በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (በናይል ወንዝ) ጉዳይ የግብጽን ፕሮፖጋንዳ መመከት እንዳለብን የሚያሳስብ መጣጥፍ በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አቅርቤ ነበር። በዚህ መጣጥፍ ላይ የሚዲያ ተቋማት (ኦንላይን ሚዲያን ጨምሮ)፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች በህዳሴ ግድብ ጉዳይ አንድ የጋራ መግባባት ፈጥረው አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያነሳሱትን የግብጾችን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ጭምር ነው።
በማህበራዊ ሚዲያው በተመሳሳይ መልኩ በጥቅሉ የሚዲያ አጠቃቀማችን ጉዳይ እንዲታሰብበት የወተወቱ ወገኖች ብዙ ነበሩ። ይኸን ተከትሎ ባለፈው አንድ ሳምንት ሁለት አዎንታዊ ምላሾችን አይተናል። አንደኛው ዋናው ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያውያን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን የሚያወጧቸው ፕሮፖጋንዳዎችን እየተከተሉ ተገቢውን ምላሾች መስጠት መጀመራቸው ነው። የኢትዮጵያውኑ በድንገት የግብጻውያን ድረገጾች ላይ መዝመት ግብጾችን ምን መጣብን እያስባላቸው ነው። ቀደም ሲል እንደልባቸው ያወሩ የነበሩ የኦንላይን ሚዲያዎች በራሳቸው ገጽ ኢትዮጵያን የሚያጀግኑ ሀሳቦች እንዲያውጡ ተገድደዋል።
ኢትዮጵያውያን የሰጧቸው ሃሳቦች ከብዛት ብቻም ሳይሆን ከጭብጥ አንፃር ጠንከር ያሉ መሆናቸው ደግሞ ግብጻውያንን ስለማስደንገጡ አንዳንድ ምልልሶች ያስታውቃሉ። በአጭሩ እኛ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ግዛት ውሎች ልንገዛ እንደማንችል፣ የግብጽ እኔ ብቻ ልልማ ዓይነት ስግብግብ ፍላጎት እንዳማያስኬዳት፣ ግብጽ ለተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ሰሞኑን ያስገባችው አቤቱታ የግድቡን ሥራ እንደማያደናቅፍ፣ ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያውያን መሆኑን ወዘተ…ነግረዋቸዋል።
በእርግጥም ግብጻውያን ትልልቆቹ ሚዲያዎች ሊቋቋሙት ያልቻሉት ጡጫ አርፎባቸዋል። አዎ! ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቀለም፣ ጎሳ ሳይለየን እንዲህ አንድ ላይ ስንቆም ድምጻችን ርቆ ይሰማል። ሕብረታችን ጠላቶቻችን ያብረከርካል።
የግብጾቹ ታላላቅ ሚዲያዎች ማለትም Daily news Egypt, Ahram online, Egypt independent, Egyptain streets እና ሌሎች እንደለመዱት ግብጽን በፕሮፖጋንዳ ለማግነን አስበው የለጠፏቸው የተለያዩ ዜናዎችና መረጃዎች በሚያስደንቅ መልኩ በኢትዮጵያውያን ተገቢውን መልስ አግኝተዋል።
ከ48 ሰዓታት በፊት በሶሻል ሚዲያ ላይ ብቻ ከግማሽ ሚሊየን ሕዝብ በላይ ተከታይ ያለው አህራም ኦንላይን ተከታዩን ዜና አስነብቦ ነበር።”Egypt wants the United Nations Security Council to “undertake its responsibilities” and prevent Ethiopia from starting to fill its massive, newly built hydroelectric dam on the Nile River next month amid a breakdown in negotiations, Egyptian Foreign Minister Sameh Shukry told The Associated Press on Sunday, accusing Ethiopian officials of stoking antagonism between the countries.” የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን መሙላት ከመጀመሯ በፊት እንዲያስቆምላት ስለመማጸናቸው የሚያወራ ዜና ነው።
በዜናው ግርጌ ከሰፈሩት አስተያየቶች በዚህ ጸሐፊ ግምት ከ98 በመቶ በላይ የኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ነበር። ብዙዎቹ የሚኒስትሩን ተማጽኖ ሚዛን የሚገለብጡ እውነታዎችን አካፍለዋል። ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት ማንንም እንደማታስፈቅድ አስረግጠው ነግረዋቸዋል።
ሰሞኑን ከቀረቡት ዘገባዎች መካከል ሌላኛው Daily news Egypt የዘገበው እንዲህ የሚል ዜና ይገኛል።” … Egyptian Air Force personnel, President Al Sisi
said,”Be ready to carry out any mission inside or outside our borders if need be.” የግብጽ አየር ኃይል ዝግጁ መሆኑን አልሲሲ የገለፁበት ነው። ይህ ዜና ትኩረቱ ግብጽ ለሊቢያ ቢሆንም በርካታ ኢትዮጵያውያን ግን ከህዳሴ ግድብ ጋር በማያያዝ ሰፊ የመልስ ጥቃት አድርሰዋል። በድረገፁ ላይ ከተስተናገዱ በሺ የሚቆጠሩ አስተያየቶች የኢትዮጵያውያን መሆኑ ድንቅ ይላል።
በተጨማሪም በርካታ ኢትዮጵያውን “ግድቡ የእኔ ነው/ ግድቡ የእኛ ነው” የሚሉ የፌስቡክ ዘመቻዎችን በመክፈት ባለከባድ ሚዛን ጫና በግብጾች ላይ ፈጥረዋል/ እየፈጠሩም ነው።
ሌላው ሁለተኛው የሰሞኑን ክስተት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከናይል ውሃ ጋር በተገናኘ ከሚሠሩ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ጋር ተገናኝቶ የመነጋገሩ ጉዳይ ነው።
በዓባይ ጉዳይ በራሳቸው ተነሳሽነት በተለያዩ ሚድያዎች አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብለው ከተመረጡ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ተቀራርበው ከመመካከር አልፈው ለወገኖቻችን ጥረት ተገቢውን እውቅና መስጠታቸው ይበል የሚያሰኝ ትልቅ ተግባር ነው።
ይህ ጅምር እንዲጠናከር እኛም በሀሳብም ቢሆን የየአቅማችን መደገፍ ይገባናል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በዋንኛነት በሶሻል ሚድያው እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በተበታተነ ሁኔታ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ኢትዮጵያውያን አሉ። በቀጣይም የዜጎችን ግንዛቤ በማሳደግ በርካታ አስተዋጽኦ ለማድረግ አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ማግኘት ይቻላል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን ማድረግ ይችላል?
አንዳንድ ጋዜጠኞች ወይንም አክቲቪስቶች ሚኒስቴሩ በጀት መድቦ ደመወዝና አበል የሚከፈለው የሶሻል ሚዲያ ሠራዊት እንዲያቋቁም ይፈልጋሉ። መፈለግ ብቻም ሳይሆን ግፊት የሚደርጉም ብዙ ናቸው። በግሌ ግን ይህ መንገድ ያዋጣል ብዬ አላስብም። ከዚህ ቀደምም በተለያዩ አካላት ተሞክሮ ጥቂቶችን ከመቀለብ ያለፈ ውጤት እንዳላመጣ የምናውቀው ነው። በአሁን ሰዓትም በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀለብ የሚሰፈርላቸው አክቲቪስት ተብዬዎች ፓርቲው ባተኮሰው፣ ባስነጠሰው ቁጥር እየተርገፈገፉ ክንፋቸውን ጨርሰው መንቀሳቀስ እንደተሳናቸው ያስተዋልን ነው። እናም ሚኒስቴሩ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሠሩ ወገኖችን ማገዝ ያለበት በቴክኒክ፣ በመረጃ እና በሥልጠና ብቻ መሆን አለበት እላለሁ። ሥራዎች በበጎ ፈቃደኝነት በራስ አቅም ሲሠሩ የበለጠ ውጤት እንደሚያመጡ ጥቂቶች እስካሁን ካሳዩት ተሞክሮ በሚገባ የታየ ነው።
የቴክኒክ እገዛ ሲባል ምን ማለት ነው? ሚኒስቴሩ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ተገቢውን መረጃ የሚሰጥ አንድ ዘመናዊና የተደራጀ የሪሶርስ ሴንተር ወይንም የመረጃ ማዕከል የማቋቋምን ጉዳይ ነው። ሪሶርስ ሴንተር (Resource Centre) በአማርኛ የመረጃ ማዕከል የሚለው ሊተካው ይችል ይሆናል። ግን እርግጠኛ አይደለሁም። በዚህም ምክንያት እንግሊዝኛውን በመዋስ ሪሶርስ ሴንተር እያልኩኝ መቀጠልን መርጫለሁ። አንዳንድ አገራት ይህንኑ የሪሶርስ ሴንተር፤ ዳታ ሴንተር (የመረጃ ቋት) ይሉታል። ዳታ ሴንተር የሚለው ቃል ግን በአመዛኙ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወይንም ከኮምፒውተር ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሪሶርስ ሴንተርን የሚተካ አይሆንም። አሁን ግን በሀሳብ ደረጃ የማነሳው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መረጃ ለሚፈልጉ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች ወገኖች በቀላሉ የሚፈልጉትን መረጃ የሚያገኙበት በቴክኖሎጂ፣ በመጽሐፍትና በጥናታዊ መዛግብት የተሟላ ማዕከል የማደራጀት ጉዳይ ነው። ያው እንደምናውቀው ሀገራችን እንዲህ አይነት ማዕከል ቀርቶ በወጉ ስለህዳሴ ግድብ ተከታታይ መረጃ መስጠት የሚችል አደረጃጀት ኖሯት አያውቅም። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለሚዲያዎች ደስ ባላቸው ጊዜ ከሚሰጡት የተበጣጠሰ፣ ያልተቀናጀ፣ አንዳንዴም ያልተናበቡ መረጃዎች በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል የተጻፈ፣ የተጨበጠ፣ የታተመ፣ በቀላሉ በኦንላይን ለማግኘት የሚቻል መረጃ የሚሰጥ ማዕከል የለንም።
ማዕከሉ በተጨማሪም ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ቁጭ ብለው ሊሠሩበት የሚችሉ በኮምፒውተር የተደራጁ ክፍሎች እንዲሁም መረጃዎችን በድምጽና በምስል አቀናብረው ሊጠቀሙባቸው በሚችሏቸው መሣሪያዎች የተደራጀ መሆን መቻል አለበት። እንዲህ ዓይነት ማዕከል መኖር ለእኛ ለኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን ለተቀናቃኝ አካላት ጭምር በቂና የተሟላ መረጃ በመስጠት የፕሮፖጋንዳ ሚዛንን ለማስጠበቅ የሚረዳ ነው።
ማዕከሉ ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ይሰበስባል፣ ያደራጃል፣ ለተጠቃሚዎች በሀርድ እና በሶፍት ኮፒ ያዘጋጃል። ሪሶርስ ሴንተሩ ቁልፍ ሚና የመረጃ ክፍተትን መሙላት ነው። ለተጠቃሚዎች በጽሁፍ የሚገኙ መረጃዎችን ከመያዝ በተጨማሪ በሶፍት ኮፒ የተዘጋጁ መረጃዎች የሚገኙበት መሆን አለበት። በተጨማሪም ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እና ተመራማሪዎች ቁጭ ብለው እንዲያነቡ፣ እንዲሠሩ የሚያስችል ኮምፒውተራይዝ የሆነ ቤተመጽሐፍትን ያካተተ መሆን አለበት። የሪሶርስ ሴንተር ውስጥ የሚገኙ መረጃዎች በኦንላይን እንዲቀመጡ በማድረግ መረጃዎችን ተጠቃሚዎች በቀላሉ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል። የሪሶርስ ሴንተሩ ሲከፈት ይህን ለማሟላት የሚያስችል የሰው ኃይልና የማቴሪያል አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል።
የማዕከሉ ዓላማ ምን ሊሆን ይችላል? በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በቂና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ መሆን፣ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን፣ ፎቶግራፎች፣ ፊልሞች፣ ወዘተ… በቀላሉ በኦንላይን እና በኦፍላይን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ፣ በተለይ ለጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ለዘርፉ ተመራማሪዎች ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረጉ መረጃዎችን
መሰብሰብና ማደራጀት፣ ማቅረብ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎችን ማድረግና የመሳሰሉትን ይሆናል።
በተጨማሪም የሪሶርስ ሴንተሩ ሳምንታዊ ሚዲያ መግለጫ የሚሰጥበት አሠራር ቢኖረው በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ይበልጥ ማገዝ ያስችላል። የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦችን እየጋበዙ የፕሬስ መግለጫ (Press briefing) መስጠት ቢቻል በዘርፉ የሚሠሩ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ እና መረጃ ለማስታጠቅ በብዙ መልኩ ያግዛል። ከምንም በላይ ደግሞ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የመንግሥት ወቅታዊ አቋም ምን እንደሆነ በግልጽ ለመረዳት ይረዳል። የተገኘውን መረጃም በየሥራዎቻቸው ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመጠቀም ተጨማሪ ስንቅ ይሆናል።
የሪሶርስ ሴንተሩ ተጠቃሚዎችን በመረጃ ከማበልፀግ ባለፈ ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ መረጃዎች በቋሚነት በማከማቸት ለትውልድ ማስተላለፍም የሩቅ ግቡ ማድረግ ይችላል።
ሁለተኛው የቴክኒክ ድጋፍ በዚህ ዘርፍ ጥሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ግለሰቦች በጥንቃቄ ተለይተው በቁሳቁስ መደገፍ ነው። እንደላኘቶኘ እና ታብሌት፣ አንድሮይድ ስልኮች፣ ካሜራ… የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በዘርፉ ለሚሠሩና ውጤታማነታቸው ለታመነባቸው ግለሰቦች በድጋፍ መልክ መስጠት ሥራውን ለማሳለጥ ትልቅ አቅምን ይፈጥራል።
የሥልጠና ጉዳይ ቋሚና ተከታታይ በሆነ መልኩ በዕቅድ ሊሠራበት የሚገባ ነው። አጫጭር ሥልጠናዎች በዘርፉ የሚሠሩ አካላትን ለማንቃት ትልቅ መሣሪዎች ናቸው። ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ከወቅቱ አስተሳሰብ ጋር እኩል እንዲራመዱ ሥልጠና ቁልፍ እገዛ ይኖረዋል። እናም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንንም ሊያስብበት ይገባል። የዚህ ሥልጠና ጉዳይ የሪሶርስ ሴንተሩ ኃላፊነት ይሁን ወይንስ ራሱን ችሎ ይሂድ የሚለው በአደረጃጀት ወቅት ሊታይ የሚችል በመሆኑ እዚህ ላይ የምሰጠው አስተያየት አይኖረኝም።
እንደማሳረጊያ
በቀጥታ ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ሀገር አቀፍ የሪሶርስ ሴንተር የማቋቋም ሀሳብ የሚሳካ ከሆነ ለዘርፉ ተዋንያን ትልቅ አቅም ይሆናል። የሪሶርስ ሴንተሩ በአካል ሄደው ለሚጎበኙት ብቻ ሳይሆን በአካል ለመሄድ ለማይችሉና በክልል ወይንም በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግዙፍ የመረጃ ምንጭ በመሆን ሊያገለግል ይችላል። ሌላው ቀርቶ በመንግሥታቸው ፕሮፖጋንዳ ብቻ የሰከሩትን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ሚዛን እንዲጠብቁ ሊረዳቸውም ይችላል።
በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰፊ ተደራሽነት ያላቸውን የሶሻል ሚዲያዎች በማደራጀት በአግባቡ በመጠቀም በተለይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ አስተማማኝ ዜናና መረጃዎችን ለመልቀቅ የሚያስችለው አቅም ወደመገንባት ቢያተኩር እንደሀገር ጠቃሚ ውጤት ማግኘት ይችላል። ዛሬ ዛሬ የዲፕሎማሲ ሥራ በጠንካራ ሚዲያ ካልታገዘ ውጤቱ ኢምንት ነው። እናም እንደፌስ ቡክ፣ ዩቲዩብ ያሉ የሶሻል ሚዲያ አማራጮችን አሟጥጦ ስለመጠቀም ማሰብ ተገቢ ነው። ከሕዝብ ግንኙነት ወሬዎች በዘለለ ትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥነምግባርን የተከተሉ ዘገባዎችን ማቅረብ ግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ሲጠቃለል መጣጥፌ በሁለት ምክረ ሀሳቦች ላይ ያረፈ ነው። አንዱና ዋናው ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ብቻ የሚሠራ ዘመናዊና የተደራጀ የሪሶርስ ሴንተር በማደራጀት መረጃ የመስጠት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ነጥብ በተለይ የውጭውን ማህበረሰብ ግብ ያደረገ በዓረብኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ጠንካራ የሶሻል ሚዲያ አውታር በመፍጠር ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ ድምጽ እንዲሆኑ ማብቃት ላይ በትጋት እንዲሠራ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
(ፍሬው አበበ)