መጋቢት ሁለት ቀን 1968 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጸጉሩን ሹርባ በመሰራቱ ምክንያት ስለተከሰሰ ወንድ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ጸጉሩን ሹሩባ ተሰርቶ የተያዘው ወንድ ልጅ ከክሱ ነጻ ሆነ
አፍሮ ጸጉሩን ሹርባ ተሰርቶ በመገኘቱ ለባህል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ ከተከሰሰ በኋላ በቅርቡ ታስሮ የነበረው አበበ ወልደጻድቅ ከክሱ ነጻ ሆኖ መዝገቡ የተዘጋ መሆኑን የአዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ዓቃብያን ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
አበበ ክስ ቀርቦበት ሊታሰር የቻለው በቅርቡ አፍሮውን ሹርባ ከተሰራ በኋላ አዲስ አበባ ከተማ አፍንጮ በር አካባቢ ሃምሳ የሚሆኑ ህጻናትን ሰብስቦ ያልታወቀ ንግግር ሲያደርግ በመገኘቱና በሹርባውም መሰራት ምክንያት ለባህል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ ነበር። በዚህም ምክንያት ተከሳሹ ሁለተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ በእስር ቤት እንዲቆይ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ስምንት ቀን ያህል በእስር ቤት ቆይቶ እንደነበር ተገልጧል። የተከሳሹም ሁኔታ በዚሁ ጋዜጣ ተጠቅሶ ሹርባ መሰራት ወንጀል ሊሆን ይችላልን ? የሚል ትችት በማስከተል ጋዜጣው በወጣ ሰሞን ብዙዎችን ሲያጠያይቅ ሰንብቶ ነበር።
ተከሳሹ ለመልካም ባህል ተቃዋሚ የሆነ ሁኔታ አሳይቷል ከተባለም የወንድ ሹርባ መሰራት ቀደም ብሎ የነበረ መሆኑን ታሪክ የሚያስረዳ በመሆኑ ከዚህ ውጭ ወንድ እንደ ሴት ሹርባ ቢሰራ ለባህል ተቃራኒ ነው የሚያሰኝ ሕጋዊ ምክንያትና ባህላዊ ልማድ ባለመኖሩ ጭምር ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ አልተገኘም።
በዚህ መሰረት በዝርዝር በተገለጡት ምክንያቶች የወንጀል ድርጊት ፈጽሟል ለማለት የሚያስችል አጥጋቢ ማስረጃና ሕጋዊ ምክንያት አለመኖሩ ስለታወቀ የአውራጃው ፍርድ ቤት ዓቃብያን ሕግ ጽሕፈት ቤት ሕግ ጠቅሶ የወረዳው ፍርድ ቤት ዓቃቢ ሕግ ክሱን እንዲያነሳ ባስታወቀው መሰረት በተከሳሹ ላይ የቀረበው ክስ ተነስቶ መዝገቡ መዘጋቱንና ተከሳሹ ከክሱ ነጻ መሆኑን የአውራጃው ፍርድ ቤት ዓቃቢያነ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስረድቷል።
በመሰረቱ ወንድ ጠጉሩን ሹርባ ቢሰራ አድራጎቱ ለባህል ተቃራኒ ሆኖ እንደማይገኝ ተገልጧል። ነገር ግን ሹርባ ተሰርቶና ሴት መስሎ ሌላ ተግባር መፈጸም ወንጀል ነው። ነገር ግን የወንጀል ድርጊት የመፈጸም ሙከራ ሳያደርግ ወይም ወንጀል ሳይፈጽም ወንድ ልጅ ጠጉሩን ሹርባ በተሰራ ብቻ ወንጀለኛና ለባህልም ተቃራኒ አለመሆኑን ከምሁራን ተነግሯል።
************************
ታህሳስ 21 ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በቅርብ ያገኙትን አረቄ በመጠጣታቸው ምክንያት ህይወታቸውን ስላጡ ታዳጊዎች ተተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
እህትማማቾች በካቲካላ ሞቱ
ወይዘሪት ብዙነሽ ገብሬና ወይዘሪት እመቤት ገብሬ የተባሉ እህትማማቾች የእህል አረቄ ጠጥተው መሞታቸውን ከሸዋ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል የተገኘው ዜና ገለጠ። ልጆቹ ለሞት የበቁት ወላጅ እናታቸው አረቄውን ካወጡ በኋላ አልጋ ስር አስቀምጠውት ወደ ገበያ ሲሄዱ ከተቀመጠበት ቦታ አንስተው በመጠጣታቸው ነው።
ሟቾቹ አረቄውን እንደጠጡ በያሉበት ተዘርረው ወድቀው ነበር። በኋላ ግን ሰው ደርሶ ለህክምና ፍቼ ጤና ጣቢያ ተወስደው ህክምና ቢደረግላቸውም ለመዳን ተስፋ በማጣታቸው በ 10 ሰዓት ልዩነት ሁለቱም ህይወታቸውን አጥተዋል። በሁለቱ እህትማማቾች ላይ ይህ የሞት አደጋ የደረሰው ታህሳስ አራት ቀን 1965 ዓ.ም በሰላሌ አውራጃ በግራር ጃርሶ ወረዳ ግዛት ፍቼ ከተማ ውስጥ ነው። ወይዘሪት ብዙነሽ ገብሬ ዕድሜዋ ስምንት ዓመት ሲሆን ፣ የወይዘሪት እመቤት ደግሞ ስድስት ዓመት መሆኑን የማስታወቂያ ክፍሉ ባገኘው ሪፖርት መሰረት አስረድቷል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
የትናየት ፈሩ