“የአፍሪካ አዳራሽ” ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በመታደስ ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፦ “የአፍሪካ አዳራሽ” ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ዘመኑን የዋጀ ገጽታ እንዲላበስ ተደርጎ በመታደስ ላይ እንደሚገኝ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታወቀ። በመጭው ጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚመረቅም ተጠቁሟል፡፡

በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ አዳራሽ አስተዳደር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አንቶንዮ ባእዮ የእድሳቱን ሂደት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ባስጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራቾች የመጀመሪያ ጉባኤያቸውን ያካሄዱበት ታሪካዊው “የአፍሪካ አዳራሽ” እድሳቱን በማጠናቀቅ በመጭው ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ይመረቃል፡፡

እድሳቱ ከ61 ዓመታት በላይ የቆየውን አዳራሽ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ዘመኑን የዋጀ ገጽታ እንዲላበስ እያስቻለው እንደሚገኝም የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ በተለይም የአፍሪካን ታሪካዊ አመጣጥ፣ አሕጉሪቱ አሁን ያለችበትን እና የወደፊት ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የእድሳት ዲዛይን ዘላቂ፣ ማራኪ እና ጎብኚዎችን በሚስብ መልኩ የተቀረጸ መሆኑን አንስተው፤ ብዛት ያለው የሕንፃው ክፍል በአዲስ እንደተተካና የተሠራው ሥራ ሕንጻውን የማደስ ብቻ ሳይሆን የማዘመን ተግባርንም እንደሚያጠቃልል ጠቁመዋል፡፡

ለእድሳት ሥራው 57 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት እንደወጣና ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ብቃት ያላቸው ኮንትራክተሮች እድሳቱን በልዩ ትኩረት እያከናወኑት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እድሳቱ የአፍሪካ ታሪክ እና ትዝታ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ ከሕንፃው ዲዛይን በስተጀርባ ካሉት ዋና ዋና መርሆዎች ውስጥ አንዱ የአፍሪካን ታሪክ ባከበረ መልኩ እድሳቱን ማከናወን ነው፡፡ የእድሳት ሥራው ዓላማ ሕንጻው ወደነበረበት መመለስ ላይ ያተኩራል፡፡

እድሳቱ በሥነ ሕንፃ፣ በባሕልና ታሪካዊ እሴትን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ፤ በጄኔቫና በኒውዮርክ ከሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ተወዳዳሪነት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

የአፍሪካ አዳራሽ ፕሮጀክት የሲቪል እና አርክቴክቸራል ሥራዎች ሱፐርቫይዘር ኢንጂነር ጌታቸው አርዓያ በበኩላቸው፤ ሕንጻው በራሱ ቅርስ መሆኑን በመግለጽ እድሳቱ የአዳራሹን የሥነ-ሕንፃ ውበት ወደነበረበት እንዲመለስ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አንድነት እና የእድገት ምልክት የሆነውን ቦታ ዘመናዊ እንዲሆን በማስቻል ለጉብኝት ክፍት ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

አዳራሹ ፓን አፍሪካኒዝም ተቋማዊ ቅርጽ የያዘበት ቦታ መሆኑን የገለጹት ሱፐርቫይዘሩ፤ አፍሪካውያን በጉዳዮቻቸው ዙሪያ የመከሩበት የመጀመሪያው ስፍራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ኢንጂነር ጌታቸው ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ የሕንጻውን መዋቅራዊ ደኅንነት በማረጋገጥ ለቀጣይ ተጨማሪ ዓመታት እንዲቀጥል ማድረግ፣ የኮንፈረንስ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የሕንጻውን ቅርስነት ማስጠበቅና ሕንጻው ለማኅበረሰቡ ክፍት እንዲሆን ማስቻል ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You