«ስንት ወገን ከቦት ጦር የማይመልሰው ፤
እንዴት ጣና ያልቅስ ዕንባ አውጥቶ እንደ ሰው»…
ብዙዎች የጣና ጉዳይ አሳስቧቸው በቁጭት ከተናገሩት ቀንጨብ አድርጌ እኔም በቅኝቴ ላነሳሳው ወደድኩ። ጣና ሀብታችን ነው። ጣና መልካችን ነው። ዞር ዞረ እያሉ ሁሉም የሚያዩት የሀገር ኩራት ነው፤ ደግሞ ግርማ ሞገስ። ይህንን ሀብት ነው ዳዋ የወረረው አጠፋዋለሁ ብሎ የሚንደረደረው። እሱስ ታሟል አሉ መድሀኒት ነው ያጣው አለሁልህ ብሎ ቆሞ የሚያድነው።
በተፈጥሮ ሀብት በታደለች ሀገር በርካታ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ናቸው። ጣናን፣ ተከዜን፣ አዋሽ፣ አባይን፣ ገናሌን ማልማት ብንችል ዛሬ የሚራብ ዜጋ አይኖርም ነበር። ይህ ሁሉ ውሃ ባለበት ሀገር አንድ ኪሎ ሽንኩርት 40 ብር ሲባል ባልሰማን ነበር። ጣና ከሚሰጠው የተለመደው ጥቅም ውጪ ለመዝናኛነትና ለጉብኝት በማዘጋጀት ተዝቆ የማያልቅ ገቢ ማስገኛ ማድረግ ይቻል ነበር። ግን የለማ አዕምሮ ባለመኖሩ የጣና ህመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዷል። እውነት የዓድዋ ታሪካ ባለቤት ለእንቦጭ እጅ መስጠት ነበረበት? ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የገነቡ እጆች ጣናን ለማከም መሰብሰብ አልነበረባቸውም። ኢትዮጵያ ‹‹የለማ መሬት እንጂ የለማ አዕምሮ›› የላትም ማለት ይሄኔ ነው።
በተከዜ ውሃስ ምን እየሠራን ነው? ምንም። በአካባቢው ዓሣ በማስገር የሚተዳደሩ ወጣቶች በመንድ እጦት የአሰገሩትን ዓሣ ለገበያ ማቅረብ አልቻሉም። አንድ ጭልፋ ሽሮ ሃምሳ ብር በሚሸጥበት ሀገር የተከዜ ዓሣ የአሞራ ቀለብ ነው።
ከድህነት ለመውጣትና ጣናን ከህመም ለመፈወስ የለማ አዕምሮ ያስፈልጋል። የጣናን ችግር ለመቅረፍ እንሠራለንና እየሠራን ነው ከማለት ውጪ ከእንቦጭ አስፈሪነት አንፃር በመንግሥትም በኩል የተሠራ ጠንካራ ሥራ አለ ለማለት
አያስደፍርም። ለጣና ችግር መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የተቋቋመው ኤጀንሲ እቅድ ከማውጣት የዘለለ ሥራ አልነበረውም። እንቦጭ ግን ጣናን ሲወር የሰከንዶች ሽርፍራፊ ጊዜ አያባክንም። ተፈጥሮ የለገሰንን ሀይቅ እንቦጭ አይቀማንም ብሎ ወጣቱ ባይታገል ኑሮ እስከአሁን የጣና ሜዳ እንጅ የጣና ሀይቅ ማለት አንችልም ነበር።
በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺ ሄክታር በላይ የውሃው ክፍል ደርቋል። እርግጥ ነው የጣና ችግር የመድሃኒት እጦት ብቻ ሳይሆን የትኩረት እጦት ጭምር ነው። በርካታ ግሰቦችና ድርጅቶች ለእንቦጭ የሚሆን መድሃኒት አለን ቢሉም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ እንዳይገቡ ተደርገዋል። እውነት ጣናን የሚያክል የዓለም የስነ ህይወት ቅርስ ተቆርቁሮ መጮህ የሚችል አካል ቢኖር የትኛውም ሀገር ከኬሚካል እስከ ዘመናዊ የአረም መጥረጊያ ማሽን ከመርዳት ወደ ኋላ ይላል ለማለት ይከብዳል።
ጣና ደረቀ ማለት ባህርዳር ስሟም ወደ ሜዳ ዳር ይቀየራል ይባላል። ምክንያቱ ደግሞ የባህርዳር የስም መነሻ ጣናና አባይ ናቸውና። ጣና ደረቀ ማለት ከባህርዳር ቀጥሎ
ለዓይን የማይታይ ሜዳ ይፈጠራል። ጥገኛዋ ከተማም ሜዳ ዳር ከመባል የሚያተርፋት አይኖርም። የፎገራ ከብት እየተባለ የሚኮራበት በዓይነቱ ልዩ የሆነው ከብት የጣና ጥገኛ በመሆኑ እየጠፋ ነው። በደቡብ ጎንደር በጣና ዳር የከብት እርባታ በ51 ፐርሰንት ቀንሷል። ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል የነበረውና ጣና ሲነሳ አብሮ የሚነሳው የዓሣ ምርት በዓመት ከ20 ሺህ ቶን ምርት ወደ 1ሺህ ቶን ወርዷል። በጥቅሉ በአካባቢው ድህንት ተባብሷል። ከዚህ በላይ ሀገርን የሚያሳስብ ነገር ምንም የለም። በርካታ ሰዎች ጣናን ዳግም ላናየው እንችላለን በማለት በፎቶና በቪዲዮ የማስቀረት ሥራ እየሠሩ ነው። ይህ ስጋት የመጣው በየቀኑ ሁኔታ በመነሳት ነው። የእንቦጭ ጉልበተኛነትና የመንግሥት ዘገምተኛነት ተደራርበው የጣና ህመም አይሏል። ጣና ከ360 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው ቢሆንም ግማሽ አካሉ በጠላት ተወሯል። በዚህ ሁሉ ቦታ ዓሣ ማስገር ቆሟል።
ጣና በፌዴራልና በክልል መንግሥት በርካታ ቃል የተገባለት ቢሆንም ከቃል ያለፈ ሥራ የሠራ የለም። ስለዚህ አሁንም እንላለን ጣና ታሟል፤ እናድነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012
ሞገስ ፀጋዬ