የታሪካዊዎቹ ተጫዋቾች አሠልጣኝነት ሽግግር

በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቆ ለመውጣት ለተቸገረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ የመፍትሔ ሃሳቦች ሲሰጡበት ማየትና መስማት የተለመደ ነው። በተለያዩ አካላት እግር ኳሱን ለመለዋወጥና ወደ እድገት ጎዳና ለማምጣት ከሚነሱ ሃሳቦች አንዱ የስልጠና ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሥልጠና ሂደት ከተለመደው አካሄድ አውጥቶ ከሳይንስ ጋር ማስታረቅ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ተነግሯል። ለእዚህ ደግሞ ትልቁን ሚና የመጫወት ኃላፊነት ያለባቸው አሠልጣኞች ናቸው። እርግጥ ነው የካበተ የተጫዋችነት ልምዳቸውን ከሳይንስ ጋር አዋህደው ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾችን ከስር ጀምሮ ኮትኩቶ ለማውጣት የሚጥሩ ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ጥቂት ቢሆኑም፤ የሉም ማለት አይቻልም። ተጫውተው ያለፉና የአሠልጣኝነት ዘመናቸውንም በትምህርትና በአስፈላጊው የካፍና የፊፋ ሥልጠናዎች አልፈው በሙያው የተሰማሩት ቁጥር ግን እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ አያከራክርም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በእዚህ ረገድ አንድ ተስፋ ሰጪ ነገር በእግር ኳሱ መንደር መታየት ጀምሯል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከካፍ ጋር በመተባበር የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፉ ተጫዋቾችን ጨምሮ 25 የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወደ ሥልጠናው ዓለም የሚቀላቀሉበት የፋስት ትራክ “ቢ ዲፕሎማ” መርሃ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ በአራት ሞጁሎች ተከፋፍሎ ሲካሄድ ቆይቶ ሰሞኑን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲበቃ አብዛኛው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ የነበሩ ታሪካዊ ተጫዋቾች በእዚህ ሥልጠና ወደ አሠልጣኝነት ሙያው ተሸጋግረዋል። በአጠቃላይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የራሱን አሻራ ያስቀመጠው ትውልድ በእዚህ ሥልጠና መታየቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አንድ ተስፋ የፈነጠቀ ነው።

ላለፉት ስድስት ወራት ሲሰጥ የቆየው የአሠልጣኝነት ሥልጠና ለሠልጣኞቹ የጽሑፍ ፈተና ከተሰጠ በኋላ ተቋጭቷል። በመዝጊያው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ ሥልጠናውን በዋነኝነት የመሩት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ በካፍ ኢንስትራክተር መሠረት ማኒ፣ የዲሲ ዩናይትድ የምልመላ ኃላፊ ሚስተር ክላረን፣ የአደይ ሰረበለም ፓልሲ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ማስተዋል ተገኝተዋል።

የካፍ ቴክኒክ ልማት ዳይሬክተር ራውል ቺፔንዳ በቪድዮ የገፅ ለገፅ ግንኙነት አማካኝነት ለሠልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክት “እንኳን ለእዚህ ቀን አደረሳችሁ። በእዚህ ሥልጠና ሂደት ማለፍ እና መውደቅ ይኖራል። ይሄ ማለት ግን የመጨረሻ ነው ማለት አይደለም። በቀጣይ ራሳችሁን እያበቃችሁ መምጣት አለባችሁ። ሀገራችሁን የምታኮሩ ባለሙያዎች እንደምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።” ብለዋል።

የዲሲ ዩናይትድ የተጫዋቾች መልማይ ሚስተር ክላረን ለሠልጣኞች ለምን አሠልጣኝ ለመሆን እንደፈለጉና ምን አይነት አሠልጣኝ መሆን እንደሚፈልጉ ጥያቄ በማቅረብ ንግግራቸውን በመጀመር ስለ ተጫዋቾች ምልመላ ገለጻ አድርገዋል።

የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እንዲሁም የካፍ ኢንስትራክተር መሰረት ማኒ አጠቃላይ የስልጠናው ሂደትን በማስመልከት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤

ሠልጣኞችም በተወካዮቻቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን፣ ሥልጠናውን የሰጡት ኢንስትራክተሮችን፣ እንዲሁም ለስልጠናው አስተባባሪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የትምህርትና ሥልጠና ኃላፊ አቶ ደረሰ እሸቱ ምስጋና አቅርበው በሥልጠናውም ሂደት እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለእዚህ ላደረሷቸው ባለሙያዎች ስጦታ አበርክተዋል። ከሌሎች ሥልጠናዎች ስለሚለይበት መንገድ ያስረዱት ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም፤ መብራቱ የካፍን የሲ እና ቢ ፍቃድ(ላይሰንስ) በአብሮነት መያዙ እንዲሁም ከሞሮኮ ቀጥሎ በኢትዮጵያ መሰጠቱ መሆኑን አስረድተዋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለሠልጣኞቹ ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸውን የሚገልፅ የደረት ፒን ካበረከቱ በኋላ የማጠቃለያ ንግግርና የሥራ መመሪያ ሠጥተዋል። “በታማኝነት እና በሀቀኝነት ውጤታማ ልጆችን እያፈላለጉ የሚሠሩ አሠልጣኞች እንድትሆኑ እንፈልጋለን” ያሉት አቶ ባህሩ፤ ሠልጣኞቹ የተበላሸው የእግር ኳስ ሥርዓት ውስጥ እንዳይገቡና አዲስ ነገር ለመፍጠር ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ደጉ ደበበ እና አዳነ ግርማን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ የነበሩትን አብዛኞቹን ተጫዋቾች ባካተተው ሥልጠና አሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ፣ የወቅቱ የአርባ ምንጭ አሠልጣኝ በረከት ደሙ እንዲሁም ለድሬዳዋ ከተማ እየተጫወተ የሚገኘው መስዑድ መሀመድ፣ አካዳሚ ከፍቶ በመሥራት ላይ የሚገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሁለት እንስት ሠልጣኞ እና ሌሎችም ተካተውበታል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴት ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ረውዳ አሊ እና የቀድሞዋ የሉሲዎቹ አምበል ቱቱ በላይ ብቸኞቹ እንስት ሠልጣኞች ናቸው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You