ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት በውጤትና በስኬት

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ቀደምት ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የራሷ ባሕል፣ ወግ፣ ልምድ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ባሕል እና የዘመን አቆጣጠር ያላት የተለየች ሀገር ናት። በተለይም በዘመን አቆጣጠሯ ለየት ባለው የ13 ወር ጸጋዋ ትታወቃለች። ይህም የክረምት የበጋ ባለጸጋዋን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብሎም በዓለም ካሉ ሀገራት በሙሉ ልዩ ያደርጋታል።

የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆነችው 13ኛዋ ወርሃ ጳጉሜን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ስድስት ቀናት ሲኖራት ከዛው ውጭ ግን አምስት ቀናት ያሏት ትንሿ ወር ናት። የክረምቱን መጠናቀቅ አብሳሪ ለአዲሱ ዓመት መግባት ደግሞ ድልድይ የሆነችው ጳጉሜን በተለያዩ ስያሜዎች ተቀብሎ ማክበር ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዘንድሮም አሮጌው ዓመት አልፎ ወደ አዲሱ ዓመት የምታሸጋግረን ወርሃ ጳጉሜን ተራዋን ጠብቃ መጥታለች። ታዲያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች ተወክለዋል።

በዚሁ መሠረት ጳጉሜን አንድ የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች”፣ ጳጉሜን ሁለት፣ የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት”፣ ጳጉሜን ሶስት የሉዓላዊነት ቀን “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት”፣ ጳጉሜን አራት የኅብር ቀን “ኅብራችን ለሰላማችን”፣ ጳጉሜን አምስት የነገ ቀን “የዛሬ ትጋት፤ ለነገ ትሩፋት” በሚሉ ስያሜዎች አምስቱ የጳጉሜን ቀናት ተሰይመዋል።

በመሆኑም ዛሬ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ሃሳብ ቀኑ ሲታሰብ ትኩረታችን በለውጡ መንግሥት በስኬትና በውጤት የተከናወኑ ተግባራትን በመዳሰስ ይሆናል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ግንኙነትና በማኅበራዊ ጉዳዮች መጠነ ሰፊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በገቡት ቃል መሠረት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። በሪፎርም ሥራዎቻቸው መሠረትም በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ ዘርፍ መሻሻሎችና አዳዲስ ለውጦች ተመዝግበዋል። በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ሰው ተኮር የሆኑ ሥራዎችን ሰርተው በማሰራት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ሰው ተኮር ከሆኑ ሥራዎቻቸው መካከልም ማዕድ ማጋራትና የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ማደስ ተጠቃሽ ናቸው።

ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለሕዝቡ እንካችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ያዘመሙ የአቅመ ደካማ እናቶችን ጎጆ በማቅናት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰርተው አሰርተዋል። በዚህም ጥቂት የማይባሉ አቅመ ደካማ እናቶችም ካቀረቀሩበት ቀና ብለው በብዙ ተስፋ ተሞልተዋል። በእርሳቸው ተነሳሽነት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። በመሆኑም የሀገሪቷ ዋና ከተማ ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ አልፎ በክልል ከተሞች ጭምር ባሕል ሆኖ መቀጠል የቻለ ተግባር ነው።

ኢትዮጵያ በበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች እየተፈተነች የመጣችና አሁንም በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈች ቢሆንም፤ በመንግሥት መሪነት ከፈተናዎቿ ጋር እየታገለች ትርጉም ያለውና ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን እየሰራች ትገኛለች። ለዚህም መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ሲወስድ ሕዝቡም የላቀ ድርሻ አለው። ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ሆነው ትርጉም ያለው ሥራ እየሰሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በተለይም የአቅመ ደካማ እናቶችን ቤት የማደስ ሥራን በቋሚነት በመያዝ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያዘመሙ ጎጆዎችን በአዲስ ቀይረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነሳሽነት የተጀመረው በጎ ተግባርና አገልግሎት በሌሎችም ተጋብቶ በተለይም ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ የግል ባለሀብቶችን እንዲሁም ተቋማትን ጭምር በማስተባበር ማዕድ በማጋራትና የአቅመ ደካማ ዜጎችን ደሳሳ ጎጆ በማቅናት ትርጉም ያለው ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በኑሮ ውድነትና በቤት እጦት የሚሰቃየውን ሕዝብ በሚችለው ሁሉ ለማገልገል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በጥረቱም የሕዝቡን ተስፋ በማለምለም በርካታ የልማት ሥራዎችን በውጤትና በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል።

መንግሥት ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ጥቂት ወራት ውስጥ ጀምሮ በስኬት ካጠናቀቃቸው የልማት ሥራዎች አንዱ የኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ነው። በኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ የማድረግ ራዕይን ሰንቆ በርካታ አገልግሎቶችን ለሕዝቡ በማቅረብ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። ለከተማዋ ውበትን በማጎናጸፍ እውነትም ‹‹አዲስ አበባ›› ያስባለው ይህ የኮሪደር ልማት አንዱና ዋነኛው ለሕዝብ የተሰጠ አገልግሎት ነው። መንግሥት በኮሪደር ልማት እየሰራ ያለው ሥራ ለትውልድ የሚተርፍ ዘመን ተሻጋሪና ድንቅ ሥራ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ከቢሮ እስከ ከተማ አለፍ ሲልም እስከ ሀገር በሚል መርህ ኢትዮጵያን መቀየርና ገጽታዋን ማሳደግ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተጀመረ የመንግሥት ዋንኛ ተግባር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር የመምራት ኃላፊነታቸውን እንደተረከቡ ቅድሚያ የሰጡት ታሪካዊውን ጽሕፈት ቤታቸውን መቀየር ሲሆን፤ ከዛም በገበታ ለሸገር በሚል ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን ያስዋቡ ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን ገሃድ አውጥተዋል። ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ በሚል ሀገራዊ ገጽታን በያዙ ፕሮጀክቶችም እንዲሁ አዲስ አበባን ማስዋብ ሥራ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

የኢትዮጵያን ገጽታ ማየት የሚቻልባት አዲስ አበባ ክብርና ሞገሷ ሞልቶ ለኢትዮጵያ ተምሳሌት እንድትሆን፤ በኮሪደር ልማት ገጽታዋ እንዲዋብና በዚህ እሳቤም ስሟ ግብሯን እንዲመጥን ታጭታ ተሞሽራለች። ለዚህም በከተማዋ በተመረጡ አምስት የኮሪደር መስመሮች የልማት ሥራው በስኬት ተጠናቅቋል። ከሶስት እስከ አራት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰራው ሥራም ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ ማድረግ የቻለና ብዙዎችን ያስደመመ ነበር። ታጭታ ለተሞሸረችው አዲስ አበባ ድል ያለ ድግስ የደገሱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ነዋሪዎቿም የነበራቸው አበርክቶ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በከተማዋ በመጀመሪያው ዙር ለተከናወነው የኮሪደር ልማት ስኬቶች አስተዋጽኦ ላደረጉና ለተሳተፉ አካላት ዕውቅና ሰጥተዋል። ታጭታ ለተሞሸረችው አዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስኬት የተጉና የተሳተፉ አካላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕውቅናን አግኝተዋል። ዕውቅና ካገኙት መካከልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የኮሪደር ልማቱ አስተባባሪዎች ይገኙበታል።

በኮሪደር ልማቱ ስኬት ተሳትፎ የነበራቸውና ዕውቅና የተቸራቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ካለፈው ትምህርት ወስደው በቀጣይም የበለጠ ማገልገልና ስኬት ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የኮሪደር ልማት እሳቤ ሕዝብን ለመጪው ዘመን ማዘጋጀትና መጪውን ዘመን ለሕዝብ ማዘጋጀት እንደሆነ ነው የተናገሩት። እሳቸው እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማት ዋነኛ ዓላማና እሳቤ ሕዝቡን ለመጪው ዘመን ማዘጋጀትና መጪውን ዘመን ለሕዝቡ ማዘጋጀት ነው። አሁን ያለው ሕዝብ ለመጪው ዘመን መዘጋጀት አለበት። መጪው ዘመንም ከተሜነት የተስፋፋበት፣ ቴክኖሎጂ ያደገበት፣ የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሥራ ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ከነበረበት ከባቢ ወጥቶ በሚሄድበት ከባቢ አዳዲስ ነገሮችን እያየና ከተፈጥሮ ጋር እየተስማማ ማረፍ ቢያስፈልገው እያረፈ በሰው ልጅ ክብር ልክ እየተጸዳዳ የሚንቀሳቀስበትን ከተማና ከባቢ መፍጠር የመጪው ዘመን ትልም ነው።

ያ ትልም ለዚያ የሚመጥን ሰዎችን አብሮ ማዘጋጀት ይፈልጋል። የእግረኛ መንገድን ለይቶ መጓዝ የሚችል፣ መኪኖች ለሰው ልጅ ቅድሚያ የሚሰጡ፣ ለእግረኛ ቅድሚያ የሚሰጡ፣ ሥርዓትና ሕግ የሚያከብሩ እንዲሆኑ አድርጎ መቅረጽ፣ ውኃን ዛፍን፣ ንጹሕ ከባቢን በከተማችን ማየት መጠበቅ የሚያስችል ባሕል መገንባት ያስፈልጋል። የኮሪደር ልማቱ ከዚህ አንጻር የእሳቤው መሠረት ሕዝቡን ለመጪው ዘመን ማዘጋጀት፤ ዘመንን ደግሞ ለሕዝብ ማዘጋጀት ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ በምርጫ እምነት አሳድሮ ይሁንታውን የሰጠው አስተዳደር ከተማዋን የማልማትና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ኃላፊነቱን ከዚህም በላይ በመወጣት መሥራትና ሕዝቡን ማገልገል እንዳለበት አሳስበዋል። ‹‹ሕዝቡ መንግሥትን አምኖ ለሰጠው ይሁንታ አሁን የተደረገው አገልግሎትና የተሰራው የኮሪደር ልማት ሥራ ያንስበት ከሆነ እንጂ አይበዛበትም›› በማለት መንግሥት ሕዝቡን ለማገልገል በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በስኬትና በውጤት ተጠናቅቆ ለነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ ባለበት በዚህ ወቅት ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት መጀመሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብስረዋል። አጠቃላይ የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት አሀዛዊ መረጃን በሚመለከት ከፒያሳ ዓድዋ ድልድይ ተነስቶ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወስደው የመንገድ ኮሪደር ልማት አጠቃላይ ከ48 ኪሎ ሜትር በላይ የተሽከርካሪ መንገድ፣ 96 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 100 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፣ አራት የመሬት ውስጥ እግረኞች መንገድና አጠቃላይ ከ240 ኪሎ ሜትር የመንገድ መሠረተ ልማቶች ተሰርተዋል።

ከዚሁ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዘው የተሰሩ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎችንና የመዝናኛ አማራጮችም እንዲሁ በተለያዩ አካባቢዎች ተሰርተው ለነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። አጠቃላይ መዲናዋ በኮሪደር ልማቱ 32 የውሃ ፏፏቴዎች ወይም ደግሞ ፋውንቴኖች፣ የተቀናጀ የወንዝ ልማት እየተከናወነባቸው ያሉ ስምንት ወንዞች፣ 120 የሚደርሱ የመንገድ ዳር መጸዳጃዎች እና አጠቃላይ 70 የሚደርሱ የሕዝብ መናፈሻ ሥፍራዎች አግኝታለች። ከእነዚህ በተጨማሪም ለከተማዋ ድምቀት የሆኑ ዘመናዊና የደህንነት ካሜራ የተገጠመላቸው የኤሌክትሪክ መስመሮች ጭምር ተዘርግተውላታል።

ከተማዋ በአሁን ወቅት የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት አጠናቅቃ ወደ ሁለተኛው ዙር የተሸጋገረች ሲሆን፤ ከመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ልምድና ዕውቀት በመቅሰም የተሻለ ሥራ መሰራት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አንደኛው መነሻውን ካዛንቺስ አካባቢ በማድረግ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ፣ አቧሬ፣ መስቀል አደባባይ ሜክሲኮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚመለስ ይሆናል። ይህ የኮሪደር ልማት ሥራ ቀደም ሲል ከተሰራው የኮሪደር ልማት ሥራ ጋር እንዲናበብ በማድረግ ተጨማሪ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን የሚያከናውን እንደሆነ መረጃው ያመላክታል።

ሁለተኛው ከሳወዝጌት- መገናኛ፣ ከመገናኛ-መስቀል አደባባይ ሲሆን ሶስተኛው ከጣልያን ኤምባሲ ጀምሮ፣ ግንፍሌ፣ ቀበናንና አቧሬን የሚያካትት የወንዝ ዳርቻ ልማት ይሆናል። አራተኛው ከአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር- ጎሮ የሚደርስ ነው። ሌላው ከአራት ኪሎ በሽሮሜዳ እንጦጦ – ጉለሌ እጽዋት ማዕከል የሚደርስ ይሆናል። አጠቃላይ እነዚህን የኮሪደር ልማቶች ከመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ጋር የሚተሳሰሩ ሲሆን ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከፍ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የመጀመሪያውን የኮሪደር ልማት በስኬትና በውጤት እንዳጠናቀቁ ሁሉ ሁለተኛውን ምዕራፍም እንዲሁ በስኬትና በውጤት እንደሚያጠናቅቁ ይጠበቃል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያውያን ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ ያለው በአንድነት፣ አብሮነትና በመተሳሰብ እንደመሆኑ አዲሱ ዓመትም አንዳችን ለአንዳችን ደጀን የምንሆንበት፣ አንዳችን ሌላውን የምናገለግልበት፣ የምንከባበርበትና የምንደማመጥበት የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን እየተመኘን በዚሁ አበቃን ሰላም!

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You