የሰኔ ክራሞታችን፤
የሀገራችን የሰኔ ወር ለብዙ ጉዳዮቻችን በድንበርነት ያገለግላል። በጋና ክረምት ተጨባብጠው ለከርሞ ያድርሰን ብለው የሚሰነባበቱት በሰኔ ወር ነው። ፀሐያማዎቹን ቀዳሚ ዘጠኝ ወራት የሰኔ ወር የሚቀበለው “የዝናብ እንባ” እያካፋ ነው። የዓመቱ የትምህርት ዘመን ተጠናቆ ወደ መጻኢው አዲስ የትምህርት ዘመን ሽግግር የሚደረገውም “እንባ በተቀላቀለበት የተማሪዎች የናፍቆት መሰነባበቻ” መሆኑን ልብ ይሏል። ለዛሬው የ“Tech Generation” ትርጉም ስለመስጠቱ ተጠራጥሬ እንጂ የእኔን ዘመን “ሰኔ ሠላሳ” ተጠቃሽ ታሪኮች ብዘረዝር ጨዋታዬ አፍ ሊያስከፍት ይችል ነበር። ተዳፍሬ ላስታውስ ብል እንኳ አንባቢም ሆነ አድማጭ ስለማላገኝ “በወይ ነዶ!” ቁጭት አልፈዋለሁ።
የሰኔ ወር ሀገራዊው የዓመት በጀት ፋይል መዝጊያም ነው። በዚሁ ወር የበጀት ማወራረጃው ደረሰኝ ልክ እንደ ከበረው የአልማዝ ማዕድን የሚቆፈረውና የሚበረበረው በጥንቃቄና በድካም ነው። ባህላዊ የማዕድን ቆፋሪዎች “የወርቅ ቡችላ” ለማግኘት የሚከፍሉትን የድካም ዋጋ ያህል የየተቋማቱ የሂሳብ ባለሙያዎችም የሰኔ ወርን የሚቀበሉት በብዙ ድካምና በጨፍጋጋ ፊት ስለመሆኑ ማንም ይረዳዋል። የተሠራበትንም ሆነ “የተበላበትን በጀት” ለማወራረድ ያለው መተረማመስ አጃኢብ የሚያሰኝ ነው። የገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶችም “ቆጣ ቆጣ፤ ግንፍል ግንፍል” በማለት ደንበኞቻቸውን በጎሪጥና በጥርጥር የሚመለከቱበት ወርም ነው – ይሄው የዓመቱ አስረኛ ልጅ።
የኦዲት መሥሪያ ቤቶችም “አጥርቶ የሚያይ መነጽራቸውን፣ አንጥሮ የሚለይ ማይስክሮኮፓቸውን” በሠራተኞቻቸው ላይ መግጠም የሚጀምሩት በዚሁ በሰኔ ወር ነው። የመንግሥታዊ መ/ቤቶች፣ ኩባንያዎች፣ ኦዲተሮችና ግብር ሰብሳቢ ተቋማት ለግብግብ የሚሟሟቁበትን ይህንን ወር የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች ለምን በዋዛ እንደሚያሳልፉት አይገባኝም። “ዳሩ ምን ጥበብ አለና!” አለ፤ አሉ የሀገሬ ሰው። “ጊዜያዊና ሕዝባዊ የዕውቅና ኮሚሽን” አቋቁመን አሥራ ሦስቱን የሀገራችንን ወራት ለሽልማት ውድድር ብናቀርባቸው ያለጥርጥር “በዜሮ የሚወጣው” የሰኔ ወር ሳይሆን እንደማይቀር በግሌ እገምታለሁ። በጋው አኩርፎ የሚሰናበትበት፣ ተማሪው የሚሳቀቅበት ወይንም የሚፈነጥዝበት፣ ተቋማት ሂሳባቸውን ለመዝጋት የሚደነባበሩበት፣ ሀገራዊው በጀት ለራስ ጥቅምም ሆነ ለሀገር ኩራት ተሟጦ ካዝናው ጦም የሚያድርበት ወር መሆኑን ቀደም ሲል ለመጠቆም ተሞክሯል።
እርግጥ ነው ከመቼዎቹም ዓመታት ይልቅ ይህ የተያያዝነው የሰኔ ወር ይበልጥ መጨፍገጉ የሚካድ አይደለም። የኮቪድ 19 ጦስ ተማሪዎችን ቤት ስላዋላቸው ለክፍልም ሆነ ለብሔራዊ ፈተናዎቻቸው አልታደሉም። ወላጆቻቸውም ከሥራ ገበታቸው ላይ ተለይተው አብረው ቤት መዋላቸው ሌላው ሀገራዊ ፈተና ነበር። ብዙ የንግድ ተቋማት እንኳንም የድርጅታቸውን ሂሳብ ሊዘጉ ቀርቶ ብዙዎቹ ቢሮዎቻቸውን በኪሳራ ሰበብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት በግራ መጋባት ውስጥ ወድቀው እየተከዙ መሆናቸው ይደመጣል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም የመደበኛ የሥራ መስኩን ለመዝጋት ወስኖ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። የኮቪድ ጦስ ነዋ! ምን ይደረግ። ዜመኛው ነፍሰ ሄር ጥላሁን ገሠሠ፤
ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣
የስንቱ ተወርቶ የስንቱ ተነግሮ።
በዚያኛው ተገርመን ጥቂት ሳንቆይ፣
የዚህኛው መምጣት አያስቅም ወይ፣
ብዙው አሳራችን ሲጓዝ ከረመና፣
ዘንድሮ ላይ ሲደርስ ሸክሙ አጋደለና፣
ተዝረክርኮ ወድቆ በግልጽ ብናየው፣
የዘንድሮን ነገር ዘንድሮ አወቅነው።
በማለት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ያንጎራጎረው በርግጠኝነት ከዘመኑ አሻግሮና የእኛ ዘመን አሳስቦት ሳይሆን አይቀርም።
ተከታዮቹ ሐምሌና ነሐሴ፤
የሀገራችን በርካታ ጉዳዮች የታጀሉበትን ፋይል ከሰኔ ወር ላይ የሚረከቡት የሐምሌና የነሐሴ ወራት ብዙ ሀገራዊ ተግዳሮቶችን እንደሚወርሱ አለመጠርጠሩ የዋህነት ይሆናል። ችግሮቹን በጥበብ፣ በማስተዋል፣ በትእግስትና በመረዳዳት ማለፍ ካልቻልን በስተቀር “አንድ ክረምት የተከለውን ችግር በዘጠኝ ክረምት ወደማይነቀልበት ደረጃ” ማሸጋገራችን አይቀሬ ይሆናል። ከመቼውም ጊዜ በላይ ከዜጎች እስከ ሹማምንት፣ ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት፣ ከወታደር እስከ አርሶ አደር፣ ከባለመደብር እስከ ወታደር እየተናበብን የሚያጋጥሙንን ሀገራዊ ችግሮች በመደጋገፍ ከማሳለፍ ውጭ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።
በአንድ የከፋ የርሃብ ዘመን አንድ ብልህ የሀገሬ መካሪ በሚከተሉት ሦስት አንጓ ስንኞች አማካይነት የማሕበረሰቡን ህሊና እንዳነቃ ከታሪክ መጽሐፍ ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ይዘቱ እንዲህ የሚል ነበር፤
ሐምሌ ጦሩን መዟል ሰው ሊፈጅላችሁ፣
ነሐሴ ሰይፉን መዟል ሊረፈርፋችሁ፣
ሃይ አትሉትም ወይ ያላችሁ ሰጥታችሁ።
በችግር ዘመን እንኳንስ የሰው ልጅ የዱር እንስሳትም ይረዳዳሉ ይባላል። የሚቀጥሉት ሁለት ወራት ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በብዙ ጉዳዮች መደጋገፍ የሚያስፈልገን ወቅት ስለመሆኑ ሁኔታዎች እንድንዘጋጅ እየመከሩን ነው። ስለዚህም ነው በሰኔ ወር የሚዘጋው የሀገር በጀት እንጂ የሀገር ተስፋ ሊሆን አይገባም በማለት ነው ለጽሑፌ ርዕስ ለመስጠት የተገደድኩት።
ቀጣይ ሀገራዊ ተስፋዎቻችንና ተግዳሮቶቻችን፤
በጸሐፊው አመለካከት በሚቀጥሉት የክረምት ወራት የታላቁ የሀገራችን የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ተግባራዊ ሆኖ ብርሃን ሊፈነጥቅ መጋል የሚጀምረው የቤታችን አምፑሎች ብርሃን እንዲረጩ ብቻም ሳይሆን የጨፈገገውን ሀገራዊ ተስፋችንንም በብርሃን ፀዳል እንደሚያፈካ ሕዝቡ ትልቅ እምነት አሳድሯል። በሐምሌ ወር ተገድቦ ቤት መዋል የሚጀምረውን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ሳስብና በተከታታይ ወራትና ዓመታት የምንሰማቸውን የግድቡን መልካም ዜናዎች በተነቃቃ ተስፋ ሳውጠነጥን የሀገሬ አርሶ አደር የአዝመራውን ስምረት እያስተዋለ የተቀኘው አንድ ጥንታዊ ሕዝባዊ ግጥም ወደ አዕምሮዬ ይመጣል።
በመስከረም ደረሰልኝ ገብሴ፣
በጥቅምት እላለሁ ጥቂት፣
በህዳር እላለሁ ዳር ዳር፣
በታህሳስ እጅንፉ ድረስ።
ይህ ሕዝባዊ ግጥም በአብዛኞቹ የሀገራችን ክፍሎች የተለመደውን የአዝመራ ወቅት አካሄድ በሚገባ የሚያሳይ ጥሩ ገላጭ ሃሳብ የያዘ ግጥም ነው። የገብስና የስንዴ አዝመራ ፍሬ መያዙ የሚረጋገጠው በመስከረም ወር ነው። ጥቅምት የአበባና የእሸት መዳረሻ ወር ነው። በህዳር ተስፋ ይለመልማል። አርሶ አደሩና ልጆቹ በየማሳው ዳርቻ የእሸት እንኩቶ እየጠበሱ መብላትም የተለመደ ፀጋ ነው። በታህሳስ ገበሬው ምርቱን ማፈስ ይጀምራል። እንኳን አርሶ አደሩ ቀርቶ የቤት እንስሳትም ሳይቀሩ ጠግበው የሚቦርቁበት ወር ነው – ታህሳስ።
“ጅንፉ” ጠግቦ መብላትን ያመለክታል። የቃሉ መሠረት የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ሲሆን በዱላ ወይንም በጦር እጀታ ጫፍ ላይ የሚደረግ ድቡልቡል ብረት ወይንም በበትር ላይ በተፈጥሮ የበቀለ ጉጥ “ጅንፉ” ይባላል። ይህንን ለግብርናችን የተገጠመውን ሕዝባዊ ሥነ ቃል ለህዳሴ ግድባችን የውሃ አሞላል ቅደም ተከተልና ከምንናፍቀው የመብራት ፀጋ ጋር አመሳስለን ብናስተያየው ይበልጥ ትርጉሙ ይገዝፍ ይመስለኛል።
በሐምሌ ወር የሚጀመረውን የግድቡን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ሂደት “ደረሰልኝ ገብሴ” ብንል ያስኬዳል። በውስን አቅሙ ብርሃን መስጠት ሲጀምርም “እላለሁ ጥቂት” ማለቱ ተገቢ ነው። የህዳሩን ዳርዳርታም እንዲሁ በማመሳሰል ብንቀኝለት ልብን ያሞቃል። ግድቡ ተመርቆ በሙሉ ኃይሉ ከቤታችን ደርሶ በድህነት ላይ መሸለል ስንጀምር “እጅንፉ ድረስ” በማለት በሀገራዊ ዜማ ብናሸበሽብና ጮቤ ብንረግጥ ቢያንስብን እንጂ አይበዛብንም።
ተስፋችን እውን ሆኖ የምንጨብጠው ከብዙ ተግዳሮቶች በኋላ ስለመሆኑም መተንተኑ ተገቢ አይመስለኝም። የእያንዳንዳችን ሕይወት በራሱ ምስክር ስለሆነ። የሀገራዊ ተስፋችንን ነዶ እየወዘወዝን ለመዘመርም እንዲሁ ውጣ ውረድ የበዛባቸውን ኮረኮንች ተግዳሮቶች በጥበብና በማስተዋል ማለፍ ግድ ይሏል።
በጸሐፊው ግምት በፊታችን ባሉት ወራት ከሚፈታተኑን ዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል ሦስቱን ብቻ ማስታወስ ይገባ ይመስለኛል። አንድም የብሔራዊ ግድባችንን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት በተመለከተ “ድርድርን ሳይሆን ዘራፍ ማለትን ከመረጡ” ስግብግቦች የሚገጥመንን ተግዳሮት በቀዳሚነት መጥቀስ ይቻላል። ሁለትም ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዘው የሚመሰቃቀሉት ሀገራዊ ጉዳዮቻችንና ኑሯችን ቅኝቱም ዜማውም ለጆሮ የሚጥም ላይሆን ይችላል። ሦስትም “ምርጫ ካላካሄድኩ ሞቴን እመርጣለሁ” በማለት ፉከራና ቀረርቶ እያሰማ ያለው ህወሓት ዛቻውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲሞክር ሊፈጠር የሚችለው ሀገራዊ ቀውስ በቀላሉ እንደማይታይ መገመቱ አይከብድም። ሌሎች ሀገራዊ ተግዳሮቶች የሉም ማለት ሳይሆን ለማሳያነት እነዚህን ሦስቱን መጥቀሱ ለአብነት ያህል በቂ መስሎ ስለታየኝ ነው።
ጥልቅ ሕዝባዊ ምክክርና መንግሥታዊ መፍትሔ የሚጠይቁት እነዚህ ተግዳሮቶች በአንድ ልብ፣ በሰፊ ማስተዋል፣ በጥንቃቄ ውሳኔዎች እስካልተፈቱ ድረስ ችግራችንን ለትውልድ ማስተላለፋችን አይቀሬ ይሆናል። የህዳሴ ግድባችን በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ በተለይም
በግብፅ ላይ ምንም ጉዳት እንደማያስከትል በተባበረ ድምጽ ሳንሰለች ጮክ በማለት አስረግጠን ልንነግራቸውና ልንመክራቸው ይገባል። “ምከረው ምከረው እምቢ ያለ እንደሆን መከራ ይምከረው” አማራጭ ሊሠራ የሚገባው ሙከራዎችና ጥረቶች በሙሉ ተሟጠው ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ መውደቁ በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ ብቻ መሆን ይገባዋል። የሀገራችን ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና በአክቲቪስትነት ካልተቀበላችሁን እያሉ ግራ የሚያጋቡን ወገኖችና ቡድኖች ሁሉ የሚፈተኑበት የ“ብሔራዊ ፈተና ወቅት” መቼ ነው ከተባለ ጊዜው አሁን ይመስለኛል። የተጠናከረና የተናበበ የዲፕሎማሲ ዘመቻና የምክቶሽ ተግባር ለዓለም ሕዝብ ለማሳየትም ወቅቱ አሁን እንደሆነ ማመን ይኖርብናል።
በሀገራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ እያንጎላጀጁ የሚያላዝኑት የኪነ ጥበባት ባለሙያዎችም ከድብርት ነፃ ወጥተው ሚናቸውን ለመወጣት ጊዜው እራሱ እየቀሰቀሳቸው ይመስላል። “መንግሥት አላሰበልንም፣ ሙያችንም አልተከበረልንም” እያሉ ከማጉተምተም “ባርነት” ራሳቸውን ነፃ አውጥተው በሙሉ ኃይላቸው ወደ ፍልሚያው ጎራ ለመቀላቀል ጎትጓች ሊያስፈልጋቸው አይገባም።
የመንግሥትን ዕቅድና ጥረት በማጠልሸትና በማደነቃቀፍ ለሰድቦ ሰዳቢ ለመስጠትና ችግሩን ለማባባስ በተመቻቸው አቅጣጫ ሁሉ የማሰናከያ ድንጋይ የሚኮለኩሉ “ህሊና ሙት” ወገኖችም ቀልብ እንዲገዙና በሕጉ መሠረት እንዲዳኙ ማድረጉ የትእግስትን መሟጠጥ አያመለክትም። በግሌ ግብጾች በጦርነት ፕሮፓጋንዳ ባበዱና “ና ደሞ ገለል” እያሉ በማቅራራት በየሚዲያውና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እብደታቸውን በገለፁ ቁጥር “ኑና ይዋጣልን!” እያልን በትንሽ በትልቁ መካረር በግሌ አይመቸኝም። የሚበጀው “ውሾቹ ይጮኻሉ ግመሎችም ይጓዛሉ” በማለት የራሳቸውን ተረት እያስታወስናቸው ሥራችንን መሥራቱ ይበጅ ይመስለኛል። ሀሰትና ዕብሪት የሚመክነው በመርህና በእውነት ብቻ ስለሆነ።
የኮቪድ ወረርሽኙም ሊገታና ሊሸነፍ የሚችለው ለራሳችን ተጠንቅቀን ለሌሎችም ማሰብ ስንችል ብቻ ነው። ደህንታችን በእጃችን ላይ መሆኑን ልናምን ይገባል። አታድርጉ የተባልነውን ባለማድረግና አድርጉ የተባልነውን እንደተነገረን በመተግበር የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ልንታደግ ይገባል።
ከሕግና ከሥርዓቱ ውጭ በጀብደኝነትና በእብሪት ራሳቸው አስመራጭ፣ መራጭና ተመራጭ ለመሆን እሪታ እያሰሙ ያሉት ውሱን የወያኔ አመራሮችም ቆም ብለው ሕዝቡን በማክበር ቋንቋቸውን ቢገሩ፣ ፉከራቸውንም ቢያጤኑ ይበጃል። የፌዴራል መንግሥትም ቢሆን “አድምጡኝ” ብቻ ሳይሆን ልበ ሰፊ ሆኖ “ላድምጣችሁ” የማለት ወኔ ሊኖረው ይገባል። “የብልጽግናን ስም” የተሸከሙት አመራሮችና ካድሬዎችም የስብዕና ብቃታቸውና የሥነ ምግባር ጥንቁቅነታቸው በሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ ሊፈተሽ ይገባል። “ለስድብሽማ ስድቤ በቂ ነው፤ ትርፉ ሰው መስማቱ ነው” እንዳለችው ሴት “ፊት-ቀደም የፖለቲካ መሪዎችም ሆኑ የየፖለቲካው ጋሻ ጃግሬዎች ‹‹ሕዝቡን ስድብ ባያስተምሩት››፤ ጠንከር ካለም ‹‹ ነውራቸውን ክብራቸው አድርገው›› አደባባይ ባይወጡ ለእኛ ለተራ ዜጎች ህሊና ውለታ የዋሉ ያህል ያስመሰግናቸዋል።
ሀገራዊ ችግራችን ብዙ ነው። ጨለማችንም የከበደ ይመስላል። ነገር ግን ጨለማው ሲከፋ ከዋክብቶች እጅግ መድመቃቸውን ልንዘነጋ አይገባም። ሀገራችን ተስፋ አላት። በርግጥም የሚያስጎመጁት የልማት ጅምሮችና መነቃቃቶች ውስጣችን እንዳይቀዘቅዝና ተስፋችን እንዳይዳምን ልባችንን ይደግፉታል። የዛሬው ችግራችን የነገ ስኬታችን ትምህርት ቤት መሆኑን አምነን ልንቀበል ይገባል። በሰኔ ወር ሀገራዊ በጀት ይዘጋ ካልሆነ በስተቀር ሀገራዊ ተስፋችን በፍፁም ሊቆለፍበት አይገባም። ቁዘማችን ወደ ተነቃቃ ተስፋ ተለውጦ ከተግዳሮቶቻችን ባሻገር የነገን ብሩህና ውብ የተስፋ ጀንበር ልንናፍቅ ይገባል። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)