አንዳንድ ሰዎች ለመዝናናት ወደ ሌሎች ከተሞች ሲወጡ በቅንጡ ቤት ወይም ሆቴል ማረፍን ይፈልጋሉ። ይህን ፍላጎት ለማስተናገድ የሚያስችሉ ውብና ቅንጡ ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ወዘተ ተፈጥረዋል። የሰው ልጅ ፍላጎት ማቆሚያ የለውም፤ ይህን ፍላጎት ለማስተናገድ ሲባል የማይገነባ ስላለመኖሩ የእስከ አሁኑ ግንባታዎች ያመለክታሉ።
የሰው ልጅ በመሬት ላይ መዝናኛዎቹ አላቆመም፤ በባህር ውስጥ በተሰሩ መዝናኛዎች መገልገል እንደ ጀማመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ህዋን መጎብኘት መጀመሩም ይታወቃል። ማን ያውቃል በዚያም ምቹ ማረፊያዎች ሊገነቡ ይችሉ ይሆናሉ።
በዛሬው እትማችን የሰው ልጅ ለመዝናኛ በሚል በመሬት ውስጥ የገነባቸውን የምድር ውስጥ መስህቦቹን እንመለከታለን። እነዚህ ቤቶች ዋሻና ተራራ በመቦርቦር አልፎም ተርፎ በውስጣቸው ሕንፃዎችን በመገንባት የተሰሩ ናቸው። ቤቶቹ በተለያየ ዓይነት ቅርፅ የተሰሩ ሲሆኑ፣ ለቱሪስት መዳረሻነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
ዶሙስ ሲቪታ
በጣልያን የሚገኘው የዶሙስ ሲቪታ ቤት የተገነባው በ14ኛው ክፍለዘመን ነው፤ በኢቱስካን ዋሻና ሐውልት አጠገብ ይገኛል። በአካባቢው የሚያማምሩ ቦታዎች አንድ ላይ ከመገኘታቸው ባሻገር የመሬት ውስጥ ቤቱ አራት ተደራራቢ ሕንፃ መሰል ነገሮች አሉት። ዋሻው 2600 ዓመት የሞላው ሲሆን የሮማን ክርስቲያኖች ቦታውን ከያዙ ሁለት ሺ ዓመት እንደሆነ ይገመታል።
ሂልሳይድ ሆም ቪላ
በተለየ ሁኔታ የተሰራው ይህ ቪላ ቫላስ የተገነባው በስዊዘርላንድ ቫልስ በሚገኝ ተራራ ስር ነው። የቤቱ ንድፍ የተሰራው በአርክቴክት ክርስቲያን ሙለር ሲሆን፣ በአካባቢውም የመዋኛ ስፍራ ይገኛል።
ዱን ሀውስ
ይህ ቤት በፍሎሪዳ ግዛት አትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ የተገነባ ነው። እያንዳንዳቸው 750 ጫማ ርዝመት ወይም 69 ነጥብ 7 ሜትር ስኩዌር ስፋት ያላቸው ቤቶችን ያካተተ ነው። ቤቶቹ እ.አ.አ 1975 በአርክቴክት ዊልያም ሞርጋን ለመዝናኛነት ታስበው የተገነቡ ናቸው። አርክቴክቱ መኖሪያውን እዚያው አካባቢ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ አዲስ የሰራው ቤት የባህር ዳርቻውን እንዳይከልለው በሚልም ቤቶቹ ተፈጥሯዊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለዚህ ደግሞ ሞርጋን ቤቶቹን በአሸዋ እንዲሸፈኑ በማድረግ ከሩቅ እንዳይታዩ አድርጓቸዋል።
አውትርያል ሀውስ
በሳር የተሸፈነውና ማጭድ ዓይነት ቅርፅ ያለው ይህ ቤት በአርክቴክት ፐሮምስ በፖላንድ ተራራ ጫፍ ውስጥ የተገነባ ነው። የቤቱ ቅርፅ ዘመናዊ የሚባል ባይሆንም፣ ቤቱን የጎበኙ ሰዎች በቤቱ አገነባብና በውስጡ በያዛቸው ቁሳቁስ ተደምመው ተመልሰዋል።
ቦልተን ኢኮ ሀውስ
በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ ይገኛል፤ ምንም ዓይነት የካርቦን ልቀት በሌለበት ስፍራ የተገነባው ይህ የቦልተን ኢኮ ሀውስ፣ «የቀጣይ ዘመን» ቤት በመባልም ይታወቃል። ቦልተን ኢኮ ሀውስ በዲዛይንና በግንባታ በኩልም እስካሁን የሚደርስበት አልተገኘም።
ዲቲኮን
ይህ አስደናቂ የመሬት ውስጥ ቤት የሚገኘው በስዊዘርላንድ ዲቲኮን ከተማ ሲሆን፣ ከተማዋ በትልቅነቷ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ነች። በዙሪክ ከተማ ውስጥም ዲልክተን በሚል የተሰየመ ጎዳናም ይገኛል።
ናሰ ሞንታንሀስ ዴ ፋፌ
በአስደናቂ ሁኔታ በድንጋይ የተሰራው ቤት ነው፤ በፖርቱጋል የሚገኘው ይህ ቤት፣ በድንጋይ በተሰራ ቤት ውስጥ መኖር እንደሚቻል እንደ ማሳያ ተደርጎም ተወስዷል። እንደ ማንኛውም ቤት በር፣ ጣሪያ እንዲሁም መስኮቶች አሉት። በቤቱ ጎን በኩል የሚገኙት ክፍት ቦታዎች በድሮ ታሪኮች ላይ ተፅፈው የሚገኙ የአኗኗር ሁኔታዎችን ያስታውሳሉ።
ሳላ ሲልቨርማይን
ሰፊ የሆነ አዳራሽ ያለው በስዊድን የሚገኘው የመሬት ውስጥ ቤት 155 ሜትር ርዝመት አለው። በውስጡም የስዕል ማሳያ ጋለሪ ይገኝበታል።
ቦች ኦፍ ኮኢጋች
ቦች ኦፍ ኮኢጋች በልዩ ንድፍ የተሰራ ነው፤ ይህ በመሆኑም የቅንጡዎች ምርጫ አድርጎታል። በስኮትላንድ አቺልቲቢዊ መንድር የሚገኘው ይህ ቤት፣ በጣም ጠንካራ በሆነ ድንጋይ ነው የተሰራው። ቤቱን የገነቡት ሰዎች ለእርሻ ሥራቸው እንዲመቻቸው አድርገው ነው ያስቀመጡት።
ባድ ብሉማኡ
ባድ ብሉማኡ ንድፉ የተሰራው ፍሬድሪች ሀንደርዋሰር በሚባል አርክቴክት ሲሆን፣ የተገነባውም ለሆቴል፣ ለመዝናኛ ስፍራ እንዲሁም ለተለያዩ የሥነ ጥበብ ማሳያዎች እንዲሆን ታስቦ ነው። ቦታው በኦስትርያ ውስጥ ይገኛል።
የቫርዲዛ የዋሻ ከተማ
ቫርዲዛ በደቡባዊ ጆርጂያ የሚገኝ የዋሻ ስፍራ ነው። በኢሩሽቲ ተራራማ አካባቢ፣ በምትካቫሪ ወንዝ በስተቀኝ በኩል ሰላሳ ኪሎሜትር ርቆ ይገኛል። ግንባታው የተከናወነው በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲሆን፣ 500 ሜትር ርዝመትና ዘጠኝ የውስጥ ደረጃዎችም አሉት።
ሆጋን
በጥንት ጊዜ እንደተገነባ የሚነገርለት ሆጋን «የደረቀ እንጨት» በሚል ስያሜም ይታወቃል። ይህ ጥንታዊ የመሬት ውስጥ ቤት፣ በውስጡ ሦስት ደረቅ እንጨቶች እንደ አካፋይ ሆነው ቆመዋል። በሌላ በኩል ግድግዳው በጭቃ መሰል ነገር የተቀባ ነው። የግማሽ ክብ ቅርፅ የሚመስል ንድፍ ያለው ይህ ቤት፣ ጣሪያው በቆሻሻ ቅጠሎች የተሞላ ነው።
ስካሮሞንቴ ዋሻ
ይህ የዋሻ ቤት በውስጡ የአትክልት ስፍራዎችን የያዘ ነው፤የተለያዩ ሦስት ክፍሎችም አሉት። ሁለቱ ክፍሎች ሁለት አልጋ የሚይዙ ሲሆን፣ አንዱ ግን አንድ አልጋ ብቻ የሚያዘረጋ ነው። ዋሻው በስፔን በስካርሞንቴ ከተማ እንብርት ላይ የሚገኘው ይህ ቤት፣ ከፍላሚንኮ፣ ላቫንታ ኢል ጋሎ፣ ኢል ካርማን ዴላ ኩቫስ፣ ላ ቡላርያና ኡሱላ ፍላሞንካ ማኖልቴ የሚባሉ መዝናኛዎች በዋሻው አካባቢ ይገኛሉ።
ካፓዶሲካ ዋሻ
ካፓዶሲካ በማዕከላዊ አናቶሎያ የሚገኝ ታሪካዊ ስፍራ ነው። አናቶሊያ በቱርክ ከሚገኙ ከተሞች አንዱ ሲሆን ስሙም በቀድሞ አካባቢውን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የክርስትና እምነት ተከታይ ንጉሶች እንደወጣ ይነገራል። የካፓዶሲካ የዋሻ ቤት በአሁኑ ወቅት በበርካታ ቱሪስቶች እየተጎበኘም ነው፤ በታሪካዊነቱም በቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
መርድ ክፍሉ