ሀገራችን በታሪኳ ከፈጸመቻቸው እየፈጸመቻቸው ካሉ ግዙፋን ፕሮጀክቶች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ አንድ ላይ ቢደመሩ የ«አረንጓዴ አሻራ»ን ያህል ክብደት አልሰጣቸውም፡፡ የህዳሴውም ሆነ የሌሎች ታላላቅ ግድቦች ህልውና የሚወሰነው ዛሬ በትጋት በምንከውነው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ነውና፡፡ አምና ከአራት ቢሊዮን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ለዚያውም ከሞላ ጎደል ሥነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረጉ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች መትከል ተችሏል:: የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴርም 84 በመቶ መፅደቃቸውን አረጋግጦልናል:: የዘንድሮውን ጨምሮ በተከታታይ አራት ዓመታት አምስት አምስት ቢሊዮን በአጠቃላይ 20 ቢሊዮን ሀገር በቀልና እንደ ማንጎ ያሉ ፍራፍሬዎችን ለመትከል ግብ ተጥሏል፡፡ የዘንድሮው በሀዋሳ ታቦር ተራራ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበትና አሻራቸውን ባኖረ ሥነ ሥርዓት ይፋ ሆኗል፡፡ እንደ ሀገር መሪ ለሕዝብ፣ ለማህበረሰብና ለቤተሰብ በተለይ ለነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ምሳሌና አርዓያ ለመሆን ሕፃኑ ልጃቸው ሳይቀር ልጆቻቸውና ባለቤቶቻቸው በጽሕፈት ቤታቸው ችግኞችን ተክለዋል፡፡ የአንድ መሪ ዋና ባህሪና መስፈርት ስለሆነው ምሳሌነት፣ ምልክትነና አርዓያነት ለማውሳት ከዚህ የተሻለ መልካም አጋጣሚ ስለማላገኝ እግረ መንገዴን የተወሰኑ መገለጫዎችን ላነሳሳ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ምሳሌ፣ አርዓያ የሚሆን መሪና ተቋም ፍለጋ እግራችን እስኪቀጥን አገር ለአገር ዞረን ዞረን ደክሞንና ተስፋ በቆረጥንበት ሰዓት የተገኙ ምሳሌና አርዓያ የሚሆኑ መሪ መሆናቸውን ያለንፍገትና ስስት እውቅና መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ቤተ መንግሥቱና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤትም ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር (ኤርጎኖሚክስ) እና መልሶ በማልማት ለተቋማት ምሳሌና አርዓያ በመሆን ማገልገሉን በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና በሌሎች ተቋማት የመጡ ለውጦችና ማሳያዎች ጥሩ እማኝ ናቸው፡፡ በሀገር ፍቅር፣ በሕግ የበላይነት ፣ በዴሞክራሲያዊነት ፣ በቡድን ሥራ ፤ እንዲሁም በችግኝ ተከላ ፣ በደም ልገሳ ፣ በችግረኛ አረጋውያንን ቤት ጥገና ፣ በጽዳት ፣ ማዕድ በማጋራት ከዚህ ከፍ ሲልም ሰርቶ በማሰራት፣ የተናገሩትን ሆኖ በመገኘት፣ የመልካም ሥነ ምግባር ምሳሌ በመሆን፤ ፍቅርን ፣ ሰላምን ፣ እርቅን ፣ ይቅር መባባልን ፣ ትህትናንና መከባበርን በመኖርና ሆነው በመገኘት እያሳዩን ነው፡፡ ስንፍናን፣ ጥላቻን ፣ አቅላይነትን ፣ ሌብነትን ፣ አድሎአዊነትን ተጸይፈው ፤ ታማኝነትን ፣ ፈሪሀ ፈጣሪነትን ፤ ታሪክን ፣ ታላቆቻቸውንና የሃይማኖት መሪዎችን ያለ ልዩነት ማክበርን ፣ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት በተግባር በማክበር ምሳሌ ሆነው ዓይናችንን ከፍተውልናል፡፡ በዚህም ምሳሌና አርዓያ የሚሆኑ መሪዎችና ተቋማት እየተፈጠሩ ሲሆን ዜጎችም በተለይ ወጣቱ ዳናውንና ፈለጉን የሚከተሉት መሪ አግኝተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ነገ ላይ ተስፋን የሚያሰንቅ ትውልድ እንዲፈጠር እርሾ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ ፣ ችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥን ፣ የዓለም ሙቀት መጨመርንና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንም ሆነ ድህነትን ፣ የምግብ ዋስትና ጉድለትን ፣ የምርታማነት ተግዳሮትን ፣ ድርቅን ፣ ርሀብን ፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት ፣ የውሀ እጥረትን ፣ የኑሮ ውድነትን ፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተትት ፣ ሥራ አጥነት ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን ፣ የጸጥታና የደህንነት ችግርን ፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡ ለዚህ ነው ችግኝ ተከላን የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ማስተር ኪይ ነው ያልሁት፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ደጋ የነበሩ ወይና ደጋ ፣ ወይና ደጋ የነበሩ ቆላ ፣ ቆላ የነበሩ በርሀ ፣ በርሃ የነበሩ አካባቢዎች እንደ ሳህራ እጅግ በርሃማ እየሆኑ ነው፡፡ ዓመት እስካመት ይገማሸሩ የነበሩ ወንዞች ፣ በየገመገሙ ፣ በየጋራና በየሸንተረሩ ይንፎለፎሉ የነበሩ ምንጮች ደርቀዋል፡፡ ወደ 60 በመቶና ከዚያ በላይ የነበረው የደን ሽፋን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሦስት በመቶ የማይበልጥ ነበር፡፡ አሁን በተደረገ ርብርብ የደን ሽፋኑ ወደ 17 በመቶ ከፍ ብሏል ቢባልም አኃዙን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጥራት ለሙግት ክፍት ነው፡፡ በአየር ንብረት ለውጡ የተነሳ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ ከመመላለሱ ባሻገር በበልግና በመኸርም መከሰት ጀምሯል፡፡ ከዓመት ዓመት ይከሰት በነበረ የዝናብ እጥረት የተነሳ የከርሰና የገፅ ምድር ውሃ እጥረት ተከስቷል፡ ፡ እየተቆራረጠና እየተዛባ የሚጥለውን ዝናብ ቢሆንም ደኖች በመራቆታቸው የተነሳ አፈሩ ውሃ መያዝ ባለመቻሉ ጠብ ባለቁጥር ስለሚሸረሸር የአፈር መከላትን እያባባሰ ግብርናውን አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
በዚህ የተነሳ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር ተመጣጣኝ ምርት ማምረት አልቻለችም፡፡ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አይደለም አግሮ ኢንዱስትሪውን ዜጋውን መመገብ እንደተሳነው ከመንገድ ቀርቷል፡፡ በቅርብ የወጡ ጥናቶች 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ያትታሉ፡፡ በቅርብ ይፋ የሆኑ መረጃዎች ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የምግብ እህል እርዳታ እንደሚያስፈልገው የተገለጸ ቢሆንም ከኮሮና ቫይረስና ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 30 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እየተገለጸ ነው ፡፡ ሕዝቧን ለመመገብ በሌለ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ስንዴን ጨምሮ የምግብ ሸቀጣሸቀጦችን ለማስገባት ተገዳለች::
የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ ጥሩ ዜና የለውም፡፡ እየታረሰ የነበረው መሬት ለምነቱን በማጣቱና በመራቆቱ የተነሳ እየቀነስና እየተራቆተ ይገኛል፡፡ ግብርና ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ ቢሆንም ፤ መታረስ ካለበት መሬት 17 በመቶ ብቻ ነው እየታረሰ ያለው፡፡ ይህ በሌላ በኩል እርስ በርሱ የሚቃረን ይመስላል ፡፡ የከፋ የምግብ እህል እጥረት ፣ ድህነትና የበዛ ሥራ አጥ ባለበት ሀገር መታረስ የሚገባው 83 በመቶ መሬት ጦም ያድራል፡፡ አበው እማት የወለፈንዲ ስልቻ ጤፍ ይቋጥራል፣ ባቄላ ያፈሳል እንዲሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ሀገራችንን ጨምሮ በዓለማችን እያየናቸው ያሉ የደን ቃጠሎዎች ፣ ድርቅ ፣ ጎርፍ ፣ ውሽንፍር ፣ የበርሀ መስፋፋት ፣ የወቅቶች መዛነፍ ፣ ወዘተረፈ የዓለም ሙቀት መጨመር እነ ትራምፕ እንደሚሉቱ የደባ ኀልዮት ሳይሆን የዕለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኝ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
የበለጸጉ ሀገራት ዛሬ ድሀ ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ ባለው የኢንዱስትሪ አብዮት ባካበቱት ሀብት እየተቋቋሙት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ያለዕዳቸው ውድ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ በግብርናችን ያለ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር የራሱ ድርሻ ቢኖረውም የዓለም ሙቀት መጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጋሬጣ እየሆነ ይገኛል፡፡ ግብርናችን ዛሬም ከበሬ ጫንቃ ያልወረደ ፣ በተበጣጠሰ መሬት ላይ የተመሰረተ ፣ የግብርና ቴክኖሎጂውም በተለይ የማዳበሪያና የምርጥ ዘሩ አቅርቦቱ የየአካባቢውን ሥነ ምህዳርን ከግምት ያላስገባ ስለነበር ከሞላ ጎደል የገጠር ልማት ፖሊሲው የታለመለትን ያህል ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ዛሬም ከተመፅዋችነት ሊያወጣን አልቻለም፡፡ ዛሬም በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ አልቻልንም፡፡ ይሁንና በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የኩታ ገጠም ግብርናን ፣ በተወሰነ ደረጃ ሥነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ እገዛ ፣ የከርሰና የገጸ ውሃን አሟጦ የመጠቀም ፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመሰራት ፣ በተለይ ዘንድሮ የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ግብ መጣሉ የአተያይ ለውጥ በማምጣቱ ተስፋ ያስቆረጠን ግን ደግሞ ብቸኛ ሊባል በሚችለው ግብርና ከምግብ ዋስትና ባሻገር ተስፋችንን እንድናድስ አድርጎናል፡፡ ለዚህ ተስፋ ሰጪ ጅምር እውቅና መስጠት የሚያስፈልገው፡፡
ችግሮቻችንን ሁሉ ፈታተን ፣ በታትነንና አገላብጠን ብንመረምራቸው አብዛኛዎቹ ከአንድ ቅርጫት የሚገኙ ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ካለመንከባከብ ፣ ካለመጠበቅና ካለማልማት ቅርጫት፡፡ የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የተፈጥሮ ሀብታችን እየተጎሳቆለ በመምጣቱ ማለትም መሬታችን የተራቆተ ፣ ዝናባችን የአጠረና የተቆራረጠ በመሆኑ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃችን በመመናመኑ ግብርናው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ በግብርና ላይ የተመሰረተው የዜጋው ሕይወት ፤ የሀገሪቱ ልማት ችግር ላይ ወድቋል፡፡ ይህ የሀብት ውስንነትን ፈጥሯል፡፡ በዚህ የተነሳ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከዓመት ዓመት እየተባባሱ መጡ፡፡ እነዚህን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችን እንዲያገግም ሌት ተቀን መሰራት አለበት፡፡ መሬት ማገገም ፣ ውሃ መያዝ አለባት፡፡ ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ችግኝ በመትከልና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን ነው፡፡ «አረንጓዴ አሻራ» የበሽታውን ምልክት ከማከም ይልቅ መነሻውን በማያዳግም ሁኔታ የመፈወስ አቅም እንዳለው በማመን ነው ፤«አረንጓዴ አሻራ ! » የእንቆቅልሾቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ( ማስተር ኪይ) ያልሁት፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)