አካባቢው በደን የተሸፈነ ነው። መሬቱ ደግሞ እጅግ በጣም ለም። የወደቀና የሚዘራ ፍሬ ሁሉ የሚበቅልበት፤ በጥቂት ቦታ ብዙ የሚታፈስበት። ምን ይሄ ብቻ ለእንሰሳት እርባታ ምቹ ነው። የወተትና የስጋ አገር ነው። አካባቢው የሚገኘው በቀድሞ አጠራሩ «አርሲ ክፍለ አገር» በአሁኑ ደግሞ »አርሲ ዞን›› ውስጥ ነው። ከዞኑ ከተማ አሰላ 60 ኪሎ ሜትር አካባቢ ራቅ ብሎ የዝዋይ ሃይቅ ተራራማ አካባቢን ተንተርሶ ይገኛል – የኤረራ የገጠር ቀበሌ ሰቀላ መንደር። መንደሩ ደግሞ ታታሪ፣ ስራ ወዳድ፣ ሃቀኛና ጉምቱ ሰው ለኢትዮጵያ አበርክቷል። እኚህ ሰው የዛሬው የ «ህይወት ገጽታ» እንግዳችን አድርገን አቅርበናቸዋል። ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶን። አቶ ገመቹ በተለያዩ መድረኮች በተለይም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያንዳንዱን የመንግስት መስሪያ ቤት ገመና ገላልጠው በማሳየት በክርክርና በአሳማኝ የሂሳብ መረጃና ማስረጃ ባለስልጣናትና የስራ ሀላፊዎችን በማርበድበድ ይታወቃሉ። ዛሬስ ምን አሉ?
ትልቁ ቤተሰብ
የአቶ ገመቹ አባት አቶ ዱቢሶ በሰቀላ አካባቢ የአገር ሽማግሌ፣ የተራበን የሚያበሉ፣ የተጠማን የሚያጠጡ ለአካባቢዋ ችግር ግንባር ቀደም መፍትሄ ፈላጊ፣ በስራቸውም ታታሪና ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ይጠቀሳሉ። ህይወታቸው ካለፈ በኋላ እንኳ ‹‹አቶ ዱቢሶ እንዲህ አድርጎልን ነበር›› በማለት የሚያነሳቸው የአካባቢው ሰዎች ‹‹ዋርካ›› እያሉ የሚጠሯቸው ሰው እንደነበሩ ይነገራል። በጎ ስራቸው ደግሞ ስማቸውን ከመቃብር በላይ አውሎታል። ለቤቱ ታላቅ የነበሩት እኚህ ሰው አራት ሚስቶች ነበሯቸው። ከእነሱም 19 ልጆች አፍርተዋል።
አቶ ገመቹ በ1957 ዓ.ም ከሁለተኛ ባለቤታቸው የተወለዱ ናቸው። የእሳቸው እናት 13 የወለዱ ሲሆን ለእናታቸው አምስተኛና የመጀመሪያ ወንድ ልጅ ናቸው። አባታቸው ከሌሎቹ ሚስቶቻቸው ሁለት ሁለት ልጆች ወልደዋል። በአሁኑ ወቅት የአቶ ዱቢሶ ቤተሰብ እስከነ ልጅ ልጆቻቸው ከመቶ በላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ዝምተኛው ልጅ
የያኔው ህጻን ያሁኑ ጎልማሳ አቶ ገመቹ የቤቱ ወንድ ልጅ ስለሆኑ እንደ ብርቅዬ ልጅ ቢቆጠሩም ልታይ ልታይ አይሉም። ተጨዋችም አይደሉም። ዝምተኛና እርግት ያሉ ነበሩ። ብዙ ጊዜ ከቤት አይወጡም፤ ከልጆችም ጋር አይጫወቱም። አልፎ አልፎ በአካባቢው የሚበሉ የእጽዋት ፍሬና ስር በመልቀም ከልጆች ጋር በደስታ ከሚያሳልፉት ውጭ። ለነገሩ ልጫወትም ቢሉ በመንደሩ ነዋሪዎች እንደ ሽንብራ ጥሬ ተበትነው ተራርቀው ይኖሩ ስለነበር ከልጆች ጋር ለመገናኘት ዕድሉም ጠባብ ነበር።
በልጅነታቸው ያስደስታቸው የነበረው ከእንቅልፋቸው ተነስተው ተንጣሎ የተኛውን የዝዋይ ሀይቅን ቁልቁል መመልከት ነበር። ከብቶች በመልካ ላይ ተሰማርተው ሳር ሲግጡ ማየት። ማታ ደግሞ ላሞች ጡታቸው አግቶ እየጮሁ ሲመጡ መመልከት ይሄ ለእሳቸው ትልቁ የደስታ ምንጭ ነው።
የፈተና መንገድ
በአካባቢው አባታቸውን በሃብትና በዝና የሚወዳደሯቸው ነበሩ። ከእነዚህም አንዱ አጎታቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ከሃብትና ከዝና ባለፈ ልጆችን በማስተማርም ይፎካከሯቸው ነበር። አባታቸውም በፉክክሩ አቶ ገመቹን ትምህርት ቤት ለመላክ ይከጅላሉ። “መቼ አድጎልኝ ትምህርት ቤት ባስገባሁት” እያሉ ይጓጉ ነበር። ልጅ ግን ለመማር ዝግጁ አልነበሩም። ሆኖም እድሜያቸው ትንሽ ከፍ ሲል ትምህርት ቤት መሄድ ግድ ሆነ። “እጅህን በራስህ ላይ አዙረህ ጆሮህን ንካ” ሲባሉ ግን እጃቸው ጆሯቸው ላይ መድረስ ባለመቻሉ ትምህርቱ አለፋቸው።
አቶ ገመቹ በሌላ ጊዜ የአጎታቸው ልጅ ትምህርት ቤት ሄዶ ሲመለስ ደብተር ይዞ መንገድ ላይ ያገኙታል። አሳየኝ ይሉታል “እምቢ” ይላቸዋል። ቤት ገብተው እሪታውን ያቀልጡታል። ሲያለቅሱ አባታቸው ትምህርት ቤት እንደሚገቡ በመንገር ደለሏቸው።
በማግስቱም ገበያ ይዘው ሄደው ኮትና ሱሪ ገዝተው በ1964 ዓ.ም በአካባቢያቸው ባለው ሚሽን ትምህርት ቤት አስገቧቸው። የአባትና ልጅ ፍላጎት ሰመረ። አራት ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ትምህርትን መከታተላቸውን ቀጠሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ሶስተኛ ክፍል ደረሱ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ግን የሚማሩባት ክፍልን ጣራ ነፋስ ወሰዳት። አማራጭ በማጣታቸውም በዛፍ ጥላ ስር ሆነው አጠናቀቁ። ችግሩን የተረዱት አባታቸው ለቀጣይ ትምህርት ወደ ኢረራ ወረዳ ይዘዋቸው ሄዱ።
አራተኛ ክፍል ለመመዝገብ ሲሞክሩ ግን ኮሚሽን ትምህርት ቤት የሚመጡ ተማሪዎች ሰነፎች ናቸው በሚል ምክንያት ሁለተኛ ክፍል መለሷቸው። ዳይሬክተሩን ቢለመኑም አሻፈረኝ በማለታቸው አማራጭ አጥተው ሁለተኛ ክፍል ተመዘገቡ።
ዳይሬክተሩን ግን በየቀኑ ይለምናሉ። “ከፈለክ ፈትነኝና ወደ ቀድሞ ክፍሌ መልሰኝ” በሚል ተማፀኑ፤ ሶስተኛ ክፍል እንዲገቡ ተፈቀደላቸው። አሁንም ግን ወደ አራተኛ ክፍል እንዲገቡ መለመናቸውን አላቆሙም። ትምህርት ቤቱ ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛ ለማስጀመር ህንጻ እየተገነባ ነው። አንድ ቀን አቶ ገመቹ የሚሰሩትን በማገዝ ላይ እያሉ ርዕሰ መምህራቸው ለጉብኝት ይመጣሉ። እየጎበኙም “አንተ ልጅ ስንተኛ ክፍል ገባህ” ሲሉ ይጠይቋቸዋል። እሳቸው “ሶስተኛ ክፍል” ሲሉ ይመልሳሉ። ዳይሬክተሩም እጃቸውን ይዘው በመውሰድ ትምህርት በተጀመረ በሁለተኛ ወር አራተኛ ክፍል አስገቧቸው።
ህልማቸው ተሳክቶ በትምህርታቸውም ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ድረስ የደረጃ ተማሪ ሆነው አጠናቀቁ። እጅ ጽሁፋቸውን ቆንጆ ስለነበረ መምህራኖቻቸው ሰሌዳ ላይ ያጽፏቸው ነበር። በጉብዝናቸው ከፍተኛ እምነትም ነበረችው። ስምንተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤታቸው 90 በመቶ በማምጣት ነበር ያለፉት።
ህይወት ቀጥሏል። በአሰላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1972 ዓ.ም መከታተል ቀጠሉ። በ1973 ዓ.ም ግን እናታቸውን በሞት አጡ። በጊዜው በሀዘናቸው ምክንያት ከክፍል ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ። ከዚያ ውጪ እስከ አስረኛ ክፍል አንደኛ እየወጡ ነው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት። በመምህራን ያላቸው ተወዳጅነት ከፍተኛ ነበር። መፅሃፍት እንዲያነቡም ያግዟቸው ነበር። በቤታቸው ምግብ ያበሏቸውም ነበር። ይሄ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ።
አስረኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ የትምህርት ፖሊሲውን ለመለወጥ በአገር አቀፍ ደረጃ በአምስት ትምህርት ቤቶች ፓይለት ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የአሰላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበርና ፕሮጀክቱ ከአንድ እስከ አስር የሚወጡ ተማሪዎች በተለያየ ሙያዎች ማሰልጠን ነበር። እድሉን አግኝተው እሳቸውም በአካውንቲንግ ሙያ ሰለጠኑ። በጥሩ ውጤትም አጠናቀቁ። ጎን ለጎን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ለመግባትም የአስራ ሁለተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወሰዱ።
እልኸኛው ገመቹ
ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ፈተና ከማለፍ በተጨማሪ በእረፍት ሰዓትን መሰረተ ትምህርት ማስተማር ያስፈልጋል። አቶ ገመቹ በአካባቢያቸው እንዲመደቡ ቀበሌውን በደብዳቤ ጠየቁ። ቀበሌው ግን ወደ ባሌ መደባቸው። በጊዜው ከአካባቢው በመራቃቸው በየሳምንቱ በወጣቶች የውይይት መድረክ ለመሳተፍ አለመቻላቸውን ለቀበሌው በማመልከታቸው እንደ አመፀኛ ተቆጥረው ነበር። በዚህ እልህ ገብተው ቀበሌው ወደ አካባቢያቸው እንዲቀይራቸው በተደጋጋሚ ጠየቁ። መልሱ ግን ‹‹አንቀይርም›› ነበር።
ይባስ ብሎ “አትሄድም ወይስ ትሄዳለህ” በማለት የማህበሩ ሊቀመንበር አስፈራሯቸው። እሳቸውም ተናደውና እልህ ይዟቸው አልሄድም አሉ። ሊቀመንበሩም አገር ወዳድ አይደለህም በማለት ‹‹መልቀቂያም አይሰጥም፤ መሰረተ ትምህርት ማስተማርህን የሚገልጽ ደብዳቤ አይጻፍም›› አሏቸው። ጓደኞቻቸው እንዳይጎዱ ቢለምኗቸውም አሻፈረኝ ብለው ወደ ቤተሰባቸውም ተመለሱ።
ከተመለሱ በኋላም በቀበሌያቸው ማስተማር ጀመሩ። መስከረም ደረሰ። የአገር አቀፍ ፈተናም ወጣ። አልፈው አዲስ አበባ ዩየኒቨርሲቲ ተመደቡ። እድል ቀንቷቸው መሰረተ ትምህርት ማስተማራቸውን ከሚኖሩበት ቀበሌ አጻፉ። በአስተማሪዎቻቸው በኩል ደግሞ መልቀቂያና ውጤታቸውን በድብቅ አስወጡ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንም ተቀላቀሉ።
የገና ጎርፍ
አቶ ገመቹ የደረሳቸው መማር የሚፈልጉትን ትምህርት ነበር – አካውንቲንግ። ይህን ትምህርት የፈለጉበት ምክንያት ግን ፈገግ ያሰኛል። ከሰዎች ጋር ሳይጋጩ ስራቸውን ለመስራት በማሰብ ነው። ዛሬ ላይ ቆመው ሲያስቡት ግን እንደ አካውንቲንግ ከሰዎች የሚያጋጭና የሚያገናኝ ሙያ የለም።
በ1976 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ አንድ ሺ ተማሪዎችን በመቀበሉ ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ነበር። በዚህ ምክንያት 250 የንግድ ኮሌጅ ተማሪዎች አዲስ ተገንብቶ ወደ ነበረው የህንጻ ኮሌጅ ተሸጋገሩ። ከተላኩት ውስጥ እንግዳችን አንዱ ነበሩ።
የህንፃ ኮሌጅ ተማሪዎች ልምድ ቀን መተኛት ሌት ደግሞ ዲዛይን ሲሰሩ ማደር ነው። በዚህ ምክንያት ሌሎች ተማሪዎች ይዘናጉ ነበር። በተቃራኒው የስድስት ኪሎ ጓደኞቻቸው ቀን በጥናትና በግርግር ነው የሚያሳልፉት። በዚህ ምክንያት አብረዋቸው ከሄዱት 55 በመቶ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት በገና ጎርፍ ተወሰዱ። እሳቸውም ተፍጨርጭረው ለትንሽ ጎርፉን አለፉ። ወደ ስድስት ኪሎ ከጓደኞቻቸው ጋርም ተደባለቁ።
በውጤቱ ግን በጣሙን አዝነዋል። ለማሻሻልም
ከፍተኛ ትግል አደረጉ። ሆኖም ዝቅተኛ ውጤት መጀመሪያ አስመዝግቦ ከፍ ለማለት መጣር ውሃን ሽቅብ እንደመግፋት ሆነባቸው። ሆኖም የአቅማቸውን ታግለው በአጠቃላይ ውጤት 2 ነጥብ 47 በመያዝ ከፍተኛ ነጥብ ካላቸው አስር ተማሪዎች ውስጥ ሆነው መመረቃቸውን ያስታውሳሉ።
የአምስት መቶ ብር ደመወዝተኛ
በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ የሚጨርስ ተማሪ በእጣ ወደ ስራ ይመደባሉ። እርሳቸውም የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስቴር በ500 ብር ደመወዝ ስራ ጀመሩ። ለግብር፣ ለእናት አገር ጥሪና ለዩኒፎርም ተቀንሶ 383 ብር ይደርሳቸዋል። በሚኒስቴሩ ካሉት ሶስት የስራ ዘርፎች በፋይናንስ የስራ ክፍል ነበር የተመደቡት። የአራት ድርጅቶች የፋይናንስ ትንተና በማድረግ ምክረ ሀሳብ የማቅረብ ስራ ተሰጣቸው። የቅርብ አለቃቸው የነበሩት አቶ ምህረተአብ ሃጎስ ጠንካራ ባለሙያ እንዲሆኑና ለዛሬው ማንነታቸው መሰረት እንደሆኑዋቸው ይመሰክራሉ። በ1984 ዓ.ም የሽግግር መንግስት ሲቋቋም በሚኒስቴሩ የሂሳብ ክፍል ኃላፊ ሆነው ለስድስት ወራት ሰሩ።
የስራ ሽክርክሪት
በኦሮሚያ ክልል የንግድ ቢሮ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሀላፊ በመሆን ለስድስት ወራትም ሰርተዋል። ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለነበሩት አቶ ሀሰን አሊ አማካሪ እንዲሆኑ ወደ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተዛውረው ለሁለት አመት ተኩል በአማካሪነት ማገልገላቸውን ይናገራሉ።
በእድሜም ሆነ በልምድ እየበሰሉ የመጡት አቶ ገመቹ በጊዜው አዲስ እየተቋቋመ ወደ ነበረው ኦሮሚያ ልማት ማህበር እንዲዛወሩ ሲጠየቁ ‹‹ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ›› ምክንያታቸው ደግሞ ወደ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሄዱ ጡረታ ይቀርብኛል የሚል ነበር። የክልሉ አመራሮችም የተወሰነ ደመወዛቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት፤ ቀሪውን ከልማት ድርጅቱ እንዲወስዱ በማድረግ የጡረታ ባለመብት እንደሆኑ ያዛውሯቸዋል። ለስድስት ወራት እንደሰሩም በድጋሚ ለሌላ ለላቀ ሀላፊነት ይታጫሉ።
ሹመቱ የኦሮሚያ ክልል የስራና ከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊነት ነበር። አቶ ገመቹ “ከእኔ ሙያ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የማልፈልገው ቦታ ነው” በማለት አሻፈረኝ አሉ። ከሃላፊዎቹ ጋር ብዙ ተጨቃጨቁ፤ “ስራ እለቃለሁ” እስከማለት ደረሱ። አመራሮቹ ግን አልተቀበሏቸውም። የወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኩማ ደመቅሳና ምክትላቸው አቶ ሀሰን አሊ፤ ሌሎች ስራ አስፈጻሚ አባላት እሳቸውን ለማሳመን ስብሰባ ተቀመጡ። በቢሮው ያለው ችግር “ካንተ ውጪ አይፈታም” አሏቸው። እንዲሄዱም ግፊት አደረጉባቸው። እሳቸው ግን ቅሬታቸውን እያሰሙም ቢሆን ሃላፊነቱን ተቀበሉ።
የታጩበት ቦታ ለሙያቸው ቅርብ አይደለም። ደግሞም ቢሮው ‹‹በሙስና የተጨማለቀ ነው›› የሚል የጎደፈ ስም አለው። “በዚያ ቤት ውስጥ ገብቼ መጨማለቅ አልፈልግም። ስሜን መጠበቅ እፈልግ ነበር” ይላሉ ስለወቅቱ ስሜታቸው ሲናገሩ። ደግነቱ ብዙ ሳይቆዩ በሶስተኛ ወራቸው ለቀቁ።
ትምህርት እንደገና
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በውጭ ሀገር ለመማር በመጻጸፍ ብዙ ገንዘብ አውጥተዋል። በክፍያ አቅም ማነስም በተደጋጋሚ ሃሳባቸውን ቀይረው ትተዋል። አንድ ቀን ግን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የክልል ዘርፍ ሪፖርት አድርግ ይሏቸዋል። ምን ሪፖርት እንደሚያደርጉ አልተነገራቸውም ነበር። በመጨረሻ ግን ትምህርት እንዲማሩ መሆኑ ተነገራቸው። ፎርሙን ሙሉ። በ1988 ዓ.ም ለትምህርት ወደ ተባበራቸው እንግሊዝ አቀኑ። በዚያ በግላስኮ ካሊዲኒያን ዩኒቨርሲቲ ‹‹ፋይናንሻል ማኔጅመንት›› አንድ ዓመት ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ። ለትምህርት ልዩ ፍቅር ያላቸው አቶ ገመቹ በፕሮፌሽናል አካውንታሲ ለመቀጠልም ተፈትነው አለፉ።
ትምህርት እስከሚጀመር ስድስት ወር እረፍት ስለነበረ ቤተሰብ ጠይቀው ለመመለስ መንግስትን አስፈቅደው ወደ አገር ቤት መጡ። ከቤተሰባቸው ጋር ካሳለፉ በኋላ በመስከረም ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚመለከተውን አካል በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አለመፈቀዱ ይገለጹላቸዋል። ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው ዕለት ለጥያቄያቸው ምላሽ ሲሹ ለጓደኞቻቸው ተፈቅዶ እሳቸው መከልከላቸውን ሰሙ።
አቶ ገመቹ ለሌሎቹ ተፈቅዶ ለእሳቸው ለምን
እንደተከለከሉ ይጠይቃሉ። “ወደ አገር ቤት ልመለስ ብልህ ጠይቀሀል” ይሏቸዋል። እሳቸውም ቆፍጠን ብለው “ወደ አገር ቤት መመለስ ወንጀል ነው እንዴ?” ይላሉ። ጸሀፊውም “ይህ የመንግስት ውሳኔ ነው” አሏቸው። “እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን” ብለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ለኦሮሚያ ክልል መመለሳቸውን በመግለጽም ስራ እንዲጀምሩ ጥያቄ አቀረቡ።
ስኬት በአዲስ ሃላፊነት
ከሳምንት በኋላም ተጠርተው የኦሮሚያ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሰሩ ሀላፊነት ተሰጣቸው። አዲስ የተቋቋመ መስሪያ ቤት ነበር። የተቋሙን ስራ የንግድ ፍቃድ በመውሰድ ጀመሩ።
አቶ ገመቹ የተቋሙን ስኬት “በህይወቴ የረካሁበት ነው” ይላሉ። ለውጡን በአይናቸው ያዩበት እንደነበረ ያነሳሉ። ሰራተኞቹም ልጅ ወልደው ቀርጸው እንደሚያሳድግ ኮትኩተው ያሳደጓቸው እንደሆኑ በድፍረት ይናገራሉ። ሰራተኞቻቸው እሳቸው ትክክል ናቸው ብለው ካመኑ “ገደል ግቡ ብላቸው እንኳ ገደል የሚገቡ ነበሩ” ይላሉ በአድናቆት። ከዜሮ አንስተው በሁለት እግሩ ማቆማቸውንም ይናገራሉ። የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል። ድርጅቱ ከዜሮ ተንስቶ እስከ ለቀቁበት ድረስ የ500 ሚሊዮን ብር ባለቤት ሆኖ ነበር። ለ11 ዓመታት በሃላፊነት ቆይተውም በካሳንችስ አካባቢ የዋና መስሪያ ቤቱ ኦዳ ታወር ህንፃ ግንባታን አስጀምረዋል።
ጥርሱ የተሳለው ዋና ኦዲተር
በ2000 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው አቶ ገመቹን ቢሯቸው ጠሯቸው። “የስራ ልምድህን አምጣ” አሏቸው። ለምን ብለው ሳይጠይቁ ልምዳቸውን ሰጡ። ከቀናት በኋላ የፌዴራል ዋና ኦዲተር እንዲሆኑ መፈለጋቸው ተነገራቸው። “ከቤተሰብና ከጓደኞቼ ጋር ልምከርበት” አሉ። ከእራሳቸው፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸውም መከሩ። የተሰጣቸውን ክብርና እምነት በማሰብ “ሁልጊዜ እምቢ ከማለት የተወሰነ ጊዜ ሰርቼ እለቃለሁ” በሚል ሹመቱን ተቀበሉ።
በኦዲት ትምህርት ውጤታቸው ጥሩ ቢሆንም ስለተመደቡበት ተቋም ግን ብዙም እውቀቱ አልነበራቸውም። ሆኖም ከስራው ጋር ለመላመድ ብዙ አልፈጀባቸውም። ፈጣሪ ሰጠኝ በሚሉት ጸጋ ባላቸው ተሰጦ በመስራት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት አልተቸገሩም። ለሰራተኞቻቸው የተግባር አርዓያ በመሆን የመሪነት ሚናቸውንም ቀጥለዋል።
አቶ ገመቹ ሃላፊነታቸውን መወጣት ብቻ ሳይሆን ውለው ሲያድሩ ስራውን በጣሙን ወደዱት። በዚህ ሀላፊነት አገርን ማገልገል የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን አመኑ። ስራው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሚንስትሮች ምክር ቤትና በተወሰነ ደረጃ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱን የተቋማት ክፍተት ለማሳየት፤ መፍትሄዎችን ለማመላከት ዕድል የሰጠ ነው።
ለ11 ዓመታትም የፌዴራል ተቋማትን ኦዲት በማድረግ ችግሮቻቸውን አንጥረው አሳይተዋል። በአሰራራቸው ግልጸኝነት እንዲሰፍንና እንዲሻሻል፣ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ህጸጾች እንዲታረሙ ታትረዋል። ተቋሙ የሰላ ጥርስ እንዲኖረውም የድርሻቸውን እያበረከቱ መሆናቸው ይሰማቸዋል።
አገሪቱ በሙስናና በብልሹ አሰራር ስትዳክር፣ ተቋማት ሚናቸውን ረስተው ለሙስና ሲጋለጡና ሃላፊዎች ጥቅማቸውን ሲያስቀድሙ፤ አቶ ገመቹና የሚመሩት ተቋማቸው ሳይንበረከኩ በአደባባይ ህጸጾቹ እንዲታረሙ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮኸዋል። ለዚህም ምስክሮቹ ያለፉት 11 ዓመታት የኦዲት ሪፖርቶች ናቸው። “የእኔ ሀላፊነት ከውጪ የሚመጣን ተጽእኖ ተጋፍጦ በገለልተኛነት በጥራት፣ በጥልቀትና በብዛት ተቋማትን ኦዲት ማድረግ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ዓላማ እንደሌለን በስራ ማሳየት ነው” ይላሉ። ይህን በተግባር ማረጋገጣቸውንም በድፍረት ይናገራሉ።
እጁ የማይጠመዘዝ ጀግና
ዋና ኦዲተር በሚሰራቸው ኦዲቶች ልክ ጫና ለማድረግ የሚሞክሩ እንዳሉ ይናገራሉ። ባለፉት ዓመታት ጥራት ያለው ስራቸው፣ የህዝቡና የአንዳንድ ሰዎች ድጋፍ ጫናውን እንዳቀለለላቸውም ይገልፃሉ። “ፈጣሪ የሰጠኝ ጸጋ እውነትን መናገርና አለመፍራት ነው። ክፉ ነገር በሰው ላይ አለማድረግ ነው። በእኔ ላይ ደግሞ ሌሎች እንዳያደርጉ ፈጣሪ ይጠብቀኛል። ስለዚህ ተጽዕኖ ቢኖርም በግሌ ጉዳት አልደረሰብኝም” ይላሉ።
በሚሰሯቸው የኦዲት ስራዎች በተለይም ከደህንነት ተቋማት ቀጥታ የሚመጡ ክርክሮች ነበሩ። ዋና ኦዲተር በሌለበትና እራሱን በማይከላከልበት በሚንስትሮች ምክር ቤት ስም ማጠልሸት ሁኔታም ነበር። ሆኖም የተወሰኑ ሰዎችና ፓርላማው ድጋፍ ያደርጉ ስለነበር ተቋማቸውና እሳቸው የሚመጣውን ጫና ተቋቁመው አልፈዋል። በሚሰሩት ስራ ጥራትና ታታሪነት፣ ለግል ጥቅም አለመንበርከክ የተቋማቸውን ነፃነት በማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን በጀግንነት ተወጥተዋል።
አቶ ገመቹ እጅግ ሲበዛ የመርህ ሰው ናቸው። ሰው በእምነት ለገባው ቃል መኖር አለበት ይላሉ። እያንዳንዱ ስራቸውና ህይወታቸው ከመርህ ጋር የተጣበቀ ነው። “እኔ ፓርላማ ፊት ሆኜ ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ ቃል ገብቻለሁ። ይህን ቃል እስከሞት መጠበቅ አለብኝ። በገደል እንኳን አስር ጉድጓድ አላበሰብስም አንድ ነው። በመሆኑም ቃሌን መጠበቅ አለብኝ” ይላሉ።
አብሪ ባህሪያት
አቶ ገመቹ ከሰው የሚለያቸው ብዙ አብሪ ባህሪያት አሏቸው። የመጀመሪያው ለስራ ያላቸው ፍቅር ነው። ከቢሮ የሚወጡት በእራት መቅረቢያ ሰዓት ነው። ቅዳሜና እሁድ የስራ ቀናቸው ነው። በቢሯቸው ያሳልፋሉ። በሆነ ምክንያት ጸሃይ ሳትጠልቅ ድንገት ወደ ቤታቸው ቢሄዱ እንኳን ቤተሰቦቻቸው ‹‹በጤናህ አይደለም›› ብለው ሊደነግጡ ይችላሉ። አስገራሚው ነገር 32 ዓመታትን በመንግስት ስራ ላይ ሲያሳልፉ እረፍት የወጡት ለ15 ቀናት ብቻ ነው። ይህም እረፍት የሰርጋቸው ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ። የእሳቸው ህይወት ስራና ስራ ብቻ ነው። “እረፍት ውጣ ብትለኝም ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም” ብለው ፈገግ አድርገውኛል። ያለስራ ማሳለፍ የገደል አፋፍ ላይ እንደመሆን እየተሰማቸው።
ሌላው የተለየ ባህሪያቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ስብሰባ ሲሄዱ ስብሰባው እንዳለቀ ቢሯቸው ሲበሩ መመለሳቸው ነው። ጊዜ ቢኖራቸው እንኳ እንደሰው ልዝናና እቃ ልሸምት አይሉም። አምስት ሳንቲም እላፊ ገንዘብ ከመንግስት ወደ ኪሳቸው አትገባም። ሃላፊዎች በገንዘብ አወጣጥ ጠንቃቃና አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ያምናሉ። እምነታቸውንም ለሰራተኞቻቸው በተግባር ያሳያሉ።
ሌላው ከገንዘብም በላይ አገርን ማገልገል የሚል እምነት አላቸው። ገንዘብ ባይጠሉም አገርን ከማገልገል በላይ እንዳልሆነ ያምናሉ። ለዚህም ደመወዛቸውን በመቀነስ ሰርተው አሳይተዋል። ከኦሮሚያ ክልል ወደ ዋና ኦዲተርነት ሲመጡ ከሰባት ሺ ብር ደመወዝ ወደ አምስት ሺ ብር ቀንሰው ነው። ዋና ኦዲተር ሆነም ከእሳቸው በታች ያሉ ዳይሬክተሮች በደመወዝ ይበልጧቸው ነበር። ገንዘብ ከአገር ማገልገል ቢበልጥባቸው ኖሮ ውጭ አገር ሲመላለሱ እንደብዙዎቹ በዚያውም ኮብልለው መቅረትም ይችሉ ነበር።
በተለይም የፖለቲካ አባል ሳይሆኑ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ታምነው መሰጠታቸው ከፈጣሪ የተሰጣቸው ጸጋ ነው። እንደ አንድ ዜጋ የሚችሉትን ጠጠር መወርወራቸውን ይናገራሉ። ለዚህ አብረዋቸው የሰሩ ሰዎችን ምስክር ናቸው።
ቤተሰብ
አቶ ገመቹ፤ ሚስት ያጩት ዩቨርሲቲ ሲገቡ ነው። ሽማግሌ የላኩትም ትምህርት ሲጨርሱ ለማግባት ነበር። በቃላቸው መሰረትም ዲግሪያቸውን ባገኙ በዓመታቸው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የነበሩ ባለቤታቸውን አግብተዋል። ትዳራቸውም ተባርኮላቸው ከባለቤታቸው አንድ ወንድና አራት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። የመጀመሪያ ልጃቸው በምህንድስና፣ ሁለተኛዋ በአካውንቲንግ፣ ሶስተኛዋ በማኔጅመንት ተምረው አጠናቀዋል። አራተኛዋ ልጃቸው የአራተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ስትሆን፤ የመጨረሻዋ ደግሞ የሶስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ነች። አቶ ገመቹ በቤተሳባቸው እጅግ ስኬታማና ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንደ መውጫ
ለእሳቸው የስራና የኑሮ ደረጃ በእውነትና በመርህ መኖር ነው። ጥሮ ግሮ በላቡ መኖር የሚችል ሰው ይወዳሉ። ጠንካራና ስኬታማ ቤተሰብ የሚመሰርት ሰው ለእሳቸው አገር ወዳድ ነው። ሁሉም በያለበት ተግቶ በመስራት ማህበረሰቡን መለወጥ እንደሚችል ያምናሉ። እንደዚህ አይነት ዜጋ ጥሩ መሪ መሆን እንደሚችልም ይናገራሉ። ለዚህ ነው የህይወት መንገዳቸውን በሙሉ ፍቃደኝነት ሌሎችን እንዲያስተምር የሚያጋሩት።
‹‹መሪነት ከፊት ብቻ መሆን አይደለም›› ይላሉ፤ መንገድ የሚያሳይ፣ ሌሎችን የሚያስከትል፤ የጋራ ዓላማ ያለውን ሃብት የሚያንቀሳቅስ ጭምር እንጂ። እየተማረና እያደመጠ የሚመራ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በፍቅር የሚገስጽና የሚቀጣ ነው። ከስሩ የተሻሉ እንዳሉ በማሰብ የሌሎች ሃሳብ ተቀብሎ አካታች መሆን ነው። ራዕይ ያለውና እርሱንም ለሌሎች በማጋራት በዙሪያው የሚያሰልፍ መሆን አለበት። ንቁና እረፍት የሌለውም ጭምር። አብዛኛው በዚህ መንገድ ቢቃኝ ምርጫቸው ነው። ለወገኖቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያውያንም እድገት፣ ብልፅግናና የደስታ ዘመን ይመኛሉ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ