ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት የዳበረ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሃብት ባለቤት፣ ከሁሉም በፊት የነቃች፣ የሰው ዘር መገኛና የሰው ልጆች ስልጣኔ መነሻ እርሾን የጣለች አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ ሃገር ብትሆንም ቀድማ ወደፊት መጓዝ ያልቻለች መሆኗ ማስረጃ የማያሻውና ማንም ሊያስተባብለው የማይችለው ሃቅ ነው።
የቀደምትነቷን ያህል በጀመረችበት ፍጥነት መጓዝ ባትችል የያዘችውን አስጠብቃ መቀጠል አቅቷት በብዙ መልኩ ከነበረችበት ተንሸራታ ጀማሪ ሃገር መሆኗን የአሁኑ ታሪካችን ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ነው። “የቁልቁለት ጉዞ” እንዳሉት ሦስት ትውልድ የማየት ዕድልን ያገኙትና ጎምቱው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ይህ እጅግ የሚያሳዝን ቢሆንም መሰረታዊው ነገር ግን “መሆኑ” ሳይሆን “ለምን ሆነ?” የሚለው ጥያቄ ይመስለኛል። መሆኑማ በቃ አንድ ጊዜ ሆነ፤ ደግሞም ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራምና፤ የፈሰሰ ውሃም አይታፈስምና ቀድመን ጀምረን ኋላ ቀሪ መሆናችንን እያስታመምን ሁሌም “መሆኑ” ላይ ቆሞ መቅረቱ ዋጋ የለውም። የሚሻለው “ለምን ሆነ?” የሚለውን የቀዳሚ ኋላቀርነታችንን መሰረታዊ መንስኤ በጥልቀት በመመርመርና ወደፊት እንድንጓዝ የኋልዮሽ አስሮ የያዘን ዋነኛ ችግራችን ምን እንደሆነ በማወቅ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ከወደቅንበት ተነስተን ታላቋ ሃገራችን እንደጅማሬዋ ከፊት ቀድማ የምትገኝበትን ብልሃት መዘየድ ነው። ለዚህም በቅድሚያ የችግሩን መንስኤ ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል።
ለመሆኑ ታላቋን ሃገር ኢትዮጵያን በጀመረችው ፍጥነት ወደፊት እንዳትጓዝ፤ ባለችበት ቆማ እንድትቀርና ይባስ ብሎ በየጊዜው ወደ ኋላ እየተንሸራተተች ኋላ ቀሪ እንድትሆን ያደረጓት ችግሮች ምንድናቸው? ብለን የጠየቅን እንደሆን በርካታ ምክንያቶችን እናገኛለን።
ኢትዮጵያን ባለችበት እያስረገጣት አንዳንዴም የኋልዮሽ እያስጓዛት ከዓለም ቀድማ ከጀመረችው የመሪነት ጉዞ አሰናክሎ ያስቀራት ክፉ ጠላት የስልጣኔና የዕድገቷ አቀንጭራ ግን አንድ ነው። እርሱም በመንግስትና በሕዝብ አስተዳደር ሥርዓቷ ውስጥ ሰርፆ የገነገነው፣ ሁል ጊዜ የማያድገውና ከዓለም ኋላ ቀርቶ ኋላ የሚያስቀረው ቆሞ ቀሩ የፖለቲካ ባህሏ ነው። በእኔ ዕምነት ከብሉይ እስከ ሐዲስ ታላቂቷ ሃገር ታላቅ መሆን በሚገባት ደረጃ ታላቅ እንዳትሆንና በተነሳችበት ልክ ወደፊት እንዳትጓዝ ከኋላ ሆኖ ሲጎትታት የኖረው የኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር በሴራ፣ በጥላቻና በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተው ይኸው ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን ነው።
በእርግጥ ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሃገሩ “ቀድማ ኋላ ቀሪነት” የሚቆጨውና የወደፊት መጻኢ ዕድሏ የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚጠይቀው መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ይህ ጉዳይ ካሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን መካከል “ሰላማዊ ትግል 101” በሚል ርዕስ በ 2006 ዓ.ም መጽሃፍ ያሳተሙት በሞያቸው የኤሌክትሪክ መሃንዲሱ አቶ ግርማ ሞገስ አንዱ ናቸው። ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1998 በኢሕአፓ አባልነት መቆየታቸውንና በቆይታቸው ከተማሯቸው በርካታ ቁም ነገሮች በተጨማሪ በህቡዕ ተደራጅቶ ስለሚደረግ የፖለቲካ ትግል አደገኝነት እንዲያስተውሉና በጠብመንጃ ስለሚፈጸም የሃገራችን የመንግስት ሽግግር ባህላችን እንዲመራመሩ ዕድል የፈጠረላቸው መሆኑን የሚናገሩት መሃንዲሱ የፖለቲካ ተመራማሪ ካነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚነግሩን በጥናታቸው ያገኙት ግሩም ቁም ነገር አለና ከእርሳቸው ጋር ትንሽ ላቆያችሁ።
በተለይም ከረጅም ዘመናት ሕዝባዊ ትግል በኋላ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር በ1997 ዓ.ም ተገኝቶ የነበረው ታሪካዊ ዕድል ሆን ተብሎ መቀልበሱ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የኢትዮጵያን የመንግስት ሽግግር የፖለቲካ ባህል እንዲመረምሩ እንዳስገደዳቸው የሚገልጹት አቶ ግርማ “ኢትዮጵያ ቀድማ ሰልጥና ለምን ወደ ኋላ ቀረች ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ታሪካችንን መመርመር ያስፈልጋል” ይላሉ። “ለኢትዮጵያ ቀድሞ ሰልጥኖ ከኋላ መቅረት ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው” ። እነርሱም ዘመናዊ ትምህርት ቀደም ብሎ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መደረጉና በእርስ በእርስ ጦርነት አንዱ አንዱን በመግደል የሚፈጸም የመንግስት የሽግግር ባህላችን ናቸው።
ዘመናዊ ትምህርት በምዕራብ አውሮፓ ተጀምሮ የሕብረተሰቡን ባህል መቀየር ከጀመረ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በኋላ ዘግይቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባ መሆኑና
ሃገሪቱ እርሱን ተከትሎ ለሚመጣ ዘመናዊነትና ስልጣኔ ጀርባዋን ሰጥታ መቆየቷ በዕድገት ወደ ኋላ ለመቅረቷ ምክንያት ነው። የእኛ ትኩረት ሁለተኛው ስለሆነ ስለ እርሱ በደንብ እንመልከት።
ይህን አስመልክቶ አቶ ግርማ የጥናታቸው ውጤት በሆነው መጽሐፋቸው ከገጽ 33 ጀምሮ ሲያብራሩ፤ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ከአክሱም ስልጣኔ መውደቅ በኋላ አንባገነኑ ሕወኃት/ኢህአዴግ ስልጣን እስከጨበጠበት 1983 ዓ.ም ድረስ በእርስ በእርስ ጦርነት አማካይነት በትጥቅ ትግል ስልጣን መያዝ ጀግና የሚያሰኝ ባህል ነበር / ነው” ይላሉ። ይህም ነፍጥንና ጉልበትን መሰረት ያደረገው የመንግስት ሽግግር ፖለቲካ ባህሏ ኢትዮጵያን እጅና እግሯን ተብትቦ ለስልጣኔና ለዕድገት የምታስብበት መተንፈሻ ጊዜ እንኳን እንዳይኖራት አድርጓት ቆይቷል። ምን ያህል ወይም ስንት ዓመታትን? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለመስጠት እያንዳንዱ የመንግስት ሽግግር ጦርነት ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀ አውሮፓውያኑ እንደሚያርጉት አባቶቻችን ጽፈው ያስቀመጡልን ታሪክ የለም።
“…ምን ያህል ስለ ጦርነት እየዘመርንና የጦርነት ነጋሪትን እየጎሰምን አጠቃላይ ግምት ለማግኘት ግን ምርምራችን እንቀጥል…”። ለጥናቱ እንዲያመቸን ከአፄ ኢዛና(320 ዓ.ም) ለመንግስት ሽግግር(ለስልጣን) የተደረጉትን የእርስ በእርስ ጦርነቶች በሙሉ ከግምት አናስገባም። ለጊዜው ጥናታችንን ይበልጥ ቀላል ለማድረግ ስንል ከአፄ ኢዛና ወዲህ ተሞክረው ያልተሳኩትን ቁጥር ስፍር የሌላቸው የመንግስት ሽግግር ጦርነቶችንም በሙሉ ወደ ጎን እንተዋለን። ጥናታችን ከአፄ ኢዛና ወዲህ በተደረጉትና በተሳኩ የመንግስት ሽግግር ጦርነቶች ላይ ብቻ ያተኩራል።
“በዚህ መልኩ ስናሰላው በ 320 ዓ.ም አፄ ኢዛና ከነገሱበት ጊዜ ጀምሮ አምባገነኑ ሕወኃት/ኢህአዴግ ስልጣን እስከያዘበት 1983 ዓ.ም ጊዜ ድረስ በነበሩት 1ሺ 662 ዓመታት ውስጥ በተደረጉ የተሳኩ የመንግስት ሽግግር ጦርነቶች ሳቢያ በጦርነትና በመገዳደል ላይ የተመሰረተው የመንግስት ሽግግር የፖለቲካ ባህሏ በግምት ከ 360 እስከ 400 የሚደርሱ ዓመታትን እንደ እሳት ለብልቦ በልቶ፣ ስልጣኔ ከውስጥም እንዳታበቅል ከውጭም እንዳትቀስም እጅና እግሯን ተብትቦ፣ ወደ ፊት እንዳትራመድ አስሮ አስቀርቷታል።” በማለት ደራሲው የጥናት ውጤታቸውን ይገልጻሉ ።
በዚህ ላይ ያልተሳኩት የመንግስት ሽግግር ጦርነቶችና አገሪቱ ከውጭ ወራሪዎች ጋር ያደረገቻቸው በርካታ ጦርነቶች ቢቆጠሩ ደግሞ በጦርነት የባከነው ጊዜ በጥቂቱ ከ500 ዓመታት እንደሚበልጥ ያላቸውን ግምትም ያመላክታሉ።
“ትንሽ ሰላም ጊዜና ጥሩ መሪ ተገኝቶ ብልጭ የሚሉ የስልጣኔ ጅማሮዎች ብዙም ሳይቆዩ በስልጣን ሽኩቻ በሚነሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ይወድማሉ። አገሪቱም እንደገና ተመልሳ ብዙ እርምጃ ወደ ኋላ ትሄዳለች” ይህንን የተመራማሪውን ድንቅ ትዝብታዊ ድምዳሜ ከምርም የሚያስደንቅ ጥናታዊ ምልከታ በአዕምሯችሁ እያሰላሰላችሁ ተከተሉኝ።
አዎ! አውዳሚውና ጎታቹ የፖለቲካ ባህላችን እንዲህ ታሪካችንን እያበላሸ እነሆ ዛሬም ተከትሎናል። እንዳለመታደል ሆኖ በረጅሙ አኩሪ ታሪካችን ውስጥ የተሰነቀረው አስፋሪው የፖለቲካ ባህላችን ከላይ በተገለጸው መንገድ የዕድገታችንና የስልጣኔያችን ዋነኛው ባላንጣ የሆነው ዕድሜ ልካችንን እየተከተለ ኋላ ሲያስቀረን የኖረው አውዳሚው የፖለቲካ ባህላችን ዛሬም የለቀቀን አይመስልም። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ወትሮም በመገዳደልና በጦርነት ላይ የተመሰረተው ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለይም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ደግሞ “የብሔር ብሔረሰቦች መብት” በሚል ሽፋን በሌላ አስቀያሚ በሽታ ተመርዞ ህመሙ ተባብሶበታል። እናም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ለጆሮ የሚከብዱ፣ ለሰሚ የሚያርዱ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥኑ፣ በጥቅሉ እጅግ በጣም የሚዘገንኑና የሚያሳፍሩ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችንና ተዘርዝረው የማያልቁ ሌሎች ታህተ ሰብዕ ክንዋኔዎችንም በየፈርጁ ለማስተናገድና የታሪካችን አካል ለማድረግ ተገድደናል። ከዚህ ሁሉ የቁልቁለት ዘመን በኋላ ደግሞ በርካታ ዓመታትን በፈጀና አያሌ መስዋዕትነትን ባስከፈለ የሕዝብ ትግል ከሁለት ዓመታት በፊት በተደረገ ጥገናዊ ለውጥ የብዙዎችን ተስፋ ያለመለመ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ሃገራዊ ለውጥ መጥቶ ለዘመናት አስሮ ከያዘን ፖለቲካዊ አዙሪት የወጣን መስሎን ብንደሰትም ዳሩ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በቆየው ችግራችን በአዲስ መልክ መፈተናችን አልቀረም።
የፖለቲካ ባህላችን የጥፋት መሳሪያነት የገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ሃገራዊ አንድነት ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተጋመደ፣ የተሰናሰለና የተዋደደ መሆኑን አመላካች ነው። የሃገራችን ብሔሮች እጣ ፋንታ በጋራ ለማደግ የተሰራ ብቻ እንጂ ተለያይተን ወይም ተነጣጥለን ሉዓላዊ ሃገር ሆነን፤ የነጠላ ህልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም። ሃገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር ነው” የሚል መዳኛ መንገድን አመላክተዋል። ሆኖም ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር “መብት” እና ለህዝቦች “እኩልነት” በሚል ሽፋን የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም በሚታትሩ፣ እነርሱ ብቻ የበላይ ሆነው ለመኖር በሚፈልጉ ጊዜ ያለፈበት “እኔ አውቅልሃለሁ” የሚመራው የድህረ ዋለልኝና መለስ ፖለቲካችን ከእስካሁኑ በባሰ ሁኔታ ሃገሪቱን ክፉኛ ችግር ውስጥ ከቷታል። የፖለቲካችን ፊታውራሪዎች ዛሬም “ጨቋኝ-ተጨቋኝ” የሃሰት ፍረጃ ፖለቲካቸው “ምናባዊ ተጨቋኝ” ፈጥረው የጭቁን ተቆርቋሪ መስለው ለመጨቆን ባላቸው ድብቅ ፍላጎት በለመዱት የጠላትነትና የፍረጃ ትርክታቸው ህዝብን አለያይተው፣ በጠላትነት አቧድነው ተከፋፍሎ የተዳከመ ህዝብን ያለ ተቃውሞ በበላይነት ቀጥቅጦ ለመግዛት አዛኝ መስለው ሕዝብን ለጦርነት በመቀስቀስ ላይ ናቸው።
ለዚህ እኩይ ዓላማቸው መሳካት ያመቻቸው ዘንድም አንድ ጊዜ ለሃገራዊ አንድነት ሌላ ስም በመስጠትና ከእውነታው በተቃራኒ ለቃሉ አሉታዊ ትርጉም በመፈብረክ፣ የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚነፍግ፣ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የሚንድ፣ ፌደራላዊ ሥርዓቱን የሚያጠፋ፣ ወደ አሀዳዊ ሥርዓት የሚመልስ፣ ብሔር ብሔረሰቦችንም የሚውጥ ወዘተ… የሚሉ የሃሰት ውንጀላዎችን በስፋት ሲያሰራጩ ከርመዋል። አሁን ላይ ከራሱ ጥቅም ውጭ ሌላውን ለማዳመጥ የማይፈልገው፤ መግባባት እንዳይኖር ሆን ተብሎ በልዩነቶች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ በጥላቻና በጠላትነት ተረክ የሚመራው የጎራ ፖለቲካ ከዕድገት እንቅፋትነት አልፎ የህልውናዋም ስጋት የመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል።
ይህም “ትንሽ ሰላም ጊዜና ጥሩ መሪ ተገኝቶ ብልጭ የሚሉ የስልጣኔ ጅማሮዎች ብዙም ሳይቆዩ በስልጣን ሽኩቻ በሚነሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ይወድማሉ። አገሪቱም እንደገና ተመልሳ ብዙ እርምጃ ወደ ኋላ ትሄዳለች” የሚለውን የፖለቲካ ባህላችን ተመራማሪው አባባል ያስታውሰናል። እናም በብዙ መከራና መስዋዕትነት የተገኘውንና ሃገር ትልቅ ተስፋ የጣለችበት ታሪካዊ ለውጥ ወደፊት ከመራመድ ይልቅ ወደኋላ እንዲመለስ መልካም ነገርን በአጭሩ የመቅጨትና ሁል ጊዜ በችጋርና በሃዘን ውስጥ መኖርን የለመደው “የቡዳ ፖለቲካችን” በተቃዋሚነት ቆሞ በእጅጉ እየተዋጋው መሆኑን መታዘብ ይቻላል።
በግለሰቦች ምርጫ ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት
ሰዎች ላይ በተጫነ መንጋ አቧድኖ ጎራ ለይቶ ህዝብን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ለማስገባት ላይ ታች እያለ የሚገኘው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በስፋት ሲሰራ የቆየው ይህ ከፍተኛ የጥፋት አጀንዳ በርካታ ማባበያዎች ቢደረጉለትም እጅጉን እየባሰበት ሄዷል። ምክንያቱም ኋላ ቀሩን የመጠፋፋትና የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ ወገኖች ነጻነትን እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው፣ ሃሳባቸውን በነጻ ገልጸው፣ በሃሳብ አሸንፈው የበለጠ ነጻነትንና ዲሞክራሲን ለማምጣት ሳይሆን እየታገሉበት ያለው ያለ ምንም ገደብ የራሳቸውን ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ነውና። ያለ ምንም ገደብ አፍራሽ ሃሳባቸውን ለማስፋፋትና በህዝብ ስም የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት ነው ነጻነትን እየተጠቀሙበት ያለው። በዚህም ያለ ማንም ከልካይ ጥላቻን ይሰብካሉ፣ ህዝብን በህዝብ፣ ሃይማኖትን በሃይማኖት፣ እንዲሁም ህዝብን በመንግስት፣ መንግስትን በህዝብ ላይ ያነሳሳሉ። ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲነገራቸው “ነጻነታችን ተገደበ” በማለት ከሳሽ ሆነው ይቀርባሉ። እናም በእኔ ዕይታ ለውጡ ከመጣ ወዲህ እስካሁን ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት በሃገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ሁሉ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች በነጻነት ስም ወንጀል እየፈጸሙ በነጻነት እየኖሩ ያሉት የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው። አሁን ደግሞ ዓለም ባወቀው ፀሃይ በሞቀው ከባድ የህልውና ችግር ምክንያት ሕዝብ በህይወትና በሞት መካከል ሆኖ እየተጨነቀ ጥፋትን ሊያስከትል በሚችል አኳኋን ምርጫ ካልተደረገ አገር እንደሚያፈርስ እየዛተ ይገኛል። ገሚሱ “ከመስከረም በኋላ በኃይልም ቢሆን ስልጣን እንይዛለን”፣ ገሚሱ ደግሞ “በራሴ ክልል ላይ ምርጫ ካላካሄድኩ አገር ትፈርሳለች” በሚል ለውጡ ያመጣውን ነጻነት ተጠቅሞ ያለ ምንም ፍርሃት በነጻነት፣ ያውም ሃገርን ለማፍረስ እየፎከረ ይገኛል።
ይህ እንግዲህ በብልሹው የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት የተፈጠረና ህልውናችን ላይ የተደቀነ ፈታኝ ችግር ነው። ወደድንም ጠላንም ችግሩ የውጭ ወራሪ ጠላት የፈጠረው ሳይሆን ከላይ ለማመላከት እንደሞከርነው በረጅሙ አኩሪ ታሪካችን መሃል ሲወርድ ሲዋረድ ተከትሎን የመጣ አዋራጅ የታሪካችን ክፍል ነው።
እናም የራሳችንን ችግር መፍታት የምንችለው ራሳችን እንጂ ማንም ሊፈታልን አይችልም። ታዲያ ከሰሞኑ ሁኔታው ያሳሰባቸው ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ይህን ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ በራሳቸው ተነሳሽነት ለሽምግልና ወደ መቀሌ መሄዳቸውን ሰምተናል። ይህም የራስን ችግር ለመፍታት ከራስ ተነሳሽነት መምጣቱና ችግሩን ልንፈታ ያሰብንበት መንገድም በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ለዘመናት አብሮን የኖረ አንዱ የታሪካችን አኩሪ ዕሴት እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖት አባቶችና በሃገር ሽማግሌዎች አማካይነት የተጀመረው የሽምግልና ተግባር ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ይህ ከሆነ ዘንዳ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በራሳችን እጆች ተጽፎ ከስድስት ወራት በፊት ህዳር ወር ላይ ቀርቦ የነበረውን ድንቅ አገር በቀል ችግር ፈች ፕሮጀክትን በማስታወስ “የት ደረሰ” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ምክንያቱም በመግቢያችን ላይ እንዳመለከትነው አንድ ችግር በትክክል እንዲፈታ ከተፈለገ መጀመሪያ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ተለይቶ መታወቅ ያለበት በመሆኑ “ኢትዮጵያ ከሁሉ ቀድማ ሰልጥና በዕድገት ወደ ኋላ የቀረችበት ዋነኛ ምክንያት በመጠላለፍና በመጠፋፋት ላይ የተመሰረተው የክፍፍል ፖለቲካ ባህሏ መሆኑን አውቆ ችግሩን ከሥሩ ለመፍታት አልሞ የተነሳ ፕሮጀክት በመሆኑ ነው።
ሃገራችንን አስሮ ይዞ ለዘመናት ወደ ኋላ ላስቀረን ለዚህ አሳሳቢ ችግር ዋነኛው መፍትሔም “የዛሬን ችግሮች በውይይትና በመቀራረብ በመፍታት የነገ የጋራ መጻኢ ዕድልን በጋራ መገንባት” መሆኑንም አመላክቷል። በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታም በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መካከል አሁን ላይ የተፈጠረውና አሳሳቢ በመሆኑ ሽምግልና የተጀመረበት ችግርም ከስድስት ወራት በፊት አስቀድሞ በትክክል ተተንብዮ የነበረ በመሆኑ ነው ከሽምግልናው ጎን ለጎን “የምንፈልጋት ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት ችግሩን ለመፍታት ጥቅም ላይ እንዲውል የምንጠይቀው! እናም እንዲህ ዓይነቶችን ሃገር በቀል የችግር መፍቻ ዕሴቶችና መፍትሔዎችን በመጠቀም የራሳችንን ችግር ራሳችን መፍታትና ከራሳችን ጋር መታረቅ ይገባናል በማለት የዛሬውን ምልከታዬን በዚሁ የማጠናቅቀው። መልካሙን ሁሉ ለሃገራችን ያድርግልን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
ይበል ካሳ