
አዲስ አበባ፡- ሳይንስን ሕዝባዊ ማድረግ ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት ያስችላል ሲሉ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ገለጹ፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ሳይንስን የመረዳት ችግር እንዳለ አመለከቱ።
ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሰሞኑን ሳይንሳዊ ገለጻ ባቀረቡበት ወቅት ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሳይንስ እውቀት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብ ጭምር እንደመሆኑ፤ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ምክንያታዊ አስተሳሰብን የሚያለማምድ ነው፡፡
ስለዚህ ሳይንስን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል እንዲያውቀው ማድረግ ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው፡፡ ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብ አስቦ አሰላስሎ ችግሮችን በንግግር ስለሚፈታ ብዙ ጊዜ ለግጭት አይዳረግም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሁለትና ሦስት ምክንያቶች በእኩል ደረጃ እውነት ሊሆኑ አይችሉም ያሉት ፕሮፌሰር ሽብሩ፤ ሳይንስን ሕዝባዊ ማድረግ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እውነት የሆነውን በመከተል ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ ሳይንስን የመረዳት ችግር እንዳለ በመግለጽ፤ ምክንያቱም ሳይንስ ማለት እውቀትን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ምክንያቱን መረዳት እና ሂደቱን ማወቅ ነው።
የሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች ያደጉት እቃ ሳይሆን እውቅት በመግዛታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ከምዕራባዊያን መኪና ከገዙ በኋላ ፈታተው ይማሩበት እና መልሰው የራሳቸው ያደርጉታል፡፡ ስለዚህ እንደማህበረሰብ መኪና ወይም ቴክኖሎጂ መግዛት ሳይሆን፤ እውቀት መግዛት ባሕል ሊሆን ይገባል ሲሉ አመላክተዋል፡፡
ሳይንስን ሕዝባዊ ለማድረግ በእያንዳንዱ ነገር ላይ በማስተዋል እና በሙከራ ላይ የተመሠረተ ጥናት በማድረግ ምክንያታዊነታቸውን መዘርዘር እና መማር የሚያስችል መንገድ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት ሕጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሳይንሳዊ አካሄድ እየተነገራቸው ነው የሚያድጉት፡፡ ለአዋቂዎችም ሳይንሳዊ የሆኑ ልቦለዶች አሏቸው ሲሉ አንስተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሽብሩ እንደተናገሩት፤ በሳይንሳዊ ትምህርት ሕጻናትን ለማነጽ፤ በየትምህርት ቤቱ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮችን እና ግብአቶችን ማደራጀት አስፈላጊ ነው፡፡
በተለይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሳይንስ ክበቦችን ማጠናከር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየአካባቢው የማይታረሱ መሬቶችን በመውሰድ ዛፎችን በመትከል ተማሪዎች እየሄዱ በዛፎቹ እና በአካባቢው በሚገኙ ነፍሳት ላይ እንዲመራመሩ በማድረግ፤ ሳይንስን ሕዝባዊ ማድረግ ወይም ሁሉም ሰው እንዲያውቀው ማድረግ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህም ሳይንሳዊ አመዘጋገብ እና ያገኙትን መረጃ የማቅረብ ስልት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሲሆን፤ በተጨማሪም ነገሮችን ግልጽ በሆነ መንገድ የመናገር አቅም ያዳብርላቸዋል፡፡ አለፍ ሲልም በትምህርት ቤቶቹ የሚቋቋሙ የሳይንስ ክበቦች የተወሰነ ገጽ ያለው መጽሔት እንዲያዘጋጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ከእዚህ አንጻር ማህበረሰቡ ለአንዳንድ ነገሮች የሚሰጠውን ድምዳሜ ምንክንያት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም