– የመጀመሪያው ዙር የእንስሳት መድኅን ዋስትና ሽያጭ ተጀመረ
አዲስ አበባ፦ አርሶ አደሩ በድርቅ ወቅት የሚደርስበትን ኪሳራ የእንስሳት መድኅን ዋስትና በመግዛት ሊያካክስ እንደሚገባ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የመጀመሪያው ዙር የእንስሳት መድኅን ዋስትና ሽያጭ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሏል።
በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ቅነሳና አካታች ኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጀማል አሊይ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የእንስሳት መድን ዋስትና አርብቶ አደሩ በድርቅ ምክንያት እንስሳቱን እንዳያጣ አስቀድሞ አካባቢዎቹ በሳተላይት ከተለዩ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ውሃ፣ ሣር እና መድኃኒትን ለእንስሳት ለመግዛት የሚያስችል ሥርዓት ነው። ይህን በእንስሳቱ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በቀላሉ መከላከል ያስችላል፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ ዋስትና እንዲሸጥ ይደረጋል ያሉት አቶ ጀማል፤ በዚህም አርሶ አደሩ በድርቅ ወቅት የሚደርስበትን ኪሳራ የእንስሳት መድኅን ዋስትና በመግዛት ሊያካክስ ይገባል ብለዋል።
የመጀመሪያው ዙር የእንስሳት መድን ዋስትና ሽያጭ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የገለጹት አቶ ጀማል፤ የዚህ ዋስትና ተጠቃሚ ለመሆን በተቀመጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የዋስትና ክፍያውን ማለትም የአጠቃላዩን 30 በመቶ ክፍያ ማስገባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህ ክፍያ የሚያገለግለው ለአንድ ዓመት ሲሆን ቀሪውን 70 በመቶ ደግሞ መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሸፍን የተናገሩት አቶ ጀማል፤ ይህም አርብቶ አደሩ በድርቅ ምክንያት እንስሳቱን እንዳያጣ እና የሚያጋጥመውን ኪሳራ እንደሚከላከል ገልጸዋል።
በዓመት ሁለት ጊዜ በሚከናወነው የእንስሳት መድኅን ዋስትና ሽያጭ በዚህ ዓመት ለ80 ሺህ አርብቶ አደሮችን ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ዙር ለ35 ሺህ አርብቶ አደሮች ዋስትና ለመስጠት ታቅዷል ነው ያሉት።
የአርብቶ አደሩ 30 በመቶ ክፍያ የሚያገለግለው ለአንድ ዓመት ብቻ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጀማል፤ ዋስትናው የሚተገበረው በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት በተቋቋመው የአርብቶ አደሮች የአደጋ ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነትና በአጋር ድርጅቶች እገዛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም