ተከታታይ ክፍል
1. ስብዕና ነክ የውጥረት መንስዔዎች
ሰዎች የተለያየ አይነት ስብዕና እንዳላቸው ግልጽ ነው:: እነዚህም ስብዕናዎች እንደልዩነታቸው ሁሉ ውጥረትን የማምጣት እና የመቋቋም ባህሪያቸው ይለያያል፡፡
ለምሳሌ፡- ዓይነት A እና ዓይነት C የተባሉት የስብዕና አይነቶች ውጥረትን በማምጣት የሚታወቁ ሲሆን ሌሎች የስብዕና አይነቶች ደግሞ ውጥረትን በመቋቋም ይታወቃሉ::
ዓይነት A ስብዕና
እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች ከመጠን በላይ የመፎካከር፣ አስቸጋሪ፣ እብሪተኛ፣ ኃይለኛ፣ ትዕግስት ያጣ እንዲሁም ከመጠላላትና ከቅራኔ ጋር የተያያዘ ባህሪ ሲኖራቸው፣ ይህም ለተለያዩ አካላዊ ህመሞች እና ከልብ ጋር ተያያዝነት ያላቸው በሽታዎች ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
ዓይነት C ስብዕና
እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች ስሜትን ለሌላ ሰው ማካፈል ያለመቻል እንዲሁም የመረበሽና የፍርሀትን ስሜት መግለጽ ባለመቻል መናደድ፣ መሸበር እና ከልክ ያለፈ ቁጥብ የመሆን ባህሪ ሲኖራቸው ይህ ስብዕናቸውም ለተለያዩ አካላዊና አእምሮአዊ ህመሞች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡
2. አእምሮአዊ የውጥረት መንስኤዎች
የጋራ የሆኑ እና ሁሉም ሰው ላይ ውጥረት የሚፈጥሩ መንስኤዎች እንደመኖራቸው መጠን ሁሉም ሰው ደግሞ አንድን የውጥረት መንስኤ ሌላው ሰው እንደሚወስደው ከባድ ወይም ቀላል አድርጎ ላይወስደው ይችላል፡፡ ይህንን መሰረታዊ ልዩነት የሚፈጥረው ውጥረት በራሱ በሰዎች ግንዛቤና መረዳት እንዲሁም ለውጥረት መንስዔ በምንሰጠው
ትርጉም ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ለአንድ ተማሪ 30/100 (በፈተና አነስተኛ) ውጤት ማግኘት ውጥረት ውስጥ የሚከት ቢሆን ለሌላው ተማሪ ደግሞ ችሎታውን ወይም አቅሙን የሚፈትንበት ሊሆን ይችላል፡፡
የመረዳትና የመገንዘብ ግምገማ
ይህ ፅንሰ ሀሳብ የግለሰቡን ድርጊት አሊያም ሁኔታውን በስኬታማነት የሚቋቋምበት እምቅ ችሎታ እንዳለው እና እንደሌለው ለራሱ እውቅና የሚሰጥበት ነው፡፡ የመረዳትና መገንዘብ ግምገማ ሁለት ደረጃዎች ሲኖሩት እነሱም የመጀመሪያ (primary) እና ሁለተኛ (secondary) በመባል ይታወቃሉ፡፡
የመጀመሪያ ግምገማ
ይህ ግምገማ በቀጥታ የሚያተኩረው ስትረስ አምጭ የሆነው ጉዳይ ሁኔታ ግለሰቡን የሚመለከት ጉዳይ መሆን አለመሆኑ፤ ሁኔታው ግለሰቡን የሚመለከት ከሆነም አስቸጋሪ፣ ጎጂ ወይም መጥፎ ውጤት የሚያመጣ መሆን አለመሆኑ፤ እንዲሁም ሊፈጥር የሚችለው የስትረስ መጠን ከፍ ያለ መሆን አለመሆኑን የሚገመግም ነው፡፡ በአጠቃላይ ስትረስ አምጭ የሆነውን ጉዳይ መገምገምን ያካትታል፡፡
የሁለተኛ ግምገማ
የሁለተኛ ደረጃ ግምገማ ማለት ስትረስ አምጪው ጉዳይ ከፍተኛ ስትረስ እንዲሚያመጣ ግምገማ ከተደረገ በኋላ የሚከተል ሲሆን ይህ ስትረስ አምጪ ጉዳይን ማስወገድ ወይም መቆጣጠር መቻል አለመቻሉን፣ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ምን ያህል ጉዳት ወይም ኪሳራ ሊያደርስ እንደሚችል፣ ውጤቱስ ምን ሊሆን እንደሚችል ይገመግማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቡ ይህንን ጉዳይ ለመቋቋም ምን ማድረግ እንደሚችል እና ለመቋቋምም የሚስፈልጉትን ግብአቶች የሚመዝንበት ነው፡፡
3. አካባቢያዊ የውጥረት መንስኤዎች
ትልቅም ሆነ ትንንሽ ክስተቶች በህይወታችን ውስጥ ውጥረትን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ አስደንጋጭና
አሰቃቂ ክስተቶች ለምሳሌ: – እንደ ጦርነት፣ የመኪና አደጋ፣ የእሳት አደጋ፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ርሀብ፣ በጣም የምንወደው ሰው በሞት መለየት፣ ከፍተኛ የሥራ ጫና፣ ደስተኛ ባልሆነ ግንኙነት የሚፈጠር መጨናነቅ፣ መሸበር፣ በድህነት ጫና ውስጥ መኖር ስትረስ ሊያመጣ ይችላል:: በጠቅላላው ሁለት ዋና ዋና አካባቢያዊ የውጥረት ምንጮች አሉ እነሱም፡-
i. ከመጠን ያለፈ ጫና፣ ግጭት እና የአላማ አለመሳካት
ii. የህይወት ኩነቶች እና የዕለት ተዕለት ውጣ ውረዶች
1. ከመጠን ያለፈ ጫና፣
አሁን አሁን የቀን ተቀን የኑሮ ሁኔታ፣ ማህበራዊ እና የሥራ ህይወት በግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ በስራ፣ በቤተሰብና በማህበራዊ ኑሮ ወይም በሌሎች የኑሮ ኩነቶች በሂደት በግለሰቦች ላይ ከፍ ያለ ጫና በመፍጠር በአእምሮ፣ በአካል እና በስሜት መዛልን/መድከም ይፈጥራል፡፡ በዚህ ተፅዕኖ ውስጥ የወደቀ ሰው የድካም፣ ተስፋ የመቁረጥ፣ የመራራነትና የባዶነት ስሜት ያጠቃዋል፡፡ የተነሳሽነት መቀነስ፣ ቀድሞ ያጓጓው የነበረውን ነገር አሁን መስራት አለመፈለግና ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ፍላጎት ማጣት በጣም የተለመዱ ስሜቶች ናቸው፡፡ በአካል እና ስሜት ላይ የመዳከም ብሎም አቅም፣ ኃይል እና ጉልበት ማጣትን ያስከትላል፡፡
ውስጣዊ ግጭት
ግጭት የሚከሰተው አንድ ግለሰብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ነገር ግን አብረው መሄድ በማይችሉ ምርጫዎች ወይም ጉዳዮች መካከል መወሰን መወሰን በማይችልበት ወቅት የሚኖር መወላወል ነው፡፡ በአጠቃላይ ሦስት ዓይነት ግጭት ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡
ሀ. አዎንታዊ – አዎንታዊ ግጭት
ለ. አሉታዊ – አሉታዊ ግጭት
ሐ. አዎንታዊ – አሉታዊ ግጭት
ሀ. አዎንታዊ – አዎንታዊ ግጭት
እንዲህ ዓይነቱ ግጭት የሚከሰተው ግለሰቡ ከሁለት የሚስቡ ወይም መልካም ውጫዊ ፍላጎቶች የግድ አንዱን መምረጥ በሚኖርበት ወቅት ነው፡፡
ለምሳሌ፡- በዘንድሮው የእረፍት ጊዜህ ሀዋሳ ወይም ባህር ዳር ነው መሄድ የምትፈልገው፡፡ እንዲህ አይነቱ ግጭት ውጥረት የማስከተሉ መጠን ዝቅተኛ ቢሆንም ከሁለቱ መልካም ውጤቶች አንዱን መምረጥ አሉታዊ ውጤት ያመጣል፡፡
ለ. አሉታዊ – አሉታዊ ግጭት እንዲህ ዓይነቱ ግጭት የሚከሰተው ግለሰቡ ከሁለት የማይስቡ ወይም መልካም ያልሆኑ ውጫዊ ጉዳዮች የግድ አንዱን መምረጥ በሚኖርበት ወቅት ነው፡፡
ለምሣሌ፡- የታመመ እና የሚያሰቃይ ጥርስን ሀኪም ጋር ሄዶ ማስነቀል፤ አሊያም ከሚያሰቃይ የጥርስ ህመም ጋር አብሮ መቆየት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግጭት መጀመሪያው ከተጠቀሰው ግጭት ይልቅ ከፍ ያለ ውጥረት አምጭ ሲሆን ውሳኔ ላይ ለመድረስም የምንዘገይበት እና የመጨረሻዋን ቅጽበትም የምንጠብቅበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
ሐ. አዎንታዊ – አሉታዊ ግጭት
እንዲህ ዓይነቱ ግጭት የሚከሰተው አንድ ግለሰብ አሉታዊም አዎንታዊም ገፅታ ያለው ግብ በሚገጥመው ጊዜ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- አንድ ወጣት አብራ ካለችው ወጣት ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ይመኛል፤ በአንድ በኩል ወጣቱ ፍቅር የሚያመጣውን የስሜት መረጋጋት፣ የአእምሮ እርካታ፣ እና አብሮ መረዳዳት ይስባል በሌላ በኩል ደግሞ የፍቅር ግንኙነቱ ከተጀመረ በኋላ በሚከሰት ቅርርብ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ-ስጋ ግንኙነት ቢከሰት ላልተፈለገ እርግዝና ተጋላጭ መሆንና በወጣትነት እድሜ የኢኮኖሚ ነጻነት ሳይኖር በቤተሰብ ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር የሚከሰተውን ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ቀውስ ያስባል:: ከላይ የተጠቀሱት አዎንታዊ እና አሉታዊ ውጤቶችን በመመልከት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያዳግተዋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ግጭት በአሁኑ ዘመን ብዙ ሰዎች በቀን ተቀን ህይወታቸው የሚያስተናግዱት ጉዳይ ሲሆን በጣም ከፍተኛ ውጥረትን የሚያስከትል የግጭት ዓይነት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ወርቅነህ ከበደ እና ሲሳይ የማነ (ዶ/ር)
(ሳይኮሎጂ ት/ቤት – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)