ኢንጂነር ብርሀኑ ኃይሉ የተወለዱት ያደጉትም በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነው። አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ተከታትለው ጨርሰዋል። ከፍተኛ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሕንድስና ኮሌጅ ገብተው በመማር በሲቪል ኢንጂነርነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ቀጥሎም መንግስት በሰጣቸው የትምህርት እድል ወደ ኔዘርላንድ በመሄድ በማስተር ኦፍ ኢንጂነሪንግ ተምረው ተመርቀዋል። ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በተለያዩ መንግስታዊ ኃላፊነቶች በሲቪል ኢንጅነርነት በተለይም በመንገድ ስራው ዘርፍ ሲሰሩ ቆይተው ለቀው በመውጣት የራሳቸውን የሆሀ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ አቋቁመው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከኮንስትራክሽን ስራዎች ጋር በተያያዘ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ይከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡– በሥራ አለም የት የት ሰሩ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ ፡-ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከያዝኩ በኋላ ለሶስትና አራት አመታት ያህል በዚያው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ውስጥ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች አገልግያለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ምን ምን ኃላፊነቶች ላይ ሰሩ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– በመጀመሪያ የጀመርኩት ከተራ መሀንዲስነት ነው። ከዚያ በኮንትራት አስተዳደር ውስጥ ቀጥሎም የምሕንድስና መምሪያ ኃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ በመንግስት በተሰጠኝ የትምህርት እድል ማስተር ኦፍ ኢንጂነሪነግ ለመማር ወደ ኔዘርላንድ ሄድኩ። ተምሬ ከተመለስኩ በኋላ በዚያው ክልል የቤንሻንጉል ገጠር መንገዶች ስራ አስኪያጅ ሆኜ ተሾምኩ። ከ8 አመታት በላይ በዛው አገልግያለሁ። ሕዝብህን በተማሩበት የሙያ መስክ ከልብ ማገልገል ከፍተኛ እርካታ ይሰጣል። በነዚህ አመታት ከፍተኛ የመስክ የስራ ልምድና እውቀት አግኝቼአለሁ።
አዲስ ዘመን ፡– እንዴት ወደ ግል ተቋራጭነት ስራ ገቡ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ከመንግስት ስራ በኋላ ወደግሉ ስራ ገባሁ። የኮንትስራክሽን አማካሪ ሆኜ ወደ አፋር አካባቢ ሄድኩ። የተለያዩ መንገድ ስራዎች ላይ ተጠሪ መሀንዲስ ሆኜ አገለገልኩ። በዚህ አይነቱ ስራ ቢሮ ቁጭ ብለህ የምትሰራበት ጊዜ ውስን ነው። አብዛኛው የመስክ ስራ ነው። ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ ላይ በአካል መገኘት መቆጣጠር መምራት ግዴታ ነው። ስለዚህ ከተማ ውስጥ የምትሆንበት ጊዜ የለህም። በረሀማ ቦታዎች በጣም ሩቅ የሆኑ ገጠሮች ውስጥ መንገድ የሌለባቸው አካባቢዎች መንገድ ለመስራት ለወራትም ሆነ ለአመታት ልታሳልፍ ትችላለህ። ስራው ፈታኝ ነው። ችግሮችን በመቋቋም ስራውን ውጤታማ ማድረግ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው።
አዲስ ዘመን፡– አፋር አካባቢ ምን ያህል ጊዜ ሰሩ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– እስከ 4 አመት ያህል ሰራሁ።
አዲስ ዘመን፡– የትኛውን መንገድ ሰራችሁ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ያው እንደምታውቀው አፋር በረሀ ተብሎ የሚጠቀስ አካባቢ ነው። የሙቀቱ መጠን በተለያየ ጊዜ ይጨምራል። በዚያ አካባቢ ተጠሪ መሐንዲስ ሆኜ ከሰመራ ከተማ ወደ መሆኒ የሚሄደውን የውስጥ መንገድ አንደኛውን ክፍል
ነው የሰራነው። ኢንጂነር ዘውዴ በሚባል አማካሪ ድርጅት ውስጥ ነው ተጠሪ መሀንዲስ ሆኜ የሰራሁት። ቀጥሎም የኮንትራክተር ፈቃድ በማውጣት ትምህርት ቤቶች ሰራን።
አዲስ ዘመን፡– የት ቦታና ምን አይነት ትምህርት ቤቶች ሰራችሁ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡- አሁን በደምብ አላስታውሰውም። ወደ ጭፍራ አካባቢ ሆኖ በጣም ሩቅ ገጠር ውስጥ ነው። በአካባቢው ውሃ የለም። ወደዚያ አካባቢ ከአንድ አመት በላይ ቆይተን በትምህርት ቤቶች ስታንዳርድ መሰረት እስከ አራት የሚደርሱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሰርተናል። ትምህርት ቤቶች ሲሰሩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩበት በተለይ የተቀመጠ ደረጃ አላቸው። በዚህ መሰረት ብቻ ነው የሚሰራው። ከዚህ ቀጥለን ድልድዮች ሰርተናል።
አዲስ ዘመን፡– የት አካባቢ ነው ድልድዮቹን የሰራችሁት ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አራት የሚሆኑ ትላልቅ ድልድዮችን ሰርተናል። ቤኒሻንጉል አካባቢ ሰርተናል። አውራ ጎዳና የትም ቦታ ላይ በሚያወጣቸው ጨረታዎች ላይ እየተሳተፍን እድሉን ከተሰጠን እንሰራለን። ሰርተናልም።
አዲስ ዘመን፡– አሁን በስራ ላይ ያለው የድርጅት ስሙ ማን ይባላል?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ሆሀ ይባላል።
አዲስ ዘመን፡– ሆሀ ትርጉሙ ምንድነው ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ሆሀ ማለት እዛው ተወልጄ ያደኩበት አሶሳ አካባቢ ያለ ወንዝ ነው። ይሄ ወንዝ ወደታች ወረድ ሲል ቱመት ይባላል። የአባይ ወንዝ ገባር ነው። አሶሳ ትምህርት ቤት ስንማር ሆሀ ቁጥር አንድ ሆሀ ቁጥር ሁለት የሚባሉ ትምህርትቤቶች ነበሩ። በልጅነታችን የሰፈር ልጆች የትምህርት ቤት ጓደኞች ተጠራርተን ወንዙ ጋ እንሄዳለን። እንዋኛለን። ከላይ ፏፏቴም ነበረው። አሁን የለም ጠፍቶአል። ሆሀ ወንዝ ከአሶሳ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ከአሶሳ አካባቢ እዛው ከፍ ካለ ቦታ ነው የሚነሳው። ከዚያ ተነስቶ ወደ በረሀው ይወርዳል።
አዲስ ዘመን፡– በመሀንዲስ አይን ሲያዩት የድሮዋና የአሁንዋ አሶሳ ምን ያህል ለውጥ አላት?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ባለፉት 20 እና 25 አመታት ውስጥ አሶሳ በጣም ትልቅ ለውጥ ያመጣች በጣም አስገራሚ እድገት ያሳየች ከተማ ነች። ከተማው መንገዱ የኮንስትራክሽን ግንባታው ሁሉም ነገር አድጓል። አሶሳ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማም ነች። ከድሮው በተለየ ሁኔታ በጣም አድጋለች።
አዲስ ዘመን፡– ሆሀ ኮንስትራክሽን ከተቋቋመ ስንት ጊዜ ሆነው ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– 8 አመት ሆኖታል።
አዲስ ዘመን፡– የት የት ሰራ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– በአብዛኛው የምንሰራው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። በተለይ በመንገድ ላይ ስለምንሰራ ራሳችንን ችለን ትልልቅ ስራዎችን የምንወስደው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ነው። አንድ ሁለት ኮንትራቶች ወስደናል። የመንገድ ጥገና ስራ ነው። ይሄ ባሌ ውስጥ ነው። በዋና ኮንትራክተርነት የምሰራው ነው። በሰብ ኮንትራት የምንሰራው ስራ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ላይ ቻይኖች በሚሰጡን መሰረት ነው። በመጀመሪያ ባሕርዳር አካባቢ ከባሕርዳር ወደ ሞጣ የሚሄድ መንገድ ጀማ ወንዝ በሚባል መንገድ ውስጥ 92 ኪሎሜትር ነው። ከዚያ ውስጥ 19 ኪሎሜትር መንገድ ወስደን ሰራን። ያው ቀደም ሲልም የመንገድ ስራ ላይ ልምድ ስለነበረኝ ማለት ነው። መጀመሪያ የሠራነው እዛ ነው። መንገዱንና ተያያዥ የስትራክቸር ስራዎችን ነው የምንሰራው። ቻይኖቹ አስፋልቱን ይሰራሉ። ትልቁ ድርጅታችን በብቃት ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ያስመዘገበበት ስራ ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡– አዲስ አበባ ወስጥ ፕሮጀክቶች አሏችሁ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– አዲስ አበባም አሉን። ከአውራ ጎዳና ጋር ከአዲስ አበባ ውጪ የምንሰራቸውም መንገዶች አሉን። ጅጅጋ ከተማ የሰብ ኮንትራት ስራ እንሰራለን። ከዚህ ውጭ ወደ አራት ስራዎች አሉን ። እነዚህን በአግባቡ ሰርተን እየጨረስን ወደ ሌላው እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡– አዲስ አበባ ውስጥ የትኞቹን መንገዶች ሰራችሁ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– አዲስ አበባ ከመካኒሳ አደባባይ እስከ ብስራት ገብርኤል አደባባይ ያለውን መንገድ ከቻይናዎች ሰብ ኮንትራት ወስደን ሰርተናል። ሌላው መገናኛ አካባቢ ያሉ 40/60 ቤቶች አሉ። ኮንዶሚኒየሞች ናቸው። እዛ ውስጥ ያሉ መንገዶችን ከቻይናዎች ወስደን ሰርተናል። አይ ኤፍኤች ከሚባል የቻይና ካምፓኒ ሰብ ኮንትራት ወስደን ነው የሠራነው። እንደገና መገናኛ ውስጥ በ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚሰራ መንገድ ነበር። እሱንም ሰብ ኮንትራት ወስደን እኛ ነን የሰራነው። ቀደም ሲል እንደገለጽኩልህ በአብዛኛው የምንሰራው መንገድ ላይ ነው። ቤት ላይ አይደለም።
ሌላው ከሲኤምሲ ጉርድ ሾላ አካባቢ መስቀለኛ መንገድ አለ። እሱንም የሰራነው እኛ ነን። ይሄ መንገድ ለአካባቢው ሕብረተሰብ በጣም ጥሩ የሆነ መንገድ ነው። በዚሁ አፈጻጸማችን ምክንያት ከጎተራ አደባባይ እስከ ቄራ በግ ተራው ድረስ ያለውን መንገድ አሁን እየሰራን ያለነው እኛ ነን። ይሄኛውም በቻይና መንግስት በኩል የሚሰራ መንገድ ነው። አሁን ነው የተሰጠው። በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ ያለ መንገድ ነው። ከጎተራ እስከ ሳር ቤት ድረስ ያለው ማለት ነው። እስከዛሬ ተሰርቶ አያውቅም። እንደ አዲስ ነው የሚሰራው። ከቻይና ካምፓኒዎች ጋር ነው የምሰራው። አይ ኤፍ ኤች ኢንጂነሪንግና ቄራ ያለውን ደግሞ ሲኤች ኤፍ ኢሲ
የሚባል የቻይና ካምፓኒ ነው የሚሰራው።
አዲስ ዘመን፡– ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ሲሰራ ልምድ ልውውጡና አዲስ እውቀት በማስገኘት ረገድ ምን ያህል ጥቅም እያስገኘ ነው?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ከቻይና የመንገድ ስራ ኩባንያዎች ጋር በሰብ ኮንትራት አብሮ መስራት ጥቅሙ ምንድነው ካልን የመጀመሪያው የቻይና ኩባንያዎች ልምዳቸውን ለእኛ ባለሙያዎች ያጋራሉ። ሁለተኛ እነሱ የዳበረ በበርካታ አመታት ውስጥ ከልምድና ከተግባራዊ ተሞክሮዎች በመነሳት ያካበቱት ዘመናዊ የማኔጅመነት አሰራር አላቸው። እኛም የማኔጅመነት አቅማችንን ከእነሱ አንጻር እያሻሻልን ነው። እንደ ፓርትነር ነው የምንሰራው።
የቻይና ኩባንያዎች ትልቁ ጥቅማቸው ምንድነው ካልን ደግሞ የገንዘብ ፍሰታቸውንና የማቴርያል አቅርቦታቸውን የራሳቸው መንግስት ስለሚሸፍንላቸው ከእኛ በእጅጉ የተሻሉ ናቸው። የቻይና መንግስት ኩባንያዎች ናቸው። በውላቸው መሰረት መንግስት ከፈላቸው አልከፈላቸው የገንዘብ ፍሰታቸው ለስራው የሚሆነውን ነገር የማቅረብ አቅማቸው በጣም የተሻለ ነው። በእኛ በኩል ደግሞ በአካባቢ ማቴርያሎች የሚሰሩ ስራዎችን ቶሎ ቶሎ መስራት ፤በእነሱ ፕሮግራም መሰረት መሄድ፤ በእነሱ ፍላጎትና እቅድ ላይ ተመስርተን ስራውን ስኬታማ ለማድረግ ተግተን እንሰራለን ማለት ነው። በዚህ ምክንያት እነሱም እኛን ተመራጭ ያደርጋሉ። ሰፊ እውቀትና ልምድ ይገኝበታል።
አዲስ ዘመን፡– የእኛ ሰዎች ልምድ መቅሰሙና ተግባራዊ ማድረጉ ላይ እንዴት ናቸው?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– እኔ የመንግስትም ፖሊሲ የሚመስለኝ በሀገር ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ገብተው ሲሰሩ የእኛ ሰዎች ብዙ ልምድና እውቀት አብረው ከስራው ጋር ያገኛሉ የሚል እምነት ያለ ይመስለኛል። ትክክልም ነው። ይሄ በሂደት ራስን በሙያተኛ ደረጃ ለማብቃት ብዙ ይጠቅማል። ቻይናዎቹ የበለጠ እኛ ብዙ ትኩረት ሰጥተን የማንሰራቸው ስራዎች አሉ። ለምሳሌ የአስፋልት ፕላንት፤ ቱቦ ማምረቻ ፕላንቶች፤ የክሬሸር ፕላንቶች የመሳሰሉት አሉ። እዛ ላይ ሰፊ እውቀቱና ልምዱ አላቸው።
አዲስ ዘመን፡– ክሬሸር ፕላንት ምንድነው ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– ክሬሸር ፕላንት የምንላቸው የአፈር መፍጫዎች፤ ሰብ ቤዝ የጠጠር መፍጫዎች፤ የኮንክሪት ፕላንቶች ወዘተ. እነሱ አሉዋቸው። እኛም አለን። ግን እኛ አቅም የለንም። አሁን በእኔ ደረጃ ይሄ አቅም ስለሌለኝ እነሱ አላቸው። እነሱ ያኛውን ሲያመርቱ እኛ ደግሞ በአካባቢ ማቴርያሎች ጋራጋንቲ ሰርቤዝ ዲስኮስ እነኚህን እያጓጓዝን ስራውን እንሰራለን። ልምድ እናገኛለን። ወደፊት እንግዲህ እኛም አላማችን እነሱን ተክተን ለመስራት ነው። የእኛም አንዳንድ ኮንትራክተሮች እንደዛ የሆኑ አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ስራውን ለመስራት ምንድነው የሌላችሁ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– እኛ ማቴሪያሎቹ የሉንም። ፕላንቶቹ የሉንም። የእነሱን ሪሶርስ በዚህ መንገድ እየተጠቀምን የሀገር ውስጥ ቁሶችን ማሽነሪዎችን እያቀረብን እንደ ፓርትነር ሆነን ስራ እንሰራለን። በዚህ መልኩ ስራው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ይደረጋል። ትልቁ ነገር ምንድነው አንደኛው ነገር ኮንትራቱ በቻይናዎቹ በመሆኑ በጣም በዝርዝርና በቀላሉ በሚሰራ ስራ ላይ ትኩረት አድረገው መስራት አይፈልጉም። እነሱ እኛ ጋ የሌሉትን ክፍተቶች እየሞሉ መስራት ነው የሚፈልጉት። ለእኛም ጥሩ ነው። የሥራ እድል ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡– የቻይናዎቹ ኩባንያዎች የመንግስት ናቸው ያሉትን ቢያስረዱኝ ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– አዎ። ትላልቆቹ ግዙፍ ኩባንያዎች የቻይና መንግስት ናቸው። እኔ በግሌ መንግስት አሁን በእኛ ሀገር ደረጃ ክፍያ በተለያየ ደረጃ ቢዘገይ የእኛ ስራዎች የመስተጓጎልና የመቆም እድል አላቸው። ስራውን ለማስቀጠል ማቴርያል ለማቅረብ ለሰራተኛው ለመክፈል ትልቅ ችግር ይፈጠራል። የቻይናዎቹ ግን አይቆምም። የገንዘብ ከፍተቱን ራሳቸው ይሸፍናሉ። በዚህ ምክንያት እነሱ በሚሰጧቸው ኮንትራቶች ላይ እንደዚህ አይነት ነገሮች አይፈጠሩም። ለስራው የሚያስፈልጉትን ነገሮች
በሙሉ ያሟላሉ።
አዲስ ዘመን፡– ከመንገድ ሥራ አንጻር እኛ ሀገር ውስጥ ያስተዋሉት ዋነኛ ችግር ምንድነው ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– እኔ በአጠቃላይ መንግስት ሴክተሩ ላይ ትልቅ ችግር ነው ብዬ የማስበው በአብዛኛው ወሰን የማስከበር ጉዳይ ነው። መንገድ የሚወጣባቸውን ቦታዎች ካሳ ከፍሎ ቶሎ ነጻ አድርጎ የመልቀቅ ችግር ብዙ ቦታ ላይ አለ።
በአብዛኛዎቹ ቦታዎች መንገድ የመስራቱ ነገር ቶሎ የማይከናወንበት አንዱ ጉዳይ ይሄ ነው። በተለይ በወረዳ ደረጃ ያሉት ካሣ ከፍሎ በወቅቱ የማስነሳት ከዚያ በኋላ ለሚሰራው ኮንትራክተር ነጻ የማድረግ ችግር አለ። ካሣ ገምቶ እንዲነሳ ለማድረግ ብዙ ወገኖች ይሳተፉበታል። መብራት ኃይል፤ውሃ ክፍል፤ ሌሎችም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ የሚሰሙ ነገሮች አሉ። ካሣው ተመጣጣኝ ያለመሆን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ገምቶ ያለመስጠት ችግርም ይነሳል።
በአጠቃላይ በሌሎች ሀገሮች ምን አይነት ልምድ አለ የሚለውን በደምብ ማጥናት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። መንገድ ለመስራት ሲታሰብ ወይንም መንገዱ ሲሰራ ቦታው ከምንም አይነት ነገሮች ነጻ ሆኖ መረካከብ አለበት። እኛ ሀገር ትልቁ ችግር ይሄ ነው።
ሌላኛው የአካባቢ ማቴርያሎችን እንደዚሁ ከወሰን ችግር ጋር በቀላሉ ማግኘት አለመቻልም ራሱን የቻለ ትልቅ ችግር እየሆነ ነው። ለምሳሌ ጋራጋንቲ። የጠጠር ማምረቻ ቦታዎች፤ አፈር መፍጫ ቦታዎች እንደዚህ አይነት ነገሮች በጣም ትንሽና ቀላል የሚመስሉት ነገሮች ከወሰን ጉዳይ ያለመፈታት ጋር አብረው እየተከሰቱ ነው። ምክንያቱም አንድ ኮንትራክተር ሄዶ ለጋራጋንቲ ለመንገድ ስራ የሚጠቅም ስለሆነ እፈልገዋለሁ ሲል ያንን ነገር ግምትና ካሣ ተከፍሎ ነጻ ተደርጎ ለሚሰራው ኮንትራክተር የማስረከብ ግዴታ ባለቤቱ አለበት። ይህን ለማድረግ ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በጣም ሰፊ ጊዜ ይወስዳል። እነኚህ ነገሮች በጣም በመንገድ ግንባታ ስራው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አላቸው። ኮንትራክተሮች በወቅቱ ስራቸውን ላለመጨረስ እንደገናም ኮንትራክተሮችን ወደ ኪሳራ የሚያስገባው መሰረታዊ ምክንያት አንዱ ይሄ ነው።
ኮንትራክተሮች ደግሞ ብዙ የሰው ኃይል ብዙ ማሽኖች አስገብተው ውጤታማ ካልሆኑ ለተወሰነ ወቅት በሠራተኛው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል፤ ማሽኑም በጣም ይጎዳል። ተጽዕኖው በጣም ከባድ ነው። እነኚህ በእኛ ሀገር በትልቁ የሚታዩ ችግሮች ናቸው።
በከተማ አካባቢ ምናልባት የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማቅረብ አለመቻል (የመብራት፤ የስልክ፤ የውሃ፤ የጽዳት) ይስተዋላል፤ እነዚህ ነገሮች የየራሳቸው መዋቅር ያላቸው ናቸው። እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ አቀናጅቶ የሚመራ ተናበው እንዲሄዱ የሚያደርግ መንግስታዊ አካል ሊኖር ይገባል፤ ቢዚህም ስራው በተጠናከረ ሁኔታ መስራት አለበት።
ሌላው በእኛ ሀገር የሚታየው መሰረታዊ ችግር የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጀት አግኝቶ ስራን ያለማስጀመር አለ። ሁልጊዜ አንድ ፕሮጀክት የተወሰነ የፕሮጀክት ወጪ አለው። ወጪ፣ ጊዜና ጥራት የምንላቸው አሉ። በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ በሚገባው ጥራትና ዋጋ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እነዚህ ሁሉ መሟላት አለባቸው፤ አንዱ ከተጓደለ ሶስቱንም ይጎዳል። እንዲህ አይነት ነገሮች በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ዋጋ) ላይ ተጽዕኖ አላቸው።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ለመውጣት ምንድነው መደረግ ያለበት ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– በእኛ ሀገር በፕሮጀክቶች ደረጃ በጣም የማደንቃቸው ተቋሞች አሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ትልቅ የሰው ኃይል ያለው ተቋም ነው፤ በሚገባ የተደራጀ የአሰራር ስርዓት ያለውና ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የሀገራችን ትልቅ ተቋም ነው። እጅግ በጣም ብዙ ባለሙያዎች አሉት። መስሪያ ቤቱ ረዥም ጊዜ የዘለቀ ሲስተም አለው። የራሱንም የሰው ኃይል በብቃት የሚያሰለጥን መስሪያ ቤት ነው።
ከእነሱ ውጭ ያሉ የማይፈቱ ችግሮች አሉ። አሁን የምንላቸው ወሰኖችን የማስከበር የኮንትራክተሮችን አቅም የመገንባቱ ጉዳይ የመንግስትን ትኩረት ይጠይቃል። እንዴት አቅማቸው ይገነባ ለሚለው በመንግስት ፖሊሲ ደረጃ ደጋፊ ነገሮች ያስፈልጋሉ። እንደዛ ማድረጉ የተሻለ ለመስራት ያስችላል። ካለው የሰው ኃይል አንጻር ገበያው ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሄዶ ሰርቶ ሰፊ የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት ሰፊ እድልም አለው። በዛ ደረጃ ቢታሰብበት ውጤታማ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የኮንትራክተሮች መሰረታዊ ችግር ነው የሚሉት ምንድነው ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡- የእኛ ኮንትራክተሮች እውቀቱና ችሎታው ቢኖራቸውም በሀገር ውስጥ የተገደቡ ናቸው። በእኛ ሀገር ገበያ ብቻ ነው የምንሳተፈው። የግለሰብ ኩባንያዎች ናቸው። የግለሰብ ኩባንያዎች ደግሞ በግለሰቡ አቅም ጥንካሬ ላይ የሚወሰኑ ናቸው። ያ ይመስለኛል አንዱ ችግር።
ሌሎቹ እንደ ሱር አይነት ትላልቅ ኩባንያዎች በአብዛኛው መንገድ ላይ ነው የሚሰሩት፤ በዚህም ውጤታማ ናቸው። የእኛ ኮንትራክተሮች በመንግስት ፖሊሲ ደረጃ ተደግፈው ወደውጭም ሄደው ሰርተው ጠንካራ የሚሆኑበት መንገድ ከተቀረጸ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደረሳል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከመንግስት ጋር የምትሰሩበት የተቀናጀ መድረክ የላችሁም ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– የኮንትራክተሮች ማሕበር አለ። እነሱ እየተጠናከሩ በሄዱ ቁጥር እንደነዚህ አይነት ችግሮች እየተፈቱ ይሄዳሉ የሚል እምነት አለኝ። በጣም መጠናከር አለበት ። ማህበሩን አለማጠናከራችን የራሳችን ድክመት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኮንትራክተሮች ለፕሮጀክቶች ስራ ገንዘብ ሲፈልጉ ከባንኮች ብድር የማግኘት ሁኔታው ምን ይመስላል?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– የባንክ ብድር ለማግኘት እድሉ አለ። ይህ ግን እንደ የድርጅቶቹ አቅምና የባንክ ግንኙነት የሚወሰን ነው። ይሄም ቢሆን ለኮንትራክተሩ የሚያግዙ ነገሮች በመንግስት ፖሊሲ የተደገፉ ነው መሆን ያለባቸው። ለምሳሌ ከቀረጥ ነጻ ሁነው እንዲገቡ ብዙ ነገሮች ይፈቀዱልናል። ይሄ ለማበረታታት የሚደረግ በመሆኑ የሚደገፍ ነው። በዚህ ረገድ መንግስት ትልቅ ስራ ሰርቷል፤ አግዟል ። ማሽኖች ስናስገባ የታክስ ፕሪቪሌጅ አለን።
ትልቁ ነገር በተናጠል ሳይሆን በተደራጀ መልኩ ለመንግስት የሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ ይችላሉ። መንግስትም ከየትም አያመጣውም። ይሄ ይሄ ብለህ በተደራጀ መልኩ ጥያቄ ስታቀርብለት ችግሮች የሚፈቱ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– አዲስ አበባ ላይ ብዙ የመንደር ውስጥ መንገዶች በዘመናዊ መልኩ አልተሰሩም። ይሄን እንዴት ነው መፈታት የሚችለው ?
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– የከተማ መንገዶችን ከከተማው እድገት እኩል አስቦ ወይንም ቀድሞ ማስፋት ያስፈልጋል። ይሄንን በተመለከተ የአዲስ አበባ የመንገዶች ባለስልጣን ብዙ መንገዶችን እየሰራ ነው። ያም ሆኖ እየሰራም እያለ ትልቁ ነገር አቅምም ይወስነዋል። አቅም ስል በጀት ማለቴ ነው። ለምሳሌ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ አምስት ፈጣን መንገዶችን እንስራ ቢባል ትልቅ ገንዘብ ያስፈልጋል። ከሰሜን ወደ ደቡብ አንድ ስድስት ፈጣን መንገድ ያስፈልገናል ብንል ግዙፍ በጀት ይጠይቀናል።
ከበጀት ጋር የተያያዘ ነገር ካልሆነ በስተቀር በከተማው አስተዳደር በኩልም ብዙ እቅዶች ያሉ ይመስለኛል። በአጠቃላይ እየተሰራ ያለው ስራ በጣም ጥሩ ነው። ከከተማው እድገት የሚመጥኑ ብዙ ነገሮች መታሰብ አለባቸው የሚለውን ሀሳብ የመንገድ ኤጀንሲዎቹ የበለጠ ቢያብራሩት ጥሩ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመ፣ን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመ ሰግናለን።
ኢንጂነር ብርሀኑ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
ወንድወሰን መኮንን