የ13 ወራት ባለጸጋ የሆነችው ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም ለየት ከሚያደርጓት ወራት መካከል አንዷ የጳጉሜ ወር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያንም በየዓመቱ አምስት ቀናት እንዲሁም በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ስድስት ቀናት ያሏትን ወርሃ ጳጉሜን በተለያዩ ስያሜዎች ማክበር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም ጳጉሜ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ‹‹የነገ ቀን›› የሚል ስያሜን “የዛሬ ትጋት፤ ለነገ ትሩፋት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡
እኛም ይህንኑ ሃሳብ መሰረት በማድረግ በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የዲጂታል ዓለምን ለመቀላቀል የምታደርጋቸው ጥረቶችና ይህን ተከትሎ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች ለነገ ወይም ለመጪው ትውልድ ምን ያህል ትሩፋትና ተስፋ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቃኝተናል፡፡
አደጉና በለጸጉ የሚባሉት አገራት ወደ ተራቀቀ የቴክኖሎጂ ጥግ ለመድረስ በፍጥነት እየገሰገሱና እየተሽቀዳደሙ ባሉበት በዚህ ‹‹በዘመነ ዲጂታላይዜሽን›› ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ሁሉ መሠረታዊና አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል፡፡ እኛም በዚህ መጠን አስፈላጊነቱ እየጨመረ ከመጣው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጪ መሆን የማይታሰብበትና የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየደረስን እንገኛለን፡፡
ቀድመው የዲጂታሉን ዓለም እየመሩ ያሉት የበለጸጉት አገራት ዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳደጉ ከፍተኛ ሀብት እያከማቹ ይገኛሉ፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲህ የዓለም ከፍተኛ ሀብት እያንቀሳቀሰ ኢኮኖሚውን እየመራ ባለበት በዚህ ዘመን ከዚህ ሀብት አለመጠቀምና ከዲጂላይዜሽን እሳቤ ውጪ መሆን የማይታሰብ ነው፡፡ የማይታሰብ ብቻ ሳይሆን ዲጂታላይዜሽን ውስጥ ተሳታፊ መሆን አለመቻል በራሱ ከዓለም ወደኋላ ቀርቶ እንደመጓዝ ይቆጠራል።
በሌላ በኩል ዲጂታላይዜሽን ከመቀላቀል ጋር ተያይዘው የሚነሱ ስጋቶች አሉ፡፡ ስጋቶች ቢኖሩም ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› እንደሚባለው ሁሉ ቀድሞ ተዘጋጅቶ ስጋቶችን መመከት የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት ከዓለም ጋር አብሮ ወደፊት መጓዝ የግድ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዲጂታላይዜሽንን ማስፋፋት ተከትሎ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የዓለማችን ቀዳሚ ስጋት እየሆነ ቢመጣም ከቴክኖሎጂው ውጪ መሆንም ስለማይቻል በዚያው ልክ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡
መረጃዎች የሚያመላክቱትም ዲጂታላይዜሽን መስፋፋትን ተከትሎ የሳይበር ደህንነት ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃቶች የሚያስከትሉት ኪሳራ እየተበራከተ መምጣቱን ነው፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2023 ስምንት ትሪሊዮን ዶላር የሳይበር ጥቃት ኪሳራዎች የደረሱ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2025 ዐሥር ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ዲጂታላይዜሽንን በመቀላቀል ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ዓለም የደረሰበት ለመድረስ በፈጠነ ሁኔታ ወደፊት መጓዝ የሚያስችላቸውን አካሄድ በመከተል ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ ቀድመው በመረዳት ዲጅታላይዜሽንን በፍጥነት ተቀላቅለው ተግባራዊ እያደረጉ ካሉ አገራት መካካል ትመደባለች፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ዘርፉን ትኩረት ተሰጥቶት ከአምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንዱ ምሰሶ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያም 2025 ስትራቴጂ የዚሁ አንዱ አካል ነው፡፡
በቅርቡም የዲጂታል ኢትዮጵያ አስፈላጊነት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እንዲኖርና በሁሉም ተቋማት ተሰናስሎ እንዲመራ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ቀደም ሲል እንደሀገር የነበረው ችግር ለመወጣት በማሰብ ነው፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ወጣ ያለ አስተሳሰብና አሰራር በመከተል ዲጂታል ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ አስፈልጓል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህም ከዚህ ቀደም ሲል የነበረውን እሳቤና ልምምድ የሚቀይር ነው፡፡ ለአብነትም ቀደም ሲል አንድ ኩባንያ በሁሉም ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ቢሳተፍ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ለማግኘት ቢያንስ 20 ዓመታት ይፈጅበታል፡፡ በዲጂታል ኢንዱስትሪው ውስጥ ግን አብዛኞቹ ኩባንያዎች ቢሊዮን ዶላር በአራት ዓመት ውስጥ ያገኛሉ፡፡ ይህም አንደኛ በፍጥነት ገንዘብ ያስገኛል፡፡ ሁለተኛው በርካታ ሀብት ይገኝበታል፡፡ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ ሰፋ ያለ የሰው ሀብት ስላላት ይህንን ዘርፍ በተወሰነ ደረጃ መጠቀምና ዲጂታል ኢኮኖሚውን እንደ አንድ ምሰሶ ወስዶ መስራት ካልተቻለ የሚታሰበውን ማሳካትና የታለመውን ለውጥ ማረጋገጥ አይቻልም ከሚል እሳቤ በመነሳት ዲጂታል ዘርፍ ከኢኮኖሚ ዋና ዋና ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ እንዲሰራበት ተደርጓል፡፡
ይህ ዘመን ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባትን ይጠይቃል፡፡ በዓለም ላይ አሁን ካሉ አሥር ሀብታም ኩባንያዎች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ የያዙት በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ከዚህ የሚበልጠው ደግሞ ሰባተኛ፣ ስምንተኛ፣ ዘጠነኛና አስረኛ ደረጃ የያዙት ተራ ኩባንያዎች አይደሉም። ለምሳሌ እንደ ቴስላ፣ ቪዛ ካርድ እና ትልቁ የሳውድ አረቢያ የነዳጅ ኩባንያ ጨምሮ ከስድስቱ በታች ባሉ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ። እነዚህ አራቱ ኩባንያዎች ያከማቹት ሀብት ተደምሮ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙት ሁለቱ ኩባንያዎች ያከማቹትን ሀብት አያህልም፡፡ ይህ የሚያሳየው አብዛኛው ሀብት ያለው በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ለዚህ መንግሥትም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ዘርፍ አንድ መሠረት አድርጎ ወስዶ ዲጂታል 2025 ስትራቴጂም ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል። የዲጂታል ስትራቴጂው አንዱ አቅጣጫ ደግሞ የዲጂታል ምህዳሩን በማስፋት ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመፍጠር አካታች የሆነ ከባቢን መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መንግሥት ብቻ ተዋናይ ሆኖ መገኘቱ የሚገባውን ያህል ትርፍ ማግኘት አያስችልም፡፡ ስለዚህ አውዱን ማስፋት በዚህ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የግሉን ዘርፍ እንዲሳተፍ፣ ስታርትአፖችን እንዲስፋፋ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላው የአእምሮ ዝግጁነት /ማይንድ ሴት/ ሊኖር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ችግሮችን መደርደርና ጽዱ ሆኖ አለመገኘት እንደጥሩ ባህል የሚታይና የተለመደ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ይህ አሰራር በመቀየር ቢሮዎችና የሥራ አካባቢዎች ንጹሕ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህና መሰል ሳንካዎችን ተራምደን እንዳንሄድ ያሰሩን ነገሮች ካልተነቀሉ በስተቀር በዲጂታል ዘርፉ የሚጠበቀውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ መለወጥ ብቻ ሳይሆን በዚህ ረገድ አሁን ድረስ ሰፊ ሥራ መስራትን ይጠይቃል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ይህንንም ሲያስረዱ ኢትዮጵያ አምስተኛ ትውልድ የሞባይል ኔትዎርክ ኢንተርኔት 5ጂ ጥቅም ላይ ስታውል አብዛኛው ሰው እንደቅንጦት ሊያየው ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ለኢትዮጵያ በእጅጉ የሚያስፈልገን እና የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመቀላቀል የሚያስፈልጉ አስቻይ ሁኔታዎች አንዱ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሊኖሩ ከሚገባቸው አስቻይ ሁኔታዎች መካከል የመጀመሪያው ኢነርጂ ነው፡፡ ሁለተኛው ዳታ ሲሆን ሦስተኛው ዲጂታል መታወቂያ ነው፡፡ እነዚህ በእጅጉ የዲጂታልን ለመቀላቀል አጋዥ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ዲጂታሉን ዓለም ስንቀላቀል ስጋት የሆኑ ነገሮች ስላሉ እነዚያን ቀድሞ አውቆ ለዚያ ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ይሰነዘራሉ። ጥቃቱም እንዳለ ሆኖ ግን የመከላከል አቅሙም አብሮ እያደገ ሄዶ ሀብቶችን እንዳይጠፉ መከላከል እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በዲጂታሉ ዘርፍ ለምሳሌ ሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርተፊሻል ኢንተለጀንስ/ ወስደን አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ብንመለከት እኛ ዛሬ የምንሰራቸው መሰረቶች አሁኑ የሚታዩ አይደሉም፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት እኤአ በ2030 በዓለም አጠቃላይ ምርት /ጂዲፒ/ ላይ 16 በመቶ እድገት ያመጣል። ይህ ማለት ደግሞ ሰው ሰራሽ አስተውሎት 15 ትሪሊዮን ተጨማሪ ሀብት ያስገኛል፡፡ ይህን ሀብት የሚቀራመቱት ግን ጥቂት አገራት ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ አንጻር ያለው እሳቤ ልክ እንደ መኪናና አውሮፕላን ያሉ መገልገያዎችን ለማስገባት የነበረው ትግል መቀነስን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስለጉዳዩ የሚወያዩ፣ የሚያነቡ፣ የሚማሩ እና የሚሞክሩ ልጆች መፍጠር ሲቻል ከዚያ ትልቁ ሀብት ትንሽዬ ድርሻ ማግኘት ያስችላል በማለት አብራርተዋል፡፡
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስልን በበላይነት የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአንድ ወቅት የዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባት ለሀገር ልማት የሚያመጣውን ቱሩፋት አስመልክተው ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በሁሉም ዘርፎች ላይ የቴክኖሎጂ አስፈላጊነት እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር እጅግ የተሳሰሩ የቴክኖሎጂ አማራጮች እንዳሉ ሆነው አጠቃላይ አገራዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የኢኮኖሚ ዘርፍ በብዛት እንዲኖር አድርጓል፡፡ በዲጂታል ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን እያሳደጉ የሥራ እድልን እንዲፈጥሩ አስችሏል።
‹‹ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማሳደግ የመንግሥትን አገልግሎት ለማሳለጥ፣ ለማህበራዊ ተሳትፎ መጎልበት እና የስራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለታዳጊ አገሮች ከድህነት ለመውጣት ኢኮኖሚን ለመገንባት ዘርፉ ትልቅ ኢኮኖሚ አመንጪ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ትልቁ ፈተና የመንግሥት አገልግሎቶች አሰጣጥ ግልጸኝነት የጎደላቸው፣ ተደራሽ ያልሆኑ እና ብዙ ችግሮች ያሉባቸው መሆናቸው ነው።
በመሆኑም ታዳጊ አገራት ቴክኖሎጂ እንደ ትልቅ መሳሪያ የሚጠቀሙት አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ካሏት አስቻይ ሁኔታዎች መካከል አንደኛው በሕዝብ ብዛቷ የምትታወቅና ከዚህም ሕዝብ አብዛኛው ወጣት መሆኑ ነው። ወጣቱ ለቴክኖሎጂ ያለው መሰጠት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከአምስቱ (ከግብርና፣ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከቱሪዝም እና ከማዕድን) ዘርፎች ቀጥሎ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እንደ አንዱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው፡፡ ይህም መሆኑ ኢኮኖሚን በማመንጨት የመንግሥት አገልግሎትን በማዘመን፣ ለብዙ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል፡፡
ሦስተኛው የመሠረተ ልማት እድገት ሲሆን መሠረተ ልማት በዳታ ተደራሽነትም ሆነ ከሌሎች አንጻር ሲታይ እያደገ መጥቷል፤ መንግሥት በፕራይቬታይዜሽን በሰጠው እድል መሠረት ሳፋሪኮም የተሰኘው ኦፕሬተር ወደ ሀገሪቱ ገብቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። ተጨማሪ ኦፕሬተሮች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከመሠረተ ልማት አኳያም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የማልማት ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ መሰረተ ልማቱም በተሻለ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ አንጻር ሲታይ ዲጂታል ኢትዮጵያን በማሳደግ የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ፣ አገልግሎቶችን ማቀላጠፍ እንደሚቻል አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል 2025 ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ቀርጻ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ በ2025 በአጠቃላይ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ እያሳደገች ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ መውጫ
በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ እውን የማድረጉ ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዲጂታላይዜሽንን ማስፋፋትና ማሳለጥ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችም እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን ወደ ዲጂታል መቀየር፣ የክፍያ ሥርዓቶችን በኤሌክትሮኒክስ እንዲሆኑ ማስቻል እና ለዲጂታል ሥራዎች አጋዥ የሆኑ መተግበሪያዎች በልጸገው ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን ይጠቀሳሉ፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጂን እውን የማድረጉን ሂደት በቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ፣ በሲስተሞች ልማት፣ በአስቻይ ምህዳር ፈጠራ እና በሰው ሀብት ልማት ረገድ የዲጅታል ኢትዮጵያ ጉዞ መደላድል የሚሆኑ ሥራዎችን በመስራት የሚታዩ ለውጦች እየመጡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
መንግስት ይህን ለውጥ ለማስቀጠል አሁንም መስራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ወጣቶች በዘርፉ ያላቸውን ሚና በመረዳት መንግስት የተለያዩ ተግባሮችን እያከናወነ ሲሆን፣ አምስት ሚሊየን ወጣቶች በኮዲንግ ስልጠና እንዲከታተሉ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መንግስት ጋር ያደረገው ስምምነትና እሱን ተከትሎ መስጠት የጀመረው ስልጠናም ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል፡፡
‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ›› ጸድቆ ተግባራዊ ከተደረገ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም የዲጂታል ቴክኖሎጂን ተደራሽነትን በማስፋፋት ረገድ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ በተለይ የዲጂታል ፋይናንስን በማሳደግ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ገና በጅማሮ ላይ ያለ እንደመሆኑ፣ የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች ያሉበት ቢሆንም ዲጂታል ሥርዓትን በማስፋት በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትና የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆኑ መደረጉ ለውጦች እንዲመጡ ውጤቶች እንዲመዘገብ ያስቻሉ ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለሙያዎችም ይመሰክራሉ፡፡ ይህም ጤናማ የዲጂታል ፋይናንስ በማስፈን ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን መሆን መሠረት የሚጥል በመሆኑ ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መውጣት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም