስጥ፣ የእውቀትና የልምድ አድማሳቸው አንዲሰፋ የቤተሰባቸው ደጋፍ እንዳልተለያቸው ያስረዳሉ። ወጣቱ ትውልድ ከእርሳቸው የሕይወት ልምድ መልካሙን እንዲቀስምም ይመኛሉ። ‹‹ትውልዱ ራዕይ እንዲኖረውና ስኬታማ አንዲሆን መሰረት ልንጥልለት ይገባል›› የሚል ፅኑ አመለካከት አላቸው።
‹‹ዓለምን የምናይበት አዕምሯችን የሚመነጨው ከሥርዓት ነው›› የሚሉት አቶ ሳሕሉ፤ ለወጣቱ መሰረት ለመጣል ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነት መውሰድ አለበት ይላሉ። ለትውልዱ የሚጠቅም ወጣት ለማፍራት የመጀመሪያው ቀለበት ቤተሰብ መሆኑን በማንሳትም ትምህርት ቤት፣ ጎረቤት፣ አካባቢ እና ማኅበረሰብ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
አቶ ሳሕሉ በርካታ ሀገራትን (አውሮፓ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ሌሎቸ ሀገሮችን ጨምሮ) መጎብኘታቸውን ይናገራሉ። ሆኖም ኢትዮጵያን የመሰለ በተፈጥሮና በባህል ፀጋ የተባረከ ሀገር አለማየታቸውን ይመሰክራሉ። እነዚህን አሴቶች መጠበቅ የሚችል ወጣት ለማፍራት የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚገባም ይመክራሉ። ዓለም አሁን የደረሰበት ደረጃ ሰዎች ከተረጂነት እሳቤ እንዲላቀቁ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን በማንሳት ከእርዳታ ይልቅ ወጣቶችን ማስተማር፣ አቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት እና ታዳጊ ሕፃናትን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ማነፅ መፍትሄ እንደሆነ ይመክራሉ። የድርጅታቸው ዓላማም ይህ መሆኑንን በመግለፅ ሁሉም የድርሻውን በዚህ ዙሪያ እንዲሠራ ጥሪ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አቶ ሳሕሉ ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ ሁሉም ዜጋ በጋራ መረባረብ አለበት ይላሉ። ኢትዮጵያ በአየር ፀባይ፣ በተፈጥሮ ፀጋ፣ በባሕል፣ በቱሪዝም፣ በብዝሀ ሃይማኖት የታደለች ሀገር እንደሆነች ደጋግመው የሚናገሩት እንግዳችን ይህንን እምቅ ሀይል ወጣቱ ጠብቆ ማቆየት እንዲችል፤ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ከምንም በላይ ዛሬ መሰረት ማኖር አለብን ይላሉ። ‹‹ወጣቱ ትውልድ እራሱን ከአላስፈላጊ ነገሮች ይቆጥብ›› በማለት እንግዳችን ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ንባብ የሕይወት የስኬት መሰረት ነው። ‹‹ይህ ትውልድ ጠንካራ፣ ብዙ አውቀት ያለው ብልህ ነው›› የሚሉት አቶ ሳሕሉ እራሱን በንባብ በተጨማሪነት ቢያዳብር የወደፊት ሀያል ሀገር መገንባት በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። የዝግጅት ክፍላችንም አንግዳችን ቀሪ ዘመናቸውን ትውልዱን የሚያነቁበት ሀገራቸውን ያለድካም የሚያገለግሉበት እንዲሆንላቸው እየተመኘን በዚሁ አበቃን። ሰላም!
በዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም