በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ተወልዳ ያደገችው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አባድር ኢንስቲትዩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ፓስተር አካባቢ በሚገኘው አሜሪካን ሚሽን ትምህርት ቤት ተከታትላለች።
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ቀጥላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ካምፓስ /አራት ኪሎ ግቢ/ በስታትስቲክ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቋን ትገልጻለች። የዕለቱ የስኬት ገጽ እንግዳችን ወይዘሮ አዲላ እስማኤል የአዲላስ ማኑፋክቸሪንግ መስራችና ባለቤት ናት።
ሥራ ወዳድ፣ ታታሪና አዲስ ነገር የመፍጠር ውስጣዊ ፍላጎት ያላት አዲላ፤ ከወላጅ እናቷ የተማረችውን የእጅ ሥራ ትጠበብበታለች። ክርን ከኪሮሽ በማዋደድ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የእጅ ሥራዎችን መስራት ከልጅነት እስከ ዕውቀት አብሯት የኖረ ሙያዋ አርጋዋለች። የእጅ ሥራ ሙያዋን የበለጠ ያዳበረችው ደግሞ ወደ ትዳር በገባችበት አጋጣሚ ነው።
ሴት ልጅ በቶሎ ትዳር መያዝ አንዳለባት ጽኑ ዕምነት ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ የተገኘችው አዲላ፤ ትምህርቷን ባጠናቀቀች በሳምንቱ የትዳሩን ዓለም መቀላቀሏንም ታስታውሳለች። ‹‹በወቅቱ ገና ልጅ በመሆኔ ወደ ትዳር መግባቱን ብዙ ባልወደውም ወላጅ የሚለውን መቀበል ደግሞ የግድ በመሆኑ አሜን ብዬ ተቀብያለሁ። ያም ቢሆን ታድያ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ወላጆቼ የሚጠቅመኝን እንዳደረጉልኝና በትልቁም እንደዋሉልኝ ተረድቻለሁ፤ ስለዚህ ወላጆቼን ሁልጊዜም አመሰግናቸዋለሁ›› ትላለች። ገና በለጋ ዕድሜዋ የጀመረችው ትዳር በልጆች ተባርኮ ዛሬ ላይ እኩዮቿን ማድረስ መቻሏንም ትናገራለች።
በትዳር ዓለም ልጅ ወልዶ በማሳደግ ሂደት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ ታሳልፍ የነበረችው ወይዘሮ አዲላ፤ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን በቤት ውስጥ ትሰራ ነበር። ከወላጅ እናቷ የተማረችውን የእጅ ሥራ በተለይም የኪሮሽ ሥራን በመስራት ውጤታማ መሆን ችላለች። የተለያዩ ዲዛይኖችን በማዘጋጀት ውስጣዊ ፍላጎቷና የነብሷ ጥሪ የሆነውን የእጅ ሥራ ልጆቿን ከማሳደግ ጎን ለጎን ደስ እያላት ከውስጥ በመነጨ ፍቅር ስትሰራ ቆይታለች።
ታታሪ፣ ሥራ ወዳድና ብርቱዋ አዲላ፤ በቤት ውስጥ ደስ እያላት እንደቀልድ የምትሰራቸው የእጅ ሥራዎች በብዙዎች ዘንድ ይወደዱላትም እንደነበር ታስታውሳለች። አንድ ሁለት እያለች ቀስ በቀስ የምትሰራቸው የእጅ ስራዎች ልጆች ከማሳደግ ጋር አንድ ላይ ተደምረው የሙሉ ጊዜ ሰራተኛ ቢያርደርጓትም ደስተኛ ነበረች። የእጅ ሥራዎቿ ከልጆቿ እኩል እየተወለዱና እያደጉ ቤቷን መሙላት ጀመሩ። ይህን ጊዜ ወይዘሮ አዲላ፤ ከልጆቿ እኩል እያሳደገች ያመጣችውን የእጅ ሥራ ወደ ገበያ ማውጣት እንዳለበት በማመን እንቅስቃሴ ጀመረች።
የእጅ ሥራዎቿ ገበያ ላይ ይወጣሉ ብላ ሳታስብ ውስጣዊ ፍላጎቷን በማዳመጥ የፈጠራ ችሎታዋን በሥራ ያሳየችው አዲላ፤ ከዓመታት በኋላ ቤት ውስጥ የተከማቹትን የእጅ ስራዎች ወደ ገበያ ይዛ ወጥታለች። በወቅቱ ገበያ ላይ ስታቀርበው በዙሪያዋ የነበሩ ሰዎች ከሚያደንቁት በብዙ እጥፍ ብዙዎች የእጅ ሥራዎቿን አድንቀው ሲደነቁ አስተውላለች። ክርና ኪሮሽን አስማምታ ከሰራቻቸው የእጅ ሥራዎች መካከልም የልጆችና የአዋቂ ቦርሳ፣ ሹራብ፣ ቀሚስ፣ የአንገት ልብስ፣ ካልሲ፣ ኮፍያ ይገኙበታል። ከአልባሳቱ በተጨማሪም የእጅና የእግር ብራስሌቶችን በክርና በጨሌ ትሰራለች።
እነዚህን ምርቶች ማኅበረሰቡ ዘንድ ለማድረስና ስራውን ወደ ቢዝነስ መቀየርን ስታስብ መሸጫ ሱቅ መከራየት የግድ ነውና መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ያመረተችውን በክራይ ሱቅ ለገበያ በማቅረብ ብዙዎች ዘንድ መድረስ ችላለች። በወቅቱ ብዙዎች ሥራዋን ወደው ሲገዙላት የበለጠ ትበረታታለች። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኋላ የሚጎትቷት በርካታ ደንቃራዎች ይገጥሟት እንደነበር የምታስታውሰው አዲላ፤ እሷ ግን ከሚያበረታቷት ጋር በርትታ ሥራዋን በጥራት መስራቷን ቀጥላለች። በወቅቱ ስምንት ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥራለች።
የእጅ ሥራ በባህሪው በፍጥነትና በብዛት የሚሰራ ባለመሆኑ ፍላጎት ያላቸውንና ቤት ውስጥ የቀሩ ስምንት አካል ጉዳተኞችን በማሰልጠን ወደ ሥራ አስገብታለች። ‹‹አካል ጉዳተኞቹ በቤታቸው ሆነው በሰለጠኑት መሰረት ይሰሩ ነበር›› የምትለው አዲላ፤ የሚያስፈልጓቸውን ክርና ሌሎች ግብዓቶችን በማቅረብ ታሰራቸው እንደነበር አጫውታናለች። በወቅቱ ከሰራተኞቿ ጋር በመሆን የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ሰርታ ወደ ገበያ መውጣት ጀምራለች።
ይህን ጊዜ ታድያ ሥራዋን ማሻሻልና ማስፋፋት የሚያስችላት አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። እሷ እንዳለቸው በወቅቱ ደጃፏን ያንኳኳው አጋጣሚ የጀርመን ፕሮጀክት ነበር። ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮችን በተለያየ ዘርፍ አወዳድሮ ማሰልጠን ነው። የሰራቻቸውን የእጅ ሥራዎች የተመለከተው የውጭ ዜጋም በእጅ ሥራዎቹ በጣም ተደንቆ የሚፈልገውን አይነት ሥራ እንድትሰራ ትዕዛዝ ይሰጣታል። ትዕዛዙ የተለያዩ ቀሚሶችን በእጅ መስራት ሲሆን እሷም ቀሚሶቹን በተባለው ጊዜና ጥራት አደረሰች። የውጭ ዜጋውም አዲላን ጨምሮ ሌሎች ዲዛይነሮችን ከምርቶቻቸው ጋር ይዞ ወደ ጀርመን አገር በመጓዝ በጀርመን በተለያዩ ዘርፎች የፋሽን ትርዒቱ ማሳየት ችለዋል።
‹‹ይህ ለእኔ ትልቅ አጋጣሚ ነበር›› የምትለው አዲላ፤ በወቅቱ የውጭው ዓለም ለእጅ ሥራ የሚሰጠውን ትልቅ ቦታ መረዳት እንዳስቻላት ተናግራለች። በመሆኑም ሥራውን የበለጠ አጠናክራ ለመቀጠል ትልቅ ሞራል ሰንቃ ተመልሳለች።
በተለያዩ ምክንያቶች ከፕሮጀክቱ ጋር መቀጠል ባትችልም በቤት ውስጥ አምርታ በክራይ ሱቅ የምትሸጣቸውን የእጅ ሥራዎች በተለያዩ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ይዛ በመቅረብ ሥራዋን አስፋፋች። በዚህ ጊዜ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታ የማምረቻ ቦታ ማግኘት ችላለች።
በወቅቱ ስምንት አካል ጉዳተኞችን ይዛ ስትሰራ የነበረችው አዲላ፤ ከወረዳው ባገኘችው የመስሪያ ቦታ ሥራዋን ለማስፋፋት በር ከፍቶላታል። በመሆኑም ሁለት የስፌት ማሽኖችን በማስገባት ከእጅ ሥራው ጎን ለጎን ቦርሳዎችን በማምረት ለገበያ አቅርባለች። በተለይም ዕቃ መያዣ ቦርሳዎችን ለሱፐርማርኬቶች ታቀርብ እንደነበር ታስታውሳለች።
ሥራው ራሱን እየመራ ሲሰፋ የትራስና የመጅሊስ አልባሳትን ጭምር በማምረት ይበልጥ ስራዎቿን ማውጣት ቻለች። በዚህ ጊዜ ከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች ዩኒፎርም ለማዘጋጀት ባወጣው ጨረታ ተወዳድራ የመጀመሪያውን የተማሪ ዩኒፎርም በጊዜና በጥራት አምርታ አቅርባለች።
የዩኒፎርም ሥራ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረላት አዲላ፤ ከእጅ ሥራ ይልቅ ወደ ዩኒፎርም ሥራ በማድላት ሙሉ ለሙሉ ዩኒፎርም ወደማምረት ገብታለች። የተለያዩ አይነቶች ዩኒፎርሞች እንዳሉም ጠቅሳ፣ ባደረገችው የገበያ ጥናት ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ዩኒፎርሞች እጥረት መኖሩን ትረዳለች። ያለው ፍላጎትና አቅርቦት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ለሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ዩኒፎርሞችን ለማምረት አቅዳ ወደ ሥራው ገብታለች።
ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ዩኒፎርሞችን በጥንቃቄና በጥራት ማምረትና መጠቀም የግድ ነው የምትለው አዲላ፤ አልባሳቱን በከፍተኛ ጥራት በጥንቃቄ እንደምታመርት አጫውታናለች። እሷ እንዳለችው፤ ለኦፕራሲዮን ክፍል ብቻ የሚያስፈልጉ አልባሳት አሉ። እነሱን በማጥናት የተለያዩ ፓኬጆች ይዘጋጃሉ። አንድ ባለሙያ የሚለብሰው ዩኒፎርም ከሌላኛው ባለሙያ ይለያል። እያንዳንዱ የሕክምና ባለሙያ የሚለብሰው ዩኒፎርም በቀለምና በአይነት የተለያየ በመሆኑ ታካሚው ሀኪሙን በዩኒፎርሙ ቀለም ለይቶ ያውቀዋል። ስለዚህ ታካሚው በተለምዶ ነጭ ገዋን የለበሰውን ሁሉ ዶክተር ብሎ አይጠራም። አዲላም ይህን በጥናት በመለየት በጥንቃቄና በጥራት እያመረተች ለሆስፒታሎች ታቀርባለች።
በቤት ውስጥ በክርና በኪሮሽ የተጀመረው የእጅ ሥራ ዛሬ የሕክምና ባለሙያዎች የሚለብሷቸውን የተለያዩ አይነት ዩኒፎርሞችን እያመረተ የሚገኘው አዲላስ ማኑፋክቸሪንግ፤ የታካሚዎችን ዩኒፎርም ጭምር እያመረተ ይገኛል።
‹‹ጤና ሲባል ሁልጊዜ ከጽዳት ጋር የተያያዘ ነው›› የምትለው ወይዘሮ አዲላ፤ ሥራው ሰፋ ያለ ቦታና ጥንቃቄን እንደሚፈልግም ትናገረለች። ድርጅቷ አሁን ላይ ወደ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ የተሸጋገረ ቢሆንም፣ ስራውን 126 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ነው የሚያመርተው። በቀጣይም ሥራውን የማስፋ ዕቅድ እንዳላት ጠቅሳለች።
በቤት ውስጥ በእጅ ሥራ ስትጀምር ለስምንት ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠረችው ወይዘሮ አዲላ፤ በአሁኑ ወቅት 30 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥራለች። በቀጣይም የሥራ ዕድል ለማስፋት ዕቅድ ያላት ሲሆን፤ ለዚህም ሥራውን የበለጠ ማስፋፋትና በጥንቃቄና በጥራት መሥራት የግድ ነው ትላለች። በአሁኑ ወቅትም የማስፋፊያ ጥያቄ አቅርባ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። ከመንግሥትም አጥጋቢ ምላሽ እያገኘች እንደሆነ ነው የተናገረችው።
ከዚህ ቀደም የሆስፒታል ባለቤቶች ሆስፒታል ሲገነቡ የሕክምና አልባሳቱን ጨምሮ ቁሳቁሱን ከውጭ ያስገቡ እንደነበር ያነሳችው ወይዘሮ አዲላ፤ አሁን ግን በአገር ውስጥ እየተመረቱ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች አልባሳት በመኖራቸው እረፍት ሰጥቷቸዋል ትላለች። በመሆኑም አሁን ላይ አብዛኞቹ የሕክምና ተቋማት ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአገር ውስጥ የተመረቱትን የሕክምና ባለሙያዎች አልባሳት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። አልባሳቱ አላቂ እንደመሆናቸው ገበያ ውስጥ በስፋት እንደሚፈለጉም አመላክታለች።
የሰውን ሕይወት እያዳኑ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ፍጹም ምቹ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው መሥራት እንዳለባቸው አምናለሁ የምትለው ወይዘሮ አዲላ፤ ለዚህም ‹‹እኔ በሙያዬ ምቾት የሚሰጥ ዩኒፎርም እንዲለብሱ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ›› ትላለች። እሷ እንዳለችው፤ ምቾት የሚሰጥ ዩኒፎርም ለማምረት የጨርቁ አይነት ይወስነዋል። ፖሊስተር የሚባለው ጨርቅ የሚያቃጥል ባህሪ አለው። ይህም ምቾት አይሰጥም። ስለዚህ ኮተን የሆኑ ጨርቆች ተመራጭ ናቸው። አዲላስ ማኑፋክቸሪንግ ይህንኑ ከግምት በማስገባት ኮተን እና ፖሊስተር በመቀላቀል አልባሳቱን ያመርታል።
አንድ ክር በሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም፤ አራት ክር በአስር ብር ገዝታ በቤት ውስጥ ጀመረችው የእጅ ሥራ በአሁኑ ወቅት አምራች ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ገበያ ውስጥ በስፋት መግባት ችሏል። የድርጅቱ የገበያ መዳረሻዎች በአብዛኛው ሆስፒታሎች ሲሆኑ፤ እሷም እነሱን ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ገበያ የማፈላለግና የማስተዋቅ ሥራ ሰርታለች። በመሆኑም ድርጅቱን ፈልገው የሚመጡ በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የተለያዩ ሆስፒታሎች ጋር መድረስ ችላለች።
የማምረት አቅሙን በሚመለከትም እንዳብራራችው፤ አዲላስ ማኑፋክቸሪንግ ባሉት 30 የመስፊያ ማሽኖች በቀን 150 ሙሉ ልብስ እያመረተ ይገኛል። ይሁንና ድርጅቱ ከዚህ በበለጠ ለማምረት የማምረቻ ቦታ ውስንነት አለበት። በቀጣይ በሚያደርገው ማስፋፊያ ሥራውን የበለጠ በማስፋት በቀን የማምረት አቅሙን ከ150 ወደ 1000 ከፍ የማድረግ እንዲሁም የሥራ ዕድል የመጨመር ዕቅድ አለው። ምርቶቿንም ከአዲስ አበባ ውጭ በአገሪቱ በሚገኙ ክልሎች አንዲሁም በአፍሪካ አገራት ጭምር የመድረስ ትልቅ ዕቅድ እንዳላት ወይዘሮ አዲላ ተናግራለች።
በአስር ብር መነሻ ካፒታል በቤት ውስጥ የተጀመረው እጅ ሥራ አሁን ላይ ከፍ ያለ ካፒታል ማስመዝገብ እንደቻለና ወደፊትም እያደገ እንደሚሄድ የገለጸችው አዲላ፤ በአሁኑ ወቅት አዲላስ ማኑፋክቸሪንግን እየመራች ያለችው እኩያ ከሆኑ ልጆቿ ጋር በጋራ እንደሆነና ልጆቿ በብዙ እያገዟት መሆኑን አጫውታናለች።
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የተለያዩ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ የጠቀሰችው አዲላ፤ በተለይም ወላጅ አልባ ልጆችን ከሚረዱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር እንደምትሰራ ተናግራለች። ለልጆቹ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን በየጊዜው ታደርጋለች። ወላጅ አልባ ሕጻናት መታየትና መደገፍ እንዳለባቸውም ታምናለች። በዚህ ተግባሯም የተለያዩ የምስጋናና የምስክር ወረቀቶችን ከተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅት አግኝታለች። በአካባቢዋም እንዲሁ አቅመ ደካሞችን በመርዳት ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች መሆኗን አስታውቃለች።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚሰሩ የሥራ ዘርፎች እና መስራት የሚችሉ እጆች አሉ›› የምትለው አዲላ፤ ይህንን አስማምቶ መጠቀም የሚቻልበት ጊዜ አሁን መሆኑን አስታውቃለች፤ በተለይም መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪውን እየደገፈ ያለበት መንገድ አበረታች እንደሆነም አመልክታ፣ ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግራለች። መስራት የሚችሉ እጆች ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥል ብላለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2017 ዓ.ም