ለዓባይ ውሃ 86 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ በማይጨበጠው የግብጽ አቋም ስትፈተን ኖራለች፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኢትዮጵያን ውድቀትና መፈራረስ የምትመኘውና ለዚህም አበክራ የምትሰራው ግብጽ አንድ ጊዜ ድርድር በሌላ ጊዜ ደግሞ ውንጀላና ስም ማጥፋትን እንደመርህ በመያዝ በሁለት ቢላዋ ኢትዮጵያን ለማረድ የማትቆፍረው ድንጋይና የማትስለው ሰይፍ አልነበረም፤ አሁንም የለም፡፡
ግብጽ ባለሁለት ቢላዋ መሆኗን የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ኢትዮጵያውያን ሊረዱ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያውያን ማደግና መበልጸግ ለግብጽ ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሰቻትን የተፈጥሮ ሃብት እንዳትጠቀም ልዩ ልዩ ሴራዎችን ከመጠንሰስ አንስቶ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ብድርና ድጋፍ እንዳታገኝ ያልሄደችበት መንገድ የለም፡፡ይባስ ብሎም ሀገሪቱ በሁከትና ብጥብጥ እንድትታመስ የእጅ አዙር ጦርነት ማካሄድና ተቃዋሚዎችን መርዳት በወጉ የሰለጠነችበት ተግባሯ ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ከአሁን በኋላ በግብፅ መሰሪነት ሊታለሉ አይገባም፡፡ ይኸው የግብጽ ተንኮልና ሴራ ድንበር ተሻግሮ አሜሪካን በአጋርነት አሰልፏል፡፡ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ጥቅም ለማስከበር ኢትዮጵያውያንን ለመስዋዕትነት ማቅረቧ የግብጽ አንዱ የሴራ አካሄድ መገለጫ መሆኑን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊረዳው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በገዛ ውሃዋ በራሷ ግዛት ውስጥ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ መገንባት ተፈጥሯዊ መብቷ መሆኑንና ማንኛውም ዓይነት ምድራዊ ኃይል ከመገንባት ሊያግዳት እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ለብሔራዊ ፕሮጀክታቸው ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈልዝግጁ መሆናቸውንም ለግብጽ ሊነገራት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን እንዳታደርግ የሚያግዳት ስምምነትም ሆነ ህግ ስለሌለ በቀጣዩ ሐምሌ ወር ውሃውን እየሞላች በቀሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄዷን ትቀጥላለች። በዚህ መሰረት በመጀመሪያ ዓመት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይሞላል፤ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ በአጠቃላይ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳል። እንዲህ እንዲህ እያለች ኢትዮጵያ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃውን እንደምትሞላ ግልጽ አድርጋለች።ይህ ለግብጽና መሰሎችዋ ባይዋጥላቸውም ኢትዮጵያውያን ግን እስከመጨረሻው የሚገፉበት አቋማቸውና መብታቸው ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ማህጸን በሚመነጨው የአባይ ውሃ ከ98 በመቶ በላይ የግብጽ ህዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሲሆንሀገሪቱም ይህንን ወንዝ በመጠቀም በዓለም ላይ ካሉት አትክልትና ፍራፍሬ ላኪ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ህዝብ ከ45 በመቶ የበለጠ አይደለም፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ አንድ አምፖል የሚያበራው ኢትዮጵያዊ ጭምር ተቆጥሮ እንጂ ከኤሌክትሪክ ሌሎች አገልግሎቶች የሚያገኘው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ከ11 በመቶ የዘለለ አይደለም፡፡
በሌላም በኩል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ድርቅ የምትጠቃና በምግብ ሰብልም እራሷን ያልቻለች ሀገር ናት፡፡
በውሃ ላይ ተቀምጣ ውሃ የሚጠማት ኢትዮጵያ በከተማም ሆነ በገጠር የንጹህ ውሃ አቅርቦቷ ከ60 በመቶ የበለጠ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ይህንን የድህነት ታሪክ መለወጥ ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ የተራበውን ህዝቧን ማብላት፤የተጠማውን ወገኗን ማጠጣት ትሻለች፡፡ በጨለማ ውስጥ ኑሮውን የሚገፋውንም ህዝብ ብርሃን ማቋደስ ታልማለች፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ የአባይን ውሃ ከመጠቀም የተሻለ አማራጭ አይኖራትም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን ለመለወጥ የሚያስችላቸውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ጅምራቸውን ለመጨረስም ከዳር ደርሰዋል፡፡ ይህ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህልውና ነውና ግድቡን ከመጨረስ የሚያግዳቸው ምንም ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012