እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን! ከወራት በፊት በዚሁ የሕግ ዓምዳችን ላይ የወንጀል ክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመንና አቆጣጠሩን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ማቅረባችን ይታወሳል።
በዚህኛው ዕትማችን ደግሞ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ የይርጋ ዘመንን በተመለከተ የግንዛቤ ስንቅ ቋጥረንላችኋል – እነሆ።
“ይርጋ” የሚለው ቃል ተደጋግሞ ሲነገር እናደምጣለን። “ይርጋ አግዶታል”፤ “በይርጋ ቀሪ ሆኗል”፤ “የይርጋ ጊዜው አልፎበታል” ወዘተ ሲባል እንሰማለን።
ለፍትሐብሔርም ሆነ ለወንጀል ጉዳዮች የይርጋ ጊዜ ይቀመጣል። በፍትሐብሔር ሕጉ በውል፣ ከውል ውጪ፣ በንብረት፣ በውርስ፣ በሽያጭና በመሰል ጉዳዮች የይርጋ ጊዜዎች ተቀምጠዋል። በንግድ ሕጉም የተለያዩ የይርጋ ደንቦችን እናገኛለን። በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እና በሌሎችም አዋጆች ይርጋ ደንጋጊ አንቀጾች አሉ።
ጠቅለል ባለ አገላለጽ የይርጋ ደንብ የአንድ ሰው የመብት ጥያቄ በጊዜ ማለፍ ቀሪ የሚሆንበትን፤ በአንጻሩ ደግሞ በጊዜው ማለፍ ምክንያት ሌላኛው ወገን የመብቶች ባለቤት የሚሆንበትን የሕግ መርሆ የሚያሳይ ነው።
በይርጋ መርህ መሰረት የአንድ ንብረት ባለቤት ያልሆነ ሰው ያንን ንብረት በይዞታው ሥር አቆይቶ ሕግ በሚጠይቀው አግባብ የተጠቀመ መሆኑ ከታወቀ ባለቤት ሊሆን የሚችልበት አግባብ አለ።
በዚሁ መነሻ የይርጋ ደንብ አንድም የባለዕዳውን ግዴታ የሚያስቀር ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ መብት ላልነበረው ሰው መብትም የሚሰጥ ነው።
የባለዕዳን ግዴታ የሚያስቀር ይርጋ የተደነገገው በግዴታ ሕጎች ውስጥ ነው። የባለዕዳ ግዴታ ደግሞ ከውል ወይም ከውል ውጪ ሊመነጭ ይችላል።
በሁለቱም ግዴታዎች የይርጋ ዘመኑ ርዝማኔ የተለያየ ቢሆንም ቅሉ ይርጋው ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ በግዴታው ውስጥ ባለገንዘብ (ባለመብት) የሆነውን ሰው መብት ያስቀራል።
ምክንያቱም ባለገንዘቡ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ባለዕዳውን ጠይቆ መብቱን ሳያስከብር ጊዜው ካለፈ መብቱን ያጣል። ለዳተኛ ሰው ሕግ ከጎኑ አይቆምምና። ባለዕዳው ደግሞ የጊዜውን ማለፍ ተከትሎ በባለገንዘቡ ከመጠየቅ ይድናል፤ ግዴታውም ቀሪ ይሆንለታል።
ሕጉ የጊዜውን ገደብ ያስቀመጠበት መሰረታዊ አመከንዮም በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ባለገንዘቡ መብቱን ካልጠየቀ ከዚያ በኋላ የመጠየቅ ፍላጎቱ እየተዳከመ ይሄዳል የሚል ግምት በመውሰድ ስለመሆኑ የሕግ ልሂቃን ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ቀን አልፎ ቀን በተተካ ቁጥር የማስረጃዎች መገኘትና አስተማማኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ስለሚገባ የመብት መጠየቂያ ጊዜን ገድቦ ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው።
ከባለዕዳውም አንጻር ቢሆን ዕድሜ ልኩን አበዳሪውን ወይም ባለገንዘቡን ባየ ቁጥር መንገድ እያሳበረ መሄድ ስለሌለበትና ይህ ስጋቱም የሆነ ጊዜ ላይ ሊቋጭለት ስለሚገባ ነው ሕጉ የይርጋ ገደብ ያስቀመጠው።
ያልነበረ መብትን የሚያስገኘው የይርጋ ደንብ ደግሞ አንድን ጠያቂ ያጣ ንብረት ለረዥም ጊዜ በይዞታው ሥር ያደረገ ሰው በሕግ የተቀመጡ ግዴታዎችን እያሟላ ሲጠቀምበት ከቆየ በኋላ በሕግ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ሲጠናቀቅ የንብረቱ ባለቤት የሚሆንበት ነው።
ሕጉ አንድ ሰው አንድን ጠያቂ የሌለው ንብረት ለረዥም ጊዜ በይዞታው ሥር አቆይቶ ሲጠቀምበት በመቆየቱ ምክንያት “የንብረቱ ባለቤት ነኝ” የሚል ስሜትን እንደሚያሰርጽበት ግምት በመውሰድ ነው የባለቤትነት መብትን እንዲጎናጸፍ የፈቀደለት።
በዚህም መነሻ በሕጉ የተቀመጠው ጊዜ ካለፈ በኋላ አንድ ሌላ ሰው “የንብረቱ ባለቤት እኔ ነኝ” ብሎ ከበቂ የባለቤትነት ማስረጃዎች ጋርም ቢመጣ እንኳን ሕጉ “ካንተ ይልቅ ከንብረቱ ጋር የአካልም የስሜትም ተዛምዶ አድርጎ ለዓመታት በእጁ ያቆየው እሱ ስለሆነ ላንተ ሳይሆን ለእሱ ነው የሚገባው” በማለት የንብረቱን ባለቤትነት
በይዞታው ሥር ላቆየው ሰው ያስተላልፍለታል።
እንዲህ ዓይነት ያልነበረ መብትን የሚያስገኙ የፍትሐብሔር ይርጋ ደንቦችን በንብረት፣ በውርስ፣ በተላላፊ ሰነዶች፣ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት፣ በታክስ አስተዳደር እና በሌሎችም ሕግጋት ላይ እናገኛቸዋለን።
የይርጋ መከራከሪያን የማንሳት መብት የማን ነው?
በፍትሐብሔር ጉዳዮች የይርጋ ክርክር በባለጉዳዮች ካልተነሳ በስተቀር ዳኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ሊያነሱት አይችሉም። ምክንያቱም የአንዱን ወገን የሙግት ደካማነት በመደገፍ ሌላኛውን ወገን እንዳይጎዱና የተከራካሪዎችን በሕጉ ፊት በእኩልነት የመዳኘት መብትን እንዳይጥሱ ለማድረግ ነው።
ለዚህም የ1949ኙን የወንጀል ሕግ ያረቀቁትና በሕጉ ላይ “An Introduction to Ethiopian Penal Law” በሚል ሰፊ የማብራሪያ መጽሐፍ የጻፉትን ፊሊፕ ግራቨንን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።
በወንጀል ጉዳዮች ግን የይርጋን ጥያቄ ተከሳሽ ባያነሳውም ዓቃቤ ሕግም ሆነ ዳኞች ነገሩን መርምረው በይርጋ ከታገደ በራሳቸው አነሳሽነት ይርጋን በማንሳት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
በምርመራ ላይ የሚገኝ ጉዳይ የይርጋ ጥያቄ ካለበት ዓቃቤ ሕጉ መዝገቡን መዝጋት ይገባዋል። ያለአግባብም ክስ ተመስርቶ ከሆነም ዓቃቤ ሕጉ ጉዳዩን ማቋረጥ አለበት። ዳኞችም ቢሆኑ በይርጋ የታገደ ጉዳይ ከቀረበላቸው መዝገቡን መዝጋት አለባቸው።
የውል እና ከውል ውጪ የይርጋ ደንቦች
ከፍ ሲል በመግቢያው ላይ እንዳተትነው የፍትሐብሔር ይርጋ ደንብ አንድም የባለዕዳውን ግዴታ የሚያስቀር በሌላ በኩል ደግሞ መብት ላልነበረው ሰው መብትም የሚሰጥ ነው።
በዚሁ መነሻ የባለዕዳን ግዴታ የሚያስቀር ይርጋ የተደነገገው በግዴታ ሕጎች ውስጥ ሲሆን የባለዕዳ ግዴታ የሚመነጨው ደግሞ ከውል ወይም ከውል ውጪ ነው።
በሁለቱም ግዴታዎች የይርጋ ዘመኑ ርዝማኔ የተለያየ ቢሆንም ቅሉ ይርጋው ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ በግዴታው ውስጥ ባለገንዘብ (ባለመብት) የሆነውን ሰው መብት ያስቀራል።
በውል ሕግ ውስጥ ዓይነተኛው የይርጋ ደንብ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845 ላይ ሰፍሮ የምናነበው ነው። ይኸውም ውሉ እንዲፈጸምለት ወይም ባለመፈጸሙ የተነሳ ጉዳት የደረሰበት ወገን የጉዳት ካሣ የሚጠይቀው አልያም ውሉ እንዲፈርስ የሚጠይቀው በአስር ዓመት ውስጥ ስለመሆኑ የሚደነግገው ነው።
ይህ የአስር ዓመት የይርጋ ደንብ ግን በሌሎች ልዩ ውሎችን በሚመለከቱ ድንጋጌዎች የተቀመጡትን የተለያዩ የይርጋ ጊዜያት የሚመለከት እንዳልሆነ ሕጉ ያመለክታል። “ሕግ በሌላ አኳኋን ካልወሰነ በቀር…” በሚል በድንጋጌው የተቀመጠው አገላለጽም ይህንኑ ያሳያል።
ለምሳሌ በንግድ ሕግ ውስጥ በየብስና በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ውሎች መሰረት በመንገደኞች ወይም በተጓዥ ላይ ስለሚደርስ ጉዳት ወይም መጥፋት ክሱ ሊቀርብ የሚገባው መንገደኛው ወይም ዕቃው በመድረሻ ስፍራ ከደረሱበት ወይም መድረስ ይገባቸው ከነበሩበት ቀን ወይም ጉዞው እንዲቆም ከተደረገበት ቀን አንስቶ በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። ከዚህ የይርጋ ጊዜ በኋላ ክስ ቢቀርብ ግን አጓጓዡ ጉዳቱን ለመካስ እንደማይገደድ ማወቅ ያስፈልጋል።
በባህር ትራንስፖርት ደግሞ አስጫኙ የንግድ ዕቃውን ከተረከበበት ቀን ጀምሮ ወይም የማስረከቡ ጉዳይ ሳይፈጸም ቀርቶ ከሆነ ከቀረበት ቀን አንስቶ የአንድ ዓመት ጊዜ ካለፈ በኋላ በዕቃው ላይ ለደረሰው ጉዳት ወይም ጉድለት ወይም መጥፋት የሚቀርብ ጥያቄ በይርጋ እንደሚታገድ የባህር ሕጉ ያመለክታል።
የባህር ላይ መንገደኞችን በተመለከተም የጉዳት ኪሳራ ማቅረቢያ ይርጋው አንድ ዓመት ነው። ከባህር ትራንስፖርት ጋር የተያያዙ የመድን ውሎች ይርጋ ደግሞ ሁለት ዓመት ነው።
በተመሳሳይ በንግድ ሕጉ ውስጥ በመድን ውል ላይ የተመሰረተ ክስ ሊቀርብ የሚገባው ጉዳቱ ከደረሰበት ወይም ከጉዳቱ ጋር ጥቅም ያላቸው ሰዎች ጉዳቱን ካወቁበት ቀን ጀምሮ ባለው ሁለት ዓመት ውስጥ ስለመሆኑ ተደንግጓል።
አሁን በሥራ ላይ ባለው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ውስጥ ደግሞ ከሥራ ውል ጋር በተያያዘ በርካታ የይርጋ ደንቦች ተደንግገዋል። (ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ በሌላ ጽሑፍ አሰናድተን እናቀርባለን)
ከውል በተጓዳኝ የባለዕዳን ግዴታ የሚያስቀር ይርጋ የተደነገገው ከውል ውጪ ኃላፊነትን በሚመለከተው የፍትሐብሔር ሕጉ ክፍል ውስጥ ነው።
በዚሁ መሰረት ከውል ውጪ በሚመጣ ኃላፊነት ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ ክስ በሁለት ዓመት ይርጋ እንደሚታገድ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2143 ደንግጓል። ይርጋው የሚቆጠረውም ተበዳዩ ካሣ የሚጠይቅበት ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ነው።
ይህ መሰረታዊ ደንብ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከውል ውጪ በሆነው ኃላፊነት በተበዳዩ ላይ የደረሰው ጉዳት በወንጀልም ጭምር የሚያስቀጣ ከሆነና በወንጀል ሕጉ ለወንጀሉ ክስ ማቅረቢያ የተቀመጠው ይርጋ ከሁለት ዓመት የሚበልጥ ከሆነ የፍትሐብሔር ካሣ ክስ የማቅረቢያ ጊዜውም ይህነኑ የወንጀሉን ይርጋ እንደሚከተል ነው ሕጉ የሚገልጸው።
ለምሳሌ በቸልተኝነት በተፈጸመ የመኪና አደጋ የሚደርስ ከባድ የአካል ጉዳት የሚያስቀጣው ከስድስት ወር የማያንስ (እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ) ቀላል እስራት በመሆኑ በወንጀል ሕጉ የተቀመጠው ክስ የማቅረቢያ ይርጋ አምስት ዓመት ነው።
በመሆኑም የአካል ጉዳት የደረሰበት ተበዳይ የካሣ ጥያቄውን ማቅረብ የሚችልበት የይርጋ ጊዜ የወንጀሉን ይርጋ ስለሚከተል አምስት ዓመት ነው ማለት ነው።
ከግዴታ ሕግ ውጪ ያሉ የይርጋ ደንቦች
የባለዕዳን ግዴታ ከሚያስቀሩት የውልና ከውል
ውጪ ኃላፊነቶች ማለትም ከግዴታ ጋር ከተያያዙት የይርጋ ደንቦች በተጨማሪ ሁለተኛው የፍትሐብሔር ይርጋ ደንብ መብት ላልነበረው ሰው መብት የሚሰጠው ነው።
ይህን ያልነበረ መብትን የሚያስገኝ የፍትሐብሔር ይርጋ ደንብ በንብረት፣ በውርስ፣ በተላላፊ ሰነዶች፣ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት፣ በታክስ አስተዳደር እና በሌሎችም ሕግጋት ላይ ሰፍረው እናነባቸዋለን።
ከንብረት ጋር በተያያዘ የመጀመሪያው የይርጋ ደንብ ይዞታው የተወሰደበት ሰው ንብረቱ ይመለስልኝ ወይም ሁከት ይወገድልኝ በሚል አቤቱታ የሚያቀርብበት ጊዜ ነው። ይኸውም የሁለት ዓመት ይርጋ ነው።
ሌላው የንብረት ሕግ ይርጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት በእጁ አድርጎ ተፈላጊውን ግብር ለአስራ አምስት ተከታታይ ዓመታት ሲገብር የኖረ ሰው የንብረቱ ባለቤት ሊሆን የሚችልበት ነው።
ከውርስ ጋር በተያያዘ ከተቀመጡት ይርጋዎች የመጀመሪያው የኑዛዜ መቃወሚያ ጊዜ ነው። በዚሁ መሰረት የኑዛዜን መፍረስ የሚፈልግ ሰው ተቃውሞውን በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ለውርስ አጣሪው መግለጽ አለበትⵆ
ከዚህ ሌላ ይህ የተቃውሞ መግለጫ ከተሰጠበት ቀን አንስቶ እስከ ሦስት ወር ድረስ ክሱን ለፍርድ ቤት ወይም ለሽምግልና ዳኞች ማቅረብ ይኖርበታል።
ከዚህ ውጪ ግን በሌላ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ይህ መብት ከአምስት ዓመት በኋላ ቢቀርብ ተቀባይነት እንደሌለው ሕጉ ያስገነዝባል።
ሁለተኛው የይርጋ ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ደግሞ ያለአግባብ የውርሱን ንብረት በእጁ ካደረገው ሰው ላይ ንብረትን ለማስመለስ የሚቀርብ ጥያቄን የተመለከተው ነው።
በዚሁ መሰረት ከሳሹ የውርስ ንብረቶች በተከሳሹ መያዛቸውን ባወቀ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥያቄውን ሊያቀርብ ይገባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ከሳሹ ይህንን ጉዳይ አወቀም አላወቀ ሟቹ ከሞተ ወይም ከሳሹ በመብቱ ለመሥራት ከቻለበት ጊዜ አንስቶ አስራ አምስት ዓመት ካለፈ የውርስ ንብረት የማስመለስ ጥያቄ ለማቅረብ አይቻልም።
በንግድ ሕጉ ተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች የሚባሉ አሉ። እነዚህም የንግድ ወረቀቶች ሲሆኑ እንደገንዘብ ሆነው በገንዘብ ምትክ በላያቸው ላይ የሰፈረውን ያህል ዋጋ ያላቸው ተላላፊ ሰነዶች ናቸው።
የሐዋላ ወረቀት፣ ለመክፈል የሚሰጥ የተስፋ ሰነድ፣ ቼኮች እና በመጋዘን ለሚቀመጥ ዕቃ የሚሰጥ ምስክር ወረቀት ተላላፊ ሰነዶች ናቸው።
በዚሁ መሰረት ሕጉ ከእነዚህ ሰነዶች ጋር በተያያዘ የይርጋ ጊዜ አስቀምጧል። የሀዋላ ወረቀትን በተቀበለ ባለዕዳ ላይ የሚቀርብ ክስ የመክፈያው ቀን አልፎ በሦስት ዓመት ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል።
ከዚህ ሌላ የሀዋላ ወረቀት አምጭው ሰው (ሰነዱን ለክፍያ ያቀረበው) በጀርባው ፈራሚዎች (ፈርሞ ያስተላለፈው) እና በአውጪው (ሰነዱን አዘጋጅቶ ለአምጭው ወይም ለጀርባ ፈራሚው የሰጠ) ላይ የሚያቀርበው ክስ በአንድ ዓመት ይርጋ የታገደ ነው።
የጀርባ ፈራሚዎች ደግሞ እርስ በእርሳቸውና በአውጪው ላይ የሚያቀርቡት ክስ በስድስት ወር ይርጋ እንደሚታገድም ማወቅ ያስፈልጋል።
ቼክን በተመለከተ ደግሞ ቼክ ለክፍያ ለባንክ መቅረብ ያለበት ከተጻፈበት ቀን አንስቶ በስድስት ወራት ውስጥ ነው። ከዚህም ሌላ አምጭው የቼኩ ማቅረቢያ ጊዜ ካለፈ በኋላ በስድስት ወር ውስጥ በአውጪውና በሌሎች ተገዳጆች ላይ ክስ ካልመሰረተ በይርጋ ይታገዳል። አምጭው በከፋዩ (በባንኩ) ላይ ክስ ሊያቀርብ የሚችለው ደግሞ በሦስት ዓመት ውስጥ ነው።
በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ከተደነገጉት የይርጋ ደንቦች የመጀመሪያው ፍርድ ወይም ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ይግባኝ በስልሳ ቀናት ውስጥ መቅረብ እንዳለበት የሚደነግገው ነው። የፍርድ አፈጻጸም ጥያቄ የማቅረብ መብት ደግሞ በአስር ዓመት ይርጋ የተገደበ ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
በገብረክርስቶስ