የዘረኝነት አስከፊ ገጽታዎች
እስከአሁን ድረስ በሰው ልጆች ላይ ከደረሱ ጥፋቶች መካከልም የዘረኝነትን ያህል አውዳሚ ጉዳትና እልቂት ያስከተለ የለም፡፡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁዶች ከምድረ ገጽ የጠፉት ዘረኝነት በፈጠረው የጥላቻ መንፈስ ነው፡፡ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን በባርነት የተጋዙበትና ለህሊና ሊከብድ በሚችል አኳኋን አሰቃቂ ግፍና ስቃይ የተፈጸመባቸውና መራራ የህይወት ጽዋን የተጎነጩት ሰውን ከሰው በሚያበላልጠው በሰይጣናዊው የዘረኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰው ልጅ በግፍ ለእልቂት የተዳረገባቸው አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች የዘረኝነት ውጤቶች ናቸው፡፡ በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ ከ 800 ሺ በላይ ሩዋንዳውያን እንደ እንስሳ እየታረዱትና በአሰቃቂ ሁኔታ በገዛ ወንድሞቻቸው የተጨፈጨፉት የክፋቶችና የጭካኔዎች ሁሉ ጥግ በሆነው በዘረኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ክቡር በሆነው በሰው ልጆች ሥጋ ሳሙና እስከ መሥራት የተደረሰበት በናዚ ሂትለር አማካኝነት በአይሁዶች ላይ የተፈጸመ ዘግናኝ ድርጊት፤ በተከለከለ የመርዝ ጋዝ ሰው የራሱን ገላ ሲፈርስ እየተመለከተ ተሰቃይቶ እንዲሞት ያደረገ የፋሽስት ሞሶሎኒ ሰቆቃዎች መነሻና መድረሻቸው “ሰው እኛ ብቻ ነን” የሚለው ህይወት አልባው ግኡዛን የዘረኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡
ዘረኝነትና አሜሪካ
አሁን ከሰሞኑ ደግሞ አንድ ሰው በሌላው ሰው ያውም የሰዎችን ደህንነትና ሰው የመሆን መብት የማስጠበቅ ታላቅ ኃላፊነት በተጣለበት ሰው ለዘጠኝ ደቂቃዎች ያህል አንገቱን በእግር ተረግጦ፣ ፈጣሪ የሰጠውን የህይወት እስትንፋስ በዘረኞች ተቀምቶ፣ “መተንፈስ አልቻልኩም” እያለ እንዳይተነፍስ አየር ተከልክሎ እጅግ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ተሰቃይቶ እንዲሞት ተደረገ፡፡
ይህ አሰቃቂ የዘረኝነት ድርጊት የተፈጸመው ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም በስደት ሄደው በውስጧ ለሚኖሩ የሌላ አገር ዜጎች ሁሉ በምትሰጠው ነጻፃትና የኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት የዘመናችን “የተስፋዋ ምድርና የዴሞክራሲ ተምሳሌት” ተደርጋ በምትወሰደው በልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን “ከቄሱ በጳጳሱ ባሰ” ያስብለዋል፡፡ በእርግጥ የሃገሬ ሰው እንደሚለው “ከተለመደ ሰይጣንም መላዕክ ይሆናል” እንደሚባለው ሆኖ እንጂ በነጭ ፖሊሶች አማካኝነት በጥቁሮች ላይ የሚፈፀመው ይህ ዓይነቱ አሰቃቂ የዘረኝነት ግድያ በዚያች ሃገር አዲስ አይደለም፡፡
ዋሽንግተን ፖስት የተባለውን የሃገሬውን ጋዜጣ ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳስነበበው ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2019 ዓመት ብቻ አሜሪካ ውስጥ 1ሺ 14 ሰዎች ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት የሞቱ ሲሆን፤ ሟቾቹ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ጥቁሮች ናቸው፡፡ አንድ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት በሠራው ጥናት መሰረት ደግሞ በፖሊስ የመገደል ዕድላቸው ሲሰላ ጥቁር አሜሪካውኑ ከነጮቹ በሦስት እጥፍ የላቀ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በሰኔ 2014 ኤሪክ ጋርነር የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ በህገ ወጥ መንገድ ትንባሆ ትሸጣለህ ተብሎ ተጠርጥሮ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ በአንድ ነጭ የፖሊስ አባል አማካኝነት ልክ እንደ ጆርጅ ፍሎይድ አንገቱን በጫማ ተረግጦ “እባካችሁ መተንፈስ አልቻልኩም” እያለ በተመሳሳይ ሁኔታ በአሰቃቂ መንገድ ተገድሏል፡፡ ይህን ዘግናኝ የዘረኝነት የወንጀል ተግባር የፈፀመው ዳንኤል ፖንታልዮ የተባለው ነጭ የፖሊስ አባልም በወቅቱ ምንም ያልተደረገ ሲሆን፤ ሕዝብ ቁጣ በመቀስቀሱ ከአምስት ዓመት በኋላ ባለፈው ዓመት ነበር ዕርምጃ የተወሰደበት፡፡ ዕርምጃውም የሰውን ህይወት በማጥፋት ከተፈጸመ ወንጀል ጋር ፍጹም ተመጣጣኝ ያልሆነ ከሥራ ገበታው ከማባረር ያልዘለለ መሆኑ በዚያች ሃገር የሚፈጸመውን ዘረኝነት ወንጀል ስልታዊ በሆነ መንገድ በህግ የሚደገፍ አስመስሎታል፡፡
በእርግጥም እ.አ.አ. ከ1965 በፊት ዘረኝነት በዚያች አገር ህጋዊ ነበር፡፡ ዘረኝነትን በተለይም የነጭ የበላይነትን የሚከለክለው የ1965ቱ የስደተኞችና የዜግነት ጉዳዮች ህግ ከመጽደቁ በፊት አሜሪካ ውስጥ ነጮች በተለይም ሰሜን አውሮፓ ዝርያ ያላቸው ነጮች ሁሉንም ነገር የማድረግ ልዩ መብት የተሰጣቸው “የበላይ ዘሮች” መሆናቸውን በግልጽ የሚደንግግ ህግ እደነበር የማህበራዊ ሳይንስ
ጥናት ሳይንቲስት የሆኑት ሰቴቨን ክሊንበርግ ጽፈዋል፡፡ በደቡባዊ ካሮሊና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሌላንድ ቲ. ሳይቶ በበኩላቸው ዘረኝነት ለአሜሪካ አዲስ ነገር እዳልሆነና እንዲያውም መላው የአሜሪካ ታሪክ የዘረኝነት ታሪክ መሆኑን “ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መገለሎችን እና ልዩነቶችን ለመፍጠርና የነጮችን ልዩ ተጠቃሚነት ህጋዊ ለማድረግ ዘር እንደ መሳሪያ ሲያገለግል ኖሯል” በማለት ያብራራሉ፡፡
የሌለውን ዘር ፍለጋ
እናም ዘር የሚባል ነገር በእርግጥ አለ ወይስ የለም? ከሌለስ “መሰረቴ ዘር ነው” የሚለው እና እንዲህ የሰው ልጆችን እያመሰ የሚገኘው ዘረኝነት ከየት መጣ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ የአስከፊውን የዘረኝነትን ምንነት ለማወቅ፣ እውነታውን ለመገንዘብና የሚያስከትለውን ጥፋት በዕውቀት ለመከላከል መሰረት ይሆናል፡፡ የአንድን ነገር ምንነት ለማወቅ ደግሞ አፈጣጠሩን ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ዘረኝነት የሚለው በሽታ የሚታወቀው ደግሞ በእኛ በሰዎች ዘንድ እንጂ በእንስሳትም ሆነ በዕፅዋት ፍጥረታት ስላልሆነ የዘረኝነትን ምንነት ለማወቅ በቅድሚያ የሰውን ምንነት ማወቅ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ይህም ሰው ምንድነው የሚለውን ለማወቅ የሰውን አፈጣጠር እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ ከዚህ አኳያ የሰውን አፈጣጠር በተመለከተ በዓለም ላይ ሁለት ገዥ አስተሳሰቦች ሰፍነው እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው ፍጥረታዊ (Creationist View) የሚባለው ሲሆን፤ ይህም ሰው ሁሉን ቻይ በሆነ አምላክ ከአለመኖር ወደ መኖር መምጣቱንና መፈጠሩን የሚያምን እና በመንፈሳዊውና ሃይማኖታዊው ዓለም ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው አስተሳሰብ ነው፡፡ ሃይማኖት ሰው የፈጠረውን አምላኩን የሚያውቅበትና ከእርሱም ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመራበት፣ አምኖ ከሚገዛለት ፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት ድልድይ ነው፡፡ እናም በዚህ አስተሳሰብ መሰረት ሰው ሁሉ እኩል ሆኖ ነው የተፈጠረው፡፡ በምድር ላይ ያሉ የሰው ዘሮች ሁሉም ከአንድ አባትና እናት ከአዳምና ከሔዋን የተገኙ ናቸው፡፡ በቀለም፣ በነገድ ወይም በጎሳ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በዕምነት፣ በሃይማኖት፣ በአኗኗር ዘይቤ ቢለያዩም ጥቁሩም፣ ነጩም፣ ቢጫውም በሰውነት ግን ሁሉም ከአንድ አባትና እናት የተገኙ፣ በአንድ ፈጣሪ አምሳል የተፈጠሩ የማይለያዩ አንድ ዓይነት ፍጥረቶች ናቸው፡፡ የነጭ ዘር፣ የጥቁር ዘር፣ የእከሌ ዘር…የሚባል የተለያየ የሰው ዘር የለም፤ አንድ የሰው ዘር ብቻ ነው ያለው፡፡ ወይም ከነጭራሹ ዘር የሚባል ነገር የለም፣ ሰው የሚባል ፍጥረት ነው ያለው፡፡ በፍጥረታዊው የሰው ልጅ አፈጣጠር እሳቤ መሰረት ዘር፣ ብሔር፣ ጎሳ የሚባል ነገር የለም፤ ሰው ሰው ነው፡፡ እናም የተለያየ የሰው ዘር ስለሌለ ዘርን መሰረት ያደረገ ልዩነት ወይም ዘረኝነትም በጥብቅ የተወገዘ ነው፡፡
ለአብነት በክርስትና ዕምነት ቅዱስ መጽሐፍ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፤ ባሪያ ወይም ጌታ የለም፣ ወንድ ወይም ሴት የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና›› (ገላ. 3፥26-28) በማለት ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን በግልጽ ይደነግጋል፡፡ በቆዳ ቀለም፣ በብሔር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ… ሰበብ በሰዎች መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሚታትሩትን ዘረኞችም “በወንድማማቾች መካከል ፀብን የሚዘራ” እግዚአብሔር ነፍሱ አጥብቃ እንደምትፀየፈው በመግለጽ የዘረኝነትን ርኩሰት በጽኑ ያወግዛል፡፡ እስልምና በበኩሉ “ዘረኝነት ጥንብ ናት” በማለት ምን ያህል ክፉ ነገር እንደሆነ አስረግጦ ያስተምራል፡፡
የሰውን አመጣጥ በተመለከተ የሚታወቀው ሁለተኛው እሳቤ ደግሞ በፈረንሳዊው የሃሳቡ አመንጪ እና በተከታዮቹ ዘንድ የሚራመደው ዝግመተ ለውጣዊ (Evolutionist View) የሚባለው ሲሆን፤ ህይወት የተገኘው ህይወት ከሌለው ነገር ነው ብሎ ያምናል፡፡ የሰው ልጅም በረጅም የዝግመተ ለውጥ ሂደት ከጦጣ መሰል ፍጡራን መምጣቱን ያስተምራል፡፡ በዚህ ዘርፍ የተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶችም “የአካባቢ፣ የባህልና የአኗኗር ዘይቤ የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ተፈጥሯዊ የዘር ልዩነት መኖሩን የሚያሳይ አንድም ሳይንሳዊ መረጃ የለም” በማለት በሰዎች መካከል ዘር ልዩነት አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
ታዋቂው እንግሊዛዊ ጄነቲክ ሳይንቲስት፣ ደራሲና ብሮድካስተር “ዘረኞች እንጂ ዘር የሚባል ነገር አለመኖሩን በቅርቡ ባደረኩት የዘረመል ጥናት ደርሽበታለሁ” ማለቱን
“ዋይ ሬሲዝም ኢዝ ኖት ባክድ ባይ ሳይንስ” በሚል ርዕስ ከአራት ዓመት በፊት ዘ ጋርዲያን ድረ ገጽ ያስነበበው ዘገባ አመላክቷል፡፡
ታዲያ ዘረኝነት ከየት መጣ?
እንግዲህ ሃቁ ይህ ከሆነ “ዘር” ን መሰረት ያደረገው አሰቃቂው የሰው ልጆች በሽታ ዘረኝነት ከየት መጣ? የሚለውን ምላሽ ማግኘት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ይህን ጥያቄ በተመለከተ የጄነቲክ ሳይንቲስቱ አዳም ራዘርፎርድ ዘ ጋርዲያን ላይ ባሳተመው ጽሑፍ እንደሚከተለው ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ “ኦን ዚ ኦሪጅን ኦፍ ስፔሽየስ” በሚለው ዘመን አይሽሬ መጽሐፉ ካስቀመጠው “የተመረጠ ዝርያ” ጽንሰ ሃሳብ ጋር በተያያዘ ስለ ዘረኝነት ሲነሳ ብዙዎቹ ዘረኛ አድርገው የሚወስዱት ቻርልስ ዳርዊንን ነው፡፡ “ሆኖም ዳርዊን “ዘር” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ህይወት በሌላቸው ፍጡራን መካከል የሚገኙ የተለያዩ መደቦችን ለመግለጽ እንጂ ለሰው አልነበረም”፡፡ ስለሆነም ዳርዊን ዘረኛ ነበረ የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን የሚጠቁመው ደራሲና ሳይንቲስቱ አዳም ራዘርፎርድ በእርግጥ ታዋቂውን የቀድሞውን የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልን ጨምሮ በታሪክ ትልልቅ ስሞች ያላቸው ታዋቂ ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል፡፡
አሁንም ድረስ የዘረኝነትን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ታዋቂ ግለሰቦች መኖራቸውን የጠቆመው ጄነቲክ ሳይንቲስቱ ከዳርዊን ይልቅ ግን በዘመናዊው ዓለም የዘረኝነትን ጽንሰ ሃሳብ እንዲሰርጽ ያደረገው የዘረኝነት ጽንሰ ሃሳብ አፍላቂና ዋነኛው ዘረኛ በአንድ ወገኑ የዳርዊን የአክስት(የአጎት ልጅ) የነበረው ፍራንሲስ ጋልተን የሚባል እኩይ ሰው ነው ይላል፡፡ በአጠቃላይ የዘረኝነት መነሻ በሰዎች መካከል ተፈጥሯዊ የዘር ልዩነት ስላለ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በታሪክ፣ በጥቅም የበላይ ለመሆን የሚፈልጉ በተለይም ከነጭ አውሮፓውያን አብራክ የተገኙ ሐሰተኛ ሳይንቲስቶች ሆን ብለው
የፈጠሩት መሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናታዊ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡
የዘረኝነት አፍላቂዎች ሐሰተኛ ሳይንቲስቶች የተባሉበት ምክንያትም ሃሳባቸውን እውነተኛ ለማስመሰል በትክክል ሳይንሳዊ ያልሆነ፣ በጥናት ባልተረጋገጠ መንገድ በመነሳት ሆን ብለው “አንዱ ከአንዱ የሚበልጥ የሰው ዘር መኖሩን በሳይንስ አጥንተን አግኝተናል” በማለታቸው ነው፡፡ ይህም በሐሰተኛ ሳይንስ ላይ ተመስርቶ ሆን ተብሎ የተፈበረከ በመሆኑ “ሳይንሳዊ ዘረኝነት” በመባል ይታወቃል፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ የሰው ልጅ ሲሰለጥን ራሱንና ወገኑን ለማለያየትና ለማጥፋት ጥፋትን በሐሰት በሳይንስ ሲፈበርክ!
ዘረኝነት መጥፊያው እየደረሰ ይሆን?
እንግዲህ ጥንትም ተፈጥሯዊ መሰረት የሌለው ሐሰተኛው ዘረኝነት እንዲህ እንዲህ እያለ ጥፋቶችን እያስከተለ ዛሬም ድረስ ከሰው ልጆች ጋር ቢዘልቅም ዘረኝነት በገነገነባት በምድረ አሜሪካ በጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ላይ ከሰሞኑ የተፈጸመው አሳፋሪ የዘረኝነት ድርጊት በኋላ የተመለከትነው ክስተት ግን ሄዶ ሄዶ ዘረኝነት ራሱን ሊያጠፋ የተቃረበ መሆኑን ያመላከተ ሆኗል፡፡ እንደለመዱት ሰውን አሰቃይተው ገድለው የበታችነት ስሜት በሽታቸውን ለማስታገስ የሞከሩት “የበላይ ነን” ባዮች ዘረኞች ባልጠበቁት መንገድና መጠን ከፍተኛ ፍርሐትና ጭንቀት ውስጥ ገብተው ተመልክተናል፡፡ ጥቁሩ ሰው በግፍ ከተገደለበት ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰው ልጆች በአንድ ላይ ሲቆሙ፤ አንድ ላይ ሆነው በጋራ ዘረኝነትን ሲያወግዙ፤ በቃ! ሲሉ ተስተውለዋል፡፡ ለወትሮው ጥቁሮች በነጭ ዘረኞች ሲገደሉ ጥቁር አሜሪካውያን ብቻ ነበሩ ተቃውሞ የሚያሰሙት፡፡ አሁን ግን ጥቁርና ነጭ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁላችንም ሰው ነን፤ ጆርጅ ፍሎይድ ሰው ነው ጥቁርም ነጭም “እኔም ጆርጅ ፍሎይድ ነኝ” ብለዋል፡፡ መላ አሜሪካውን ያለ ቀለም ልዩነት በሰውነት ቆመዋል፡፡
ራሳቸው የፖሊስ አባላት ሳይቀር “ከዚህ በኋላ ልትለዩን አትሞክሩ፣ እኛ ሰው ነን አንለያይም” በማለት ለፕሬዚዳንት ትራንፕ ማስጠንቀቂያ አዘል ሰብዓዊ ማሳሰቢያ አሰምተዋል፡፡ አርባ አምስተኛው የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ፕሬዚዳንት የኒውዮርከሩ ቱጃር ዶናልድ ጁኒየር ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻው ወቅት አብዝተው ከተጠቀሙባቸው ፕሮፓጋንዳዎች መካከል “ቅድሚያ ለአሜሪካውያን” ና “አሜሪካ እንደገና ታላቅነቷን ማረጋገጥ አለባት” የሚሉት ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ በተለይም “አሜሪካን እንደገና ታላቅ ማድረግ ያስፈልጋል” የሚለው የትራምፕ አባባል “አሁንስ አሜሪካ ታላቅ አይደለችም ወይ?” “ሰውየው የትኛዋን አሜሪካ ነው ታላቅ ማድረግ የፈለጉት ?” የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄና ትችት ያስከተለ ቢሆንም የኋላ ኋላ ሰፊ ድጋፍን ታላቋን ሃገር በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ያሉት ትራምፕም ከራሳቸው ዜጎች እንዲህ ዓይነት ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ሰውዬው የነጭ የበላይነት አቀንቃኝ መሆናቸው በይፋ ስለሚታወቅ ነበር፡፡
እናም ለወትሮው በትልቅ በትንሹ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት የሚታወቁት ትራምፕ ያደላልኛል ብለው የሚያስቡት ነጭ አሜሪካውያን ከወገኖቻቸው ጋር በቀለም ሳይሆን በሰውነት አንድ ሆነው ሲመለከቷቸው “ምነው ጆርጅ ፍሎይድ በህይወት ኖረህ ይህን ታሪክ ባየህ” በማለት ሲለማመጡ ተደምጠዋል፡፡ መላ አሜሪካውን ብቻ አይደሉም፤ ጀርመን፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ መላ አውሮፓ፣ በጠቅላላው ዓለም ማለት ይቻላል በሰውነቱ አንድ ሆኖ መቆም ችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በነጭ ምዕራባውን ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጣቸውና እንደ ጀግና ተቆጥረው ሐውልት የቆመላቸው በጥቁር ህዝብ ላይ አሰቃቂ ግፍ የፈጸሙ እንደ የቤልጅየሙ ንጉሥ ሊዮፖልድና እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ኮልስቶን ዓይነት “የሰው ነጋዴዎች” (የባሪያ ነጋዴዎች አልልም) እና የቅኝ ግዛት አበጋዝ የነበሩ ግለሰቦች ሐውልቶች ነጭና ትቁር ሳይል በሁሉም የሰው ልጆች ትብብር እየፈረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቀላል የሚባል ዕድገት አይደለም፤ ዕድሜ ለራሳቸው ለዘረኞች ዘረኝነት ራሱ እየፈረሰ ያለ ይመስላል!
በአጋጣሚ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት በአንጻራዊነት ከሌላው በጉልበት በልጦ በመገኘቱ እንደሚጠፋ እንስሳ በኃላፊ ጠፊ ጡንቻው ተመክቶ፣ በሳጥናኤላዊ “የእኔ እበልጣለሁ” ትዕቢት በሰው ልጆችና በሰውነት ላይ ይቅር የማይባል ወንጀል ሲፈጽም የኖረው ዘረኝነት ሲጠፋ ከማየት የሚበልጥ ምን ታላቅ ነገር አለ?
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
ይበል ካሳ