አዲስ አበባ፡- በ2017 ዓ.ም በሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል የሚታደሙ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ ለሚከበረው የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ለ2017 ዓ.ም በከተማዋ በድምቀት ለሚከበሩት ኢሬቻና የመስቀል በዓል ከሦስት ወራት በፊት ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ በከተማው እንግዶችን የመቀበል ልምድና ተሞክሮዎች መሠረት በሆራ አርሰዲ በዓል የሚታደሙ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡
ለዘንድሮው የሆራ አርሰዲ በዓል አከባበር ዙሪያ ከከተማው ሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ በሁሉም ዘርፎች ላይ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ የከተማው ማኅበረሰብ የኢሬቻና የመስቀል በዓላትን በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማክበር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ሆቴሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት ስለማድረጋቸው ግምገማ መካሄዱን በመግለጽ፤ የሆራ አርሰዲ ክብረበዓል በሠላም እንዲከበር በየደረጃው ካሉ የኅብረተሰብና የፀጥታ መዋቅሮች ጋር ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በከተማው ሆቴሎችን፣ መኝታ ቤቶችና የመስተንግዶ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ የዋጋ ጭማሪዎች እንዳይደረጉ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በተቋቋመው ግብረኃይል በኩል ቁጥጥር እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በዓመት አንዴ በከተማዋ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ለቱሪዝም ዘርፉ፣ በኢኮኖሚና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ የሆራ አርሰዲ በዓል የከተማዋ የገጽታ ግንባታ፣ የገቢ ምንጭ በመሆኑ የማጠናከር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና ድክመቶች ተለይተው መገምገማቸውን ጠቅሰው፤ የዘንድሮው በዓል በተሻለ መልኩ እንግዶችን ለመቀበል ከአመራር እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ቢሾፍቱ ከተማን የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በከተማው ኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ መንገዶችን የማስፋት ከተማን የማስዋብ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም