በዕድሜ ተገቢነት የደበዘዙ ፉክክሮች

የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በድሬዳዋ ስቴድየም እየተካሄደ ይገኛል። ቻምፒዮናው ወጣትና ተተኪ አትሌቶች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ለመወከልና ወደታላቅነት የሚሸጋገሩበት ቢሆንም ከዕድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የጎሉ ችግሮች ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው። ይህም በተለያዩ ውድድሮች የሚደረጉ ፉክክሮችን አደብዝዞ ቻምፒዮናው ዛሬ አምስተኛ ቀኑን እንዲይዝ አድርጓል። የውድድሮች ተመልካች ማጣትና ለአሸናፊዎች የሚሰጠው ሽልማት አጓጊ አለመሆንም ከዕድሜ ተገቢነት ባሻገር ብርቱ ፉክክሮች እንዳይታዩና ቻምፒዮናው እንዳይደምቅ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኞቹ ናቸው።

የቻምፒዮናው አላማ ናይጄሪያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ነው። ይሁን እንጂ ከዕድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ችግር ፌዴሬሽኑ በናይጄሪያው ቻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶችን በድሬዳዋው ቻምፒዮና በሚያስመዘግቡት ውጤት መሰረት እንደማይሆን መጠቆሙን ተከትሎ ፉክክሮቹ በተወሰነ ደረጃ ደማቅ እንዳይሆኑ አንዱ ምክንያት እንደሆነ መታዘብ ተችሏል።

ከስፖርት ቤተሰቡ እስከ ባለሙያዎች፣ ከአሰልጣኞች እስከ ራሳቸው ተወዳዳሪ አትሌቶች እንዲሁም የውድድሩ ባለቤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረስ የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ ማደባበስ በማይቻልበት ሁኔታ ጎልቶ መታየቱ ቢታመንም ውድድሮች ቀጥለዋል። ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ የተለያዩ የፍፃሜ ፉክክሮችን እያስተናገደ የሚገኘው ቻምፒዮናም እየተጋመሰ ይገኛል።

ትናንትና ከትናንት በስቲያ በተካሄዱ በርካታ የፍፃሜ ውድድሮች አሸናፊዎች የተለዩ ሲሆን፣ ዛሬን ጨምሮ በቀጣይ ሦስት ቀናትም በርካታ የፍፃሜ ውድድሮች ይከናወናሉ። ኢትዮጵያ በተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ የሆነችባቸው ርቀቶችና በድሬዳዋው ቻምፒዮና የፍፃሜ ፉክክር የተደረገባቸውን ስንመለከት፣ ባለፈው ረቡዕ የተቋጨው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች 5ሺ ሜትር ፍፃሜ ቀዳሚው ነው።

በእዚህ የፍፃሜ ፉክክር አትሌት ገመኔ ማሚቴ ከኮዬፈቼ ክለብ 15:48.07 ርቀቱን በማጠናቀቅ አሸንፋለች። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አትሌት የሆነችው ማስተዋል ሙሀባ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የተመዘገበላት ሰዓትም 15.48.36 ነው። የአፍረንቀሎ አትሌቲክስ ክለብ አትሌቷ ዓለምነሽ ጥላዬ በ15:48.80 ሰዓት ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች።

በተመሳሳይ እለት በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች 800 ሜትር ሴቶች ፍፃሜ፣ አስቴር አረሬ ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን በ2:06.55 አሸናፊ ስትሆን፣ አልጋነሽ ማረማ ከጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ 2:06.79 በመግባት ሁለተኛና ሹሬ ጃርሶ በ2:07.20 ከአዳማ ከተማ ሦስተኛ ሆናለች።

ተመጣጣኝና የተሻለ ፉክክር በታየበት ከ18 ዓመት በታች የወንዶች 800 ሜትር የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛው አትሌት ተገኔ ወንድሜነህ 1.50.36 በሆነ ሰዓት ሲያሸንፍ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚዎቹ ኡመር ሀሰን በ1:50.84 ሰዓት፣ስጦታው ዳዊት በ1:50.98 ሰዓት ተከታትለው በመግባት ሁለተኛና ሦስተኛውን ደረጃ ይዘዋል።

ከ18 ዓመት በታች 800 ሜትር የሴቶች ፍፃሜ ሀረገወይኒ ካልዩ ኢ.ኮ.ስ.ኮ ቀዳሚ ስትሆን 2:02.53 ያጠናቀቀችበት ሰዓት ነው። ጫልቱ ነጋሽ ከኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት 2:03.66 ሰዓት ሁለተኛ ስትሆን፣ ነጋሴ ጋሮምሳ ከቢሸፍቱ በ2:04.74 ቀጣዩን ደረጃ ይዛለች። ከ20 ዓመት በታች በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ሳሙኤል ቡቼ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 1:47.47 አሸናፊ ሲሆን አማኑ ገልግሎ በ1:48.65፣ ሀይሩ ሻውሜ በ1:48.79 ሁለቱም ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠና የብርና የነሐስ ሜዳሊያውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ከሌሎች ውድድሮች በተሻለ በርካታ ወጣቶች በታዩበት የ100 ሜትር ሴቶች ፍፃሜ ሲምቦኔ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በ12’26 ቀዳሚ ሆና አጠናቃለች። ትዕግስት ባንቴ ከተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ 12’31በማጠናቀቅ ሁለተኛ ስትሆን፣ ሩፎ ጥላዬ ከኦሮሚያ ክልል በ12’55 ሰዓት ሦስተኛ ሆናለች።

በቻምፒዮናው አራተኛ ቀን ውሎ ትናንት በርካታ የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በሁለቱም የዕድሜ ካታጎሪዎች ፍፃሜ ያገኙ ሲሆን፣ ዛሬ በ3ሺ ሜትር፣ በ10ሺ ሜትር ርምጃ እና በ200 ሜትር የሚካሄዱ የፍፃሜ ውድድሮች ይጠበቃሉ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You