ሰዎች ራስን የማዳን ትጋታቸው የህልውና ፍላጎት ይሰኛል። ህልውና በህይወት ከመቆየት እና አለመቆየት ጋር የተያያዘ ነው። ማንኛውም ሰው በግልፅ ራሱም ሆነ ሌላ ሰው ሊለየው ባይችልም፤ ህልውናው የሚነካበት ሁኔታ ካጋጠመው ህልውናውን የማረጋገጥ ፍላጎቱን ለማሳካት ይታትራል። ይህ ማለት ሰዎች እያወቁም ሆነ ሳያውቁ በደመነፍስም ቢሆን፤ በህይወታቸው ከሚመጣባቸው አደጋ ራሳቸውን ለማስመለጥ ሰማይ መቧጠጥ ካለባቸው ሰማይ እስከመቧጠጥ የደረሰ ጥረት ያደርጋሉ። ሰዎች ህይወታቸውን ከሚነጥቃቸው ወይም ህልው መሆናቸውን ከሚያስቆምባቸው ከጦርነት እና ከበሽታ እንዲሁም አሁን አሁን በእጅጉ በተለይ በኢትዮጵያ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ ከሆነው የመኪና አደጋ ለማምለጥ ይጠነቀቃሉ።
ችግሩ አንድ ሰው ብቻውን የሚያደርገው ጥንቃቄ ውጤቱን የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለማድረሱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በተቃራኒው ሆነ ብለው ባያስቡም የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በማሰብ የሌሎች ሰዎችን የህይወት ጉዞ የሚገቱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በሰዎች ህልውና ላይ አደጋ የሚጥሉ ብዙ ቢሆኑም ለጊዜው የራሳቸውን ጥቅም በማሰብ በቀጥታ መንገድ የሚዘጉትን እንጥቀስ።
የእግረኛ መንገድን ዘግተው በየአደባባዩ ንግድ የሚያካሂዱ ሰዎች፤ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን መንገደኛውን ጨምር ለመኪና አደጋ የሚያጋልጡበት ሁኔታ በስፋት ይታያል። እነዚህ ነጋዴዎች በመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸው ሳይሆኑ በራሳቸው ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚያጋጥማቸው ማሳደድ ከንግድ ተግባራቸው በላይ ጎልቶ ይታያል። እነዚህኞቹን ለጊዜው ‹‹የመኖር ህልውናቸው ‹ግድ› ብሎ ገፍቷቸው ነው›› ብለን እንለፋቸው። ለዛሬ በየአደባባዩ በግልፅ ላስቲክ ዘርግተው እየተንቀሳቀሱ የሚነግዱትን ሳይሆን፤ ከመንግሥት አካል ፈቃድ ያገኙ ነጋዴዎች ሱቅ ገንብተው የሚፈፅሙት የመንገድ መዝጋት ተግባርን እናንሳ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 አካባቢ አንዳንድ የጀሞ 3 የጋራ መኖሪያ ቤት ነዎሪዎች እንደገለፁት፤ ከሁለት ወር ወዲህ ‹‹ፈቃድ ተሰጥቶናል›› ያሉ ሰዎች በቆርቆሮ ታጥሮ ዓመታትን ባሳለፈው ቦታ ላይ አስፓልት ዳር መደዳውን ሱቅ ሠርተዋል። ሱቆቹ መሠራታቸው እና ሰዎች ሥራ ማግኘታቸው ባያስከፋም፤ በሱቆቹ እየተሸጠ ያለ የግንባታ ዕቃን ለማውረድ እና ለመጫን ሲባል የእግረኛ መንገድ ሙሉ ለሙሉ እየተዘጋ መዋሉ ግን፤ የነዋሪዎቹን ህይወት እያመሰቃቀለ እና በሥጋት ውስጥ እየጨመረ ነው። በዋናነት አሳሳቢው ጉዳይ ነዋሪዎችን ለመኪና አደጋ ማጋለጡ ነው። በመንገዱ በትልልቅ ተጎታች መኪናዎች ላይ ተጭኖ የሚመጣው ሲሚኒቶ እየቦነነ የመንገደኛውን ልብስ ከማቆሸሹም ባሻገር፤ እግረኞች አቧራውን ለመሸሽ ወደ መኪና መንገዱ መሐል ገብተው እንዲሄዱ እያሰገደዳቸው ‹‹መኪና ገጨኝ አልገጨኝ›› በሚል ጭንቀት መግቢያ እና መውጫ ማጣታቸው ከፍተኛ ጫና እየፈጠረባቸው ይገኛል።
ከሥጋት እና ከጭንቀት አልፈው ለመኪና አደጋ በመጋለጥ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑት ወይዘሮ ሂሩት ማሞ፤ ‹‹የቴዎድሮስ አደባባይ የልማት ተነሺዎች ነን። በጀሞ ቁጥር ሦስት የጋራ መኖሪያ ቤት ተሰጥቶን መኖር ከጀመርን አራት ዓመታትን አስቆጥረናል። የ13 ዓመት ልጅ አለችኝ። እርሷን የምንከባከበው እና የማሳድገው እኔ ነኝ። ›› ካሉ በኋላ፤ የእግረኛ መንገዱ መዘጋት የመኪና አደጋ ያደረሰባቸው መሆኑ በእርሳቸውም ሆነ በልጃቸው አዕምሮ ላይ ከፍተኛ የሥነልቦና ጫና መፍጠሩን ይገልፃሉ።
እንደወይዘሮ ሂሩት ገለፃ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካባቢው በባጃጅ፣ በጋሪ እና በጭነት መኪና በመጨናነቁ እግረኛ መንቀሳቀሻ አጥቷል። ወደ አካባቢው የሚገባው የተሽከርካሪ መንገድ ሳይቀር ተሳቢ መኪናዎች ለማጠምዘዣነት እየተጠቀሙበት መላወሻ ጠፍቷል። ሰኞ ሰኔ አንድ ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ እርሳቸው ላይም በዛው አካባቢ የመኪና አደጋ ደርሷል።
በዕለቱ በቅርብ ርቀት ያለውን ከባድ መኪና አልፈው ለመሻገር ሲያስቡ ‹‹አይቶኛል›› ብለው ገምተው ነበር። ሆኖም የከባድ መኪናው አሽከርካሪ ስላላያቸው መኪናውን ሲያዞር ሮጠው ለማምለጥ ቢጥሩም ቦታው ምቹ ባለመሆኑ በመኪናው ተገጭተው እግራቸው ይሰበራል። ሮጠው በተወሰነ መልኩ ማምለጣቸው
ጉዳቱን የቀነሰው ቢሆንም፤ ለሰባት ቀን ሆስፒታል ገብተው በእርሳቸው ላይ ከደረሰው የአካል ጉዳት ባሻገር በልጃቸው እና በእርሳቸው ላይ በብዙ መልኩ የደረሰው ጉዳት ግን ከፍተኛ መሆኑን ያብራራሉ።
‹‹ጊዜው መጥፎ ነው። የኮቪድ ወረርሽኝ በመኖሩ ኮቪድ ሳልመረመር ሕክምና ለማግኘት ተቸግሬ ነበር። ቫይረሱ እንደሌለብኝ ሲታወቅ ተገቢውን ሕክምና አግኝቻለሁ። ›› የሚሉት ወይዘሮ ሂሩት፤ አሁን ተመላላሽ ታካሚ መሆናቸውን እና መመላለሱ በራሱ አደጋ ያለው መሆኑን ይገልፃሉ። ሕክምናው ቶሎ አለመሰጠቱ፤ በዛ ላይ ለቤተሰቡ አውራ ሆነው ቤታቸውን ሲያስተዳድሩ የነበሩት እማወራ አልጋ ላይ መዋላቸው፤ ልጃቸው እና እርሳቸው ላይ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ ሂሩት ገለፃ፤ በሱቆቹ ምክንያት የውስጥ መንገዱ ሙሉ ለሙሉ እየተሸፈነ ነው። የወረዳ ደንብ አስከባሪዎች ጉዳዩን እየተከታተሉ ችግሩን እያቃለሉ አይደለም። አቅመ ደካሞች፣ ትልልቅ ሰዎች እና ነፍሰ ጡሮች፣ ደክሟቸው ሥራ ውለው ወደ ቤታቸው የሚያመሩ ሰዎች፣ ዕቃ የያዙ ሰዎች መተላለፊያ አጥተዋል። በአጋጣሚ አሽከርካሪዎች ካላዩዋቸው ከመኪና አደጋ የሚያመልጡበት ዕድል የለም።
ሱቆቹ ወደ ውስጥ መጠጋት ብቻ ሳይሆን፤ እንዲህ አይነት የእግረኛን መንገድ ሙሉ ለሙሉ የሚዘጉ ሱቆች መኖር የለባቸውም። መኖር ካለባቸውም መሐል ላይ ያሉ ክፍት ቦታዎች ላይ መሥራት ይችላሉ። አሁን ግን ወደ ሰበታ እና ፉሪ በሚወስድ ዋነኛ መንገድ ላይ የእግረኛውን ቦታ ይዘው ሲሚንቶ የሚጭኑ ጋሪ እና ባጃጆች፣ አይሱዚ እና ተጎታች መኪናዎች መላ ካልተበጀላቸው በእርሳቸው የደረሰው አደጋ በሌሎች ላይም የሚደርስ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
በዛው ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጀሞ ሦስት ገብርኤል ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ከስምንት ዓመት በላይ በአካባቢው የኖሩት አቶ አሰፋ … እንደሚናገሩት፤ ከዋናው የመስመር መንገድ ወደ ጋራ መኖሪያ ቤት የሚወስደው መንገድ የእግረኛ መንገድ ላይ የተለያዩ ሱቆች መሠራታቸው የጋራ መኖሪያ ቤቱ ነዋሪዎች ከትራንስፖርት በመውረድ ወደ ቤት በቀላሉ መግባት እንዳይችሉ አግዷቸዋል።
በሱቆቹ ሲሚንቶ እና የአርማታ ብረት እየሸጡ፤ እዛው መንገዱ ላይ ማራገፋቸው ለሽያጭ የቀረበውን የሚያደርሱ ጋሪዎች፣ ባጃጆች፣ አይሱዚዎች እንዲሁም የሚሸጠውን የሚያመጡ ትልልቅ ተሳቢ መኪናዎች በየቀኑ ያለዕረፍት የእግረኛውን መንገድ ዘግተው
ይውላሉ። ሲኖትራኮች ሳይቀሩ የእግረኛ መንገዱ ላይ ይወጣሉ። ስለዚህ እግረኛዎች መተላለፊያ ስለሚያጡ የሚቦነውን ሲሚንቶ በመሸሽ ወደ ተሽከርካሪ መንገድ በመግባት ለአደጋ በመጋለጥ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
‹‹ሰዎች ከታክሲም ሆነ ከአውቶብስ ከወረዱ በኋላ የሚቆሙበትም ሆነ የሚሄዱበት ቦታ እያጡ ነው። በመሐል ግራ ሲጋቡ በዋናው መንገድ ወደ ፉሪ የሚሄድ መኪና ሊገጫቸው ይችላል። ይሄ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ሲሆን ነዋሪዎችን ሥጋት ላይ ጥሏል። በተለይ ሰዎች ከኋላቸው በከፍተኛ ፍጥነት የሚመጣውን ተሽከርካሪ ለማምለጥ የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል›› በማለት፤ የችግሩን አሳሳቢነት ያብራራሉ።
እንደ አቶ አሰፋ ገለፃ፤ ሱቆቹ ከተሠሩ ገና ከ3 ወር ያላለፈ ጊዜን ቢያስቆጥሩም ሰዎች የህልውና ሥጋት ውስጥ ገብተዋል። አሁን ደግሞ ነዋሪዎች በተሽከርካሪ መገጨታቸው እየተነገረ ነው። በዓይን አይቶ መፍረድ ይቻላል። ‹‹ጋሪ ገፋኝ አልገፋኝ›› ብሎ እየተሳቀቀ የሚደናበር እግረኛ፤ ‹‹ከጋሪ አመለጥኩ›› ሲል ሳያስበው በፍጥነት በሚሽከረከር መኪና ይመታል። በዚሁ መልክ ከቀጠለ የበለጠ ብዙ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አያጠራጥርም። ስለዚህ ከወዲሁ መፍትሄ ማበጀት ይሻላል።
‹‹ሥራው ነዋሪው ላይ ችግር በማያስከትል መልኩ መሠራት አለበት። ቦታው እየተካሄደ ላለው አይነት ንግድ የሚሆን አይደለም። ምክንያቱም አካባቢው ከፍተኛ የመንገድ እንቅስቃሴ ያለበት እና ለዋናው መንገድ የቀረበ ነው። ነጋዴዎቹ ገባ ብለው ለማውረድ እና ለመጫን የሚያመች ቦታ ላይ መሥራት አለባቸው። ወረዳውም ሆነ ክፍለ ከተማው እንዲሁም የትኛውም የመንግሥት አካል ጉዳዩን በአካል አይቶ እና መርምሮ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል። ›› ብለዋል። በእነርሱ በኩል ከአካባቢው የነዋሪዎች ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ኮሚቴው ለወረዳው ሪፖርት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
የጀሞ 3 የአንድነት ኮንደሚኒየም ማህበር ሊቀመንበር አቶ ብሥራት ነጋሽ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚተው መሬት ለትምህርት ቤት፣ ለጤና ጣቢያ ወይም ለሌላ መሠረተ ልማት ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል። ጀሞ ሦስት ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መግቢያ አካባቢ በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቱ ሲሠራ ይኸው ቦታ የተተወው ለጤና ጣቢያ መሆኑ ተገልፆ ነበር። ጤና ጣቢያ በቅርብ የለም። አሁን ግን መሬቱ ለተለያዩ ግለሰቦች በጊዜያዊነት ይሁን በቋሚነት ለሱቅ ብቻ ሳይሆን ለመጋዘንም የተሰጠ ነው።
‹‹የእግረኛ መንገድ በመዘጋቱ ነዋሪው በጣም ተቸግሯል። አሁን እንደመጋዘን አድርገው ብዛት ያላቸው መኪናዎች ያለረፍት ይጭናሉ፤ ያወርዳሉ። ሰዎች መተላለፍ አልቻሉም። የበለጠ አደጋ ከመድረሱ በፊት ችግሩን መቅረፍ ቢቻል የተሻለ ነው። ›› በማለት የሚናገሩት አቶ ብሥራት፤ ቦታው ላይ የጭነት መኪና እስከነተሳቢው ቆሞ ሲሚንቶ ሲያራግፍ ትራፊኮች ቢያዩም የእግረኛ መንገድ ተዘጋ ብለው አይቀጡም። ነጋዴዎቹ የእግረኛ መንገድ ዘግተው የተሽከርካሪ መንገድ ድረስ ገብተው ሲጭኑ፤ ለሌላው ተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ የማይመች መሆኑን ለወረዳው በቃል ተገልፆ እንዲያስቆም ቢጠየቅም፤ ሰው እንደሌለ ተደርጎ መፍትሔ ማግኘት አለመቻሉ እጅግ ያሳዘናቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የጀሞ እና አካባቢው ወረዳ 01 ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዳነ ፊጣ እንደሚናገሩት፤ ሱቆች የተሰጡት ከእግረኛ መንገድ ውጭ ባለ ቦታ ላይ ነው። ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የንግድ አካባቢ ከሆነ ሱቅ መክፈት ይቻላል። ነገር ግን በሱቁ ሲሠራ ከፊት ለፊቱ የእግረኛ መንገድ ካለ እግረኛ መንገድ ላይ ማስቀመጥ እና መንገድ መዝጋት አይቻልም። ነጋዴው ዕቃ ካስቀመጠም በደንብ ቁጥር 54 መሠረት ክትትል ይደረጋል። አንዳንዴ መንገድ የሚዘጋ ነጋዴ አጋጥሞ ችግሩን ደንብ ማስከበር ካስተካከለው በኋላ መልሶ መንገድ የመዝጋት ሁኔታ ያጋጥማል። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ክትትል ይደረጋል።
የጀሞ ሦስትን ብቻ ሳይሆን ጀሞ ሁለትም የሲሚንቶ እና የህንፃ መሣሪያ መሸጫ ሱቆች ከቤታቸው ወጣ ብለው የእግረኛ መንገድን ሲዘጉ ይታያል። ከደንብ ማስከበር ጋር በመነጋገር ሁልጊዜ እርምጃ ይወሰዳል። ለተወሰነ ጊዜ ያስተካከላሉ፤ ሆኖም በድጋሚ መንገድ ይዘጋሉ። ስለዚህ አሁንም ጥቆማውን በመውሰድ ህዝብ ላይ ቅሬታ በፈጠሩት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ቦታው እንዲለቀቅ ይደረጋል በማለት፤ በቀጣይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ይገልፃሉ።
ሕብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን መንገዶች ባለሥልጣንም ‹‹ለእግረኛ የተሠራው መንገድ በሕገወጥ ነጋዴዎች እየተያዘ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ እና ለሚፈለገው ዓላማ እየዋለ አይደለም›› የሚል ቅሬታ እያቀረበ በመሆኑ፤ ከሠላምና ፀጥታ ሃይሎች፣ ከደንብ ማስከበር እና ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እርምጃ በመውሰድ ችግሩ ይፈታል በማለት፤ አቶ አዳነ በልበሙሉነት ችግሩ እንደማይቀጥል አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
ምህረት ሞገስ