የአደባባይ በዓላት የሠላምና የአብሮነት መገለጫ፣ የቱሪዝምም አቅም ሊሆኑ ይገባል!

ኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴትን የተላበሱ በዓላት ባለቤት ናት፡፡ እነዚህ በዓላት ደግሞ አንድም ሀገራዊ ገጽታን ተላብሰው የሚከበሩ፤ በሌላም መልኩ አካባቢያዊ እና ማኅበረሰባዊ ገጽታን ይዘው የሚከወኑ ናቸው፡፡ ከአካባቢያዊ እና ሀገራዊ ገጽታቸው አለፍ ሲልም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕል፣ የቋንቋ እና የታሪክ ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መዝግቦ የያዛቸውም በርካታ ናቸው።

በተለይ ከእነዚህ ሃይማኖታዊም ሆኑ ባሕላዊ በዓላት በአመዛኙ የአደባባይ በዓል እንደመሆናቸው፤ እነዚህ በዓላት ከፍ ያለ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ የእርስ በእርስ መተሳሰብና አብሮነት የሚገለጽባቸው ናቸው፡፡ ይሄ አብሮ መዋልና በዓላትን በጋራ የማክበር ሂደት ደግሞ በአንድም ከፍ ያለ ሠላምን የሚሻ፤ ሁለተኛም የሕዝቦች ዘርፈ ብዙ የባሕል ትሩፋቶች የሚንፀባረቅበት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ እነዚህ የአደባባይ በዓላት በአንድ በኩል የሕዝቦች አብሮነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በሕዝቦች አብሮነት ውስጥ ደምቆ የሚታይ የባሕል (የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ የባሕላዊ ክዋኔዎችና ሌሎችም) ክዋኔዎች ዓውድም ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ይሄ የአብሮነት እና የባሕል ክዋኔ ዓውድነቱ ተጣምረውና ከፍ ብለው እንዲገለጡ የሚያደርጋቸው የሠላም ድባብን የሚፈልጉም ናቸው፡፡

እነዚህ በዓላት ጎልተው ከሚገለጡባቸው ወራት መካከል ደግሞ መስከረም አንዱ ነው፡፡ ወርሐ መስከረም የዘመን መለወጫ በዓልን ጨምሮ፣ የመስቀል፣ የኢሬቻ፣ ዮዮ መስቀላ፣ ያሆዴ፣ ጊፋታ እና ሌሎችም ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩበት ነው፡፡ እነዚህ በዓላት ደግሞ በዋናነት ሕዝቦች በአብሮነት ወጥተው የሚያከብሯቸው የአደባባይ በዓላት ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ እነዚህ የአደባባይ በዓላት በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የብዝኃነት ዓውድ መሆኗ የሚገለጽባቸው ሲሆኑ፤ በሌላ በኩል ይሄ ብዝኃነት ከፍ ያለ ድምቀትን የተላበሰ ኢትዮጵያዊ ቀለም መገለጫዎች ናቸው። ለዚህም ነው በእነዚህ በዓላት የበዓሉ ባለቤት ከሚባለው የሃይማኖት ተከታይ ወይም የባሕሉ ባለቤት ከሚባለው ብሔርና ሕዝብ ባሻገር ያሉ ሃይማኖቶችና ብሔሮች ተሳታፊ ሆነው የሚገለጡበት፡፡

እነዚህ በዓላት የአደባባይ በዓላት እንደመሆናቸው፤ የበዓላቱ ተሳታፊዎች ደምቀው ሊታዩባቸው የሚያስችሏቸውን አልባሳትና ጌጣጌጦች ባሕልና እምነታቸው በፈቀደላቸው ልክ ተውበው የሚታዩት። ማንነትና እሴታቸውን ሊያሳይ በሚያስችላቸው ኅብረትም ባሕላዊ ጭፈራዎችና ክዋኔዎች ታጅበው የሚያከብሩት፡፡

ይሄ ሁነት ደግሞ ለበዓላቱ ከፍ ያለ ድምቀትና መስሕብን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ አልባሳቱ፣ ጌጣጌጥና ጭፈራዎቹ ተዳምረው የሚፈጥሩት ኅብር ለተመልካቹ ቀልብን የሚይዝ፤ ልብን በሐሴት የሚያረሰርስ ነው። ለዚህም ነው እነዚህ በዓላት በደረሱ ቁጥር ከውስጥም፣ ከውጪም የጎብኚዎች (ቱሪስቶች) ቁጥር ሲጨምር የሚታየው፡፡

ምክንያቱም፣ ጎብኚ ለዓይኑ የሚስብ ነበር ይፈልጋል፤ ልቡን የሚያስደስትነት፣ ለነፍሱም ሐሴትን የሚያጎናጽፈው ሁነት ይሻል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የአደባባይ በዓላት ደግሞ እነዚህን በሙላት የሚሰጡ ዓውዶች ናቸው፡፡ በአልባሳቱ የተማረከ ዓይንን፤ በጭፈራዎቹ ክዋኔ የተደመመ ልብን፤ በሃይማኖታዊ ሁነቶቹ የተመሰጠች ነፍስን፤ በእነዚህ በዓላት መመልከት የተለመደ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

ይሄ ብቻ አይደለም፣ እነዚህ በዓላት በሕዝቦች ከፍ ያለ የአብሮነት እና ወንድማማችነት ስሜት ታጅበው የሚከበሩ እንደመሆናቸው፤ ከድምቀትና ውበትነታቸው ባሻገር የሠላም ዓውድነታቸውም ጎልቶ የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሄ ሠላማዊ ሁነትም ነው በየጊዜው ቱሪስቶች በብዛት በበዓላቱ ላይ እንዲገኙና እንዲሳተፉ እያደረገ የሚገኘው፡፡

አሁን ያለንበት መስከረም ወር ደግሞ፣ እነዚህ በዓላት የሚከበሩበት እና የበዓላቱ ሁነቶች በብዛት የሚታዩበት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እነዚህን ሃይማኖታዊም ሆኑ ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት፤ በአንድ በኩል የአብሮነት መድረክነታቸው፤ በሌላ በኩል ኅብረ ብሔራዊነታቸው የሚፈጥረው የውበት ሰገነት መገለጫነታቸው፤ አለፍ ሲልም የቱሪዝም መስሕብነታቸው ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

ይሄ እንዲሆን ደግሞ የበዓላቱን የሠላም እሴት ዓውድነት ከፍ ባለ መልኩ እንዲገለጥ ማስቻል ይገባል። ምንም እንኳን ሕዝቡ የሠላሙ ባለቤት ሆኖ በዓላቱን የሚከውን ቢሆንም፤ እነዚህን ዓውዶች ለሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማዋል የሚፈልጉ ኃይሎች ይጠፋሉ ማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም በዓላቱ ከቀደሙት ጊዜያት ከፍ ባለ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከወኑ፤ የአብሮነት እና ወንድማማችነት መገለጫነታቸውን እንዲመሰክሩ፤ የቱሪዝም መስሕብነታቸውም ከፍ እንዲል ለማስቻል፤ ከዚህ በተቃራኒው ሊፈጸሙ የሚችሉ ጉዳዮችን ከወዲሁ መገንዘብና ሠላማዊነቱን ጠብቆ እንዲከናወኑ ማድረግ ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ትልቅ የቤት ሥራ ይሆናል!

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You