የሰው ልጅ በባህሪው ውሎው ብቻውን እንዳይሆን ይፈልጋል፤ ሲሆን ሲሆን የቅርቤ ከሚለው ጋር ደስታውንም ሆነ ሀዘኑን በተመለከተ የሆድ ሆዱን መጫወት ይፈልጋል። በዚህም እፎይታን ያገኛል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ብቸኝነቱን የሚያጣጥምበትንም ጊዜ መሻቱ አይቀሬ ነው። ታድያ የልቡን ለማካፈልም ሆነ የውስጡን ለማብሰልሰል ምቹ ቦታ ቢኖር ይመርጣል። ይህ ስፍራ ወጪ የማያስወጣው ቢሆን ይመርጣል። ለዚህም ምቹ ህዝባዊ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ቦታዎችን ይፈልጋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ህንፃ ኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ኢንስቲትዩት መምህርት እንዲሁም በፐብሊክ ስፔስ (ህዝባዊ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ቦታ) ላይ የዶክትሬት ትምህርታቸውን በመማር ላይ የሚገኙት ወይዘሮ ጽዮን ለማ እንደሚሉት፤ በከተሞች አካባቢ ለሰው ልጅ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ከፍት ቦታዎች /ፐብሊክ ስፔስ/ ወሳኝ ነው። ፐብሊክ ስፔስ ሲባልም በርከት ያሉ ብያኔዎችን የያዘ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ አጥኚዎች ስለጉዳዩ የተለያዩ ሐሳቦችን ይሰነዝሩበታል። ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስናየው በቀጣይ የተሻሉ ከተሞች እንዲፈጠሩ የሚሠራው ‹‹ዩኤ.ን ሀቢታት ››የተሰኘው ተቋም በመጀመሪያ የከተማ ቦታን ለሁለት ይከፈላል፤ እነዚህንም የህዝብና የግል ቦታዎች አሊያም ደግሞ በህዝብና በግል የሚለሙ ቦታዎች ሲል ይገልፃቸዋል።
የህዝብ ቦታ ሲባል ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በሚል ክፍት የተተው ቦታዎችና አረንጓዴ ሥፍራዎች እንደ ማለት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም ሰፋ ባለ መልኩ ይተረጎማል። ለምሳሌ መንገዶችን፣ አደባባዮችን፣ ፓርኮችን ከዚያ በተጨማሪ ፐብሊክ ፋሲሊቲ የምንላቸውን እንደ ቤተ መጽሐፍት፣ ቲዓትር ቤቶችንን እና የመሳሰሉትን ሁሉ በፐብሊክ ስፔስ ውስጥ (ህዝባዊ ጠቀሜታ) ይጠቃለላሉ። ከዛም ከፍ አድርገው ከተማ ራሱ በዚህ ውስጥ የሚያጠቃለልበት ሁኔታም አለ። ምክንያቱ ደግሞ ከተማ ለህዝብ ጠቀሜታ የሚሰጥ ስፍራ ነው የሚል ነው። ይህ ብያኔው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሆነ በጣም ሰፊ ነው።
‹‹ወደ እኛ አገር ስንመጣ ፐብሊክ ስፔስን በከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር አገላለፅ አረንጓዴ ቦታንና ክፍት ቦታን ለይቶ ያስቀምጠዋል። ›› ሲሉ በመጥቀስ፤ በአብዛኛው አረንጓዴ ሽፋን ያላቸውን ቦታዎች አረንጓዴ ቦታዎች በማለት ሲገልፁ፣ ክፍት ቦታዎች የሚባሉትን ግን ግንባታ ያላረፈባቸው መዝናኛ ሥፍራዎች አሊያም ደግሞ ያልለሙ ቦታዎች ሊባሉ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ቦታዎቹ ክፍትና አረንጓዴ ቦታዎች በሚል ይታወቃሉ። ስለዚህም ፐብሊክ ስፔስ ለሚለው ብያኔ ሲሰጡ ሁለቱን ማለትም ክፍትና አረንጓዴ ቦታዎች በሚል ነው የሚጠሯቸው። ስለዚህ ፐብሊክ ስፔስ የሚባሉት ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ በአብዛኛው ክፍትና አረንጓዴነት ያላቸው ቦታዎች በሙሉ ናቸው። እነዚህ ቦታዎች ለትርፍ ሳይሆን ለህዝብ ተደራሽ የሚሆኑ ቦታዎች ናቸው፤ በዚህ መልኩ ብያኔውን መረዳት ይቻላል።
እነዚህ ነገሮች ጠቀሜታቸው በጣም ሰፊ ነው። ይህንንም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ኢንቫይሮመንታል በሚል በሦስት ይከፈላሉ። ማህበራዊ ጠቀሜታዎች የሚባሉት፤ ሰዎች በቦታው ላይ መሰባሰብ፣ መወያየትና መዝናናት መቻላቸውን የሚያመላክት ነው፤ ሰዎች በእነዚህ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በነፃነት ሊያደርጉባቸውም ይችላሉ።
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሲታይ ደግሞ የተለያዩ ነገሮችን በመሸጥ፣ በመግዛትና ከዛም የሚገኝ ጠቀሜታ ነው። ከዚህም መካከል ዋና ዋና የሚባሉት ሰዎች በነፃነት ክፍያ ሳይከፍሉ ሊዝናኑባቸው የሚችሉባቸው መሆናቸው ነው።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ ኢንቫይሮንመንታል የሚባለው ደግሞ የአካባቢን በተለይ የሥነ ምህዳሩን ሚዛን ከመጠበቅ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው፤ አረንጓዴ ቦታዎቹ በመጥፋታቸው ነው የሥነ ምህዳሩን ሚዛን ለመጠበቅ ችግር እየታየ ያለው። ከፍተኛ ሙቀት፣ የአፈር መሸርሸር ብሎም ጎርፍና መሰል ነገሮችን እያየን ነው። ይህ
የሚከሰተው በተለያየ ደረጃ ያለው ፐብሊክ ስፔስ እየጠፋ በመምጣቱ ነው። ስለዚህ እነዚህ ቦታዎች የአየር ፀባይ ሚዛንን ለማስጠበቅ እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን ለማግኘት የሚጠቅሙ ይጠቅማሉ።
ከተማ ፐብሊክ ስፔስን ጨምሮ ሁሉም ነገር ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከሌላ አካባቢ መጥቶ ፓርክ ውሎ ቢሄድ ከተማ መጥቶ ተገልግሏል በሚል ክፍያ አይጠየቅም። ስለዚህ ፐብሊክ ስፔስ በተለያየ መልኩ ለሰዎች ጥቅም ይሰጣል።
መምህርት ጽዮን እንደሚናገሩት፤ አዲስ አበባ ከአመሠራረቱ ጀምሮ በፕላን የተደገፈ ከተማ አልነበረም። በራሱ እያደገ የመጣ ከተማ ነው። ምንም እንኳ የፕላኒግ አስተሳሰብ የነበረው ባይሆንም፣ ፐብሊክ ስፔስ የሚባለው በጣም በስፋት ያለው ከተማ ግን ነበር። ካለፉት አስርና አስራ ሦስት ዓመታት በፊት ከተማው በጣም በፍጥነት እያደገ ሲመጣና የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ እንዲሁም የኢኮኖሚውም ዕድገት በዛው መጠን ከፍ እያለ ሲመጣ ነው እነዚህ አረንጓዴና ከፍት የሚባሉ ቦታዎች በጣም እየጠበቡና እያጠሩ የመጡት።
የአዲስ አበባ ከተማ እ.ኤ.አ ከ1986 የአርንጓዴው ሽፋኗ 32 ሺህ 083 ሄክታር ነበር። ይህ አሀዝ በ2003 ላይ ወደ 21 ሺህ 518 ወርዷል። 2016 ላይ እንደገና ወደ 16 ሺህ 265 ሄክታር ዝቅ ብሏል። ይህ ቁጥር ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል ብለው አጥኚዎች ሞዴል ሠርተው ያዩት ነገር ቢኖር በ2040 በዚሁ አጠቃቀም ከተቀጠለ ክፍት ቦታው ወይም አረንጓዴ ሥፍራው ወደ 2 ሺህ 085 ሄክታር ሊወርድ እንደሚችል ነው ያስቀመጡት።
የአዲስ አበባ ከተማን የአረንጓዴ ሥፍራ ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የነፍስ ወከፍ ድርሻ ጋር ሲታያይ ሰፊ ክፍተት አለው። ድርጅቱ አንድ ከተማ ዘጠኝ ሜትር ስኩዬር አረንጓዴ ቦታ ለአንድ ሰው ሊኖር እንደሚገባ ያስገነዝባል። አዲስ አበባን ብንመለከት ግን ከ0 ነጥብ 4 እስከ 0 ነጥብ 9 የቦታ ስፋት ብቻ ነው ለአንድ ሰው ያለው። ይህ በአዲስ አበባ ውስጥ በነፍስ ወከፍ የሚገኘው ቦታ ማለት ነው። ይህም ቦታው ምን ያህል እያነሰ መሄዱን ያመለክታል። ከዚህም ዳር ላይም ሆነ መሐል ላይ ያሉ ቦታዎች በልማቱ ሳቢያ ምን ያህል እየተወሰዱና እየተዋጡ ማለቃቸውን መረዳት ይቻላል።
የአረንጓዴ ሥፍራው ምን ያህል እየጠፋ እንደሚሄድ ሲታይ ተጽዕኖው በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ከወዲሁ ብዙ ለመሠራትን እንደሚጠይቅ ወይዘሮ ጽዮን ያስገነዝባሉ።
‹‹የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን መስፈርት መሠረት አድርገው እየተመሩ ያሉ ከተሞች አሉ። ለምሳሌ ከኢስያ ከተሞች የደቡብ ኮሪያዋን ሴኡል ከተማ ብንመለከት በጣም ብዙ ህዝብ ያለባት ከተማ ናት፤ ከአስር ሚሊየን በላይ ሰዎች ይኖሩባታል። ነገር ግን በጣም
ሰፊ የአረንጓዴ ሽፋን ነው ያላት። በጣም በትንሽ ቦታ ላይ በጣም ብዙ ህዝብ የሰፈረ ሲሆን፣ በጣም ሰፊ ቦታ ለአረንጓዴ ሥፍራ ትታለች። ከአፍሪካ ደግሞ እነ ኬንያም ቢሆኑ ከእኛ የተሻለ የአረንጓዴ ሽፋን አላቸው። ደቡብ አፍሪካ እንደዚሁ ትሻላለች። ›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንዴት ነው በቀጣይ ይህን አስፈላጊ ቦታ ማስጠበቅና ማስመለስ የሚቻለው ለተባለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዳብራሩት፤ በዋናነት የከተማ ፕላንና ዲዛይን ሥራ ትልቅ ሚና አለው። እነዚህን ቦታዎች ከመለየትና ከማልማት እንዲሁም ከማስጠበቅም አኳያ የፕላኒግ ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። ገና ፕላን ሲሠራ ጀምሮ በጣም ጠቃሚ ቦታዎችን መለየት ያስፈልጋል። ውሃ ገብ፣ ተራራማ እና የወንዝ ዳር ቦታዎችንና ሌሎች መተኪያ የሌላቸውን ቦታዎች በመጀመሪያ በመለየትና መሬቱን በጀት ማድረግ ያስፈልጋል፤ የመሬት አጠቃቀም ፕላን ማዘጋጀት የግድ ይላል።
ይህን ሥራ ገና አዲስ በሚያድጉ ከተሞች ላይ ለመተግበር መነሳሳት ነው። ልማቱ ዳር ድረስ ስለደረሰ አዲስ አበባ ላይ ይህን ማድረግ ትንሽ ያስቸግራል። በአዲስ አበባ በቅርቡ ማስተር ፕላን ላይ 30 በመቶ ለመንገድ፣ 30 በመቶ ለፐብሊክ ስፔስና 40 በመቶ ብቻ ለግንባታ የሚል ሕግ ወጥቶ ነበር። አሁን ይህን እንዳለ ማስፈፀም በጣም ሊከብድ ይችላል፤ ነገር ግን ይህንን በተለያየ መንገድ ማድረግ ይቻላል። አንደኛ ከመንገድ ጋር የተያያዙ አረንጓዴ ቦታዎችን በማስተር ፕላኑ ላይ ማስጠበቅ ይገባል።
አሁን ያሉትን ፓርኮች፣ ፕላዛዎች፣ አደባባዮች፣ የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎችን እና በሌሎች ተራራማ ቦታዎች ላይ ያሉ ክፍት ቦታዎችን ባሉበት በመረጃ በደንብ ይዞ እንዲጠበቁ ማድረግም ያስፈልጋል። ይህንንም በኢንስትቲዩሽን ደረጃ ማኔጅ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህ በቂ ባለመሆናቸው ደግሞ ተጨማሪ ሌሎች ነገሮችን ማየትም ይጠቅማል።
ከሰፋፊ መኪና ማቆሚያዎች ሰፊ ቦታ ማግኘት እንደሚቻልም ይጠቁማሉ። መንገዶችን፣ የቀላል ባቡር መስመሩንና ወደፊት የሚገነቡ መስመሮችን ወደፊት በመሬት ውስጥ እንዲገቡ ቢደረግ ፐብሊክ ስፔሱን ማስፋት ይቻላል ሲሉ አብነቶችን ጠቅሰው ያብራራሉ። የህፃዎች ጣራያ፣ ግድግዳዎች፣ በህንፃና በህንፃ መካከል ያለ ቦታ፣ ተዳፋትና መሰል ቦታዎችን በመፈጠር የፐብሊክ ስፔስን ከፍ ማድረግ ይቻላል። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ የከተማው ዕድገት ዳር ላይ ስለደረሰ እነዚህን ቦታዎች በዚህ መልክ ማግኘት ይቻላል።
የመልሶ ማልማት ሥራዎች በሚሠሩበት ጊዜ የሚፈለገውን ያህል የሕንፃዎችን ጥግግት በመፍጠር ቦታዎቹን መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነም ያመለክታሉ። እንደዚህ ካልተደረገ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም የቀነሰ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
አስቴር ኤልያስ