
በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የዘርፉ ተሳትፎ እየጨመረ እንዲመጣ እያደረጉ ይገኛሉ። ባለሀብቶቹ ወደ ዘርፉ ይዘው የሚመጡት ካፒታልም ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል እየፈጠሩ ያሉበት ሁኔታም እያደገ ነው።
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በሀገሪቱ በአጠቃላይ በተካሄደው ሪፎርም ውጤት የታየባቸው ተብለው ከሚነሱት ውስጥ አንዱ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ነው። ኢንቨስትመንቱ ከ2015 ጀምሮ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። በ2016 ዓ.ም ከአጠቃላይ ጂዲፒ የኢንቨስትመንቱ ዘርፉ 20 በመቶ መያዙ እንዲሁም በ2017 ደግሞ ይህ አሀዝ ወደ 23 ከፍ ማለቱም በዘርፉ ያለውን ለውጥ ይጠቁማል።
ሀገሪቱ ለአንቨስትመንት ካላት እምቅ አቅም አኳያ አሁንም ባለሀብቶችን ለመሳቡ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉና የመሳሰሉት መድረኮችም ዘርፉን ለማስተዋወቅ፣ የዘርፉ ምርታማነት እንዲያድግ ለማድረግ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚከናወኑ ተግባሮች ናቸው።
በክልሎችም ተመሳሳይ ተግባሮች እየተከናወኑ ውጤቶችም እየታዩ ናቸው። በሀረሪ ክልል በዘርፉ እየተከናወነ ያለው ተግባርና የተገኘው ስኬትም ይህንኑ ያመለክታል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የኢንቨስትመንት ልማትና ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ተስቲ አብዱራህማን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ በክልሉ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚከናወኑት ከክልሉ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ጋር በተቀናጀ መልኩ ሲሆን፣ የኢንቨስትመንቱ ውጤታማነት የሚለካውም ለክልሉ እና እንደ ሀገር ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንጻር ነው።
በዚህ መሠረት በተለይ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችንም ለማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ተግባሮች ሲከናውኑ ቆይተዋል። ለዚህም እንደ መነሻ ያገለገለው በፌደራል መንግሥት በኩል ለኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ነው። የሀረሪ ክልልም ያንን መሰረት በማድረግ እንደ ክልል ያቀደውንም፣ ሀገራዊ እቅዶችንም ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል ያሉት አቶ ተስቲ፣ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ የበጀት ዓመቱን ሥራውን የጀመረው በቅድሚያ ራሱን በመገምገም ነበር ሲሉ አስታውሰዋል። ግምገማው በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የተቀናጀ አሠራር አለመኖሩን ማመላከቱንም ተናግረዋል።
እንደ መንግሥት በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የተቀላጠፈ አካሄድ ባለመኖሩ በሚፈጠሩ መዘግየቶችና መጉላላቶች በኢንቨስተሮች በኩል ሲነሳ የነበረው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋግጧል ሲሉ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለረዥም ዓመታትም በቀላሉ ውሳኔ ሊያገኙ የሚችሉ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ እየወሰዱ ተገልጋይን ለድካምና ለተደራራቢ ወጪ ሲዳርጉ ኖረዋል። የዚህ ክፍተት አጠቃላይ ውጤት በክልሉ ሊካሄድ የሚገባው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሚጠበቀው ደረጃና ፍጥነት እንዳይከናወን አድርጎታል። በተጨማሪ ቀልጣፋ የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩ ተገቢ ባልሆነ መንገድና ከሕግ ውጪ በዘረፋና ማጭበርበር በዘርፉ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉትንም ለመቆጣጠር እንዳይቻል አድርጎ ቆይቷል።
በመሆኑም የ2017 በጀት ዓመት ሲጀመር አንደ ቀዳሚ እቅድ የተቀመጠው ቢያንስ በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በመንግሥት አገልግሎት አቀራረብ ረገድ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር መዘርጋት እንዲቻል ማድረግ የሚለው ነበር። በዚህ መሠረትም በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ የተገባው ከከተማ ልማት፤ ከኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ የተውጣጡ አባላትን የያዘ የኢንቨስትመንት ንቅናቄ ኮሚቴ በማዋቀር ነው።
ኮሚቴው ያለፉትን የሥራ ክንውኖች መሠረት በማድረግ የመጀመሪያ ሥራውን ያደረገው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደውና ሥራ ጀምረው ያቋረጡ ተቋማትን በማወያየት ነበር። ይህ የተደረገበትም ምክንያት በቅድሚያ ችግራቸውን ለመለየት ሲባል ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የባለሀብቱን ተሳትፎና አብሮ የመሥራት ልምድ ለማሳደግም ነው። በውጤቱም በክልሉ አንዳንድ የኢንቨስትመንት እንቅስቀሴዎች ከግብዓት እጥረት፤ ከፋይናንስ መዳከም እና ሌሎች ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ሥራ ማቆማቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።
በተጨማሪም በዚሁ ኮሚቴ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የፕሮጀክት ሃሳብ አቅርበው በኢንቨስትመንት ቦርድ ውሳኔ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃ እንዲፈተሽ ተደርጓል።
በዚህ መነሻነትም ቦርዱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሸን ቢሮ ጋር በመቀናቀጀት የተላለፉ ውሳኔዎች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መረጃዎችን የመሰብሰብ ሥራ ተከናውኗል። በውጤቱም አብዛኛዎቹ ፈቃድ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፣ በዛ መሠረት ሲንቀሳቀሱ አንዳልነበር ለማረጋጋጥ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን መነሻ በማድረግ በየወቅቱ ቦርዱ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ወደተግባር እንዲገቡ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ችግሮች እየተፈቱ ይገኛል ሲሉ አቶ ተስቲ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል እንደ አዲስ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩትን ቁጥር ለመጨመርም ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ይላሉ። በዚህም የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶችን (የዳያስፖራ ማኅበረሰብ) በማሳተፍ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያሳድጉ ተግባራትን ለማከናወን መቻሉን አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ለ11 የዳያስፖራ ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጥቶ መሬት እንዲያገኙ በካቢኔው ጸድቆላቸው ቦታቸውን ለመረከብ በሂደት ለይ ይገኛሉ። እነዚህ ባለሀብቶች በሀብት ደረጃም ከዘጠኝ ሚሊየን ዶላር በላይ ያስመዘገቡ ናቸው።
ይህም በተለይ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏል፣ በአጠቃላይ በከተማዋ የበርካታ ዜጎች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል እያረገም ይገኛል።
ስለ ኢንቨስትመንት ሲታሰብ ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እና አገልግሎት የሚሰጠው አካል በሰው ሀብትም ሆነ በቁሳቁስ ተገቢ አቋም እንዲኖረው ይጠበቃል የሚሉት አቶ ተስቲ፣ በዚህም ረገድ ክልሉ የቢሮውን አገልግሎት አሰጣጥና አሠራርን የበለጠ ቀልጣፋና ፈጣን እንዲሆን ለማስቻል በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል አፈፃፀምን በየወቅቱ የመገምገም፣ መረጃዎችን በዋትስአፕና በቴሌግራም ከተገልጋይ ጋር የመለዋወጥ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። የቀረጥ ነፃ አገልግሎትንም በገንዘብ ሚኒስቴር በተዘጋጀ መተግበሪያ አማካይነት በዘመናዊና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ መስጠት ተጀምሯል።
እንደ ክልል የኢንቨስትመንት አገልግሎት ለማሳለጥ በተከናወኑ ተግባራት በዘጠኝ ወራት ለ60 አዲስ እና ራሳቸውን ላሳደጉ ባለሀብቶች (ያደገ የማስፋፊያ) የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ79ኙ መሰጠቱንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ይህን አስመልክተው እንዳብራሩትም፤ ይህም በዘርፍ ሲታይ በማኑፋክቸሪንግ 10 በሆቴል 21፤ በግብርና አንድ እና በሌሎች ዘርፎችና በገበያ ማዕከል 47 ናቸው።
እድሳትን በተመለከተም ለ72 ነባር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የፍቃድ እድሳት ሥራዎችን ለማከናወን, ታቅዶ ለ61 የኢንቨስትመንት ፍቃዶች እድሳት ተሰጥቷል።
በዘጠኝ ወራቱ ወደ ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ከተሠማሩ ኢንቨስትመንቶች 375 ሚሊዬን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ መታቀዱን ጠቅሰው፣ አፈጻጸሙም ከዕቅድ በላይ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር በላይ መሆን መቻሉን አመልክተዋል። በዘርፍ ሲታይ በማኑፋክቸሪንግ 147,433,345.80፤ በሆቴል 791,823,348.30; በግብርና 4,980,000 በሌሎች ዘርፎች 809,855,100.90 ብር በላይ መሆኑን አብራርተዋል።
ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ለ950 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ሁሉም ባለሀብቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ በመግባታቸው ከእቅዱ በላይ አንድ ሺ 730 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በዚህ ዓይነት የተጀመረው ውጤታማ እንቅስቀሴ ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚጠበቅ አስገንዝበው፣ ይህንን ማረጋጋጥ እና ባለሀብቶች ዘንድ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የተፈጠረውን አመኔታ ማሳደግ የግድ እንደሚል ገልጸዋል።
ይህንንም ለማድረግ የተገልጋይን የእርካታ ደረጃ ለማወቅ አንድ ጊዜ በውስጥ የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ታቅዶ ሁለት ጊዜ የዳሰሳ ጥናት ማካሄድ መቻሉን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሶሰት ጊዜ በራሪ ጽሁፍና (ብሮሸር) ለማዘጋጀት ታቅዶ ሶስት ጊዜ ተዘጋጅቶ ተሰራጭቷል፤ ለቴሌቪዥንና መገናኛ አውታር ሶስት ጊዜ መግለጫ ለመስጠት ታቅዶ አራት ጊዜ ተሰጥቷል። በተጨማሪ በየዘርፉ ተደጋጋሚ የመስክ ምልከታዎችንም በማድረግ ክፍተቶች ሲገኙ የማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ሶስት ጊዜ በየደረጃው ካሉ አስፈጻሚ አካላት ጋር የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ውይይት ለማድረግ ታቅዶ አምስት ጊዜ ማድረግ መቻሉንም አቶ ተስቲ ገልጸዋል። በውይይቱም ባለሀብቶች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ማቅረባቸውን ጠቅሰው፣ ችግሮቹ የሚፈቱበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ ለመቅረፍ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ አስካሁንም በመደበኛ አካሄድ ሰባት ቅሬታዎች ቀርበው ስድስቱ የተፈቱ ሲሆን፣ አንድ በሂደት ላይ ይገኛል። በቀጣይም የውይይት መድረኮችን በማጠናከር ከተገልጋዮች የሚቀርቡ ችግሮችን ለመፍታት ይሠራል። በዚህ መሠረት ባለሀብቶች በተለያዩ ወቅቶች የሚያቀርቧቸውን ቅሬታዎችና አቤቱታዎች በመፍታት የሚነሱ የመልካም አስተደደር ችግሮችን በወቅቱ ከመፍታት አኳያ ክልሉ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሠራል።
በተጨማሪ በኢንቨስትመንት መስክ እንደ ተግዳሮት ሲነሳ የነበረው በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ስም ፈቃድ ከወጣ በኋላ ለሌላ ሥራ የሚውልበት አካሄድ ነበር። ይህንንም ለመቅረፍ በበጀት ዓመቱ አዳዲስ የገቡና ነባር ፕሮጀክቶች ባወጡት ፈቃድ መሰረት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ በዘጠኝ ወራት አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ በኢንቨስትመንት አዋጅና ደንብ መሠረት የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸውም እንዳሉም አመልክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የክትትልና ድጋፍ ባለሞያዎችና የኢንቨስትመንት ንቅናቄ ኮሚቴ በጋራ በመሆን በ158 ፕሮጀክቶች ላይ የክትትል፤ የቁጥጥርና ድጋፍ ሥራዎችን አከናውኗል። ከዚህ የተገኘው ውጤት በጥሩ አፈጻጸም አምስት ፕሮጀክቶች አዲስ መሬት ተረክበው ወደ ግንባታ መሸጋገራቸውን አመላክቷል።
23 ፕሮጀክቶች አገልግሎት መሰጠት የጀመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በከፊል ሥራ የጀመረ ነው። 19 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሰባት ፕሮጀክቶች ደግሞ በግንባታ ምዕራፍ ላይ ናቸው። ሶስት ፕሮጀክቶች በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽ ቢሮ በኩል ጉዳያቸው የተያዘ መሆኑ ተለይቷል።
በድክመት ከተለዩትና የቅርብ ክትትል ከሚያስፈልጋቸው መካከልም ግንባታ ላቋረጡ ሶስት ፕሮጀክቶች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት ሁኔታ ይጠቀሳል። 68 ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ቢሆኑም ግንባታው አዝጋሚ መሆኑ ታውቆ በጽህፈት ቤቱ በኩል የማስጠንቀቂያና የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። በጥቂቶች ላይ ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ፣ የእገዳና ስረዛ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተሳሳተ መንገድ የሚጓዙትን የሚያርምና የሚያስተምር እርምጃ እንደሚወሰድ ሁሉ በተቀመጠው የሕግ አግባብና ሥነ ሥርዓት ለሚንቀሳቀሱት ደግሞ የማበረታቻ ድጋፍ ይደረጋል፤ ምስጋና ይቀርባል ሲሉም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዚህ ረገድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት ባለሀብቶች የሚያቀርቡትን ልዩ ልዩ የድጋፍ ጥያቄ መነሻ በማድረግ ለአምስት ፕሮጀክቶች በማበረታቻና ድጋፍ የቀረጥና ታክስ ነፃ መብት አጠቃቀም በሚፈቅደው ደንብ መሠረት ድጋፍ ለመስጠት ታቅዶ ለስድስት ፕሮጀክቶች ከቀረጥና ታክስ ነጻ መብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። እነዚህም በዘርፍ ሲታዩ በሆቴል አገልግሎት አራት እና በማኑፋክቸሪንግ ሁለት ናቸው።
በሌላ በኩል በዘርፉ በባለሞያዎች ላይ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመፍታትም፤ በዕቅዱ መሠረት አፈጻጸሞችን የመገምገም ሥራ ተከናውኗል። በዚህም ግብረ-መልሶችን መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቋሚ የግንኙነት ጊዜ ወስኖ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተግባብቶ እና ተስማምቶ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በተጨማሪ እንደ ተቋም የመስክ ምልከታ በማድረግ ለየፕሮጀክቶቹ የክትትልና ድጋፍ ሥራ ለማከናወን የሎጀስቲክስና የፋይናንስ አቅም ውስንንት እንዳለ ጠቅሰው፣ ይህን ለማስተካከል እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ሌላው እንደ ተግዳሮት በስፋት የሚነሳው በቂ የመሬት አቅርቦት አለመኖር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም በከተማዋ ያረጁ ቤቶች ያሉባቸውን አካባቢዎች ከኪራይ ቤቶች ጋር በመነጋጋር በመልሶ ማልማት በማንሳት ለኢንቨስትመንት ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ለተነሺዎቹ ከተማ አስተዳደሩ በሚያዘጋጀው ተለዋጭ ቦታ ላይ በባለሀብቶች ገንዘብ ቤት እንደሚገነባላቸውም አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ሲያመላክቱ እንዳስታወቁት፤ በዋና ተግዳሮትነት ከተለዩት መካከል የመሠረተ ልማት አለመሟላት አንዱ ነው። ይህንንም ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል። የመብራት ትራንስፎርመር እና ፕሮጀክቶች አካባቢ ካሉት የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ቋሚዎች መካከል ችግር ያለባቸው ተለይተዋል። እነዚህንም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲስተካከሉ ማድረግ ላይ እየተሠራ ይገኛል።
የድጋፍና ክትትል ሥራን በማጠናከር ከአቅም በታች የሚያመርቱ ፕሮጀክቶችን በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ ችግሮቻቸውን በመለየት ድጋፍ ለመስጠት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችም እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከዚህ ውስጥ የፋይናንስ እጥረት ያለባቸው የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
በራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም