ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ በመጣበት በዚህ ወቅት በርካታ ችግሮች መፍትሔ እያገኙ እንደሆነ ይታመናል። በተለይም ወጣት ተመራማሪዎች በየጊዜው የሚፈጥሩት አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች አበጃችሁ እንኳንም ተወለዳችሁ ያስብላል። አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ያሉ አብዛኞቹ ወጣቶች ሥራ ከመፈለግ ይልቅ ሥራ መፍጠር ይሻላል የሚል ጽኑ እምነት አላቸው። በኢንዱስትሪ በበለጸጉ እንዲሁም በአዳጊ ሀገራት ጭምር የሚገኙ ወጣቶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመጨመረ መጥቷል።
አሁን አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች በተለያዩ የፈጠራና የምርምር ሥራዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ሳይቀር ብቅ ብቅ እያሉ መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። እነዚህ ወጣቶች ታዲያ ሥርዓተ-ትምህርት፣ የተለያዩ ድርጅቶች ፣ ተቋማትና ማሕበረሰቡም ካበረታታቸው ፤ ለራስና ለወገን ማለት ለሀገር የሚጠቅም ተግባር የማከናወን ዕድላቸው ይበልጥ ብሩህ እንደሚሆን ይታመናል። የዕለቱ ዝግጅታችንም ትኩረቱን በኢትዮጵያዊው ታዳጊ ተመራማሪ ሔመን በቀለ ላይ አድርጓል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሔመን በቀለ ነዋሪነቱ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ነው። ገና የአራት አመት ህጻን ሳለ ወደ አሜሪካ ያቀናው ሔመን አሁን ላይ የ15 ዓመት ወጣት ተመራማሪ ሆኗል። ምርምሩም የቆዳ ካንሰር ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ የቆዳ ካንሰርን ለማከም የሚያገለግል ሳሙና ለመፍጠር በምርምሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በቅርቡም ታይም የተሰኘው መጽሔት የ2024 የዓመቱ ምርጡ ታዳጊ ሲል በፊት ገጹ ይዞት መውጣቱ ይታወሳል።
ታዳጊው ተመራማሪ ከታይምስ መጽሔት ጋር ባደረገው ቆይታ የምርምር ሥራውን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል። በዛሬው በሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችንም ስለታዳጊው ተመራማሪ ሔመን በቀለ የታይም መጽሔት እና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ያዘጋጀነውን ጥንቅር እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ አበባ ተወልዶ ነዋሪነቱን በሀገረ አሜሪካ ያደረገው ሔመን ፤ ገና በለጋነት እድሜው የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ነበር የራሱን የሳይንስ ሙከራዎች በቤት ውስጥ ማካሄድ የጀመረው። ስለቆዳ ካንሰር አስከፊነት ቀደም ብሎ የተረዳው ሔመንና መፍትሔውን በማሰብ ለዓለም ማበርከት እንደሚችል ህልሙን ሰንቆ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ህልሙን ዕውን ለማድረግ ታዲያ ሥራውን ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው በመኖሪያ ቤት ውስጥ ነው። በቤት ውስጥ ከሚገኙ ቁሳቁሶች መካከል ምርምር ለማድረግም የመረጠው ንጥረ ነገር ሳሙና ነው። በቤት ውስጥ የሚያገኛቸው ሳሙናዎች እና ኬሚካሎችን በመቀላቀል ውህዶቹ ምን እንደሚፈጥሩ ይከታተል እንደነበር ታዳጊው ይገልጻል። ሆኖም ይህን ሲያደርግ ከቤተሰቦቹ ተደብቆ እንደነበርና ሙከራው በሚያደርግበት ወቅትም እሳት ይነሳበት እንደነበር ያስታወሳል። ለቆዳ ካንሰር የሚያገለግል ሳሙናን ለመሥራት በራሱ ብዙ ጥረቶችን እና ጥናቶችን ሲያደርግ ለሦስት ዓመታት እንደቆየም ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን ይናገራል።
ሔመን የሰባት ዓመት ልደቱን ከማክበሩ አስቀድሞ ለገና በዓል ከቤተሰቦቹ አንድ ስጦታ ተበርክቶለታል። ስጦታውም የሶዲየም ሃይድሮክሳይድ ናሙናን የያዘ ኬሚስትሪ ነው። ከዚህ ጊዜ በኋላም ወላጆቹ በቅርበት ይከታተሉት ነበር። ክትትላቸውም ልጃቸው ሔመን ለሳይንስ የተሰጠና ውስጣዊ ፍላጎቱ ሳይንስና ሳይንስ ብቻ እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል። በመሆኑም ለሳይንስ ጥልቅ ፍላጎት ያለው መሆኑን የተገነዘቡት ቤተሰቦቹ ከጎኑ በመቆም በርታ እያሉ ሊደግፉትና ሊያበረታቱት ችለዋል።
ውስጣዊ ፍላጎቱን ተረድተው ቤተሰቦቹ በሚያደርጉለት ድጋፍ ተመራማሪው ሔመን፤ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ምርምሩን እያጠናከረ ሄዷል። በአሁን ወቅትም የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ የተለያዩ ውድድሮችን በማድረግ ሽልማቶችን እያገኘ ሲሆን፤ ባለፈው ጥቅምት ወር ስሪ ኤም ኩባንያ እና የዲስከቨሪ ትምህርት በውድሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊው ተመራማሪ በሚል አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ስሪ ኤም በአሜሪካ ግዙፍ ሳይንስና ሳይንስ ነክ ጥናቶች እንዲሁም ውድድሮች የሚያካሄድበት ተቋም ነው። ተቋሙ ባዘጋጀው ውድድር ተመራማሪው ሔመን የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል ሳሙናን ይዞ ቀርቧል። በውድድሩ ከቀረቡ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ጋር የተፎካከረው ወጣቱ ተመራማሪ ሔመንም በምርምር ሥራው አሸናፊ ሆኗል። በዚህም የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት ተበርክቶለታል። የሔመን ፈጠራ በሳይንስ ሙከራ ሂደት ስኬታማነቱ ሲረጋገጥ የቆዳ ህክምና ታሪክን ሙሉ ለሙሉ የሚቀይር እንደሆነ ይታመናል።
ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን ከልጅነቱ ጀምሮ ምርምር ማድረግ የነፍሱ ጥሪ ነበር። ለሳይንስ ዘርፍ ጥልቅ የሆነ ፍቅርና ህልም ነበረው። ለዚህም ነው ‹‹ሁልጊዜም ቢሆን ሳይንሳዊ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን የመፍጠር ስሜትና ጉጉት ነበረኝ። ‹ኤስሲቲኤስ› የተሰኘ የደረቅ ሳሙና ሃሳብ የመጣልኝም ስለውድድር ሳላውቅ ነው። ነገር ግን ስሪ ኤም ስለተባለው ውድድር ስሰማ ሙከራውን ዝም ብሎ ከማድረግና ሥራውን ከመሥራት በተጨማሪ ውድድሩ ውስጥ በመግባት ውጤቱ የት ያደርሳል የሚለው ለማየት እድሉን ፈጠረልኝ። ምንም እንኳን ሥራው ከውድድሩ በፊት የተጀመረ ቢሆንም ውድድሩ ሥራዬን የማቀርብበትን ትልቅ ዕድል ፈጥሮልኛል›› የሚለው።
ሔመን ጥናት በሚያደርግበት ወቅት ያጋጠመውን ሲናገር በጠራራ ፀሀይ የሚሰሩ የጉልበት ሠራተኞች ያለምንም መከላከያ ሲሰሩ ተመልክቷል። በወቅቱ በእንደዚህ አይነት ሀሩር ውስጥ የጉልበት ሠራተኞቹ የፀሐይ መከላከያ ክሬም ሳይቀቡና ተገቢውን የደህንነት ልብስ ሳይለብሱ መሥራታቸው ተገቢ እንዳልሆነና አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ወላጆቹ ነግረውት እንደነበር ያስታውሳል። በዚህ ጊዜ ታዲያ ለፀሐይና ለአልትራቫዮሌት ጨረር ለረጅም ሰዓት ተጋላጭ መሆን ለቆዳ ካንሰር ተጋላጭ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት ችሏል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ገና በለጋነት ዕድሜው ሰዎችን ለመታደግ የተነሳው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ ሰዎች ከቆዳ ካንስር በቀላሉ መፈወስ የሚችሉበትን የሳሙና መድኃኒት ለማምረት ሌት ተቀን ሲጣጣር ቆይቷል። ጥረቱም አሁን ላይ ፍሬ እያፈራ ሲሆን፤ ሰዎች ሳሙናውን በቀላሉ አግኝተው መፈወስ እንዲችሉ ለማድረግ ለብዙዎችም እፎይታን ለመስጠት የምርምር ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የቆዳን በሽታ የሚከላከል ሳሙና ለመሥራት አልሞ የተነሳው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ ከስኬቱ ለመድረስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል። ለዚህም ሳሊሳይክሊክ አሲድ፣ ግላይኮሊክ እና ትሪቲይን የተሰኙ የቆዳን በሽታን የመከላከል አቅም የሚያሳድጉ ንጥረ ነገሮችን ከሳሙና መሥሪያ ግብዓቶች ጋር በመቀላቀል የቆዳ ካንሰር ከመባባሱ በፊት ለመቆጣጠር ያግዛል የተባለውን ሳሙና መሥራት ችሏል።
የተለያዩ የቆዳ ካንሰር ዓይነቶችን ለማከም አልፎ ተርፎም ለመከላከል የሚያስችል ሳሙና ለመፍጠር ምርምር እያደረገ የሚገኘው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ ለቆዳ ካንሰር ምርምር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ከታይም መጽሔት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል። ‹‹አንድ ቀን የእኔ ሳሙና በሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብሎ ማሰብ በጣም የሚያስደንቅ ነው›› የሚለው ሔመን ፥ ይህን ጥናት የጀመርኩትም ለዚሁ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ምርት ወደ ገበያ ከመምጣቱ በፊት ዓመታት ሊወስድ ይችላል፤ ሆኖም ግን አሁን ላይ ታዳጊው ተመራማሪ ሕልሙን እውን ለማድረግ በባልቲሞር በሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት በላብራቶሪ ውስጥ በመሥራት እያሳለፈ እንደሆነ ነው የተጠቆመው፡፡
ሳሙናውን ለመሥራት ያሰበበት የራሱ ምክንያቶችና ሁኔታዎች እንዳሉት የጠቀሰው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ በተለይም የሳሙናው ዋጋ ተመጣጣኝና ማህበረሰቡ ጋር በቀላሉ ተደራሽ መሆኑ እንዳለበት ያምናል። ታዳጊው ተመራማሪው ሔመን ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ በሳይንሱ ዓለም የገነኑ ብቻ ሳይሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ በቀላል ተደራሽ የሆኑ መፍትሔዎች ላይ አተኩሬ እሰራ ነበር። እንደ ቆዳ ካንሰር ያለ መድኃኒት የተገኘለት ነገር ደግሞ ለሁሉም ሰው መድኃኒቱ ተደራሽ ያልሆነ ዘርፍ አለ። በዓለም ላይ ለቆዳ ህክምና የሚከፈለው ገንዘብ መጠን በአማካይ 40 ሺ ዶላር ይገመታል። ዋጋው ውድ በመሆኑ የተነሳ ይህንን ያህል ገንዘብ አወጥተው ለመግዛት አቅማቸው የማይፈቅድ ብዙ ሰዎች አሉ። በመሆኑም ልሰራ ያሰብኩት ነገር በዘርፉ የሚደነቅ ነገር ብቻ ሳይሆን መፍትሔው ለሰዎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ ነው›› ይላል፡፡
የቆዳ ካንሰር በአብዛኛው በታዳጊ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ላይ ነው የሚከሰተው የሚለው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ በቀላሉ ልንከላከላቸው የምንችላቸው በሽታዎች ከቆይታ በኋላ ብዙ ገንዘብ ሊያስወጡን እንደሚችሉም ይገልጻል። ይህ ሳሙናም የቆዳ ካንሰርን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ነው ያብራራው።
ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን ለፈጠራና ለምርምር ሥራ የማይደክመውና ሁልጊዜም ቢሆን የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚለፋ ወላጆቹ ይናገራሉ። እነሱ እንደሚሉት ከልጅነቱ ጀምሮ ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚፈልግ ልጅ ነው። ድፍረቱ እንዲሁም አቅሙ ብዙ የመሥራት ፍላጎት ስላለው የጀመረውን ነገር መጨረሻ ሳያደርስ እንቅልፍ አይወስደውም። አሁንም ቢሆን ያሰበውን ከግብ ሳያደርስ የሚያደርገው ጥረት እንደማያቆም መሰክረዋል።
አሁን እያደረገ ያለው ጥረትና ያገኘው ውጤት በልጃቸው ሔመን የወደፊት ሕይወት ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን በእጅጉ ተረድተዋል። ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ትልቅ ትኩረት የሰጠው የምርምር ሥራ ትምህርቱን እንዳላስተጓጎለበትና የምርምር ሥራውም በትምህርቱ ምክንያት ወደኋላ እንዳልቀረበት በመጥቀስ ሁለቱንም እኩል ማስኬድ እንደቻለና እነሱም አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እያደረጉለት እንደሆነ ተናግረዋል።
በአሁን ወቅትም ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ ከሥነ-ሕይወት ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ቪቶ ረቤካ ጋር በጋራ በመሆን የሳሙና መድኃኒቱን በአይጦች ላይ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ታይምስ መጽሔት አስነብቧል።
ሆኖም ምርምሩ የባለቤትነት ፍቃድን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን እስኪያካትት ድረስ ዓመታታን ሊወስድ የሚችል ቢሆንም፤ አስር ዓመት እንኳ ቢፈጅ ታዳጊው ሔመን 25 ዓመቱ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይህ ማለት ደግሞ የህክምና ተማሪዎች ትምህርት አጠናቅቀው የሚጨርሱበት ዕድሜያቸው እንዳልሆነ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በቀጣይም ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት ያሰበው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ አሁን የተሸለመውን የሽልማት ገንዘብ ለኮሌጁ ክፍያ የሚያስቀምጠው እንደሆነ አልያም ደግሞ ምርምሩን ለማስፋት የሚጠቀመው እንደሆነ አመላክቷል። ለዚህም ዋናው ምክንያቱ የአሜሪካ የምርምር ጥራትና ቁጥጥር ተቋም ኤፍዴኤ ማረጋገጫ ስለሚያስፈልግ ለእነዚያና ለመሰል ጉዳዮች መጠቀም እንደሚፈልግ ይገልጻል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ አምስት ዓመት በዚህ ፕሮጀክት ሊሰራ ማቀዱንም ይናገራል። የጥራትና የቁጥጥር ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን በሰው ላይ ለመፈተሽ የሚያስችል ፈቃድ የሚሰጠው ቢሮ ማረጋገጫም ያስፈልጋል። ለዚህም በዲጂታል ከተደረገው ሙከራ በተጨማሪ ሳሙናውን ለሕዝብ ይፋ ከማድረጉ በፊት በሰው ላይ ለመሞከር ፈቃድ ይሰጣል። ይህ ሂደት ሲያልቅ ለህብረተሰቡ ተደረሽ ለማድረግ የሚያስችለው የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንደሚችል ይናገራል። ‹‹ከዚህም በተጨማሪ ከአምስት ዓመት በኋላ በጎርጎርያን አቆጣጠር በ2028 ይህንን በትርፍ ጊዜ የተጀመረ ሥራ ወደ ግብረ ሰናይ ድርጅት በመቀየር በብዙዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳረፍ እችላለሁ›› ይላሉ፡፡
ከሳይንስ በተጨማሪ ለሙዚቃና ለስፖርት ጥልቅ ፍቅር እንዳለው የተናገረው ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ ‹‹ኤስሲቲኤስ›› የተሰኘ የደረቅ ሳሙና ተመራማሪ በሚል የዩናይትድስቴትስ የመድኃኒት ቁጥጥርና ጥራት ተቋም የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሚያገኝ ይሆናል። ታዲያ የምስክር ወረቀቱን ሲያገኝ የቆዳ ካንሰር መድኃኒቱን ለማግኘት እጅግ አደገኛ ወደሚሆንባቸው አፍሪካና እስያ ሀገራት የመሄድ ህልም እንዳለው ይገልጻል።
የ15 ዓመት ታዳጊው ተመራማሪ ሔመን፤ ምርምር የቆዳ ካንሰር ፈውስን ያመጣል በሚል በብዙ ታምኖበታል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም