የኢትዮጵያ የሲኒማ ታሪክ አንድ ብሎ የጀመረው ከዛሬ 123 ዓመት በፊት ነው። ይህ የዕድሜ ባለፀጋ ሲኒማ፣ አንድ ምዕተ ዓመት ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ልብ ማለት ይቻላል። ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሐፌ ተውኔት እንዲሁም የታሪክ ፀሐፊው ጳውሎስ ኞኞ፣ አፄ ምኒልክ በሚለው መጽሐፉ ላይ እንደሚያስነብበው፤ አፄ ምኒልክ አንድ ቀን ከአማካሪዎቻው ጋር ሲጨዋወቱ ስለሲኒማ ይሰማሉ። በሰሙት የሲኒማ ነገር ስለተደመሙ ሲኒማ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፈት አዘዙ። በዚህም መሠረት በ1889 ዓ.ም የሲኒማ ፕሮጀክተር ከነፊልሙ ከውጭ አገር መጣ። አፄ ምኒልክም መኳንቶቻቸውን ይዘው ሚያዝያ 1 ቀን 1889 ዓ.ም ፊልሙን ለመመልከት እልፍኝ ተገኙ።
በወቅቱ የታየው ፊልም የክርስቶስን ታሪክ የተመለከተ ነበር። ክርስቶስ በባህር ላይ እየተራመደ በእግሩ ሲሄድ በታየበት ጊዜ መኳንንቱ ሁሉ ተነስተው እጅ መንሳታቸውን ጳውሎስ በመጽሐፉ ይገልፃል። ፊልሙ ካለቀ በኋላ አፃ ምኒልክ ከራስ መኮንን ጋር በሚጫወቱበት ጊዜ ‹‹እነኚህ ፈረንጆች እኮ የማይሠሩት ነገር የለም። ሁሉንም ነገር ሲሠሩ የሰው ነፍስ ብቻ መሥራት አልቻሉም። ›› ብለው እንደነበርም ነው በመጽሐፉ የተገለፀው።
ቀጥሎም የመጀመሪያው የህዝብ ሲኒማ ቤት በ1890 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተከፈተ። ሲኒማ ቤቱን የከፈተው አንድ ከአልጀሪያ የመጣ ፈረንሳዊ ነው። ይህንኑ በዘመኑ የማይታመን ምትሐት መሰል ነገር የሚያየው ህዝብ፣ ሲኒማ ቤቱን ‹‹ሰይጣን ቤት›› ብሎ ሰየመው። በተለይ ቀሳውስቱ ህዝቡ ከሰይጣን ቤት እየሄደ ሰይጣን እንዳያይ እያሉ ስላወገዙ ሲኒማ ቤቱ ከሰረ። ባለቤቱም የሲኒማ ማሳያውን ዕቃ አዲስ አበባ ለነበረው የኢጣሊያ ሚኒስትር ለቺኮዲኮላ ሸጦ አገር ጥሎ ጠፋ።
የኢጣሊያ ሚኒስትርም ያንን ፕሮጀክተር ለአፄ ምኒልክ በስጦታ ሰጠ። አፄ ምኒልክም በቤተ መንግሥታቸው አዳራሽ ከመኳንቱና ከቀሳውስቱ ጋር መንፈሳዊ ፊልሞችን በማየት እንዲለመድ ካደረጉ በኋላ ገበያ እንደሚያገኝ እምነት ተጥሎበት በ1901 ዓ.ም ወንድማቾቹ እነ ቦይኮቢች ለህዝብ የሚሆን ሌላ ሲኒማ ቤት በምኒልክ አበረታችነት ከፈቱ። ይህ ሲኒማ ቤትም አንድ ዓመት ከሠራ በኋላ በፕሮጀክተር መበላሸት ምክንያት ተዘጋ።
በወቅቱ ይታይ በነበረው የሲኒማ ቴክኖሎጂ የተነሳ በሕዝቡ ዘንድ ‹‹ሰይጣን ቤት›› የሚል ስያሜ የተሰጠውና ከዓመታት በፊት ‹‹ሜጋ አምፊ ቴአትር ቤት›› እስከ ቅርብ ጊዜ ደግሞ ‹‹ዋፋ ሲኒማ›› በመባል የሚታወቀው ጥንታዊ ሲኒማ ቤት መሆኑ ይታወሳል። በምንጭነት በጳውሎስ ኞኞ የተጻፈውን አፄ ምኒልክ መጽሐፍ ተጠቅመናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
አስቴር ኤልያስ