የ “ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ” ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ አንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማሪያም የተወለዱት ከ91 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ነበር።
ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማሪያም ከአዲስ አበባ ወደ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ነቀምቴ ከተማ ተወለዱ። አባታቸው የነቀምቴ ነዋሪ ሲሆኑ የስዊድኑ ኤቫንጄልካል ሚሽን ያሰራው ሐኪም ቤት ውስጥ ይሰሩ ነበር። እናታቸው ወይዘሮ ወለተሚካኤል ከግምቢ ከተማ ወደ ነቀምቴ ለሕክምና ሲመጡ ከአቶ ወልደማርያም ጋር ተዋውቀው ለትዳር በቁ። ጋዜጠኛ ያቆብም በዚሁ ሀኪም ቤት ነው የተወለዱት።
ከእዚያም በአቅራቢያቸው ተፈሪ መኮንን አንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት ስለተቋቋመ እዚያ ገቡ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተሰደው ከነበሩበት ከታላቋ ብሪታንያ በ1933 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለሱ ድረስ የነበሩት ትምህርት-ቤቶች ከ1ኛ-6ኛ ክፍል ድረስ ብቻ እንደነበሩ ጋዜጠኛው ያዕቆብ ይናገራሉ። ከሁለት ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ኮተቤ አካባቢ በስማቸው የመጀመሪያውን ከ8ኛ-12ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር ትምህርት-ቤት ከፈቱ። ከየክፍለ አገሩ ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በፈተና ወደእዚህ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ሲደረግ ያዕቆብም ፈተናውን በከፍተኛ ውጤት አለፉ። አባታቸው የአብነት ትምህርት ለመማር ከነቀምት ደብረ ሊባኖስ አሥራ አንድ ቀን ያህል በእግራቸው ተጉዘው ነበር። ልጃቸውም ዛሬ ግማሽ ቀን የሚወስደው መንገድ በወቅቱ አንድ ሳምንት ይጠይቅ ነበርና ከነቀምቴ አዲስ አበባ ለመድረስ የሰባት ቀን ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው። ለአምስት ዓመታት ተምረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቃቸው በ1942 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ለንደን ተላኩ።
በደቡብ-ምዕራብ ለንደን የሚገኘው በኪንግስቶን አፕ-ኦን ቴምስ ኢንጅነሪንግ ለመማር የሚያዘጋጃቸውን የሒሳብ ትምህርትን ጨምሮ ከፍተኛ ተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ወሰዱ። በነዚህ ንድፈ ሐሳባዊ ትምህርቶች ላይ ጥሩ ውጤት ቢያስመዘግቡም ወደ ትግበራው ሲመጣ ከባድ እንደሆነባቸውም ይናገራሉ። የእጅ ሥራ መብዛቱ፣ ሜካኒካልና ድሮዊንግ ነገር መስራቱ፣ በቤተሙከራ ውስጥ መንደፋደፉ ለእርሳቸው ምቾት አልሰጠም። እናም ከዚሁ እየጠሉት ከመጡት ትምህርት ጎን ለጎን በግላቸው የተለያዩ የፍልስፍና መጻሕፍትን ማንበብ ተያያዙት።
እንደነ ዘ-ኦብዘርቬር፣ ዘ-ደይል ቴሌግራፍ፣ ዘ-ጋርድያን እና ሌሎች መፅሔቶችን ያነቡ ነበር። በዚህ ወቅት በኮሌጁ ኢትዮጵያውያን «ላየንስ ክለብ» በሚል መሰባሰቢያቸው ስር ያቋቋሙት መጽሔት ነበርና የያኔው ወጣት አቶ ያዕቆብም የተለያዩ መጣጥፎችን በማዘጋጀት ብዕራቸውን በዚህችው መጽሔት አሟሹ። ቀጠሉናም የተለያዩ የእንግሊዝ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ሃሳባቸውን የማስፈር ጥረት አደረጉ። «ኦብዘርቨር»፣ «ማንችስተር»፣ «ዴይሊ ቴሌግራፍ» የተሰኙ የህትመት ውጤቶች ላይ ጽሑፋቸው እንዲወጣላቸው መላክ ጀመሩ። የላኩት አብዛኞቹ ባይወጡላቸውም ወደ ሙያው ለመግባት ፍንጭ ያዩበት ሙከራቸው ነበር። በዚያን ወቅት ፕሮፌሰር ሲልቪያ ፓንክረስት በሚያዘጋጁት ኒውስ ታይም የተሰኘ ጋዜጣ ላይም ይጽፉ ነበር። ቀስ በቀስ እንዲማሩ የተላኩበትን የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርታቸውን እየተውት መጡ። በኋላም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ከዚያም በአዲስ አበባ አመሃ ደስታ ትምህርት-ቤት፣ እንዲሁም በነቀምቴ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች በመምህርነት ለአራት ዓመት አገልግለዋል። በነቀምቴ ከተማ በመምህርነት እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት መምህር ያዕቆብ ከአካባቢው ባለስልጣን ጋር ስለተጋጩ በ1951 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክና ሃይል ባለስልጣን ስራ አገኙ።
ቆይቶም በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በሚጽፏቸው ጽሑፎች ዝንባሌያቸውን ያውቅ የነበረ እንግሊዝ አገር አብሯቸው የተማረ ጓደኛቸው “ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ” ጋዜጣ ጋዜጠኛ እንደሚፈልግ ነገራቸው። ምክሩን ሰምተውም ወደ ጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ዘንድ ሄዱ። በእንግሊዝኛ ግሩም አርቲክል በመጻፋቸውና አንድን ጽሑፍ ጥሩ አድርገው ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎማቸው በወቅቱ ዋና አዘጋጅ የነበሩት ዶክተር ዴቪድ ታልቦት ተገርመውና ተደስተው
እንፈልግሃለን ብለዋቸው በ1951 ዓ.ም የጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቀሉ።
ስራ እንደጀመሩም ታላላቅ ጉዳዮችን እያነሱ በፊት ገጽ ዜናዎችን፣ በውስጥ ገጽ ደግሞ መጣጥፎችን በአማርኛ እንግሊዝኛ ቋንቋ ያዥጎደጉዱት ጀመር። በዚህ ጊዜ የመብራት ኃይል ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እጅግ ተገረሙ፤ ትልቅ ሰው እንዳጡ ቁጭት ተሰማቸው። የመብራት ኃይሉ ሥራ አስኪያጅ ሰይፉ ማህተመሥላሴ አግባብተው እንደገና ቢመልሷቸውም ወዲያው ግን የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት “ንጉሡ ዘንድ ሄጄ እከሳለሁ” በማለት ከፍተኛ ቁጣ ስላስነሱ እንደገና ወደ ሄራልድ ተመለሱ።
በወቅቱ ከዋና አዘጋጁ ዶክተር ታልቦት ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው እርሳቸው ነበሩ። አዘጋጅ ሆነው ጽሑፍ ያርማሉ፣ ሌሎች ጋዜጠኞችን ሥራ ያሰማራሉ፣ በፈረንሳይኛ እና በጣሊያንኛ ከውጭ የሚላኩ ዜናዎችንና ሌሎች ጽሑፎችን ይተረጉማሉ። ሥራው ፋታ የማይሰጥ ቢሆንም የሚወዱትና የሚመኙት ሙያ ነበርና በትጋት ቀጠሉ። ከዚያም ወደ ምሽት አርታኢነት ተሸጋግረው ለስድስት ወራት ሰሩ። አራት ገጽ ያለው ጋዜጣ ለማዘጋጀት እስከ ንጋት 11፡00 ሰዓት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሆነው ጽሑፎችን የማረምና ለህትመት የማመቻቸት ሥራ ይሰራሉ። ምሽት ላይ የሚመጡ መግለጫዎችን በተለይም ከማስታወቂያ ሚኒስትር በቃል እየተቀበሉ በመስራት በማግስቱ እንዲወጣ ያደርጉ ነበር።
የጋናው መሪ ኑኩርማ ዶክተር ታልቦትን ለጉብኝት ጋብዘዋቸው ለሦስት ወር ወደጋና በሄዱበት ወቅት ጋዜጣዋን በቅርብ ኃላፊነት ይከታተሉ የነበሩት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ የዋና አዘጋጅነቱን ቦታ ለኢትዮጵያውያን ለመስጠት ወሰኑ። ለምን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የውጭ ዜጋ ይሆናል የሚል ቁጭት በውስጣቸው ስላደረባቸው ለቦታው ይመጥናሉ ብለው ያሰቧቸውን ያዕቆብ ወልደማርያምን፣ ነጋሽ ገብረማርያምን እና አያሌው ወልደ ጊዮርጊስን ቢሯቸው አስጠርተው «በሉ ከሦስታችሁ አንዳችሁ ዋና አዘጋጅ ትሆናላችሁ፤ ፈተና ልስጥ ወይንስ እናንተ ከመሀላችሁ ትመርጣላችሁ? ሲሉ ጠየቋቸው። ሁለቱም ጋዜጠኞች ያዕቆብ ዋና አዘጋጅ እንዲሆኑ ተስማሙ። በ1952 ዓ.ም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የ “ዘ ኢትዮጵያውያን ሔራልድ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኑ።
የዋና አዘጋጅነቱን ቦታ እንደያዙ በጋዜጣው ቅርጽና ይዘት ላይ ለውጥ አደረጉ። ለወትሮው የውጭውን ዓለም ታሪክና ዜና ከማቅረብና የንጉሡ እንዲሁም የሹማምንቶቻቸውን አንዳንድ ክዋኔዎች በዜናነት ከማውጣት በዘለለ ሌሎች የማህበረሰቡን ክንዋኔዎች ዳስሳ የማታውቀው ሄራልድ ጋዜጣ አሁን የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ሁነቶችን በስፋትና በጥልቀት መዘገብ ጀመረች።
አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንድታተኩር መደረጓ አቶ ያዕቆብን አስመሰገናቸው። «አይችሉም!» ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ኢትዮጵያውያን አቅማቸው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነም ታየ።
የፊውዳሉን ሥርዓት በርዕሰ-አንቀፅ መተቸት ይቅርና ወንጀል መዘገብ እንደማይችሉ የሚናገሩት ጋዜጠኛው ያዕቆብ አብዛኛው ሥራቸው በአፄ ኃይለ ሥላሴ እንቅስቃሴዎች ላይ
ያተኮረ እንደነበረ ይናገራሉ። እሳቸው በዚህ ሥራ ብዙም ሳይቆዩ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣን ተወገዱ። ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለ ማርያም በ1967 ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ ስለተሞከረው ኩዴታ በርዕሰ አንቀጽ የፃፉት ትችት ስላልተወደደ ከዋና አዘጋጅነት ሥራቸው እንዲነሱ ተደረገ። ጋዜጠኛ ያዕቆብ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ሄራልድ ርዕሰ-አንቀፅን አንብበው እንደማያውቁ ይናገራሉ።
ከዋና አዘጋጅነታቸው ከተነሱ በኋላ ቀድሞ «አጃንስ» ተብሎ በሚጠራው የአሁኑ «የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ» የእንግሊዝኛው ክፍል ተመድበው ሰርተዋል። ብዙም ሳይቆይ እንደገና ወደ መነን መጽሔት ተቀየሩ። የመነን መጽሔት ዋና አዘጋጅ በነበሩበት ወቅት ከአማርኛው ጋር ተዳብላ የነበረችውን መጽሔት ራሷን ችላ እንድትወጣና በቅርፅና ይዘት ደረጃ ከውጭ አገር መጽሔቶች ጋር ተቀራራቢ ደረጃ እንዲኖራት ለማድረግ ጥረዋል። ጎን ለጎን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመውን «የቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ» ጋዜጣንም ደርበው እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። በኋላም ሙሉ ለሙሉ ወደ ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ተዘዋውረው ሰባት ዓመታት አገልግለዋል።
የእንግሊዝኛው “ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ሲዘጋ ይከፈላቸው የነበረውን ደመወዝ ይዘው ወደ “ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ” ጋዜጣ ተመልሰው በአማካሪነት ተመደቡ። የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክሱንና የህትመት ጋዜጠኞችን እያዘዋወረ ሲደለድል አቶ ያዕቆብ የደረሳቸው በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ፐብሊኬሽን ዘርፍ ነበር። በዚያም የእንግሊዝኛው የየካቲት መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። እዚሁ እየሰሩ ጡረታ ሊወጡ ስድስት ወራት ሲቀራቸው በ1980 ዎቹ አጋማሽ ላይ በእዚሁ የጽሑፍ ሥራቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመድበው በ1980 አጋማሽ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው በጽሕፈት ሥራ በማገልገል ላይ ሳሉ ጡረታ ቢወጡም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሪፖርተር የእንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ የአርታኢነት ሥራን በፍሪላንስ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሦስት ተከታታይ መንግሥታትን ያዩት ጋዜጠኛው ያዕቆብ በአገሪቱ የጋዜጠኝነት እድገት-ሂደት አዝጋሚ የሆነው በመሪዎቹ ግፍ ምክንያት ነው ባይ ናቸው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ከጥንት ጀምሮ በአሉባልታ ላይ የተመሰረተ ነው። መንግሥትም የሕዝቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ እንዲሁም ለፕሮፖጋንዳ ለመጠቀም ሆን ብሎ አሉባልታን ያሰራጫል። ግን የጋዜጠኞች ዋና ሥራ መሆን ያለበት አሉባልታውን ከእውነቱ አጣርቶ፣ አበጥሮ ለማህበረሰቡ ማቅረብ መሆን አለበት ይላሉ። የዛሬዎቹን ጋዜጠኞች በእርሳቸው ዘመን ከነበሩት ጋር ሲያነጻጽሩም ብዙ ክፍተት እንዳለ ይጠቅሳሉ። የሃሳብ ብቻ ሳይሆን የቋንቋ ችግር ውስጥም እንዳሉም ይናገራሉ።
የቀደሙት ጋዜጠኞች አንባቢዎች ሲሆኑ፤ የዛሬዎቹ በንባብ ራስን የማበልፀግ ትጋት እንደሌላቸው መታዘባቸውንም እንዲሁ። ʿየማያነብ ጋዜጠኛ እንዴት ሊጽፍ ይችላል?ʾ ሲሉም ይጠይቃሉ። አንድ ጋዜጠኛ የራሱን አቅም የሚለካው ሌሎች የደረሱበትን ሲያውቅ ነው። የሀገር ውስጥን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ጋዜጠኞች እንዴት እንደሚጽፉ መረዳት አለበት። ዓለም አቀፋዊ እውቀት ሲኖር ነው ብስለት ያለው ሥራ መስራት የሚቻለው። ያም ሆኖ ተስፋ የሚጣልባቸው ጎበዝ ጋዜጠኞች መኖራቸው ፣ ሙያው በዘመናዊ ትምህርት እየተደገፈ መምጣቱ የዘርፉን እድገት እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ጋዜጠኛ ያቆብ ወልደማሪያም በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ በጋዜጠኝነትና ሚዲያ ዘርፍ የ2007 ዓ.ም የበጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል።
አፋን ኦሮሞን፣ አማርኛን፣ እንግሊዝኛንና የፈረንሳይ ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩት ጋዜጠኛው ያዕቆብ ትዳር የያዙት በአመሃ ደስታ ትምህርት ቤት መምህር ሳሉ ነበር። በዚያን ጊዜ በአባቷ የመናዊ የሆነች አንድ ቆንጆ አገቡ። ወጣትነታቸው በውቤ በረሃ ለዳንስና ለሙዚቃ የተመቸ ነበርና በዚያ አጋጣሚ ነው የተዋወቁት። ከእርሷ አምስት ልጆችን ወልደው አለመስማማት በመፈጠሩ ምክንያት ተለያይተዋል። ቀጥሎም አሁን በሕይወት ያሉት ባለቤታቸውን አግብተው አምስት ልጆችን ወልደዋል ፤ በርካታ የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል።
የጀርመን ድምጽ “ቆይታ ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ጋር” እንዲሁም ደረጀ ትዕዛዙ “ጎምቱ ጋዜጠኛ! -ያዕቆብ ወልደማርያም” በሚል ርዕስ ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ በምንጭነት ተጠቅመናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
የትናየት ፈሩ