የራሷ አሮባት …..

አዛውንቱ የሚያስተዳድሯት ጎረቤት ሀገር በ1993 በተካሄደ ድራማዊ ሕዝበ ውሳኔ በዓለም መንግሥታት ዘንድ ዕውቅና ያገኘችበትን ዕለት 34ኛ ዓመት ባሳለፍነው ሳምንት አክብራለች። 34ኛ የስልጣን ዘመን ልደታቸውን ያከበሩት የጎረቤታችን አዛውንት ሥልጣናቸውን ያገኙበት ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር አሳድጋ ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የፈቀደችላቸውን የሥልጣናቸው ምንጭ የሆነች እናት ለማሳጣት ብዙ ርቀት ተጉዘዋል።

አዛውንቱ ተሳቅቆ ሀገር ለቅቆ ከሸሸው ሕዝብ በአስር ሺዎች እጥፍ የሚያንሱ ሰዎች በተሰበሰቡበት ስታዲየም በየቤቱ ለሚያዳምጣቸው ምስኪን ባስተላለፉት የውጭ ጉዳይ መሥሪያቤት ሪፖርት የመሰለ መልዕክት ዓለምን አስገርመዋል። አዛውንቱ በንግግራቸው መካከል “ነጻነታችንን ማጠናከር አስፈላጊ ነው” ይበሉ እንጂ ሙሉ የንግግራቸው ማጠንጠኛ የተሸከመቻቸው ሀገር ሳይሆን ሌሎች ሀገራት ነበሩ። ለወትሮም በበርካቶች ዘንድ ከሀገር ውስጥ ጉዳይ ይልቅ በሌሎች ሀገራት ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ በሚል ወቀሳ የሚቀርብባቸው አዛውንቱ በሰሞኑ መግለጫቸው ጭራሽኑ ለይቶላቸው ታይተዋል።

እስኪ አዛውንቱ ያነሷቸውን ጉዳዮች ለመዳሰስ እንሞክር። አዛውንቱ እንዲህ ስለሀገራችን ብለዋል … በኢትዮጵያ ባለፉት ሰማንያ ዓመታት በተሳሳተ ፖሊሲዎች እና በዋሺንግተን አጋፋሪዎቻቸው ምክንያት የተከሰተው ይታወቃል። ላለፉት ሁለት ትውልዶች በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታው ዕድል ጨንግፏል። ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ኢትዮጵያ ወደ ብሔር ፖለቲካ ጽንፍ አምርታለች። በኢትዮጵያ ታይተው የነበሩ ለውጦችን ተስፋ ሰጪ ሕዝባዊ ምኞቶች የውጭ ኃይሎችን ያስደነገጡ ነበሩ። የውጭ ኃይሎች በወኪላቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ያወጁት ጦርነት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ ያሳያል።

አክለውም፤ በብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የተከሰቱትን በርካታ እና ተደጋጋሚ አደጋዎች ተከትሎ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት የታቀደው ‘ለውጥ’ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ እና በሌሎች አጎራባች ሀገሮችም የፈጠረው የደስታ ስሜት እና ብሩህ ተስፋ በእውነቱ ትውስታችን ነው፤ ነገር ግን ተስፋ ሰጪ በሆኑት ዕድሎች የተናደዱ የውጭ ኃይሎች ሥራ አልፈቱም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያወጇቸው ጦርነቶች በአዲሱ ተተኪያቸው ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የራሷ እያረረባት የሰው ታመሳስላለች ማለት እዚህ ነው። እርሳቸው ሌሎች ሀገራትን በስም እየጠሩ ይዘላብዱ እንጂ የእርሳቸው ሀገር ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ፈላጭ ቆራጭነት የነገሰባት፤ አያሌ የመብት ጥሰት እና ጭቆና ያላባት፤ ነጻነት ሕልም የሆነባት በድቅድቅ ጨለማ የተመላች እና ዜጎቿ ነጉደው ያለቁባት ሆደ ባሻ መሆኗን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በየጊዜው በሚያወጧቸው ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል። በጥቂት እናውቅላቸሁኋለን ባይ ራስ ወዳዶች ሸፍጥ ከእናት ምድሯ ከተለየች በኋላ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ታይቶባት አያውቅም። አማራጭ ሀሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውባት አያውቁም። ምርጫ አካሂዳ መሪዋን መምረጥ ብርቋ ነው። ሕገ መንግሥት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚባሉ ጉዳዮች ፈጽሞ አይታሰቡም። እንግዲህ እንዲህ ያለ ጓዳ ያላቸው አዛውንት ናቸው የሀገራትን ስም በሰልፍ እየጠሩ የምድር የቋጡን የሚቀባጥሩት።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ከገለጸች በኋላ አዛውንቱ በስጋት ተውጠዋል። የውጭ ኃይሎች ባሏቸው እገዛ የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር መሳሪያ ግዢ እና የወታደራዊ ዝግጅት ላይ እንደሆነ ገልጸው የድረሱልኝ ጩኸታቸውን ለቀውታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ዓላማ የውሃ ጉዳይ፣ ዓባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ ነው ሲሉም ጭንቀታቸውን ተንፍሰዋል።

ስጋታቸው በዓባይ ግድብ ከኢትዮጵያ ጋር በጎሪጥ ከምትተያየው ግብጽ ጋር የጅብ ችኩል የሚያሰኝ ስምምነትና ትብብር እስከመፍጠር አድርሷቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችንም በሚችሉት መንገድ ሁሉ እየደገፉ ይገኛሉ። ይህንን እውነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራሳቸውን ምርጫ ወስደዋል። ተቃውሟቸውን ለማጠናከር እየተዘጋጁ ነው። የሀገሬ ሕዝብ እና መንግሥት ለታሰበው ለውጥ ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረጉ እና ድንገት በተፈጠረ ለውጥ ምክንያት አይቆጩም ባሉበት በሰሞኑ ንግግራቸው አረጋግጠዋል።

አዛውንቱ እየመጣብኝ ነው ብለው ከሚያስቡን መዓት ለማምለጥ ቢችሉና የፈረደባትን ሀገራቸውን ይዘው ለሆነ ጊዜ ያህል ወደማይታወቅ ዓለም ተሰውረው ወጀቡን ቢያሳልፉ ምኞታቸው ነበር።

የአዛውንቱ ሁኔታ በንጉሡ ዘመን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ አስቂኝ ዜናን አስታወሰኝ። ዜናውን ይዞ የወጣው የካቲት 26 ቀን 1963 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው። የዜናው አርስት “ፍርድ ቤት የቀረቡት ስድስት ተከሳሾች በአስማት አመለጡ” ይላል። ታሪኩ እንዲህ ነው። ግንቦት 21 ቀን 1962 ዓ.ም በአዳል፣ ኢሳና ጋራ ጉራቻ አውራጃ ግዛት በኤረር ወረዳ በዋይበር ቀበሌ የቡና አትክልትና ልዩ ልዩ አይነት ዛፎች በማቃጠላቸው ክስ ቀርቦባቸው ጉዳዩ በኤረር ወረዳ ፖሊስ ከተጣራ በኋላ ድሬዳዋ አውራጃ ፍርድ ቤት ተላለፈ።

በዚሁ መሰረት የካቲት 19 ቀን 1963 ዓ.ም ስድስቱ ተጠርጣሪዎች በተከሳሾች ሳጥን ውስጥ እንደቆሙ ከመካከላቸው በእድሜ ጠና ያለው በፍጥነት አስማት መድገም ይጀምራል። ወድያው የፍርድ ቤቱ ፀሓፊ በአስተርጓሚ ዝም እንዲል አስጠነቀቁት። ተከሳሹ ማስጠንቀቅያውንም ከምንም ሳይቆጥር የእጁ ጣቶችን እያነቃነቀ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ድግምቱን አጣደፈው። በዚሁ መካከል ስድስቱም ተከሳሾች ማንም ሳያያቸውና ሳያሳናብታቸው ከቆሙበት ሳጥን ውስጥ ወጥተው ከፍርድ ቤቱ ለማምለጥ ችለዋል።

ከሁለት ሰዓት በኋላ ተከሳሾቹ ወደ ወህኒ ቤት የሚገቡበት ወረቀት ተቆርጦ የፍርድ ቤቱ ፀሃፊ ለተረኛው ፖሊስ ሲሰጥ ፖሊሱ “እስረኞቹ የት አሉ” በማለት እንዲታሰሩ ትእዛዝ የሰፈረበትን ወረቀት ሳይቀበል ቀርቷል። በመጨረሻም ስድስቱም ተከሳሾች ታድነው እንዲያዙ ለኤረር ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ትእዛዝ መተላለፉን አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጿል።

ቢቻላቸው ስድስት ሰዎች ሳይሆን ስድስት ሚሊየኖችን አሰልፈው የምድራችንን የድግምት አይነቶች ሁሉ አስደግመው እየመጣባቸው ካለው ድጋሚ እድል ከማይሰጥ መዓት ለማምለጥ የማይቆፍሩት ጉድጓድ አይኖርም ነበር። ላለፉት 34 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩትን አዛውንት ስጋት ፍንትው አድርጎ ባሳየ የንግግራቸው ክፍል “በሀገሬ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ እየተፈፀመ ያለው ግልጽ እና ስውር የማፍረስ ሴራ የታወቀ ነው ብለዋል።

አትዮጵያን መውቀስ ያላበቁት አዛውንቱ ከ1953- እስከ 1959 የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከነበሩት ከጆን ፎስተር ዳላስ እስከ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያሉትን የአሜሪካ ፖለቲከኞችን እና የሶቭየት ሕብረትን አምርረው ተችተዋል። የሱዳን የውስጥ ጉዳይን ማቡካቱንም ለምን ይቅርብኝ ብለው ሄደውበታል።

በሰሞኑ የአዛውንቱ ንግግር ዙሪያ የጀርመን ድምጽ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት አዛውንቱ ደጋግመዉ የዉጪ ኃይላት የሚሏቸው ዋሽንግተኖችን ብቻ አይደለም። አካባቢው ተዋናኞች የሚባሉትን በተለይ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችን ነው። ለዚህም ምክንያት አላቸው። ኢሳያስ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር በሁለት ምክንያት ተቀያይመዋል። አንደኛው የአቡዳቢ መሪዎች አሠብ ላይ መሥርተውት የነበረውን የጦር ሠፈር (ቤዝ) ማፍረሳቸው ነው። ሁለተኛው ከሱዳን ተፋላሚ ኃይላት መካከል ኢሳያስ የመከላከያውን ጦር ኃይል መደገፋቸው ነው።

የአዛውንቱ ነገር ታገል ሰይፉ የ16 ዓመት ታዳጊ እያለ ባሳተመው “ፍቅር” የተሰኘ መጽሐፍ ስለ ጭላዳ ዝንጀሮ የከተበውን የሚያስታውስ ነው። ገጣሚው እንዲህ ይቀኛል፡-

ጭላዳ ዝንጀሮ እዩት ቂልነቱን

የዝሆኑን ማማር አጥላላ ውበቱን

አጎንብሶ አላየም መላጣ ደረቱን

ታዲያ ይህን ሁሉ ክስ የሚያዥጎደጉዱት አዛውንት አርፈው አይቀመጡም። የሀገራቸውን ዜጋ አንድ በአንድ ለወታደራዊ ግዳጅ አስመርተው ሲያበቁ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቤት ማለትን ተያይዘዋል። በአዛውንቱ የስልጣን ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ከወራት በፊት የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች እና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊን ጠርተው የድረሱልኝ ጩኸታቸውን አሰምተዋል። ጋዜጣዊ መግለጫ “ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንድታከብር ጫና እንዲያደርጉ ሲሉ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላትን እጠይቃለሁ” ብለው ጉድ አስብለውናል።

አዛውንቱ በቀጣናዊ ግጭቶች ውስጥ ዋናኛ ተዋናይ ናቸው በሚል የሚቀርብባቸውን ክስ አሳምረው ይካዱ እንጂ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት ማሳየቷን ተከትሎ ይህንኑ ሚናቸውን የቃጣናውን ሀገራት ቤታቸው ድረስ በመጋበዝ በአደባባይ ሳያሳዩ ከርመዋል። ማንም ሳይጠይቃቸው የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ “የተዛባ እና ጊዜው ያለፈበት የባሕር ዳርቻ ፍላጎት”በሚል አጣጥለዋል። አያይዘውም የኢትዮጵያ የባሕር በርና የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ምኞቷም ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉም ተደምጠዋል። ፍርሐቱ የሚያስለፈልፋቸው አዛውንቱ “ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ወይም በወታደራዊ ኃይል የባሕር ላይ መዳረሻ እና የባሕር ኃይል ሰፈር ለማግኘት ባላት የተሳሳተ እና ጊዜው ያለፈበት ምኞት ››ግራ መጋባታቸውንም ሲገልጹ ተሰምተው ነበር።

አዛውንቱ በትዕቢት እና ፍርሐት የተወጠሩ ይመስላል። አንድ ወዳጄ ትዕቢት እና ፍርሃት ዋነኛ የሰው ልጅ ጠላቶች ናቸው። ከትዕቢት እና ከፍርሃት ነፃ ከሆንክ ጤናማ ነህ ማለት ነው ይላል።

ይህ ወዳጄ እንደሚናገረው ትዕቢት ያልሆንከውን ሆነህ ሌሎችን አሳንሰህ የማየት፣ የማትችለውን እችላለሁ ብለህ የሚችሉትን የማንኳሰስ አስተሳሰብ እና ድርጊት ነው። ታላቁ መፅሐፍም “ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች” ይላል። በቀጥተኛ አባባል አንድ ሰው ትዕቢት ውስጥ ከተዘፈቀ ለመውደቅ ጥቂት ርምጃዎች ብቻ ይቀሩታል ማለት ነው። ፍርሃት ደግሞ አቅምህን በአግባቡ ተረድተህ ማከናወን የምትችለው ነገር ከመሥራት ይልቅ ውድቀትን ከሩቅ በማየት መራድና መሽመድመድ ነው። ፍርሃት በሕይወት ውጣውረድ ውስጥ የምታገኘው ዕድል ላይ አነጣጥረህ ከመሥራት ይልቅ ፈተናዎችን በመመልከት ወደኋላ እንድትመለስ ያደርግሃል። ገና ሳትጀምር ልወድቅ እችላለሁ በሚል ስጋት እንድትሸበብ ያደርጋል። ፍርሀት ባለበት ድል የለም።

በታገል ሰይፉ ሸጋ ግጥም እንሰናበት

ጭላዳ ዝንጀሮ እዩት ቂልነቱን

የዝሆኑን ማማር አጥላላ ውበቱን

አጎንብሶ አላየም መላጣ ደረቱን

መግነጢስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You