የነገው ሰው

“ሰላሳ መጸዳጃ ቤቶችን ከመንግሥት ተረክበን ሥራ ለመጀመር በመጠገን ላይ ሳለን አንዳንድ ተጠቃሚዎች በሩም እንደሰዎቹ ጉዳተኛ ነው እንዴ? ሲሉ ስንሰማ በትእግስት ከማስተማር ባለፈ ኃይለቃል አልወጣንም” አሉ የነገው ሰው ኅብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ግሩም ዘላለም በፈገግታ ታጅበው። ከሁኔታቸው እያንዳንዱ ገጠመኝ መማሪያ እንጂ ማረሪያ አለመሆኑን ሳነብ

“በጣም እንደሰት ማንንም ሳንነካ፣

በራስ ላይ መቀለድ ጤንነት ነው ለካ።”

ከሚለው የደረጀና ሃብቴ ቀልድ ባሻገር የኒክ ቩዩቺች ጨዋታ ከሃሳቤ ባሕር ተከሰተና በምናቤ ብዕር ቃኘሁት።

በኬትራ አሚሊያ ሲንድረም ሰበብ ጤናው የተሰናከለው አውስትራሊያዊው ኒክ ቩዩቺች “ደራሲነቴን፣ ወንጌል ሰባኪነቴንና ባነቃቂ ንግግር አድራጊነቴ ዓለም ስሜን ያወቀው በብዙ ጥረት እንጂ ሜዳው ደልዳላ ሆኖልኝ አይደለም” ይላል። ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመተ ምህረት እጅና እግር አልባ ሆኖ የተወለደው ኒክ አሜኬላ የወረሰውን የሰውን ልብ በጉዳቱ ሳይሆን አስተሳሰባዊ ብቃቱ፣ ከአካላዊ ማንነቱ ይልቅ ውስጣዊ ምንነቱን እንዲገነዘብ ያስቻለበት የጥበብ መንገድ የሥነልቦና ብርታቱን ያሳያልና ከጠንካራ ሞራሉ ተስፋውን አለምልሞ በእድሜ ዘመኑ ትግል ካካበተው ልምድ ቀስሞ ራሱን የቀየረ እማኝ ሳስስ ፍሪዳ ካህሎ በዓይነ ሕሊናዬ ተሳለች። ዓለም በራሷ ምስል (ሰልፍ ፖርትሬት) አድናቆት የቸራት የሜክሲኮ ተወላጇ ፍሪዳ ካህሎ በፖሊዎ በሽታ ሰበብ ቀኝ እግሯ አጥሮና ቀጥኖ እንዲሁም በደረሰባት የመኪና አደጋ ብሎም ባስገጠመችው አርቴፊሻል እግር የተነሳ “የእንጨት እግር” የሚል ሹፈት የቀላቀለ ተቀጽላ ስም ቢያሰጣትም እሷ ግን ጉድለቷን በሙላት እጦቷን በበረከት ሞልታ ያለዘበችው የተስፋ መንገድ ቀንቶ በወለደቻቸው የጥበብ ሥራዎች ምክንያት የናቋት ማህበረሰብ አፉን እንዲይዝ አድርጋለች። ሄለን ኪለርን በቀለም ያነጸቻት አን ሳሊቫን “ሌላው ማህበረሰብ ስለአካል ጉዳተኞች ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ አስቀድሞ አካል ጉዳተኛው በራሱ ላይ ከፍ ያለ በራስ መተማመን እንዲኖረው ማስቻል ትልቁ ተግባር ነው” ትላለች።

ይህንን ሃሳብም የማህበሩ የቀድሞ ሊቀመንበርና የታሪክ መምህሩ ገበያው ጥጋቤ ይጋራሉ። ማህበሩ ገና በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሲወጠንና ተመስርቶ መሬት ሲወርድም በኃላፊነት የመሩት መምህር ገበያው፤ የነበረውን ሂደት ሲያወሩት ያንገሸግሻቸዋል። ምንም እንኳን ስም የገዙበት ተቋም ቢሆንም። ለመሆኑ ለምሬት የሚያደርስ እንደምን ያለ ፈተና ነበር የገጠማችሁ? አልኳቸው ነገሩን ከስር መሠረቱ እንዲያስጨብጡኝ በመከጀል።

ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (ኢንተርናሽናል ሊብሬሽን ኦርጋናይዜሽን) ምቹ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ፈጠራ እድል የሚል ፕሮጀክት ቀርጾ ሲንቀሳቀስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ፍሊፒንስና ሌሎችም ሀገራት ገዢ ሃሳብ በማቅረብ እያንዳንዳቸው ሁለት መቶ ሺህ ዶላር በዓለም ባንክ በኩል ሲበረከትላቸው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከመንግሥት በኮንትራት ያገኛቸውን ሰላሳ መጸዳጃ ቤቶችን ጠግኖ ለሥራ ዝግጁ በማድረግ ከአምስት የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ማለትም ከዓይነስውራን፣ ከመስማት የተሳናቸው፣ ከእጅና እግር ጉዳተኞች፣ ከሥጋ ደዌና ከአእምሮ እድገት ውስንነት ማህበራት የተውጣጡ ሁለት መቶ ሃምሳ አባላትን አሳትፎ ሥራ በማጣት ለምጽዋት ተዘርግተው የነበሩ እጆችን ለሥራ ሲያበቃቸው አካል ጉዳተኛው ግን “መንግሥት ቢንቀን ነው እንጂ የተናቀ ሥራ የሰጠን የተሻለ የሥራ ዘርፍ አጥቶልን ነው?” በማለት ሥራውን ለመጀመር አቅማሙ፤ ገበያውና ባልደረቦቻቸውም ከታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ የተሻለ ልምድ በመቀመር ማህበሩን ተከሉና ለለውጥ ተነሳሽነት ያላቸውን አባላት ይዘው በሃያ አምስት ሳንቲም ክፍያ የጽዳት አገልግሎት ሥራውን ጀመሩ። በጊዜው የነበሩት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል ያደርጉላቸው እንደነበር ከማህበሩ ሰነዶች መመልከት ችያለሁ።

አባላትን የመምረጡ ሂደት ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ቢሆንም በወቅቱ የነበረው አመላመል የማይናቅ ቅራኔ ፈጥሮ እንደነበር መምህር ገበያው አልሸሸጉም። ይሁን እንጂ ሥራው ላይ የተሳሳተ አመለካከት ይዘው የነበሩ አባላት መልካም የሚባል ግንዛቤ በመጨበጥ ከራሳቸው ኑሮ አልፈው ለማህበሩ ህልውና ዘብ የቆሙ አባላት መፈጠራቸውንም አጫወቱኝ።

በ1997 ዓ.ም የተመሠረተው የነገው ሰው ኅብረት ሥራ ማህበር በሃያ ዓመት ጉዞው የአባላቱን ወርሃዊ ክፍያ ከማሻሻል በላይ ከደመዛቸው ላይ ቀንሰው በመቆጠብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል። ጃፓን ኤምባሲም ሰማንያ ሁለት ሺህ ዶላር ድጋፍ በማድረግ አንድ መቶ ስምንት የልብስ ማጠቢያ ገንዳዎችን ሠርቶ ተጨማሪ ገቢ ፈጥሮላቸዋል።

መንግሥትም ቢሆን በልማት የፈረሱ መጸዳጃ ቤቶችን ምትክ በመስጠት ከጎናቸው መቆሙን የማህበሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሀብታሙ ገብረመድህን ገልጸውልኛል። እኔም ተዟዙሬ መታዘብ እንደቻልኩት መንግሥት አካል ጉዳተኞችን አምራች ዜጋ ለማድረግ የሄደበትን ርቀት አይቼ ይበል ብያለሁ።

በማህበሩ ታቅፈው እየሠሩ ያሉ አባላትም ልጅ አስተምረው ለወግ ማዕረግ ማብቃታቸውን፣ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮ ተሻግረው ጥሪት ማበጀታቸውንና ለሀገር ግንባታ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ በሙሉ ልብ ሃሳባቸውን አካፈሉኝ። በጉብኝቴ ወቅት ትኬት የሚቆርጡ፣ ገንዘብ የሚቀበሉና የሚያጸዱ አካል ጉዳተኞችን ብመለከትም ከአእምሮ እድገት ውስንነት ማህበር ውስጥ አንድም ሰው ባለማየቴ ለዋና ሊቀመንበሩ አቶ ግሩም ጥያቄውን ሳነሳላቸው እነሱን ተክተው ከቤተሰባቸው አንድ አባል እንደሚያካትቱ ገለጹልኝ።

በመጨረሻም የማህበሩን የወደፊት ራእይ በጠየኳቸው ጊዜ ገቢውን በማሳደግ ለተጨማሪ አካል ጉዳተኞች የሥራ እድል መፍጠር መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You