ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የመሠረቱት የጥቁር አንበሳ ጦር በነቀምት አካባቢ የሰፈረ የኢጣሊያ ጦር አየር ኃይል ላይ ጥቃት ከፍቶ በእሳት ያወደመው ከ84 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 20 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር።
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር በመሰናዳት ላይ በነበረበት ወቅት ከየትምህርት ቤቱ የተመለመሉ ወጣቶች በ1928 ዓ.ም በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የጦር ትምህርት እንዲጀምሩ ተደረገ። የጦር ትምህርት ቤቱ ስራ የጀመረው በአምስት የስዊድን መኮንኖች አሰልጣኝነት ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የፋሽሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በመውረሩ የጦር ማሰልጠኛው በአግባቡ ስራውን ማከናወን አቃተው።
የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 127ኛ ዓመት ልደት በዓል በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር ‹‹በግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት የዘመናዊ ጦር ኃይሎች አመሠራረትና አደረጃጀት›› በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አቅርበው ነበር። ታደሰ ገብረማርያም የተባሉ ጸሐፊ ይህን ጽሑፍ ጠቅሰው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንደጻፉት፣ 148 ወጣቶችም ለዕጩ መኮንንነት ኮርስ ተመልምለው ጥር 21 ቀን 1927 ዓ.ም. ለሥልጠና ገነት ጦር ትምህርት ቤት ገቡ። ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ምልምሎቹንም በታላቁ ቤተ መንግሥት ተቀብለው አሸኛኘት ባደረጉላቸው ወቅት ‹‹ቤት ያለምሰሶ ሊቆም ወይም ያለ ግድግዳ ከቁር ሊያድን እንደማይችል ሁሉ የጦር ኃይል የሌለው አገር ከአደጋ ሊሰወር አይችልም›› በማለት ዕጩ መኮንኖቹ የተጣለባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አስገነዘቧቸው። ሥልጠናው ግን ልዩ ልዩ እንቅፋቶች ስለተጋረጡበት በተያዘለት የጊዜ ሰንጠረዥ መሠረት አልተካሄደም።
ዋነኛው ጋሬጣ የፋሺስት ጣሊያን ጦር በደቡብ በኩል ድንበር ጥሶ ለመግባት መሰናዶ እያደረገ መሆኑንና በሰሜን በኩል ደግሞ መረብ ወንዝ ተጠግቶ መስፈሩ መታወቁ ነው። ሁለተኛው እንቅፋት መንግሥት ቤልጅግ ከሚገኘው ‹‹ፋብሪካ ናሲዮናል›› እንደ ረጃጅምና አጫጭር ጠመንጃዎች ፣ መትረየሶች፣ መድፎች፣ ብረት ለበስ የጦርና መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ያሉ ልዩ ልዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎችን ለመግዛት ያደረገው እንቅስቃሴ መክሸፉ ነው። ግዥው ያልተሳካውም እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን ማናቸውም የጦር መሣሪያ በቅኝ ግዛቶቻቸው አልፎ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ቀደም ብለው በ1922 ዓ.ም ማዕቀብ በመጣላቸው ነበር።
ኢትዮጵያ ግዢው ባይሳካላትም ከ40 ዓመት በላይ ዕድሜ ባለው አሮጌ የጦር መሣርያ ወረራውን መከላከል የሚያስችል ዝግጅት አድርጋ ለዘጠኝ ወራት ያህል በሥልጠና ላይ የቆዩት ዕጩ መኮንኖች ሥልጠና አቋርጠው በመውጣት የጦሩን አመራር እንዲይዙ አደረገች።
ሁለት ሬጅመንት፣ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያና ልዩ ልዩ ኪነታዊ ክፍሎች ያሉት አንድ ብርጌድ እንዲቋቋም ተደረገ። ብርጌዱም ‹‹ኃይለሥላሴ ብርጌድ›› የሚል ስያሜ ተሰጠው። የብርጌድ ኃይለሥላሴ ዋና አዛዥ ሌተና ኮሎኔል ክፍሌ ነሲቡ፣ ዋና ኤታማዦር ሹም ሌተና ኮሎኔል ነጋ ኃይለሥላሴ፣ የአንደኛ ሬጅመንት አዛዥ ሌተና ኮሎኔል ከተማ በሻህ፣ የሁለተኛ ሬጅመንት አዛዥ ሌተና ኮሎኔል በላይ ኃይለአብ እንዲሆኑ ሹመትና ኃላፊነት ተሰጣቸው። ስዊድናውያን አሠልጣኞች ደግሞ በአማካሪነት ተመደቡ።
የፋሺስት ጣሊያን ጦር መስከረም 1928 ዓ.ም. በኦጋዴን፣ በደቡብና በሰሜን ወረራውን በይፋ መጀመሩን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 1928 ዓ.ም አዲግራትን ያዘ። ግርማዊነታቸውም ወደ ሰሜን ጦር
ግምባር ዘምተው ጊዜያዊ ማዘዣ ጣቢያቸውን ደሴ ላይ አደረጉ። ብርጌድ ኃይለሥላሴም በፍጥነት ወደ ውጊያው ገብቶ ከክብር ዘበኛ ጦር ጋር እንዲሠለፍ ቢታዘዝም ማይጨው ላይ ተፈታ።
ጃንሆይ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የፋሺስት ጣሊያን ጦር ቀድሞ አደጋ እንዳያደርስ በማሰብ የብርጌድ ሁለተኛ ሬጅመንት ጣርማ በር ላይ የጠላትን ጉዞ አንዲገታ የተደረገ ሲሆን፣ አንደኛው ሬጅመንትም ሚያዝያ 25 ቀን 1928 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባ። ጃንሆይም የስዊድን መኮንኖችን አስጠርተው ስለመልካም ተግባራቸውና ዕርዳታቸው ካመሰገኗቸው በኋላ የቅጥር ውላቸው መሠረዙን ገልጸው አሰናበቷቸው። ከዚህ በኋላ ጃንሆይ ወደ ጂቡቲ ተጓዙ።
ብርጌዱም ወደ ሆለታ አቅንቶ ትግሉን እንደቀጠለ፣ በትግሉም በርካታ ሲቪሎች እየተቀላቀሉት ‹‹የጥቁር አንበሳ ጦር›› የሚል መጠሪያ ይዞ በጠላትም ላይ የሽምቅ ውጊያውን አፋፋመ። ሰኔ 20 ቀን 1928 ዓ.ም በነቀምት አካባቢ የሰፈረ የኢጣሊያ ጦር አየር ኃይል ላይ ጥቃት ከፍቶ በእሳት በማውደም ድል ተቀዳጁ። የጥቁር አንበሳ አርበኞች የፋሽስት ኢጣሊያን ጦር ሲፋለሙ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ፤ ቆስለዋል ፤ ታስረዋል እንዲሁም ግዞት ተግዘዋል።
ቢቢሲ ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ባቀረበው ዘገባ “ለታሪክ የተቀመጡትና በጥቁር አንበሳ አርበኞች ድባቅ ተመተው የወረዱት የጣሊያን አውሮፕላኖች ቅሪት እስካሁን አለ። የድሮ ቀለማቸው ወይም ሙሉ ቅርፃቸው ለቆና እንዳልነበሩ ቢሆኑም የድሉ ምልክት መሆናቸውን እንደቀጠሉ ነው። በተለይ በምሥራቅ ወለጋ ላሉት የቦኒያ ሞሎ ነዋሪዎች ልዩ ትርጉም አለው።” ሲል ወደ ወለጋ በማቅናት ያነሳቸውን በጥቁር አንበሳ አርበኞች ተመተው የወደቁ አውሮፕላኖች ስብርባሪ አካሎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች የያዘ ጽሑፍ በድረ ገጹ ለጥፎ ነበር።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
የትናየት ፈሩ