ሥነ ጽሑፋዊና ሥነ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሥራዎችን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላኛው መተርጎምና ለአንባቢዎች ማቅረብ በዓለም ዙሪያ ባሉ አገራት የተለመደ ተግባር ነው። የትርጉም ሥራ ለተለያዩ አላማዎችና ውጤቶች ይሠራል።
የትርጉም ሥራዎች በሌላ ቋንቋዎች የተጻፉ ጽሑፎችን ለአንባቢያን ወይም ለተገልጋዮች በራሳቸው ወይም በሚገባቸው ቋንቋ ለማቅረብ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በተጨማሪም የአንድን ማህበረሰብ ባህሎች፣ ልምዶች፣ እና ወጎች ለሌ ላው ለማካፈል ወሳኝ ናቸው።
በአገራችንም በተመሳሳይ ሁናቴ ትርጉሞች ከውጭ ቋንቋዎች ወደ አማርኛ በብዛት የሚሠሩ ሲሆን አልፎ አልፎም ወደ ሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ይተረጎማሉ። ከአማርኛም ወደ ሌሎች ብሔረሰብ ቋንቋዎች የትርጉም ሥራዎች እንደሚሠሩ ይታወቃል።
ለዚህ ጽሑፍ ያነሳሳኝ ታዲያ አንድ ወዳጄ ነው። ወዳጄ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ‹ከቀንበር እስከ መንበር› በሚል የሠራውን ትርጉም “አንብበውና አስተያየትህን እጠብቃለሁ” አለኝ ፤ ለእሱ አስተያየት ለመስጠት መጻፌ ካልቀረ ለሌላውም አንባቢ ይጠቅም ይሆናል ያልኩትን ስለ ትርጉም ሥራዎች የሚታየኝን ወርወር ማድረጉን ወደድኩና አፈወርቅ ገብረኢየሱስ እንዳሉት ይችን ጽሑፍ “ልዶገዱግ” ወደድኩኝ።
ሌላው ከዚህ ቀደም ስለ ትርጉም ሥራ ችግሮች ከደራሲ ጌታቸው በለጠ ጋር ባጋጣሚ ያወጋነው ሁል ጊዜ ትዝ ስለሚለኝና በትርጉም ሥራዎች ላይ እኔ እስከማውቀው ድረስ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ባሉ ተቋማት ካልሆነ በስተቀር ለምልአተ ህዝቡ በሚሆን መልኩ በቂ የሂስ ሥራ ሲሠራ አላስተዋልኩም።
የትርጉም ሥራ
የትርጉም ሥራ በኢትዮጵያ በጣም ረዥም ታሪክ ያለው ነው። አገራችን የቀደምት ሥልጣኔዎች አካል በመሆኗና በነበራት ሰፊ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጥንታዊ መጻሕፍትን የማግኘትና ወደራሷ ቋንቋ የመተርጎምና የማስተርጎም ዕድሉ ነበራት። በተለይም በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአክሱም ነግሦ የነበረው ንጉሥ ኢዛና የክርስትናን ሃይማኖት መቀበሉን ተከትሎ በአቡነ ሰላማ እና በዘጠኙ ቅዱሳን አማካኝነት የመጻሐፍ ቅዱስ ትርጉም በስፋት እንዲሠራ አድርጓል።
ገና ከ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አራቱን ወንጌሎች ቀጥሎም ሙሉ መጻሕፍ ቅዱስ ተተርጉመዋል። መጻሐፍቱም ሲተረጐሙ ከየትኛው ቋንቋና ምን ዓይነት የቋንቋ ተናጋሪ እንደተረጎመው የሚያመለክቱ የመጀመሪያው ቋንቋ ቃላት ተጽዕኖ ይገኙባቸዋል። ከጥንታዊ የግዕዝ ትርጉም መጻሕፍትም መጽሐፈ ቄርሎስ እና ፊሳሎጎስ የተባሉት ይገኙበታል።
በዘመናዊ ኢትዮጵያም በርካታ ድንቅ ሥራዎች ተተርጉመው ለንባብ እንደበቁ እናውቃለን። ለምሳሌ በ1940ዎቹ እነ ከበደ ሚካኤል የሼክስፒርን ሮሚዮና ጁሌት የመሳሰሉ ሥራዎችን አበርክተዋል፣ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንም በርካታ የሼክስፒር ሥራዎችን ድንቅ በሆነ ሁኔታና ብቃት በ1960ዎቹ ተርጉሟል።
በደርግ ዘመንም የ “ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት” ተቋቁሞ በአብዛኛው ከሶሻሊስት ሶቪዬት ሕብረት የተተረጎሙ የአማርኛ ሥራዎችን በስፋት አድርሶናል። በዛው ዘመንም የዳኒኤላ ስቴልን፣ የሲድኒ ሸልደንንና የአርቪንግ ዋላስን፣ የጃኪ ኮሊንስ ሥራዎች ጨምሮ ሌሎች ልብወለዶችን በአማርኛ አግኝተናል።
ቀደም ሲል ከተሠሩ የትርጉም ሥራዎችን ጥቂቶቹን ማየት ይቻላል ለምሳሌ፦ ሄሚንግዌይ፣ “እሪ በይ አገሬ”፣ ደራሲ አላን ፒተን፣ በአማረ ማሞ ፣ “የስዕሉ ሚስጢር”፣ ደራሲ ኦስካር ዋይልድ፣ ተርጓሚ ፋሲል ተካልኝ፣ “ጠልፎ በኪሴ”፣ ደራሲ ተውፊቅ አልሃኪም፣ በመንግሥቱ ለማ ፣ “የእንስሳት እድር”፣ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል፣ በለማ ፈይሳ ፣ “ተረበኛው ነስሩዲን”፣ ደራሲ ኢድሪስ ሻህ፣ ተርጓሚ አማረ ማሞ፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው”፣ ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል፣ በነቢይ መኮንን፣ “መከረኞች”፣ ደራሲ ቪክቶር ሁጎ፣ በሳህለ ሥላሤ ብርሃነማሪያም፣
“የሁለት ከተሞች ወግ”፣ ደራሲ ቻርለስ ዲከንስ፣ በሳህለ ሥላሤ ብርሃነማሪያም፣ “የአገር ልጅ”፣ ደራሲ ሪቻርድ ራይት፣ በሳህለሥላሤ ብርሃነማሪያም፣ “ዶን ኪኾቴ”፣ ደራሲ ሚጉኤል ሰርቫንቴስ፣ በዳምጤ
አሰማኽኝ፣ “እፎይታ”፣ ደራሲ አሌክሳንደር ዱማስ ፔሬ፣ “ጃኩሊን”፣ ደራሲ አጋታ ክሪስቲ፣ “የደም ጎጆ”፣ ደራሲ አጋታ ክሪስቲ፣ በሌተናልኮሎኔል ጌታቸው መኮንን ሐሰን መጥቀስ ይቻላል። ሌሎች በርካታ የትርጉም ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል። በአሁኑ ጊዜም በርካታ የትርጉም ሥራዎችም እየተሠሩ ይገኛሉ።
የትርጉም ሥራዎች ጠቀሜታ
የትርጉም ሥራዎች በአብዛኛው በሌላ ቋንቋዎች ተጽፈው የነበሩትን አንዳንድ ጽሑፎችን ለሌላ ቋንቋ አንባቢዎች ወይም ተገልጋዮች በራሳቸው ወይም በሚገባቸው ቋንቋ ለማቅረብ ሊሠሩ ይችላሉ። እንዲሁም የአንድን ማህበረሰብ ባህሎች፣ ልምዶች፣ ዘይቤዎች፣ ወጎች፣ እሴቶች ፣ ሥነ ¬ቃሎች፣ ተረቶች፣ አፈ¬ታሪኮች፣ ሐተታ ተፈጥሮዎች፣ አገር¬በቀል እውቀቶችና የመሳ ሰሉትን ለሌላኛው ለማካፈልና ለማሳዎቅ እንዲሁም እንደመዝናኛ ለመጠቀም የትርጉም ሥራዎች ይሠራሉ።
በተጨማሪም የትርጉም ሥራዎች ሥነ ጽሑፍን ለማጎልበትና ያጻጻፍ ስልትን ከሌሎች ለመማር ያግዛሉ። እንዲሁም ለትምህርትና ለመዝናናትም ጠቀሜታው የጎላ ነው። በሌላ በኩልም ለህትመት ኢንዱስትሪውና ለሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችም የሥራ ዕድልን በመፍጠርም የራሱ ሚና ይኖረዋል።
ጥሩ ተርጓሚ የምንለው እንዴት ያለውን ነው ?
ከላይ የተጠቀሱትን አበይት ጉዳዮች ካነሳን በኋላ ጥሩ ተርጓሚ የምንለው እንዴት ያለውን ሰው እንደሆነ ማየቱ በጣም ተገቢ ነው። የቋንቋ ጠበብት በአብዛኛው የሚስማሙባቸው ብቃት ያላቸው ተርጓሚዎች ክህሎትና እውቀቶች የሚከተሉት ናቸው።
• ሞያዊና ጥልቅ የሆነ ትርጉም የሚሠራበት ምንጭ ቋንቋ እውቀትና ክህሎት Source Language (SL) skills
• ሞያዊና ጥልቅ የሆነና ትርጉም የሚሠራለት መዳረሻ ቋንቋ እውቀትና ክህሎት Target Language (TL) skills
• ሙያዊ እውቀት /Specialisation/ (አንድ ጥሩ ተርጓሚ ትርጉሙ በሚሠራበት ጉዳይ ወይም ኢንዱስትሪ ዙሪያ ጠለቅ ያለ እውቀት ቢኖረው በጣም ተመራ ጭ ነው)
• የጽሑፍ ችሎታ
• የትምህርት ዝግጅትና ጠቅላላ እውቀት
• ለትርጉም ሥራ የሚሆኑ ግብአቶችን (ለምሳሌ እንደ መዝገበ ቃላትና ማጣቀሻ መጽሐፍት ወ•ዘ•ተ•)
• ባለንበት ዘመን ደሞ ኮምፒውተር ተጠቃሚ ቢሆን ይመረጣል
ሥነ ጽሑፋዊና ሥነ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሥራዎች ትርጉም ልዩነትና አንድነት አላቸው። አንድ ተርጓሚ የትርጉም ሥራ ከመጀመሩ በፊት ሊተረጉም ያሰበው ሥራ ሥነ ጽሑፋዊ ወይም ሥነ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መሆኑን ማጤን ይኖርበታል። ምክንያቱም ሁለቱ ልዩነትና አንድነት ስላላቸው ነው።
ሥነ ጽሑፋዊ የትርጉም ሥራዎች
ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች በአብዛኛው ፈጠራ እና ምናባዊነት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ሥነ ጽሑፋዊ የሆኑ ጽሑፎችን ስንተረጉም ፊደላዊ ቅርፅን ብቻ ሳይሆን ዐውዳዊ ፍችውንም በትክክል ለማግኘት ማሰብ ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ የሥነ ጽሑፍ ባለሞያዎች ይህንን ”A literary translation must reflect the imaginative, intellectual and intuitive writing of the author” በማለት ይገልፃሉ።
በአብዛኛው ሥነ ጽሑፋዊ በሆኑ ጽሑፎች መልዕክት በቀጥታ ስለማይነገር ፀሐፊው ሊል የፈለገውን በትክክል ለማግኘት ጥንቃቄ የተከተለ አካሄድ ያስፈልጋል። ቀደም ባለው ጊዜ በሥነ ጽሑፋዊ ትርጉም ጊዜ ምሁራን ፕራገማቲዝም የተሰኘውን እና የደራሲውን ትክክለኛ መልዕክትና ፍላጎት፣ የሁኔታዎችን እና የትርጉሙን ተቀባይነት ጨምሮ ሌሎችን ዘዴዎች በመጠቀም የትርጉም ሥራን በትክክል ለመሥራት እንደሚቻል ይመክሩ ነበር።
በአጠቃላይ የሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ትርጉም ሌሎችና ሰፊ የትርጉም መመዘኛዎችና አካሄዶች ያሉት በመሆኑ እራሱን የቻለ ትልቅ ሞያ ነው።
የሥነ ጽሑፋዊ ትርጉምን ስናነሳ ከላይ የተጠቀሱት ጥቂት ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች አሉት። ለአሁኑ ሥነ ጽሑፋዊ የሆኑም ይሁን ያልሆኑ ጽሑፎችን ስንተረጉም ባጠቃላይ ምን ምን ሞያዊ ሂደቶችን ልንከተል እንደምልችል ላንሳ።
አንድ ተርጓሚ አንድን ሥራ ለመተርጎም ከወሰነ
ወይም ፈቃድ ካገኘ በኋላ እንደየሁኔታው የሚተረ ጉምበትን መንገድ መወሰን የራሱ መብት አለው። ከታቸ ከተዘረዘሩት በአንደኛው መንገድ ሊተረጉም ይችላል። ነገር ግን በሁሉም መንገድ ብቃትንና ሞያዊ መንገድን ተከትሎ መሄድ ይገባል።
ቀጥታ ትርጉም
ቀጥታ ትርጉም የሚባለው ትርጉም በሚሰራበት ምንጭ ቋንቋ የሚገኙ ዐውዳዊ ትርጉሞች እና ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ ሳይነካኩ ወደ መዳረሻ ቋንቋ መተላለፍ ሲኖርባቸው የሚሰራ ነው።
በዚህ የቀጥታ ትርጉም ሥር የሚካተቱት ደግሞ የውሰት፣ የብድር እና የቃል በቃል የሚባሉ ናችው። የመጀመሪያው የውሰት የሚባለው አንድን ቃል ወይም ቃላትነ በቀጥታ ከአንድ ቋንቋ የመውሰድና የመጠቀም ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ለአማርኛ ከእንግሊዝኛ ቴሌቪዥን ወይም ካፌ (café ) የሚሉትን ቃላት እንደምንጠቀመው ብዙ ጊዜ ተርጓሚዎች እንደዚህ ማድረግ የሚገባቸው አማራጭ ሲያጡ ብቻ እንደሆነ ይገለፃል። ሁለተኛው የብድር ትርጉም የሚባለው ደግሞ በአንድ ቋንቋ ያለን አባባል እና ገለፃ እንዳለ በሌላኛው ቋንቋ መተርጎሙ ነው። ለምሳሌ አንድ በእንግሊዝኛ የሚናገር ሰው ስለ አንድ ንብረት አንስቶ “It is a white elephant ” ቢል እና ተርጓሚው ይህን አባባል “ይሄ ነጭ ዝሆን ነው።” ብሎ ቢተረጉመው ትርጉሙ የብድር ትርጉም ይባላል። ይሄ ማለት ግን ተርጓሚው ተናጋሪው ሊለው የፈለገውን ጉዳይ በትክክል ተርጉሞለታል ማለት አይደለም። የእንግሊዝኛ ተናጋሪው እዚህ ጋር ንብረቱ ምንም የማይፈይድ ለታይታ ብቻ የተቀመጠ ማለቱ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ነው ከላይ የተጠቀሰው የፕራገማቲዝም (Pragma-tism) እና ሌሎችንም መንገዶች ማሰብ የሚያስፈልገው። ሦስተኛው የቃል በቃል (Literal) ደግሞ በአንድ ቋንቋ ያሉ ቃላትን በቃላት ደረጃ እያንዳንዱን በመልቀም ወደ መዳረሻ ቋንቋ መለወጥ ሲሆን ይሄ ትርጉም ይበልጥ ለጥንቃቄ የሚረዳ ሲሆን የትርጉሙን ሁኔታ ግን በአጠቃላይ በአረፍተ ነገር ደረጃ ሊያዛባ ስለሚችል
ጥንቃቄ ያሻዋል።
ቀጥታ ያልሆነ ትርጉም
ቀጥታ ያልሆነ ትርጉም የሚባለው ትርጉም በሚሰራበት ምንጭ ቋንቋ Source Language የሚገኙ ዐውዳዊ ትርጉሞች እና ባህላዊ እሴቶች ተለውጠውና ለአነባቢው ወይም ለተጠቃሚው በሚመች ወይም በሚመጥን ደረጃ ወደ መዳረሻ ቋንቋ Target Language መተላለፍ ሲኖርባቸው የሚሰራ ነው።
እነዚህ የትርጉም አይነቶች Transposition ፣ Mod¬ulation ፣ Reformulation or Equivalence፣ Adap¬tation እና Compensation የተሰኙ እና ለተርጓሚው ነፃነትን የሚሰጡ አካሄዶችን ያካተቱ ሲሆኑ ተርጓሚው ከሚተረጉመው ሥራ የተወሰነውን አንኳር ጉዳዮች ወስዶ በራሱ አባባልና ቋንቋ ለራሱ አንባቢ ወይም አድማጭ / ተመልካቸ የሚያቀርብበት ናቸው። የአገራችን ድንቅ ፀሐፌ ተውኔተ የነበረው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የ“ጥሩ ተርጓሚ” መስፈርቶች ያሟላ ፀሐፊና ተርጓሚ ስለነበር ቀጥታ ትርጉምም ሆነ ቀጥታ ባልሆኑ ትርጉሞች በተለይ በበርካታ የሼክስፒር ሥራዎችን በድንቅ ብቃት በመተርጎምና በማዘጋጀት በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማድረሱን ትውልድ ሲዘከረው ይኖራል።
ለመቋጨት
ጥሩ አንባቢ ከምንላቸው ጓደኞቻችን በተጨማሪም የቋንቋ ሞያ ወሳኝ ስለሆነ የመጨረሻ ቅጅዎችን ሁል ጊዜ ለቋንቋ ባለሙያዎች ማሳየት ጥሩ ይመስለኛል። ዝርዝር የቋንቋ ጉዳዮችን እና ሌሎች ሁኔታዎችን ባለቤቱ የቋንቋ ሰው እንጂ መሐንዲስ ወይም ሳይንቲስቱ ሊያየው አይችልምና ነው። ችላ ማለት ትልቅ የማናውቀው ጉድለት ይሆናል። ምክንያቱም ከሞያችን ውጭ የሆኑትን ጉዳዮች የምናውቅ ይመስለናል እንጂ ምን ያህል በጥልቀት እንደምናውቃችው እርግጠኞች አይደለንምና። የሙያው ባለቤት ግን የሞያው ሀ ፣ ሁ አለውና ልንጠቀምበት ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
በመኮንን ተሾመ ቶሌራ
(በውጭ ቋንቋችና ሥነ ጽሑፍ 2ኛ ዲግሪ)