የመጠለያን ፍላጎት ማሟላት የዓለም መንግሥታት ራስ ምታት ነው። የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል እየተሞከረ ይገኛል። ምቹ የቤት ግንባታ ለማከናወን ከንድፍ ጀምሮ እስከ ግንባታው በርካታ ቁሳቁስ ያስፈልጋሉ። ቤቶች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ በሚልም በግንባታ ወቅት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያካትቱ እየተደረገም ይገኛል።
የኢንዶልቨን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመደባለቅ በቤት ውስጥ ሙቀት እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ማሳየት ችለዋል። ተማሪዎቹ በኔዘርላንድ በተካሄደው የንድፍ ሳምንት ላይ የቤቱን ሞዴል ሰርተው ለተመልካች አቅርበዋል።
የቡድኑ የቦርድ አባል ፍሬንስ «ከዘላቂ ልማት አንፃር አሁንም ለግንባታ ዘርፍ መሻሻል ብዙ ቦታ አለ» ብለዋል። «50% ጥሬ ዕቃዎቻችን ወደ ቤት ግንባታ ይሄዳሉ። 40 በመቶው ቆሻሻችን የሚመነጨው ከቤት ነው። 35 በመቶ የሚሆነው የካርቦን ልቀታችን የሚሄደውም ወደ ቤት ነው። ሆኖም ብዙ የቴክኖሎጂያዊ መፍትሔዎች ተገኝተዋል» ሲሉም ያብራራሉ። የተማሪዎቹ የፈጠራ ሥራ የኤሌክትሪክ እና የጋዝ ፍጆታን እና ቁሳቁስን እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ላይ ያተኮረ ነው።
የፀሐይ ፓነሎች እና የሙቀት ፓምፖች ተማሪዎች ለመስራት ያቀረቡት የቤቱ የመጀመሪያ ሞዴል እንደሚያሳየው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አንድ ላይ የተሰበሰቡ መሆናቸውን ነው። ቤቱ ሁለት የሙቀት ፓምፖች እና የፀሐይ ፓነሎች አሉት። የፀሐይ ፓነሎች በበጋ ወቅት በአንፃራዊ ሁኔታ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ። በዚህም ኃይል ወደ ተዘጋጀለት ማጠራቀሚያ እንዲገባ ይደረጋል። የፀሐይ ሙቀት ሲበዛ የፀሐይ መሰብሰቢያ ፓነሎች በጣም ሞቃት ይሆናሉ:: ይህ ደግሞ ውጤታማነቱን ዝቅ ያደርገዋል። ለዚህ ደግሞ ከፀሐይ ፓነሎች
ስር ቧንቧዎች እንዲገጠሙ ተደርጓል። ከቧንቧዎቹ በሚወጣው ውሃ የፀሐይ ፓነሎች ይቀዘቅዛሉ። የፀሐይ ፓነሎች በሚቀዘቅዙበት ወቅት ውሃው የሚሞቅ በመሆኑ የሞቀውን ውሃ በቤቱ ስር ባለው የውሃ ማጠራቀሚያ ውስጥ እንዲከማች ይደረጋል።
በክረምት ወቅት ቤቱን ለማሞቅ የተከማቸው ሙቀት ጥቅም ላይ ይውላል። ተማሪዎቹ ሙቀቱ ቤቶች ውስጥ እንዲከማች ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ የፀሐይ ፓነሎችን በመትከል በበጋ ወቅት ኃይል የሚያጠራቅሙ ከሆነ ሥራው ውጤታማ መሆን አይችልም።
ተማሪዎቹ የኃይል ማጠራቀሚያዎችን በጋራ በመጠቀም ለውሃ ማሞቂያ የሚወጣን ወጪ መቀነስ ላይ ትኩረት ለማድረግ አስበዋል። ብዙ ጎጂ የሚባሉ አሲዶች ከመሬት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አሲዶቹ ሊቲየምን ለማስወገድ ያገለግላሉ። በዚህ የኃይል ማጠራቀሚያ ባትሪዎችን ለመስራት እንደሚቻል ተማሪዎቹ ተናግረዋል። ነገር ግን ሁሉም ሰው የኃይል መሰብሰቢያ ባትሪ የሚተክል ከሆነ ባትሪው ቢፈነዳ አካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
በልዩ ግንባታ ሥራ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ክፍሎች ዘላቂነት ካለው ጉልበት በተጨማሪ ተማሪዎቹ ስለ መልሶ መጠቀሚያ ቁሳቁስ ሀሳብ አመንጭተዋል። ቤቶች ለብዙ ጊዜ ማለትም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እንዲያገለግሉ አድርጎ ለመገንባት ሃሳቦች አሉ። ይህ በተግባር ብዙውን ጊዜ ሲሰራበት አይታይም። ቤቶች ከተገነቡ ከአርባ ዓመታት በኋላ መልሶ ማደስ ይከሰታል። እንደ ተማሪዎቹ ሀሳብ ቤት በሚሰራበት ወቅት የውስጥ ግድግዳዎች ተንቀሳቃሽ
እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ይህ ግድግዳውን ሙሉ በሙሉ የማፍረስና በኋላም እንደገና የመገንባት አስፈላጊነትን ያስወግዳል። ምክንያቱም ግድግዳ ሲፈርስ በጣም ብዙ ቆሻሻ ስለሚኖረው ነው። የቤቱ የፊተኛው ገጽታ በተመሳሳይ መንገድ ሊተካ ይችላል።
ተማሪዎቹ የሰሩት የግንባታ ሞዴል ሲታይ የግንባታ ዕቃዎቹ የተጣበቁት በሙጫ ነው፤ ከዚያ በኋላ የተለያዩ ቁሳቁስ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉም አሳይተዋል። ተማሪዎቹ የቤት ግንባታ ሲከናወን እንደ ቀርከሃ ያሉ ዘላቂ ቁሳቁስ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው ብለው ያስባሉ። ቀርከሃ ጠንካራ እንጨቶችን የሚይዝ እና እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል ቀላል የሆነ በፍጥነት የሚበቅል ተክል በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ለቤት ግንባታ ተመራጭ እየሆነ ይገኛል።
የተማሪዎቹ የመጀመሪያ ቤት በሚቀጥለው ዓመት በኔዘርላንድ ውስጥ በሚገኘው በብሬዚፖርት ስማርት አውራጃ ብራድቨርት ውስጥ ይገነባል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ መንደር የሚመሰረት ሲሆን፣ መንደሩም የተለያዩ ቴክኒካዊ እና የፈጠራ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩበት ሰፈር እንደሚሆንም ይገመታል።
ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ለመኪኖች እና ለአውቶቡሶች የብቻ መንገዶችም ይሰራሉ። የአገሪቱ የቤቶች ኮርፖሬሽን የተሰሩትን ቤቶች በመግዛት እንደሚከራያቸው ይጠበቃል። ተማሪዎቹ በአሁኑ ጊዜ ባለው የቤቶች ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ቤቶችን ለመገንባት እያሰቡ ናቸው።
በኤግዚቢሽን መልክ እየቀረቡ ከሚገኙት የመኖሪያ ቤት ሞዴሎች መካከል በተማሪዎቹ ለመስራት የታሰበው ቤት አንዱ ነው። የተማሪዎቹ የቤት ንድፍ ሥራ ዘላቂነት ያለው ኑሮ ሲመጣ መኖሪያ ቤቶች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። በኤግዚቢሽኑ ላይ የፈጠራ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለበርካታ ግንባታ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል። ይህም ሰዎች ከግንባታው ዘርፍ የበለጠ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ይረዳል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
መርድ ክፍሉ