ከአዲስ አበባ በሰማንያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የሙከጡሪ ከተማ ተነስቶ በስተቀኝ በኩል በመታጠፍ እስከ ደቡብ ወሎ ድረስ የሚዘልቀው የመንገድ ፕሮጀክት አካል ነው። የሙከጡሪ ከተማን ጨምሮ ለሚንና ሌሎች የገጠር ቀበሌዎችን ያገናኛል። ወደ ደቡብ ወሎ የሚደረገውን ጉዞ በግማሽ በመቀነስ የተሳፋሪዎችን እንግልት ይቀንሳል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል- የሙከጡሪ አለም ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት።
በዩናይትድ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ አማካሪ ድርጅት የሙከጡሪ አለም ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት የኮንትራት አንድ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ወንድወሰን ክፈሌ እንደሚገልፁት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ባለቤትነት፣ በቻይናው ሬልዌይ ነምበር ስሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስራ ተቋራጭነትና በዩናይትድ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ አማካሪነት እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 2017 ነው በይፋ የተጀመረው።
ፕሮጀክቱ በ990 ቀናት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 2020 እንደሚጠናቀቅ ታሳቢ ተደርጎ ውል ተገብቶለት ስራው የተጀመረ ሲሆን፣በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ 64 ቀናት ተሰጥቶት ስራ ተቋራጩም ለመንገዱ መዘግየት ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄዎች አቅርቦ በባለቤቱና በአማካሪ ድርጅቱ በኩል እየታየ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ሲጀመር በ768 ሚሊዮን 622 ሺ 741 ብር ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበ ነው፤ ከሙከጡሪ
ከተማ እስከ ኮኮብ መስክ ድረስ 58 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ሁለት የወረዳ ከተሞችን /ሙከጡሪና ለሚን/ ያቋርጣል። መንገዱ በከተሞቹ ውስጥ 20 ነጥብ 5 እንዲሁም በቀበሌ ክልሎች ውስጥ 12 ሜትር ይሰፋል። ከከተማ ክልል ውጪ ደግሞ 7 ሜትር አስፓልትና በጥቅሉ 10 ሜትር ስፋት አለው።
እንደ ተቆጣጣሪ መሀንዲሱ ገለፃ፤በአሁኑ ወቅት የመንገድ ፕሮጀክቱ 45 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፣ከዚህ ውስጥ 17 ኪሎሜትር የሚሆነው መንገድ በአስፓልት ተሸፍኗል። የቤዝ ኮርስ የተፈጨ ጠጠር ወደ 15 ኪሎሜትር ያህል ተሸፍኗል። 20 ኪሎሜትር የሚሆን የሰብ ቤዝ ስራም ተጠናቋል። የአፈር ስራውም 73 ከመቶ አልቋል። በተጨማሪም የቦክስ ካልቨርት 13 መለስተኛ ድልድዮች ግንባታ ውስጥ ዘጠኙ ተጠናቀዋል። ከ 11 ስላቭ ድልድዮች ውስጥ ደግሞ ሶስቱ አልቀዋል። የቱቦ ቀበራም 59 በመቶ ተጠናቋል።
ፕሮጀክቱ ከዝግጅት አኳያ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚገጥማቸው የአፈርና የድንጋይ መፍጨት ችግር አልገጠመውም። የአፈር ስራዎቹም በጥሩ አፈፃፀም ላይም ይገኛሉ።
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ አጋጥመው የነበሩ ችግሮች አሁንም እንደሚታዩ ጠቅሰው፣የመንገድ ፕሮጀክቱ የሚያልፋባቸው አካባቢዎች በአብዛኛው የእርሻ ቦታዎች ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ለግንባታው ትክክለኛ የሆነ አፈር ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ችግሮቹን በጋራ በመፍታት ፕሮጀክቱን ለማፋጠን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታሉ።
የመንገድ ስራ ተቋራጩም በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት የሚፈልጋቸውን የአፈር ቦታዎች እንዲያገኝ መሰራትም ይኖርበታል ይላሉ። መንገዱ በሚያልፍባቸው በሙከጡሪና ለሚ ከተሞች የሚገኙ የውሃ፣ ኤሌክትሪክና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች መነሳት ይኖርባቸዋልም ይላሉ።
ተቆጣጣሪ መሃንዲሱ እንደሚሉት፤ቀደም ሲል ካለፈው በጀት አመት ታህሳስ ወር ጀምሮ በኮንትራክተሩ አቅም ማነስ የመንገድ ፕሮጀክቱ በእጅጉ የተዳከመና አፈፃፀሙም ወደ ኋላ የቀረ ቢሆንም ከጥር ወር በኋላ የተሻለ አፈፃፀም እያሳየ መጥቷል። ኮንትራክተሩ ያለበትን የመሳሪያ እጥረትም ሙሉ በሙሉ ፈቷል። የሰቤዝ ጠጠር ብዙ ጊዜ በቶሎ ይገኘ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሳይት ደረጃውን የሚያሟላ ጠጠር ባለመገኘቱ ኮንትራክተሩ ወደ ጠጠር ወደ መፍጨት ገብቷል። ይህም በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ላይ ለውጥ መጥቷል።
ከዚህ ውጪ ከድንጋይ መፍጨትና ከጠጠር ምርት ጋር በተያያዘ ያሉ ስራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከመሆናቸው አኳያ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሲታይ በአንድ አመት ውስጥ የመጠናቀቅ እድል ይኖረዋል። በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 64 ቀናት የተጨመረ ሲሆን፣ ተቋራጩ ከሚሰራቸው ተጨማሪ ስራዎች አኳያም የሚጨመሩ ቀናት ይኖራሉ።
ዲዛይን ሲሰራ እየተቆረጠ የሚጣል የአፈር ስራ አለ። ይህም አፈር ግማሹ መልሶ ስራ ላይ ሲውል ቀሪው ደግሞ ተቆርጦ እየተጣለ ሌላ ምርጥ ጠጠር እየመጣ እንዲሞላ ይደረጋል። ወደ ስራ ከተገባ በኋም የአፈር ቆረጣ ስራው
ለውጥ አሳይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአፈር ቆረጣ ስራው መጠን በመጨመሩ ኮንትራክተሩ በተጨማሪነት የጠየቀው ቀን እየታየ ይገኛል።
ተቆጣጣሪ መሃንዲሱ፤ፕሮጀክቱ አሁን ባለው አፈፃፀም ፍጥነት መሄድ ከቻለ በቀጣዩ በጀት ዓመት የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል ሲሉ ይጠቁማሉ። ይህንንም ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
እንደ ተቆጣጣሪ መሀንዲሱ ማብራሪያ ፤የመንገድ ፕሮጀክቱ ተከታይ አካል የሆኑ ሌሎች አራት መንገዶችም ያሉ ሲሆን ከነዚሁ መንገዶች ጋር ተዳምሮ ሲጠናቀቅ እስከደቡብ ወሎ ድረስ ይዘልቃል። በፊት በነበረው ሁኔታ በደቡብ ወሎ አካባቢ ያሉ ቦታዎች በደሴ በመዞር ስለሚኬድባቸው እስከ 550 ኪሎሜትር ይርቁ ነበር። ይሁንና አራቱም የመንገዱ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ 550 ኪሎሜትር ርዝማኔ ይፈጅ የነበረውን መንገድ በ280 ኪሎሜትር እንዲቀንስ ያደርገዋል። በዚህ መስመር የሚደረገውን የትራፊክ ፍሰት በይበልጥ ያሳልጣል ተብሎም ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኮንትራት አንድ የመንገድ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎቹ ፕሮጀክቶች የሚያልፉባቸው አካባቢዎች እህል አብቃይ በመሆናቸውና ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት የያዙ በመሆናቸው ገበያቸውን በእጅጉ ያሳድገዋል። ከዚህ ባለፈም ከፕሮጀክቱ በመቀጠል ያለው አካባቢ የማዕድን ሃብትና የቱሪስት መስህብ ያለበት በመሆኑ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
አስናቀ ፀጋዬ